Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 01 September 2012 11:00

ጐርፉ የሰው ልጅ ሕይወት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

…እነይ ስላስ፤ ቆራቢ እና ቤተስኪያን ሳሚ ሆነው ልጆቻቸውን እያስተማሩ ማሳደግ ጀመሩ፡፡ ኑሮአቸው አስቸጋሪ እንደሆነ ስለሚያውቁ… መፍትሄው ልጆቻቸውን አስተምረውና ቀጥተው ሲያሳድጓቸው እና ሲጦሯቸው እንደሆነ ይታያቸዋል፡፡ ሶስቱ ልጆቻቸውን ከተለያዩ ሰዎች ከወለዱ በኋላ፤ ልጅ መውለድ ይበቃኛል ብለው የተወለዱትን አስተምሮ ማሳደግን የህይወት ተልዕኮአቸው አድርገው ወሰዱት፡፡ ገበያ በሚውልበት ቀን፤ ጨው እና ቅመማቅመም ከትላልቅ ነጋዴዎች ገዝተው አሊያም ተበድረው ገበያ ወስደው ዘርግተው አስጥተውት ይውላሉ፡፡ አንገታቸው ስር ባለች መሸምቀቂያ በተሠራች ከረጢት ገንዘባቸውን ይከቱና ተመልሰው ወደ ገበያቸው ፊታቸውን ያዞራሉ፡፡ በእህል የለወጡትን ደግሞ በተለያዩ ብጥቅጣቂ ጨርቆች ሲያጠራቅሙ ውለው… ምሽት ላይ የሚያዝሉትን አዝለው፣ የሚያንጠለጥሉትን አንጠልጥለው… ወደ ቤታቸው ይገባሉ፡፡ የተበደሩትን ከከፈሉ በኋላ ለሳምንት ማቆያ የሚሆን ያገኛሉ፡፡ ሳምንት ቆጥሮ የገበያው ቀን እስኪመጣ በዚህ ሁኔታ ይቆያሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ፤ አመመኝ ብለው ተጣጥፈው ይተኛሉ፡፡ ሌላ ጊዜ፤ ጥጥ ፈትለው እየሸጡ፣ ውሀ አምጥተው እየቸረቸሩ ተጨማሪ ገቢ ይለቃቅማሉ፡፡

የእነይ ስላስ፤ ቤታቸውም ሆነ ኑሮአቸው የሚጋጩ ነገሮች ጐተራ ነው፡፡ ቤታቸው በዘመናዊ ፋብሪካ የተሠራ ቆርቆሮ ነው፡፡ ውስጡ ግን… ከአልጋ ይልቅ መደብ… ከመብራት ይልቅ የላምባ ጋዝ… ወይም እሳት ነው የሚገኘው፡፡ ለዘመናት አገልግሎት ላይ የቆዩ መሳሪያዎች… በዘመናዊ መንገድ በተሠራ ቆርቆሮ ቤት ውስጥ በአንድ ላይ ተቻችለው ይኖራሉ፡፡ ቀኛዝማች ዮሴፍ፤ ከተማዋን ቢያሠለጥናትም ቅሉ የቧንቧ ውሀ የሚባል ነገር በአካባቢያቸው ፈጽሞ አይታወቅም፡፡ ለቤታቸው የሚጠቀሙበትን ውሀ ተለቅ ባለ እንስራ ያስቀምጣሉ፡፡

ለሺዎች አመታት ባልተቀየረ አሰራር የተሠራ እንስራ ቢሆንም ውሀ መቅጅያቸው ግን ሽክና አልነበረም፡፡ ኮካኮላ የሚል የእንግሊዝኛ ፅሁፍ የሰፈረበት ጣሳ ነበር፡፡ ጣሳዋ የተሠራችው እንኳን… ለውሀ መቅጂያ  አልነበረም፡፡

በዘመናዊ መንገድ የተሰራ መጠጥ ለማሸግ… አገልግሎቱን ሲጨርስ እንዲጣል… ወይም ተሰብስቦ እንደገና በዘመናዊ መንገድ ተስተካክሎ ዘመናዊው መጠጥ እንዲታሸግበት ነበር፡፡

በዘመናዊው ኑሮ የተጣለ ጣሳ እነ እነይ ስላስ ቤት ገብቶ በአንድ ጎኑ ጫፍ ጫፉን ተከርክሞ የውሀ መቅጃ መሆኑን እነ እነይ ስላስን ከ20ኛው ክፍለ ዘመን ጋር ያስተሳስሯቸዋል፡፡ የሚገርመው ደግሞ፤ ክፍለ ዘመኑ “ውዳቂ ነው” ብሎ የጣለው ነገር መሆኑ ነው፡፡ ዘመናዊ ኑሮ በጣለው ነገር አማካኝነት ከዘመናዊው ኑሮ ጋር ይተሳሰራሉ፡፡

ሲያማቸው ወይም ጠቀም ያለ ገንዘብ ሲያገኙ… የሚያስፈጯትን እህል ወፍጮ ቤት ወስደው በዘመናዊ ወፍጮ መሳሪያ ያስፈጫሉ፡፡ ገንዘብ አጥተው ወይም ጤነኛ ሲሆኑ ደግሞ የሠው ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ መቼ መጠቀም እንደጀመረበት በውል በማይታወቅ… የድንጋይ ዳቦ ዘመን ወፍጮ አስፈጭተው ይጠቀማሉ፡፡ እነይ ስላስ፤ በሁለት ዘመኖች ላይ ተንጠልጥለው ይኖራሉ፡፡ አንደኛው እግራቸው በ20ኛው ክ/ዘመን

(በተጣለ የኮካ ኮላ ጣሳና በዘመናዊ ወፍጮ ቤት)  ሌላኛው እግራቸው በድንጋይ ዳቦ ዘመን…፡፡

ኑሮን ሰው መስለው መኖር ሲሹ… ከሰው ጋር መቀላቀያ ብለው የገዙት ልብስ አለ፡፡ ሁልጊዜ የሚለብሷት ቀለሟን የቀየረች አቡጀዲድ ቀሚስ ግን ለአዘቦቱ ቀን አለችላቸው፡፡ አዲሷን ልብሳቸውን ቢለብሱም አሮጌዋን አቡጀዲድ አያወልቋትም - አዲሷ እንዳታረጅ በሚል፡፡

እንይ ስላስን የሚያስጨንቃቸው አዲስ ለስላሳ ጨርቅ ጀርባቸው ላይ ማረፉ አይደለም፡፡ የሚያስጨንቃቸው ከትከሻቸው ጋር የተጣበቀው ከርፋፋ እና አሮጌ ልብስ እያለ… በውጪ የሚታየው የተዋበ እና ዘመነኛ መሆኑ እንጂ፡፡ በእነይ ስላስ ዘንድ አሮጌውን አዲሱ ሸፍኖት ይኖራል እንጂ…  አይጣልም፡፡ ወደ በኋላ ላይ፤ ኑሮ ቀለል እያለላቸው ሲሄድ፤ የቤተክርስቲያን መሳሚያ ብለው ያሠሩት ጋቢም ኖራቸው፡፡ ከገዟት አቡጀዲ በላይ ይከናነቧታል - ጋቢዋን፡፡

ኑሮአቸው፤ በአጠቃላይ ከሚሸጡት ሸቀጣሸቀጥ አይለይም፡፡ ዝብርቅርቅ ያለ ነው፡፡ ይህ ግን የእነይ ስላስ እና የአካባቢያቸው ብቻ ሳይሆን… የመላው ትግራይ… ብሎም የሁሉም ኢትዮጵያ ኑሮ ነው፡፡ የተመቻቸ ኑሮ አላቸው የሚባሉት እነ ቀኛዝማች ዮሴፍም ቢሆኑ፤ መጠኑ ይለያይ ይሆናል እንጂ፤ ኑሮአቸው በድንጋይ ዳቦ ዘመን እና በ20ኛው ክፍለ ዘመን ላይ የተንጠላጠለ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡

እነይ ስላይ፤ በኑሮአቸው የተደሰቱበት በእድላቸው የረኩበት ጊዜ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ድሀ ሆነው ከግራ ቀኝ ታጥፈው አስከፊ ኑሮ ይመራሉ፡፡ በድህነታቸው ይፀፀታሉ፡፡ ለምን እንደደኸዩ ግን አስበውበት አያውቅም እሳቸው ማድረግ የሚችሉትን ቢያደርጉ እንዳያልፍላቸው የሚያደርግ ቀፍድዶ የያዛቸው ምድራዊ ሀይል አለ፤ ብለው አያምኑም፡፡

እድላቸው ሆኖ ከድሆች ተፈጥረው ድሀ ሆኑ፡፡ ገዢዎች ደግሞ እድላቸው ሆኖ፤ ከሀብታሞች ተወልደው ሀብታም ሆነው እንደተፈጠሩ አድርገው ነው የሚያስቡት ድሀ የነበረ ሀብታም ሲሆን፤ ሀብታም የነበረም ሲደኸይ ሲያዩም… አጋጣሚ የእድል ነገር እንደሆነ ነው የሚረዱት፡፡

ትልቁ ምኞታቸውም ደሀ ሆነው ተፈጥረው እድላቸው ሆኖ ሃብታም ከሆኑት አንዱ መሆንን ነው፡፡ በራሳቸው ጥረት አልተሳካላቸውም፡፡ ስለዚህ ልጆቻቸው ማስተማርን ሀብታም ለመሆን ብቸኛው መንገድ እንደሆነ አሰቡና… በታላቅ ወኔ ተነሳሱ፡፡

ኑሮአቸው ለምን እንዲያ እንደሆነና በቀጣይም የሚጠብቃቸውን አማራጮች ፈጽሞ አልተረዱትም፡፡ በአንድ መንገድ ይሞክራሉ፤ ያቅታቸዋል፡፡ ያማርራሉ፤ በሌላ መንገድ እንደገና ይሞክራሉ፡፡ በሱም ያቅታቸዋል፡፡ ያማርራሉ፡፡ ከአንድ ፈተና ወደ ሌላ… ከምሬት ወደ ምሬት እየተገላበጡ፣ የማያውቁትና የማይቆጣጠሩት የህይወት ጉዞ እየገፉ ይጓዛሉ፡፡ የጐርፍ ጉዞን ማንም አይቆጣጠረውም፣ በራሱ ህግ ካንዱ ወደ አንዱ ይወረወራል፡፡ የሰበሰበውን ግንድ እያገላበጠ ይዞ ይወነጨፋል፡፡ ግንዱ፤ የጐርፉን ጉዞ ይወቀው አይወቀው፣ ይቆጣጠረው አይቆጣጠረው ሌላ… ጥያቄ ነው፡፡ እየተገላበጠ ግን ይሄዳል፡፡ እንደ እናይ ስላስ፡፡ የሚያሰላስልበት አዕምሮ የሌለው በጐርፍ የሚገፋ ግንድ ከእነይ ስላስ ኑሮ አይለይም፡፡ በእነይ ስላስ ቀበሌ፣ በትግራይ፣ በኢትዮጵያ… በሁሉም አለም በኑሮ ጐርፍ እየተገፋ ሳያውቀው፣ ሳይቆጣጠረው እየተገላበጠ ስንቱ እየወረደ ይሆን?

 

 

Read 59823 times Last modified on Saturday, 01 September 2012 11:10