Sunday, 13 June 2021 20:05

12 በመቶ የአለም ህዝብ የኮሮና ክትባት መውሰዱ ተነግሯል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በህንድ ከፍተኛው ዕለታዊ የሞት መጠን ተመዝግቧል

           ከአጠቃላዩ የአለማችን ህዝብ 12 በመቶ የሚሆነው ወይም 932.4 ሚሊዮን ያህል ሰዎች የተለያዩ አይነት የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን መከተባቸውን ፎርቹን መጽሄት ከትናንት በስቲያ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
እስከ ሳምንቱ መጀመሪያ ድረስ በመላው አለም ከ2.2 ቢሊዮን በላይ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች መሰጠታቸውን የጠቀሰው ፎርቹን፣ ከህዝብ ብዛታቸው አንጻር ከ70 በመቶ በላይ ህዝባቸውን ከከተቡት አገራት መካከል ጅብራልታር፣ ማልታና ሲሸልስ እንደሚገኙበት አመልክቷል፡፡
በብዛት በመከተብ የሚከተሉ ሌሎች አገራት ደግሞ፣ እስራኤል በ63.1 በመቶ፣ ቤርሙዳ 63 በመቶ፣ ካናዳ 62.7 በመቶ እንዲሁም እንግሊዝ በ59.8 በመቶ እንደሚገኙበት ዘገባው አስረድቷል፡፡
ቡርኪናፋሶና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አንድም ዜጋ ባለመከተብ ስማቸው ሲጠቀስ፣ ደቡብ ሱዳን 0.1 በመቶ፣ ቤኒን 0.2 በመቶ ህዝባቸውን በመከተብ በዝቅተኛ የኮሮና ቫይረስ ክትባት እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ዜና ደግሞ፣ ኮሮና ቫይረስ በወረርሽኝ መልክ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ በአለማችን የታየው ከፍተኛው ዕለታዊ የኮሮና ቫይረስ ሟቾች ቁጥር ባለፈው ሃሙስ በህንድ መመዝገቡን የዘገበው ሮይተርስ፣ በዕለቱ በአገሪቱ 6 ሺህ 148 ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ለሞት መዳረጋቸውን አመልክቷል፡፡
በህንድ እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ ከ29 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ መጠቃታቸውንና የሟቾች ቁጥርም ከ360 ሺህ ማለፉን ዘገባው አስታውሷል፡፡Read 3151 times