Saturday, 05 June 2021 14:12

ወደ ኋላ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

    “እየሰማሽኝ ነው?”
“ለመርሳት እየሞከርኩ ነው ... ግን ትንሽ ጊዜ ስጠኝ?”
ስጠኝ ብዬ ጉዳዩን የእኔ ብቻ አስመሰልሁት እንጂ ጊዜ መግዛቱ ለእኔም፣ ለእሱም የሚበጅ፣ የማንቆጭበትንም እርምጃ ለመራመድ አዋጪ ነው። አንዳንድ ውሳኔ የውስጥን ሰላም ካደፈረሰ መፍትሔው ቆም ብሎ ማሰብ አይደል።
“አልችልም! መሄድ አለብን! አልሁ አይደል? መሄድ!” ጠንከር ያለና ቁጣ ያዘለው ትዕዛዝ ኮመጠጠኝ።
እንኳን ጉዳዩ ሌላ ሆኖ በፍቅርም መሃል በስኅተት የገባ የትዕዛዝ ቃል ስለት ሆኖ ይታየኛል። ጦርነት የተከፈተብኝ ስለሚመስለኝ የራሴን ትጥቅ መወልወል እጀምራለሁ።
“አንቺ እንደሆንሽ ከአዎ አይ ... ከእሺ እንቢ ይቀልሻል። እንግዲህ ቁርጥሽን እወቂው! አንድ ቤት በሁለት ራስ አይመራም።” መልስ ያላገኘሁላቸው ጥያቄዎቼ ቦታ ሳይቀይሩ ሌላ ነገር ... ያውም ደግሞ የሥልጣን ጥያቄ። መቼ ነው ፋሲልን በላዬ የሾምሁት?
የሔዋን ቅጣት መራራ ነው። ምሬቱ ከእግር እስከ ራሴ ይሰማኛል። አሁን ማን ይሙት አዳምና እባብ ተቀጥተዋል ይባላል? ጉልበታቸው እንጂ ነፍሳቸው ምን ደረሰባት?
ለእባብ - “በሕይወትህ ዘመን ሁሉ በደረትህ እየተሳብህ ትሄዳለህ፤ አፈርም ትበላለህ” አጭርና ግልጽ።
ለአዳም - “ምግብህን ጥረህ ግረህ ከእርሷ ታገኛለህ። ምድርም እሾህና አሜከላ ታበቅልብሃለች ... እንጀራህን በፊትህ ላብ ትበላለህ” መጠኑ ቢለያይም ሁላችንም የምንበላው በላባችን አይደል?
ለሔዋን - ሔዋን እኮ ነፍሷን ነው የተቀጣችው። ተቀጣን ልበል እንጂ! “ፈቃድሽ ወደ ባልሽ ይሆናል” ሲላት ኡ ... ኡ ... ማለት አልነበረባትም? ፈቃድን ያህል ነገር ከአስረከቡ ወዲያ የሚቀጥል ማንነት አለ?
እኔ በሔዋን ቦታ ብሆን ኖሮ ለፈጣሪ እንዲህ ስል ጥያቄ አቀርባለሁ። አንደኛ፡ ቅጣቴ ለምን ከአዳም ጋር ተገናኘ? ደግሞስ ከእኔ ጋር እንድትኖር የሰጠኸኝ ሴት እርሷ ሰጠችኝና በላሁ ሲል እኔንም፣ አንተንም መወንጀሉም አይደል? እንዴት እንዲህ ዓይነት ስጦታ ትሰጠኛለህ? ማለቱን ስለ ምን በዝምታ አለፍኸው? ይሄ በራሱ ሌላ ጥያቄ እንድጠይቅህ ያስገድደኛል።
ለመሆኑ እኔን የፈጠርክበት ምክንያት ምንድነው? አዳምን እንድረዳ ብቻ ነው ወይስ በእኔ ላይ ዓላማ አለህ? እላለሁ። በጊዜው ባልኖርም ይሄ ጉዳይ በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም። ሰማይ ቤት የጥያቄና መልስ ክፍለ ጊዜ ካለ ያኔ ከማነሳቸው ጥያቄዎች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ይሄ ይሆናል።
አዳምንም ደግሞ እጠይቃለሁ። ለምን እስከ ዛሬ አብረኸኝ ኖርህ? የምትፈልገውን የምታውቅ ከሆንህ ለምን ከእጄ ተቀብለህ በላህ? እሷ እውቀት ወዳ፣ እኔ ደግሞ በሆዴ መጨከን አቅቶኝ ... ትዕዛዝህን ተላለፍን ብትል ምን ነበረበት? እለዋለሁ።  
የሆነ ሆኖ የቅጣት ውሳኔ በተላለፈበት በዚያች ቀን ያለ ምንም ኮሽታ የስልጣን ሽግግር ተከናወነ። አዳም ሳቀ። ሔዋን ውስጥ ውስጡን አለቀሰች። ያኔ የተጀመረው የወንበር ትግል ይኸውና በእኔና በመሰሎቼ ዛሬ ድረስ ቀጥሏል።  ይቀጥላልም ...
ሰው ሁሉ መንገስ፣ ነገሮችን በቁጥጥር ስር ማድረግ ይፈልጋል። ይሄን ምኞታቸውን ያረኩ ግን ጥቂቶች ናቸው። ያልታደሉት መግዛት ባይችሉ እንኳን ፈቃዳቸውን የሚሰጡት ፍቅርን ጉልበቱ ላደረገ ነው። ምንም ቢሆን ከራስ ጋር ያለውን ግብግብ ለመቀነስ፣ እንደ ሙሉ ሽንፈትም ላለመቁጠር ይረዳል።
ከዛ ውጪ ግን በጾታው መጫን ለሚፈልግ ማጎንበስ ልክ ሊሆን አይችልም! በእርግጥ የትኛውም ኅብረት መሪና ተመሪ ሊኖረው ግድ ነው። መሪ መሆን ያለበት ማን ነው? የሚል ጥያቄ ሲነሳ ግን አእምሮ ጋ እንጂ ጾታ ጋ የሚያስኬደን ጉዳይ የለም! የአስተሳስብ ልቀት፣ የመምራት ብቃት እና የሞራል ልዕልና ከጾታ ጋር ተጣብቀው አልተፈጠሩም።
("ወደ ኋላ" ከተሰኘው የዲድያ ተስፋዬ መጽሐፍ የተቀነጨበ)

Read 1508 times