Saturday, 05 June 2021 14:32

ከችርቻሮ ንግድ እስከ ቢሊዮኖች ኢንቨስትመንት

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  • የያዕቆብ ጀነራል ትሬዲንግ አጠቃላይ ኢንቨስትመንት 2.5 ቢ. ደርሷል
     • ሁሉም የድርሻውን ከተወጣ የምንፈልጋትን የበለጸገች አገር እንፈጥራለን
     • ወላይታ ሶዶ በርካታ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ያስፈልጓታል
     • 220 ሚ. ብር የፈጀው ባለ 4 ኮከብ ሆቴል ሥራ ጀምሯል

            ተወልደው ያደጉት በወላይታ ዞን ቦብቻ ወረዳ፣ ቆብቻ ዲቅሶ ቀበሌ ነው። በቤተሰባቸው ነጋዴ ባይኖርም፣ እርሳቸው ወደ ንግድ የገቡት ገና የ6ኛ ክፍል ታዳጊ ተማሪ ሳሉ ነበር፡፡ ዛሬ ከሁለት አሰርት ዓመታት በኋላ የሰፋፊ እርሻዎች፣ የአስመጪና ላኪ ድርጅት፤ የዳሞታ ባንክ መስራችና ከፍተኛ ባለ አክሲዮን፣ የኢትዮ ስኳር ማኑፋክቸሪንግ አክሲዮን ማህበር ባለ አክሲዮንና በቅርቡ በወላይታ ሶዶ የተመረቀው ባለ 4 ኮከብ  ሆቴል ባለቤት ለመሆን በቅተዋል - የዛሬው እንግዳችን
አቶ ያዕቆብ አልታዬ፡፡
አቶ ያዕቆብ ከአርሶ አደር ቤተሰብ ወጥተው እንዴት ወደ ንግድ ገቡ? የንግድ ሥራ ጉዟቸው ምን ይመስላል? የወደፊት ራዕያቸው ምንድን ነው? የስኬታቸው ምስጢርስ? ለአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ሁሉንም አውግተዋታል። ከባለሃብቱ አቶ ያዕቆብ አልታዬ ጋር ያደረገችው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡  



             ወደ ንግድ የገቡት በልጅነት የቡረቃ ዕድሜ ላይ እንደሆነ ነግረውኛል፡፡ በዚያ ዕድሜ እንዴት አሰቡት?
 በዚያ ዕድሜዬ ከተማ ወጥቼ ሰዎችን አየሁ፡፡  “የተሻለ ኑሮ  መኖር የሚችሉት ነጋዴዎች ናቸው ማለት ነው” የሚል አስተሳሰብ በአዕምሮዬ ተቀረፀ፡፡ ከነጋዴ ቤተሰብ አይደለም የወጣሁት፤ በቤተሰባችን ነጋዴ የሆነ የመጀመሪያው ሰው እኔ ነኝ፡፡ በእርግጥ አያቴ ለተወሰነ ጊዜ ንግድ ሞክሮ እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ አልዘለቀበትም፡፡ በአዕምሮዬ የተቀረፀው ነገር እውን እንዲሆን አሰብኩኝ፤ ማሰብ ብቻ አይደለም፤ ንግዱንም በተግባር ጀመርኩኝ፡፡ ያው ሰው ያስባል እግዚአብሔር ይፈፅማል እንደሚባለው፣ ጌታ ሞገስ ሆነኝና እዚህ ደርሻለሁ፡፡
በታዳጊነት ዕድሜዎ ምን ነበር መነገድ የጀመሩት?
በትንንሽ ነገር ነው የጀመርኩት፡፡ ለምሳሌ፤ እዛው ሰፈር ውስጥ ቡና፣ ጥራጥሬና እህል በመቸርቸር ነበር ወደ ንግዱ የገባሁት። በዚያው ቀጠልኩበት፡፡ ይሄ እንግዲህ ከዛሬ 20 ምናምን ዓመት በፊት ነው፡፡ ቀስ በቀስ ከችርቻሮ ወደ ጅምላ ንግድ ከፍ አልኩኝ፡፡  ከዛም ወደ አስመጪና ላኪነት ገባሁ፡፡
ምንድን ነው የምትልኩትና የምታስመጡት?
እርግጥ ከውጭ የምናስመጣቸው ብዙ ነገሮችን ነው፡፡ ወደ ውጪ የምንልካቸው ግን ጥቂት ነገሮች ናቸው፡፡ ከዚህ በላይ ግን ሰፊው ሥራችን ግብርና  ነው፡፡ ወላይታ ውስጥ  ሰፋፊ የሙዝ እርሻዎች አሉን። ለምሳሌ ቀበላ አባያ ወረዳ፣ ኦሞ ወረዳና ቆብቻ ወረዳ ላይ እስከ 800 ሄክታር መሬት የሚደርስ የሙዝ እርሻ አለን፡፡
ሙዝ ለውጪ ገበያ ትልካላችሁ እንዴ?
የሚገርምሽ ሙዝ ለውጭ ገበያ ማቅረብ  ጀምረን ነበር፡፡ ሙዙን ወደ ውጪ በምንልክብት ጊዜ ሳይበላሽ እንዲደርስ የሚያደርገው ቴክኖሎጂ ላይ ትንሽ ችግር ስለገጠመን፣ ወደ ውጪ መላኩን ለትንሽ ጊዜ አቁመነዋል፡፡ ምክንያቱም ሙዙ ለውጪ ገበያ ሲላክ በጣም በጥራት ፍሬሽ እንደሆነ ደርሶ ገበያ ላይ ተወዳዳሪ መሆን አለበት፡፡ ያንን ለማድረግ የተጠቀምነው ማቀዝቀዣ  በምንጠብቀው ልክ ውጤታማ አልሆነም፡፡ እናም ዘመኑ ያፈራውን ማቀዝቀዣ አሟልተን፣ በልበ ሙሉነት መላክ እስክንጀምር፣ ሙዙን ለአገር ውስጥ ገበያ ነው እያቀረብን ያለነው፡፡
ከሙዝ ውጪ ሌላ ምን ታመርታላችሁ?
ከሙዝ ቀጥሎ በብዛት ካዛቫ እናመርታለን፡፡ ጥራጥሬዎችንም እንዲሁ። የጓሮ አትክልቶች እያመረትን ለገበያ እናቀርባለን፡፡ አሁን በቅርቡ ወደ ቡና ምርት ገብተናል፡፡ ኦሞ ወረዳ ላይ ቡና ተክለናል፡፡ በ20 ሄክታር መሬት ላይ ተክለን፣ ሁለተኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ በቅርቡ ምርት መስጠት ይጀምራል ብለን እናስባለን፡፡
ዳሞታ ባንክን በመመስረትም የፋይናንስ ሴክተሩን የተቀላቀሉ ሲሆን ትልቁን ድርሻ እንደገዙም  ሰምቻለሁ፡፡ እስኪ ስለ ባንኩ ምስረታ ይንገሩኝ፡፡ እንዴት አሰቡት?
የዳሞታ ባንክ መስራች ነኝ፡፡ ለአንድ ሰው የሚፈቀደውን ከፍተኛ አክስዮን መግዛቴም እውነት ነው፡፡ ከሚፈቀደው በላይ መግዛት አንችልም፡፡ የሚፈቀደው ትልቁና  ጣሪያው 100 ሚ. ብር ነው፡፡ በመቶ ሚ.ብር ትልቁን አክስዮን ገዝቻለሁ፡፡ ባንኩን ያቋቋምንበት አላማ እኛ አካባቢ ብዙ የተማረ የሰው ሀይል አለ፡፡ ለዚህ ለተማረ በርካታ የሰው ኃይል፣ የስራ ዕድል መፍጠር እንዲሁም ብዙ ሃሳብና. ራዕይ እያላቸው በፋይናንስ እጥረት ከሀሳባቸውና ከራዕያቸው ያልተገናኙትን፣ ህልማቸው እውን እንዲሆን በፋይናንስ ማገዝ ነው፡፡ ስለዚህ አላማችን ግልጽና ለሀገርና ለወገን የሚጠቅም በመሆኑ፣ ባንኩን ከመመስረት ባለፈ ትልቁን አክስዮን በመግዛት ቁርጠኝነቴን አሳይቻለሁ። ባንኩ ወደፊት በሀገራችን እንዳሉ ነባር ባንኮች፣ ተፎካካሪና ዘመናዊ ባንክ ይሆናል፡፡ ከእኛ ትርፍም በላይ ይበልጥ የሚያኮራንና የሚያረካን ለሰዎች  የስራ ዕድል መፍጠራችን ነው፡፡
አሁን ደግሞ ወደ ሆቴል ቢዝነስ ገብተዋል። በቅርቡ የተመረቀው ባለ 4 ኮከቡ “ያዕቆብ ሆቴል” በሶዶ ሥራ ጀምሯል። ወደ ሆቴል ዘርፍ የገቡበት የተለየ ምክንያት አለዎት?
ወደ ሆቴል ኢንዱስትሪው የገባንበት ምክንያት ግልጽ ነው፡፡ እዚህ ወላይታ ሶዶ ከተማ ውስጥ ብዙ ትልልቅ ሆቴሎች አልነበሩም፡፡ አሁን በቅርቡ ነው ከተማዋም መነቃቃት የጀመረችው፡፡ እርግጥ ሶዶ ከተማ ሰባት መውጫና መግቢያ በሮች ያሏት የንግድ ከተማ ናት፡፡ ብዙ የቱሪዝም ሀብት ያላትም ናት፡፡ ይህንን ለመጎብኘት ብዙ ሰው ይመጣል፡፡ በቂ ማረፊያና መዝናኛ ቦታ ግን የለም፡፡ እኔም እንደ አንድ የአካባቢው ተወላጅና ባለሃብት ይሄ ጉዳይ ይመለከተኛል፡፡ እዚህ ሶዶ ከተማ ውስጥም ቢሆን ወደ 300 ሺህ የሚጠጋ ህዝብ አለ። ከሶዶ ቀጥሎም ብዙ ዞኖች አሉ፡፡ በዚህ እስከ ኬኒያ ድረስ የሚያልፉ መንገደኞች ማረፊያቸው እዚሁ ሶዶ ነው፡፡ በአጠቃላይ ወደ ሶዶ የሚገባውና የሚወጣው ሰው ብዙ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ሰው እስካሁን ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ሶስት ብቻ ነበሩ፡፡ የእኛ አራተኛው ነው ማለት ይቻላል፡፡ አምስተኛ የሚሆነው የኃይሌ ሆቴልና ሪዞርት ነው፡፡ እሱም ግንባታው እየተጠናቀቀ ነው፡፡ ይሄም ሆኖ ሶዶ ከተማ ገና ብዙ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ያስፈልጓታል፡፡ አሁን ያሉት የእኛን ጨምሮ በቂ አይደሉም፡፡ ይህን በማሰብ ነው ሆቴሉን ገንብቼ ለምረቃ ያበቃሁት፡፡ በነገራችን ላይ የትኛውም ባለሃብት እዚህ መጥቶ ሆቴል ቢገነባ ዘርፉ አዋጭ ነው፡፡ ከፍተኛ ፍላጎት አለ፡፡ እኔ አንድ አይደለም 20 ሆቴል ብገነባ ያዋጣኛል፤ በዚህ እርግጠኛ ነኝ፡፡
የሆቴሉ ግንባታ  ምን ያህል ፈጀ?
ሆቴሉ በ13 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ነው ያረፈው፡፡ አሁን ግንባታው የተጠናቀቀው በ220 ሚ.ብር ነው፤ ነገር ግን ቀሪ ግንባታዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ እነዚህን ሳይጨምር ነው 220 ሚ ብር የወጣው ማለት ነው። ቀሪው ገንዘብ ግንባታው ሲጠናቀቅ ነው የሚታወቀው፡፡ በአጠቃላይ የስራ ዕድል በተመለከተ በያዕቆብ ጄነራል ትሬዲንግ ውስጥ 500 ቋሚ፣ ከ10 ሺህ በላይ ደግሞ ጊዜያዊ ሰራተኞች አሉን፡፡ እዚህ ሆቴል ላይ ደግሞ 168 በቋሚነት ተቀጥረዋል፤ ጊዜያዊ ሰራተኞችም አሉ፤ በሚያስፈልጉ ጊዜ እየተጠሩ ሰርተው ይመለሳሉ፡፡
የያዕቆብ ጀነራል ትሬዲንግ አጠቃላይ ኢንቨስትመንት ምን ያህል ደርሷል?
የያዕቆብ ጀነራል  ትሬዲንግ አጠቃላይ ኢንቨስትመንት ወደ 2.5 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡
የወደፊት ራዕይዎ ምንድን ነው? ለሀገርዎስ ምን ይመኛሉ?
የመጀመሪያው ምኞቴ፣ ኢትዮጵያ እንደ ቀድሞው ሰላምና አንድነቷ ተመልሶ፣ ማየት እፈልጋለሁ፡፡ ሰላም ፍቅርና አንድነት ካለ ሀገር ትበለጽጋለች፡፡ ምክንያቱም ነጋዴው በሰላም ይነግዳል፤ ተማሪው በጥሩ ሁኔታ ተምሮ ሀገር ይረከባል፤ ምሁራን ለሀገራቸው ጠቃሚ ሀሳብ ያፈልቃሉ፡፡ ይህ ሁሉ ነው ሀገርን የሚያበለጽገው፡፡ በሌላ በኩል፤  ዳሞታ ባንክ  የ20 እና 25 ዓመት ዕድሜ እንዳላቸው ሌሎች ትላልቅ  ባንኮች አድጎና ሰፍቶ፣ ለበርካቶች የሥራ እድል ፈጥሮ ማየት እፈልጋለሁ፡፡ ሌላው የኢትዮጵያ ክፍልም ሆነ ወላይታ በልጽጋ ማየት ራዕዬ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የበኩሌን አስተዋፅኦ ለማድረግ እየጣርኩ ነው፡፡ ሁሉም የድርሻውን ከተወጣ፣ የምንፈልጋትን የበለጸገች አገር እንፈጥራለን፡፡
የስኬቴ ምንጮች ናቸው፤ ያለ እነሱ ድጋፍና እገዛ እዚህ አልደርስም ነበር የሚሏቸው ሰዎች ይኖራሉ?
ለስኬቴ ዋነኛዋ ምንጭ ውዷ ባለቤቴ ፀጋነሽ ታደለ ናት፣ እጅግ አመሰግናታለሁ። ወደፊት ብዙ ራዕይ አለኝ፡፡ ለምሳሌ ያዕቆብ ሆቴል፣ ዕድሜ ከሰጠን፣ ከሶዶ ውጭ በተለያዩ አካባቢዎች ለመክፈት አስባለሁ። ሀዋሳ፣ አርባ ምንጭ፣ ጎፋ፣ ታርጫ፣ አዲስ አበባ፣ ሻሸመኔና ሌሎችም ቦታዎች ይስፋፋል፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ እንደከዚህ ቀደሙ ባለቤቴ ትልቁን ሚና ትወጣለች ብዬ አምናለሁ፡፡ ለእስከዛሬውም ሆነ ለወደፊት እገዛዋ በእጅጉ ላመሰግናት እወዳለሁ። በተጨማሪም፣ ከኔ ጋር 24 ሰዓት እየሰሩ የሚያግዙኝን ወንድሞቼን፣ የመንግስት አካላትን ከቀበሌ እስከ ክልል ያሉትን፣ ስራችን እንዲቃናና እንዲቀላጠፍ ለሚያደርጉልን ድጋፍ አመሰግናለሁ። ሌሎችም በመዘንጋት ስማቸውን ያልጠቀስኳቸው ግን ከጎኔ ሆነው ያገዙኝን ሁሉ አመሰግናለሁ፡፡


Read 2605 times