Print this page
Sunday, 13 June 2021 19:33

የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ላይ ጉድለት በተገኘባቸው የምርጫ ክልሎች የድምጽ መስጫ ቀን ተራዘመ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ሁለተኛው ዙር ምርጫ ጳጉሜ 1 ይካሄዳል

            በተለያዩ የምርጫ ክልሎች የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ላይ ጉድለቶች መገኘታቸውን ተከትሎ ጉድለት የተገኘባቸው የምርጫ ክልሎች የድምጽ መስጫ ቀን መራዘሙን የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፤ ክፍተት የተገኘባቸው የምርጫ ክልሎች፣ የጸጥታ ችግር አለባቸው ተብለው ሰኔ 14 ድምጽ ከማይሰጥባቸው የምርጫ ክልሎች ጋር ድምጽ እንደሚሰጥባቸው አስታውቀዋል፡፡
የቦርዱ የኦዲት ክፍል ባካሄደው ማጣራትም በ54 ምርጫ ክልሎች ላይ ክፍተት የተገኘ ሲሆን ሁለተኛው  የምርጫ ቀን ጳጉሜን 1 ቀን 2013 ዓ.ም ይሆናል ተብሏል።
የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ላይ ጉድለት ከተገኘባቸው 54 የምርጫ ክልሎች ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት በደቡብና ሶማሌ ክልሎች የሚገኙ መሆኑን ያመለከተው ቦርዱ፤ ከሁለቱ በመቀጠል በርከት ያሉ የምርጫ ክልሎቹ በችግሩ ተጽዕኖ የደረሱበት የአማራ ክልል ነው። አፋር፣ ጋምቤላና ኦሮሚያ በተከታይነት የተቀመጡ ሲሆን  የድሬዳዋ ከተማ በአንድ የምርጫ ክልሉ ላይ የድምጽ መስጫ ወረቀት ህትመት ችግር ተገኝቶበታል ተብሏል።    
ከድምጽ መስጫ ወረቀቶች ህትመት ችግር ጋር በተያያዘ ያጋጠመውን እክል ለመቅረፍ ቦርዱ ባለፈው ረቡዕ  ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረገው ውይይት ሁለት አማራጮችን  አቅርቦ ነበር፡፡ አንደኛው አማራጭ የድምጽ መስጫ ወረቀቶችን በሀገር ውስጥ ማሳተም ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የህትመት ችግር በተከሰተባቸው የምርጫ ክልሎች ሊካሄድ የነበረውን ምርጫ ከሌሎች አካባቢዎች ጋር ደምሮ ማካሄድ የሚል ነው፡፡
ምርጫ ቦርድ በጸጥታ ችግርና በሌሎችም ምክንያቶች የመራጮች ምዝገባ ተስተጓጉሎባቸዋል ባላቸው 40 የምርጫ ክልሎች፣ ሰኔ 14 የድምጽ መስጠት ሂደት እንደማያከናውን መግለጹ የሚታወስ ሲሆን የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ህትመት ላይ ጉድለት የተገኘባቸው 54 የምርጫ ክልሎች ከ40ዎቹ ጋር በመደመር፤ ምርጫውን በተለየ የጊዜ ሰሌዳ፣ በአንድ ላይ ማካሄድ የሚል አማራጭ አቅርቦ ነበር፡፡
በዚህም መሠረት ሁለተኛው ዙር ምርጫ ጳጉሜ 1 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚካሄድ አስታውቋል፡፡


Read 879 times
Administrator

Latest from Administrator