Sunday, 13 June 2021 19:49

የጋናዋ ልዕልት ማማ አፍሪካ ኢትዮጵያ ገብታለች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

  • “ፍቅር እና አንድነት የሁሉም ኃይል ምንጭ ነው!”
      • “ወደ ትውልድ ምድር አፍሪካ የመመለስ ጉዞ አዲስ አበባ ካልተደረሰ አይጠናቀቅም”
      • “ወጣቶች የእኛ አበባዎች ናቸው! የወደፊቱ ብሩህነትም በእጃችን ነው”
                    ግሩም ሠይፉ          ጋናዊቷ ልዕልትና የሃይማኖት መሪ ትዊላ-ማሪ ሥላሴ ሳትራ (ማማ አፍሪካ) ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያ ጉብኝት ለማድረግ ትናንት አዲስ አበባ ገብታለች፡፡ የኢትዮጵያውያን ዎርልድ ፌደሬሽን ዶክተር መላኩ በያን ማህበር (The Ethiopian world Federation DR. Melaku Beyan Association) ሥራ አስፈፃሚ አባላትና ታዋቂ ግለሰቦች ልዩ አቀባበል አድርገውላታል፡፡
በጋና የልማት ንግስት ለመባል የበቃችው ማማ አፍሪካ በኢትዮጵያ ጉብኝቷ፤ የኢንቨስትመንትና ልማት ዕድሎችን የማየት ዕቅድ አላት ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያ የኩሽዎች ምድር፤ የሀይለስላሴና የሳባ ምድር፤ አፍሪካዊና ሉዓላዊ ህዝብ የሚኖርባት አገር መሆኗን በኩራት የምትናገረው ልዕልቷ፤ ወደ ትውልድ ምድር አፍሪካ የመመለስ ጉዞ አዲስ አበባ ካልተደረሰ አይጠናቀቅም፡፡
‹‹ወጣቶች የእኛ አበባዎች ናቸው! የወደፊቱ ብሩህነትም በእጃችን ነው”፡፡ የሚለውን መልዕክት ከኢትዮጵያ ጉብኝቷ ጋር በማያያዝ ባወጣችው መግለጫ ያስተላለፈችው ማማ አፍሪካ፤  የኢትዮጵያ ወጣቶችን ለመርዳት ምን ማድረግ ይቻላል? ለሚለው ጥያቄዋ ምላሽ ለማግኘት ያላትንም ጉጉት ገልፃለች፡፡
ማማ አፍሪካ ሰኔ 6 ከጠዋቱ 5 ሰዓት ላይ በቪላ ቨርዴ ከኢትዮጵያውያን ወርልድ ፌደሬሽን ዶክተር መላኩ በያን ማህበር ጋር በምትሰጠው ልዩ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉት የኢንቬስትመንትና የልማት ዕድሎች ዙርያ የተሟላ መረጃዎችን ለመሰብሰብ ስለማቀዷ የምታብራራ ይሆናል፡፡
ማማ አፍሪካ ስለኢትዮጵያ ጉብኝቷ
‹‹የኩሻውያንን የተቀደሰች ምድር ለመጎብኘት  በመቻሌ ፍፁም ደስ ብሎኛል። በቅኝ ያልተገዛች ብቸኛዋ አፍሪካዊት ሀገር ናት፡፡ የኃይሌ ስላሴ መኖሪያ ቤት!! ህዝቦችን ከዳር እስከ ዳር ያነቃቁ ታላቅ ንጉስ ናቸው። ታዋቂው ቦብ ማርሌይ እንኳን የሊግ ኦፍ ኔሽንስ ንግግራቸውን ለትውልዶች ተስፋን ለመስጠት  በሙዚቃው ተጠቅሞበታል፡፡››
‹‹የጉብኝቴ ዋና ዓላማ ከኢትዮጵያ ምድር፣ ባህልና ህዝቦች ጋር መገናኘት ነው፡፡  የኢትዮጵያን ወጣቶች ፍላጎቶችን ለማወቅና እነዚያን ፍላጎቶችም ለማሟላት ነው የማስበው፡፡ በኢትዮጵያ የልጆቼ ድርጅት አዲስ ምዕራፍ ለመክፈትም ይሆናል፡፡ እቅዶቼ ተመሳሳይ አመለካከት ካላቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች ጋር መስራት፡፡ ዳያስፖራዎችን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ፍላጎት ካላቸው ድርጅቶች ጋር በመገናኘት ድጋፍ ለማድረግ እሻለሁ፡፡ በእነዚህ ጥረቶች እና ሌሎች ንቅናቄዎችን በመቀላቀል በእርግጠኝነት አፍሪካን በድጋሜ ታላቅ ማድረግ እንደምንችል እምነቴ ስትልም ልዕልቷ ሃሳቧን አብታለች፡፡!››
አዎ፡፡ ወደ ትውልድ ምድር መመለስ ወደ አዲስ  አበባ ጉዞ ከሌለ መመለስ አይደለም። በዓለም ዙርያ ጥቁር ጠይም ህዝቦች ኢትዮጵያውያን ተብለው የተጠሩበትን ጊዜ ብዙዎች አያስታውሱም! ወደ ትውልድ ምድራችን የምንመለስበት እንቆቅልሽ በጣም ልዩ የሆነችው ኢትዮጵያ ናት። ሁላችንም አድዋ ምን ማለት እንደሆነና በዓለም ዙርያ ለምንገኝ ጥቁር ኑቢያን ኩሾች በዓለም ዙሪያ  ምን ትርጉም እንዳለው  ማስታወስ አለበን ትላለች የጋናዋ ልዕልት፡፡
በኢትዮጵያ ልትሰራበት የምትፈልገው C.H.E.S.S ፋውንዴሽን
በኢትዮጵያ ቆይታዋ “The Children’s Health Education & Safety Society C.H.E.S.S “የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅቷን የምታስተዋውቅ ይሆናል።  በወጣቶችና ሕፃናት ጤና፤ ትምህርትና ደህንነት ላይ አተኩሮ የሚሰራው፤ በአሜሪካ፣ በጋና፣ በናይጄሪያና በጃማይካ በተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ይንቀሳቀሳል፡፡”
ለማማ አፍሪካ ፍቅር፤ ሰላምና ስነምግባር ዋና የህይወት መመርያዎች ናቸው፡፡ የፓን አፍሪካ ልዕልትና የልማት ንግስት የሚለውን የማዕረግ ስም የተቀዳጀችውም በህፃናት ጤና ትምህርት ደህንነት ላይ የሚሰራው ፋውንዴሽን መስራች ሆና ስታደርግ በቆየችው እንቅስቃሴ ነው፡፡ በአሜሪካ ኮንግረስ እውቅና ያገኘው ፋውንዴሽንና፤ በጋና የቮልታ ክልል ከ 1000 ሄክታር በላይ  መሬት አግኝቶ ማህበረሰቡን እያገለገለ ይገኛል፡፡ በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቁር ህዝቦችንን የሚረዱ ፕሮጀክቶችን በጋና እና በዓለም አቀፍ ደረጃ እየሰራም ይገኛል፡፡
C.H.E.S.S በመላው ጋና የህፃናት ማሳደጊያን በምግብ አቅርቦት በመደገፍ፤ ክሊኒኮችና፤ ትምህርት ቤቶችን በመገንባትና  በማስተዳደር፤ በጃማይካ ለትምህርት ቤት ድጋፍ በመስጠትና ከሲዝላ ወጣቶች ፋውንዴሽን ጋር ተባብሮ በመስራት፤ በአሜሪካ ፍዐሎሪዳ በችግር ላይ ያሉትን መልሶ በማቋቋም እና ወደ ትውልድ ምድር የመመለስን እንቅስቃሴ በተለያዩ የመጠጊያ ማዕከሎችን በማነቃቃት እንዲሁም ትውይ፤ ኤዌ፤ ዮሩባ እና ፓታዋ (Twi, Ewe, Yoruba, Patwa) የተባሉ የአፍሪካ ቋንቋዎችን በማስተማር ሰፊ ፕሮጀክቶችን እያከናወነ ነው፡፡
 “CHESS” ፋውንዴሽን በዓለም ዙሪያ በጥቁሮች መካከል ያለውን ክፍተት እያጠበበ መምጣቱን የምትናገረው ማማ አፍሪካ፤ ስኬታማ ጥቁር ማኅበረሰቦችን በማስተባበር ለተቸገሩ አፍሪካውያን ምግብን ፣ ልብሶችን እና መጠለያዎችን በማቅረብ እየሰራን ነው ብላለች፡፡
የባርነት ማብቃት እና
ወደ ትውልድ ምድር የመመለስ ጉዳይ
የማማ አፍሪካ የኢትዮጵያ ጉብኝት በየዓመቱ ጁን 19 ላይ በአሜሪካ 47 ግዛቶችና በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቁር ህዝቦች Juneteenth በሚል ስያሜ ከሚያከብሩት ልዩ  በዓልም ጋር ተያይዟል። በመላው አሜሪካ የሚገኙ ጥቁር ህዝቦች ከባርነት የተላቀቁበት ሳምንት የታወጀው ልክ ማማ አፍሪካ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት በገባችበት ወቅት ነው፡፡  ከ400 ዓመታት በፊት በትራንስ አትላንቲክ የባርያ ንግድ ከ10 ሚሊዮን በላይ አፍሪካውያን ወደ ሰሜን አሜሪካ ተግዘዋል፡፡ ከእነሱም መካከከል ከ2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት አሜሪካን ሳይረግጡ ነው ህይወታቸው ማለፉንም ታሪክ ያስታውሳል፡፡
በየዓመቱ ከሰኔ 6-12 ለአንድ ሳምንት የሚዘከረው በዓሉ ዘንድሮ ለ135ኛ ጊዜ የሚከበር ሲሆን  በእነዚህ ጊዜያት በአሜሪካ ውስጥ እና በመላው ዲያስፖራ የሚገኙ አፍሪካውያን ከአፍሪካዊ የዘር ግንዳቸው እና ባህላቸው ጋር እንደገና ለመገናኘት መቸገራቸውን ያስተዋለችው ማማ አፍሪካ፤ ‹‹ወደ እናታችን ወይም ወደ አባታችን መሬት፣ የትውልድ ምድር እና ማንነት ለመመለስ በአእምሮ፣ በመንፈስ፣ በሃብት እና በባህል ሙሉ ዝግጅት ያስፈልጋል›› በሚለው ምክሯ እየተንቀሳቀሰች ነው፡፡በአሜሪካና በመላው ዓለም የሚኖሩ ጥቁሮች ወደ አፍሪካዊ ማንነታቸውና  ባህላቸው በሙሉ አቅም መመለስ ይኖርባቸዋል የሚልአቋሟን WEPATRIATION በሚል ነው የሰየመችው፡፡
Wepatriation ከ5 አመት በፊት  የፈጠረችው ቃል ነው፡፡
‹‹ከእናታችን እና ከአባታችን የዘር ግን እና ከቅድመ-አያቶቻችን መሬቶች  በጋራ መገናኘትን የገለፅኩበት ነው፡፡ በአካል፣ በአእምሮ፣ በመንፈሳዊ፣ በባህል እና በሃብት ወደ ትውልድ ምድር መመለስ ነው ዊፓትሬይሽን ፡፡››
የጋና ዓለም አቀፍ ዘመቻና የአፍሪካ ዳያስፖራዎች አቅም
ከሁለት2 ዓመት በፊት የጋና መንግስት THE YEAR OF RETURN “የመመለሻ ዓመት” (በ2019 እ.ኤ.አ.) በሚል ዘመቻው፤ በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቁር ህዝቦችን አነቃቅቷል፡፡ ወደ አሜሪካ ለባርነት ከተጋዙት አፍሪካውያን 400ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ጋር አያይዞ የታወጀው ዘመቻ ላይ በባርነት ዘመን አፍሪካውያንን ለማጓጓዝ ቁልፍ መተላለፊያ ለነበረችው ጋና ታሪካዊ እና ሁሉንም አፍሪካውያን በምድሯ ለማስተናገድ ያላትን ሃላፊነት ያመለከተ ነበር፡፡ የጋና ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ-አዶ በዳያስፖራ ለሚገኙ አፍሪቃውያን ተመለሱልን ብለው ጥሪ ሲያቀርቡ እንኳን ደህና መጣችሁ እንደሚሉ ቃል በመግባት ጭምር ነው፡፡  ከጋና መንግስት THE YEAR OF RETURN ጋር ተያይዞ ከ235ሺ በላይ ጎብኝዎችን ለማግኘት የታቸለ ሲሆን የቱሪዝም ኢንዱስትሪውም በድምሩ ከ1.9 ቢሊዮን ዶላር በላይ አግኝቷል። የሆቴሎችን፣ የቱሪዝም ሥራዎችንና ሌሎች ተዛማጅ ንግዶችን ጨምሮ የአካባቢውን ኢኮኖሚ እንዲነቃቃ ማድጉም ተመልክቷል። ጋና በመላው ዓለም ለሚገኙ የአፍሪካ ዲያስፖራዎች ቁጥር አንድ መዳረሻ እየሆነች ነው፡፡


Read 638 times