Print this page
Sunday, 13 June 2021 19:44

ቻይና በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች የሚደረገውን ጣልቃ ገብነት ተቃወመች

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(3 votes)

   • ኢትዮጵያ ብሔራዊ ደህንነቷን የማስጠበቅ መብት አላት
      • በትግራይ ያለውን ሰብአዊ ቀውስ ለማርገብ እርዳታ ለመስጠት ቃል ገብታለች
      • የመጀመሪያው ዙር የምግብ እርዳታ ተልኳል ተብሏል
                  
             ቻይና አሜሪካንን ጨምሮ የተለያዩ አገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት በፅኑ እንደምትቃወምና አገሪቱ የውስጥ ጉዳዮቿን ያለምንም ጣልቃ ገብነት መፍታት እንዳለባት ገለፀች፡፡
ዥንዋ ትናንት የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሬን ጠቅሶ ባቀረበው ዘገባ ኢትዮጵያ ሉአላዊነቷን ለማስከበር የምታደርገውን ጥረት ቻይና ትደግፋለች ብሏል፡፡
ቻይና  እና ኢትየጵያ ለረዥም ጊዜ የቆየ ወዳጅነትና ትብብር እንዳላቸው ያመለከቱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዋንግ ይ፤ ቻይና በኢትዮጵያ ሉአላዊነትና የውስጥ ጉዳዮች የሚደረጉ ጣልቃ ገብነቶችን አጥብቃ እንደምትቃወም ተናግረዋል፡፡
“ኢትዮጵያ ብሔራዊ ደህንነቷን የማስጠበቅና የውስጥ ሰላሟን የማረጋጋት መብት አላት” ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አገሪቱ የውስጥ ጉዳዮቿን በራሷ ጥረት ለመፍታት የምታደርገውን ጥረት ማገዝና የኢትዮጵያን ፍቃድ አክብሮ ድጋፍ መስጠት ይገባዋል ብለዋል፡፡
አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የጣለችው ማዕቀብም ተገቢነት የለውም ሲሉ መቃወማቸውን ዥንዋ ዘግቧል፡፡
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከኢትዮጵያ  አቻቸው አቶ ደመቀ መኮንን ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት፤ ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮቿን በራሷ ለመፍታት የምታደርገውን ጥረት ቻይና እንደምታከብርና እንደምትደግፍ ያስታወቁ ፤ ሲሆን በትግራይ ክልል ያለውን ሰብአዊ ቀውስ ለማርገብ የሚያስችል እርዳታ ለመስጠት ዝግጁ መሆኗንም አመልክተዋል፡፡
የሁለቱ አገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በስልክ ባደረጉት በዚሁ ውይይትም፤ አገሪቱ እርስ በእርስ ለመተባበር ቁርጠኛ እንደሆኑ መግለፃቸውን ዥንዋ ዘግቧል፡፡



Read 10256 times