Sunday, 13 June 2021 20:28

ግልጽ ደብዳቤ፤ ለክብርት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ጉዳዩ፦ በመተከል ዘርንና ማንነትን መሰረት አድርጎ በአገው/አማራ ተወላጆች ላይ እየደረሰ ያለውን የዘር ማጥፋት ዘመቻ ለማስቆም እንዲቻል፤ አሳታፊና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ እንዲደረግ ምርጫ ቦርዱን ስለመጠየቅ እኛ በታላቋ ብሪታንያ የምንኖር ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፤ በመተከል ዘርንና ማንነትን መሰረት አድርጎ፣ በንፁሀን ዐማራዎችና አገዎች ላይ እየደረሰ ያለው እልቂት ያሳሰበን፤ የማሕበራችን ዋና አላማ፤ በመተከልና በሌሎችም የአገራችን ዳርቻዎች ሁሉ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በዜግነት ማግኘት የሚገባቸው መብት ሳይሸራረፍ እንዲተገበር፣ የሰው ልጅ መብት በሰውነቱ ታውቆ እንዲከበር የሚታገል መሆኑን እየገለጽን፤ ለየትኛውም የአገራችን ብሔረሰብ በአድሏዊነት የቆመ አለመሆኑን ለቦርዱ ፍጹም በሆነ ቃል ልናረጋግጥ እንወዳለን። ስለሆነም ምርጫ ቦርድ አቤቱታችን ቀና በሆነ መንገድ ተመልክቶና የአገራችን ህገ መንግስትና ኢትዮጵያ የተስማማችበትን የአለማቀፍ ህግ ለማስከበር ሲል ጭምር ያቀረብነውን ማመልከቻ በአዎንታዊነት ተቀብሎት፣ ሁሉም የመተከል ነዋሪዎች እኩል የፖለቲካ ወክልና አግኝተው፣ የንጹሀን ወገኖቻችን ሰቆቃ እንደሚያከትም ተስፋችን የላቀ ነው።
ምርጫ ቦርድ በተቋምነቱም ፕሮፌሽናል በሆኑ፣ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች በመመራቱ በዚህ አጋጣሚ የተሰማንን ደስታ ልንገልጽ እንወዳለን። እንደሚታወቀው የቤኒሻንጉል ክልል የሚባል የአስተዳደር መዋቅር ወያኔ ከመመስረቱ በፊት መተከል የጎጃም ጠቅላይ ግዛት/ከፍለ ሐገር አንደኛው አውራጃ ነበረ። እንደ ኃያሉ የንጉሰ ነገስታችን፣ የአፄ ቴዎድሮስ የትውልድ አውራጃ፣ እንደ ቋራ ቁጥራቸው በጣም ያነሰ፣ በሱዳንና በኢትዮጵያ ግዛት ያለ ቪዛ እየተሸጋገሩ የሚኖሩ የጉምዝ ብሔረሰቦች ሲኖሩበት፤ ነገር ግን የአማራ/አገው ብሔረሰቦች ከሌሎች ነዋሪዎች ጋር ሲወዳደር ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት እንደነበራቸው ሊታወቅ ይገባል። ለዘመናት የዐማራ፣ የአገው፣ የሺናሻና የኦሮሞ ብሔረሰቦች በንግድና በቋሚ የግብርና ስራ ላይ ተሰማርተው ኖረዋል፡፡ የተጣለባቸውን ግብር በመክፈልና ለአገር ልማት የዜግነታቸውን አስተዋጽኦ በማበርከት ይታወቃሉ፡፡ በ1888 ዓ.ም በተደረገው የኢትዮጵያና የጣልያን ጦርነት በመተከል የሚኖሩ የዐማራና የአገው ተወላጆች፣ የጎጃም ንጉስ ከነበሩት ከንጉስ ተክለሀይማኖት ጦር ጋር ዘምተው፣ ለኢትዮጵያ ነጻነት የህይወት መስዋዕትነት በመክፈል አድዋ ድረስ በግራቸው ተጉዘው ተዋግተዋል። እንደገናም በ1928 ዓ.ም ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ዘመን፣ በመተከል የሚኖሩ የዐማራና የአገው ብሔረሰብ ነዋሪዎች በወቅቱ የጎጃም ጠቅላይ ግዛት አገረ ገዥ ከነበሩት ከራስ እምሩ ሐይለሥላሤ ጦር ጋር ተቀላቅለው፣ በሽሬ ግምባር በተደረገው ጦርነት ከመዝመታቸውም በላይ፤በአምስቱ ዓመት የአርበኝነት ዘመን፣ የአማራና የአገው ብሔረሰቦች፣ ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረጋቸውን ታሪክ የሚዘክረው ነው። አፄ ኃይለሥላሤ ከስደት ወዳገራቸው ሲመለሱም የገቡት በመተከል በኩል ነበር። በዚያን ወቅት ለጎጃም አርበኞችና ለንጉሱ ጦር በመተከል ነዋሪ የነበሩ አማሮችና አገዎች፤ መንገድ በመምራትና ከእለት ምግብ እስከ ስንቅ በማዘጋጀት ከፍተኛ እርዳታ
ያደርጉ እንደነበር ተዘግቧል፡፡
በመተከል ልዩ ስሙ በላያ የተባለውም አካባቢ የኢትዮጵያውያን አርበኞች የጦር ሰፈር እንደነበር የሚታወቅ ነው። አጼ ሐይለሥላሤም “ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ” በሚለው መጻሕፋቸው፤ በመተከል የአማራ/አገው ነዋሪዎች ስለአደረጉላቸው መስተንግዶና አርበኝነት አመስግነው ጽፈዋል። ከላይ ከተጠቀሱት ብሔረሰቦች ለየት ያለ የኑሮ ባሕል ያላቸው የመተከል ነዋሪዎች፡- የበርታ፣ የጉምዝ፣ የማኦና የኮሞ ብሔረሰቦች በተለምዶ የጉምዝ ብሔረሰቦች እያልን የምንጠራቸው ናቸው። እነኝህ ብሔረሰቦች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ  ብዙዎቹ ከብት በማርባትና በአደን ስለሚኖሩ፤ ከላይ እንደተጠቀሰው ድንበር ተሻግረው በጎረቤት አገሮችም ይኖራሉ።
በነገስታቱና በደርግ ዘመን በዚህ በመተከል የሚኖሩ ብሔረሰቦች፣ በመተባበርና በመደጋገፍ በጎጃሜነት የሚኖሩ ነበሩ። በተለይም በደርግ ዘመን በመተከል የሚኖሩ ብሔረሰቦች የነበራቸው ቅርርብ፣ ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ የጎጃም የባህል ኪነጥበብ የሚንፀባረቀው ከነዚህ ብሔረሰቦች በተገኙ ከያንያንና ሙዚቀኞችም ጭምር ነበር። ከላይ እንደተጠቀሰው የአማራ/አገው ህዝብ ብዛት ዛሬ ባለቤት ናቸው ከሚባሉት ብሔረሰቦች በእጅጉ ብልጫ እንዳለው ቢታወቅም፣ ዐማራ አገውና ኦሮሞ ብሔረሰቦች የዜግነታቸው መብት ተገፎ፣ የፖለቲካ ውክልና እንዳይኖራቸው ታግደዋል። በዚህም ምክንያት በክልሉና በፌደራል መንግስቱ ውስጥ ወገን የሌላቸው አማራዎችና አገዎች በባርነት ከመኖራቸውም በላይ ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ስለተገደዱ፣ አምራች የነበሩ ገበሬዎች ወደ ሌሎች አካባቢዎች ሄደው በዘማዊነትና ባልባሌ ስራ ተሰማርተው፣ ኑሮአቸውን በችግር ለመግፋት ተገደዋል፡፡
በመተከል የተፈፀሙ ወንጀሎች በአለም ላይ ከሚታወቁ  ጭካኔዎች ሁሉ የከፋ፣ በ21ኛው ከፍለ ዘመን ብቻም ሳይሆን በሰው ልጅ ታሪክ ተፈጽመው የማያውቁ  ናቸው። በዚህ አሰቃቂ ድርጊት ወንጀለኞችንና ይህን አሰቃቂ ወንጀል የማስቆም ሀላፊነት ያለባቸው የፌደራልና የክልል ባለስልጣናት ብቻም ሳይሆኑ፤ ይህን የአረመኔዎች ወንጀል ሰምቶ በዝምታ ያለፈውን የኢትዮጵያን ህዝብ ጭምር፤ በአለማቀፉ ህብረተሰብ ዘንድ የሚያስጠይቀውና የሚያስወቅሰው ነው። ይህ ሁሉ ወንጀል የሚፈፀመው አገራችን ኢትዮጵያ በ1945 ዓ.ም የተባበሩት መንግስታት ሲቋቋም መስራች አባል የሆነችበትንና ተስማምታ የፈረመችበትን ሕግ በመጣስ ነው። በተለይም እንደ እ.ኤ.አ በታህሳስ 10 ቀን 1948 ዓ.ም ፓሪስ ላይ በተደረገው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ፤ 30 መሰረታዊ የሰው ልጆችን መብት እንዲከበሩ የሚያስገድዱ ሕጎች (30 Basic Human Rights List | Universal Declaration of Human Rights) በጸደቁበት ወቅት፣ ኢትዮጵያም በስብሰባው ተገኝታ ከግንባር ቀደምቶቹ አገራት አንዷ በመሆን ስምምነቱን  ፈርማለች። ይሁን እንጂ በወያኔና በብልጽግና ዘመነ መንግስት በመተከልና በአንዳንድ ክልሎች የሰው ልጅ መብት እንዲከበር የሚጠይቁ ዓለም ዓቀፍና የሰለጠኑ ሕጎች የሚተገበሩ ሳይሆኑ፤ በደቡብ አፍሪካ ነጮች በጥቁሮች ላይ
የበላይነታቸውን ያረጋግጡበት የነበረውን የአፓርታይድ ስርአት ዛሬ በአገራችንም ያለ ሀፍረት እየተሰራበት ይገኛል።
 ክብርት ሆይ፤ የምርጫ ቦርድ፣ የአገር መሪዎችን አስመራጭ ተቋም በመሆኑ፤ ለአንድ አገር የወደፊት ዕጣ ፈንታ ወሳኝ ሚና ያለው ነው። በመሆኑም በዚህ ዓመት በሚደረገው የአገራችን  ምርጫ ፤ በእርስዎ የሚመራው የምርጫ ቦርድ ለአገራችን የወደፊት እድል ወሳኝ ሚና ከሚጫወቱት ተቋማት ሁሉ ቀዳሚው ከመሆኑ አንጻር፤ ታሪካዊ ሀላፊነት ተጥሎበታል። ጭምብል ለብሶ ተቋማዊ በሆነ አደረጃጀት፤ በጉምዝ ታጣቂዎችና በኦነግ ሸኔ ስም በአገራችን
እየተካሄደ ያለው የዘር ማጥፋት ግድያ፣ ዘረፋ፣ አስገድዶ መድፈርና የኃብት ውድመት፤ ምክንያቱ ከመነሻው ከዚህ በፊት የነበረው የምርጫ ቦርድ ሕግን ያልተከተለ፣ ሀላፊነት የጎደለውና አድርባይነትን የተላበሰ ምርጫ እንዲደረግ  በመፍቀዱ፤ የዜጎች የመምረጥ የመመረጥ መብትና የፖለቲካ ውክልና እንዳይኖራቸው በመደረጉ ሳቢያ የተፈጠረ ነው። ከዚህም በመነሳት ያለፈው ወደ ጥፋት የመራን የምርጫ ቦርድ አሰራር ታርሞ፤ አገራችንን ከገባችበት ችግር ማውጣት እንዲቻል፣ በእርስዎ የሚመራው የምርጫ ቦርድ:
1/ መሰረታዊ የሰው ልጆች መብት ባልተከበሩበት የምርጫ ወረዳዎች፤ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ ስለማይቻል፤ በመተከል ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች ያሉ የአማራና ያአገው ብሔረሰቦች መብታቸው ተጠብቆ፣ ወደነበሩበት ቦታ እስኪመለሱ ድረስ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ምርጫው እንዲራዘም በትህትና እንጠይቃለን።
ምክንያቱም ሁኔታዎች ተሟልተው ምርጫው በሚደረግበት ወቅትም፤ ሁሉም የመተከል ነዋሪዎች ዘር፣ ቀለም እምነትና ሌሎች የልዩነት መስፈርቶች ሳይቀርብባቸው፤ የመምረጥ መመረጥ እንዲሁም የፖለቲካ ተወካያቸውን የመምረጥ መብታቸው ተጠብቆ፤ አገራችን በተባበሩት መንግስታት በፈረመችው ውል መሰረት እንዲፈፀም እንጠይቃለን።
Universal Declaration of Human Rights (UDHR) by United Nations, signed in Paris on 10 December 1948. 21. ” Right to democracy Everyone has the right to take part in the government of his country, directly or through freely chosen representatives. Everyone has the right of equal access to public service in his country.” ሌሎችም ከተራ ቁጥር 1 እስከ 30 ያሉትም የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
2/ በተረጋጉና የምርጫ መስፈርቱን ያሟላሉ በሚባሉ ክልሎችና የምርጫ ጣቢያዎች ዜጎች በእኩልነትና ወከባ ሳይደርስባቸው መብታቸው ተጠብቆ ምርጫው እንዲካሄድ፤ በተለይም በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት፤ በአንቀጽ 25፣32፣ 38 እንዲሁም ሌሎችም ሕጎች መሰረት፣ ምርጫው ዲሞክራሲያዊና አሳታፊ እንዲሆን የህይወት መስዋዕትነት በከፈሉ ወገኖቻችን ስም በአክብሮት እንጠይቃለን።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
የመተከል የድጋፍ ኮሚቴ በብሪታንያ
ሰኔ 2 ቀን 2013 ዓ.ም


Read 4165 times