Sunday, 13 June 2021 00:00

6ኛው አገራዊ ምርጫ፤ በዓለማቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

በውስጣዊ ውጥረቶችና በዓለማቀፍ ጫናዎች ታጅቦ የሚካሄደው 6ኛ አገራዊ ምርጫ የድምፅ መስጫ ቀን ከሁለት ሳምንት ያነሰ ጊዜ ቀርቶታል፡፡ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ለምርጫው ሂደት የሰጡት ሽፋን ከሌሎች ጉዳዮች አንፃር ዝቅተኛ መሆኑን በቅርቡ የተካሄደ አንድ ጥናት ይጠቁማል። በአንፃሩ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ አገር አቀፍ ምርጫ ላይ ሰፋፊ ዘገባዎችን እያቀረቡ ነው፡፡ የሚበዙት ግን ጨለምተኛነት ያጠላባቸው፣ ከብሩህ ተስፋ ይልቅ ስጋትን የሚያንፀባርቁ ዘገባዎች  ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ እንደውም ምርጫው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ምክረ ሃሳብ እስከ ማቅረብ ሁሉ ደርሰዋል፡፡
ግጭትና ቀውስን በመዘገብ የሚታወቀው አልጀዚራ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ በድረገፁ ባቀረበው ዘገባ፤ ምርጫው የቀረው ከሁለት ሳምንት ያነሰ ጊዜ ቢሆንም፣ አሁንም የፀጥታ ስጋቶች ያሉበት መሆኑን ጠቁሟል። ለምርጫው አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን በማሰራጨትም ረገድ ምርጫ ቦርድ በርካታ ተግዳሮቶች እየገጠመው መሆኑን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ኢትዮጵያውያን 6ኛውን አገር አቀፍ ምርጫው እንዴት ይመለከቱታል በሚል አልጀዚራ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን አነጋግሮ ያጠናቀረውን ሃተታ አቅርቧል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እንደሆነች በዘገባው የተጠቀሰችው ሃይማኖት ፀጋዬ በሰጠችው አስተያየት፤ “በምርጫው ሂደትም ሆነ በምርጫው ምንም ተስፋ አላደርግም፣ ትኩረትም አልሰጠሁትም፤ እንደ ማንኛውም ሰላም ፈላጊ ሰው ሰላም ነው የምፈልገው” ብላለች ለአልጀዚራ፡፡
በ6ኛው አገራዊ ምርጫ በርካቶች ተስፋ ያደረጉትን ያህል ቀላል የማይባሉትም ስጋት እንደገባቸው ያተተው የአልጀዚራ ዘገባ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ተስፋና ስጋት ላይ የተለያየ አቋም እንዳላቸው አመልክቷል፡፡ የፓርቲው አመራርና አባላት በእስር ላይ መሆናቸውን ተከትሎ፣ ራሱን ከምርጫው ያገለለው የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)፤ “ምርጫው ለሃገሪቱ ሠላምና መረጋጋትን አያመጣም፤ እንደውም የነበረውን ችግር ሊያባብስ ይችላል” የሚል ስጋት እንዳለው የዘገበው አልጀዚራ፤ ለምርጫው ከብልጽግና ቀጥሎ በርካታ እጩዎችን ያስመዘገቡት ኢዜማ እና እናት ፓርቲ  በበኩላቸው፣ ምርጫው ወደ ቀጣይ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር የሚመራ መንገድ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸው ጠቁሟል፡፡
የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ተመራማሪና ተንታኝ እንደሆኑ የተጠቀሱት ጎይቶም ገብረሚካኤል በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት፤ “ይሄ ምርጫ ጠንካራ ተፎካካሪዎች በሌሉበት የሚካሄድ ፉክክር አልባ ምርጫ  ነው”  ብለዋል፡፡ ምርጫው በትግራይ ክልል ሠላም በሌለበትና ትግራይን ባገለለ ሁኔታ መካሄዱም በቀጣይ ሃገሪቱ ለምትሻው ጠንካራ የዲሞክራሲ ሽግግር አጋዥ ነው የሚል እምነት እንደሌላቸው ለአልጀዚራ የገለጹት ተንታኙ፤ በምርጫ ክርክሮችም የትግራይን ጉዳይ የሚያነሳ መጥፋቱ በትግራይ ህዝብ ዘንድ  መከፋትን የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡
ይህም ሃገሪቱ በቀጣይ የምትሻውን የአንድነትና ዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ፈታኝ ሊያደርገው ይችላል ባይ ናቸው- የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ተመራማሪና ተንታኙ ጎይቶም ገብረሚካኤል፡፡
መተማመንን መፍጠር ያልቻለ ምርጫ ቆይቶ ሊያመጣ የሚችለው ውጤት በጎ ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም ያሉት የበርሚንግሃም ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ኒክ ቼስማን በበኩላቸው፤ ይህ ዓይነቱ ምርጫ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ያስከተለው የፖለቲካ ቀውስ የሚታወስ ነው፤ አሁንም ጥያቄው የዶ/ር ዐቢይ አስተዳደር ያንን ያለፈው ስርዓት የፈጠረውን ቀውስ ይደግመዋል ወይስ ይሻገረዋል የሚለው ነው ይላሉ፡፡
“በኢትዮጵያ የሚካሄደው ምርጫ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝንባቸው አምስት ምክንያቶች” በሚል ርዕስ የምሁራንና የፖለቲካ ተንታኞችን ሃሳብ አካትቶ በ”ሜል ኤንድ ዘ ጋርዲያን” ላይ ከሰሞኑ የቀረበው ዘገባ፤ በመጀመሪያ ደረጃ ምርጫውን ትርጉም አልባ የሚያደርገው በትግራይ ያንዣበበው የረሃብ አደጋ ነው ይላል፡፡
“ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ፤ የጦር ወንጀል ተፈጽሟል የሚል ጥርጣሬ ባለበትና የረሃብ አደጋ ባንዣበበት ሁኔታ መካሄድ አይችልም” የሚለው ዘገባው፤ ምርጫውን ትኩረት ሳቢ ከሚያደርጉት በዋናነት በትግራይ ያለው ቀውስ ነው ይላል፡፡ ምርጫው የአግላይነትና ከፋፋይነት ባህርይ ያሉት መሆኑ ምርጫውን ተዓማኒ ላያደርጉት ይችላሉ ተብለው ከተጠቀሱ ሁለተኛው ምከንያት ተደርጎ የቀረበ ሲሆን ለዚህም በትግራይ ሙሉ በሙሉ ምርጫ የማይካሄድ መሆኑ፣ በአራቱ የወለጋ ዞኖች፣ በሠሜን ሸዋ፣ በደቡብ ወሎ፣ በቤኒሻንጉል፣ በሶማሌና አፋር አዋሳኞች ያሉ አለመረጋጋቶችና የምርጫ ሂደቶች በሚፈለገው ልክ አለመከናወናቸውን ዘገባው ይጠቁማል፡፡
በምርጫው የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአሁኑ ወቅት ገዢውን ፓርቲ በጠንካራ ፖለቲካዊ አቋሞች እየተገዳደሩት አለመሆኑ ደግሞ ምርጫውን ውጤታማ ላያደርጉት ይችላል ተብሎ የተቀመጠ ሶስተኛው ምክንያት ሲሆን፣ አሁን በምርጫው የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርዎች በገዢው ፓርቲ ላይ ለዘብተኛ አቋም ያላቸው እንደሆኑና ጠንካራ አቋም ያላቸው ፓርቲዎች አመራሮችና አባላት በእስር ላይ እንደሚገኙ በዘገባው ተመልክቷል፡፡
ኦፌኮና ኦነግ ምርጫውን አቋርጠው መውጣታቸው ምርጫውን ውጤታማ ላያደርጉት ይችላሉ ተብለው ከተቀመጡ ምክንያቶች በአራተኛነት የተቀመጠ ሲሆን የእነዚህ ፓርቲዎች ከምርጫው መውጣት በተለይ በኦሮሚያ ክልል ገዢውን ፓርቲ ብቻውን የሚሮጥ ተወዳዳሪ አልባ አደርጎታል ይላል- ትንታኔው፡፡
ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ መሰረታዊ የሆኑ ለውጦችን እያደረገ ቢሆንም፣ አሁንም ከፍተኛ የአቅም ውስንነት ያለበት መሆኑ ምርጫውን በብቃትና በጥራት በማስፈፀም ረገድ እክል ሊፈጥርበት ይችላል የሚለው ዘገባው፤ የምርጫ ቦርድን በሚገባ አለመጠናከር በአምስተኛነት ያነሳል፡፡
በዚሁ የትንታኔ ዘገባ ሃገሪቱ በውጤታማ የምርጫ ሂደት ታልፍ ዘንድ አሁንም ጊዜ ተሠጥቷቸው ሊታሰብባቸው ይገባል የሚላቸውን የመፍትሄ ሃሳቦች ይጠቁማል፡፡
ከእነዚህም አንዱ ተብሎ የተጠቀሰው ምርጫውን አሁንም ቢሆን አዘግይቶ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ለውይይት መቀመጥ የሚል ሃሳብ ሲሆን ሌላኛው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ማጠናከርና ገለልተኛ የፍትህ ተቋማትን ማደራጀት የሚል ነው፡፡
ሮይርተስ በበኩሉ፤ በምርጫው ጉዳይ ላይ ተከታታይ ዘገባዎችን  እያቀረበ ሲሆን እንደ ሌሎቹ ዓለማቀፍ መገናኛ ብዙኃን ሁሉ ምርጫው ከተስፋው ይልቅ ስጋቱ የሚያመዝን መሆኑን አመላካች ሃተታዎች አቅርቧል፡፡
የአሜሪካ መንግስት ምርጫውን አስመልክቶ የሠጠው ምክረ ሃሳብ ከምሁራን አስተያየት ጋር  ተጣምሮ በቀረበበት የሮይተርስ  ዘገባ፤ ከምርጫው በፊት ምርጫውን ምርጫ የሚያደርጉና ሃገሪቱን ከቀደሙት አዙሪቶች አውጥቶ ወደፊት የሚያሻግር ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆን እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል፡፡
ምርጫውን ሊፈትኑ ከሚችሉ ጉዳዮች መካከልም ትግራይን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ያሉ የፀጥታ ችግሮች፣ የምርጫ ቦርድ ለሁሉም አካባቢዎች በብቃት ተደራሽ አለመሆን፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች እስር እንዲሁም ህዝቡ ለምርጫው ያሳየው መነሳሳት ደካማ መሆን ተጠቅሰዋል፡፡
ኦል አፍሪካን ድረ ገፅ በበኩሉ፣ “የ2013 የኢትዮጵያ ምርጫ አደገኛው ወደ አስተማማኝ ደህንነት የመሄጃ መንገድ ይሆን?” በሚል ርዕስ ባቀረበው ዘገባ፣ በምርጫው ሂደት ከታዩ ጉድለቶችና ጥንካሬዎች አንጻር የምርጫውን ተስፋና ስጋቶች በሰፊው ተንትኗል፡፡
ምንም እንኳ ምዕራባውያንና መገናኛ ብዙኃኑ በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ላይ  ያላቸውን ስጋት  በተደጋጋሚ እየገለፁ ቢሆንም፣ ምርጫው ከስጋቱ ይልቅ ይዞት የሚመጣው ተስፋ የሚያመዝን መሆኑን ኦል አፍሪካን ድረ ገፅ በትንታኔው አስፍሯል።
ምርጫው በሰላም ማለፉ አጠራጣሪ አይሆንም፤ ወሳኙ ከምርጫው በኋላ ያለው ነው የሚለው የድረ-ገፁ ትንታኔ፤ በምርጫው አሸናፊ የሚሆነው ቀጣዩን ጊዜ የሚያስተዳደርበት ሁኔታ ቀጥሎ ለሚፈጠረው ወሳኝ እንደሚሆን አመላክቷል፡፡

Read 869 times