Monday, 14 June 2021 00:00

ገና ብዙ ሕዳሴዎች እውን ይሆናሉ!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

 ከስልሳ አራት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ መንግስት፣ ግብፅና ሱዳን የናይልን ውሃ ለመከፋፈል ለድርድር በተቀመጡ ጊዜ፣ ሶስተኛ ባለጉዳይ ሆኖ ለመግባት በተደጋጋሚ ተጠይቆ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ፡፡ በዚህ ጊዜ “ኢትዮጵያ የውሃ ሃብቷን የምታየው በግዛት ክልሏ ውስጥ እንደሚገኝ እንደ አንድ ማዕድን ዓይነት ነው፡፡ ለማልማት በፈለገችና በተነሳችበት ጊዜ ከመጠቀም ሊያዳግታት የሚችል ምንም አይነት ነገር እንደማይኖር እወቁት” በማለት የኢትዮጵያ መንግስት ለሁለቱ አገሮች ሲያሳውቅ መልዕክቱ እንዲደርሳቸው ከተደረጉት አገሮች አንዷ አሜሪካ ነበረች፡፡ ኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳን በሚያደርጉት ድርድር በክብር የታዛቢነት ቦታ የተሰጣት አሜሪካ፤ በጉልበት አራሷን አደራዳሪና ውል አርቃቂ አድርጋ ቀርባለች። አሜሪካ፣ ያዘጋጀችው ውል የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ ለግብጽና ለሱዳን የሰጠ በመሆኑ ተቀባይነት ሲያጣና ኢትዮጵያ ራሷን ከዋሺንግተኑ ድርድር ስታገል፣ የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ያሉትን ሰምተናል፡፡
የታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛው የውሃ ሙሌት መቃረቡን ተከትሎ፣ ግብጽና ሱዳን የምድርና የአየር ወታደራዊ ልምምድ በማድረግ  እራሳቸውን “የናይል ጠባቂዎች” በሚል ሾመው፣ ኢትዮጵያን መጣሁልሽ በማለት ማስፈራራት ይዘዋል። የግብጽ ፕሬዚዳንትና የሱዳኗ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በመጓዝ፣ ኢትዮጵያን ከሌላው የአፍሪካ አገር ለመነጠል የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ነው፡፡ የግብጽ ፕሬዚዳንት አልሲሲ ከኬንያና እንዲሁም፣ ከጅቡቲ ጋር ወታደራዊ ስምምነት አድርገዋል። የዚህ ሁሉ ማንዣበብና መሯሯጥ ግብ፣ ኢትዮጰያ የታላቁን የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት እንዳታካሂድ ማድረግ ነው፡፡ ይህ ሊሆን እንደማይችልና ኢትዮጵያ በውኃ ሃብቷ የመጠቀም መብቷን የሚገድብ አንዳችም አይነት ስምምነት እንደማትፈርም ደጋግማ ገልፃለች፡፡ ሰሚ አልተገኘም እንጂ፡፡
ከተጀመረ ስምንት ዓመት ያስቆጠረው፣ ለጎንደር ከተማ ሕዝብ ለመጠጥ ውኃ አቅርቦት የሚያገለግለውና በመስኖ እርሻ ወደ ስምንት መቶ ሺህ ሄክታር መሬት ያለማል ተብሎ የሚጠበቀው የመገጭ ግድብ ሰባ በመቶ ግንባታው መከናውኑን፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ በመጪዎቹ ዓመታት አንድ መቶ አነስተኛና መካከለኛ ግድቦችን እንደምትገነባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሰሞኑን መግለጻቸው፣ የግብጽንና የሱዳንን የደም ግፊት  ከፍ አድርጎት ሰንብቷል፡፡ ከመቶዎች ውስጥ  የኮራ ዶቢ፣ የባኮ መንዲና ጨሞጋ ወዘተ ወንዞች  እንደሚገኙበት ይታመናል። እነዚህ ወንዞች ይዘውት የሚመጡት ጸጋ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያስፈልገውና የሚጠቅመው ጉዳይ ነው፡፡
ግብጽ በላይኛው የናይል ተፋሰስ አገሮች የክረምት ዝናብ ውሃ መያዥያ ግድቦች በመስራት ውኃ እንዲያከማቹ፣ ውሃውንም ለመብራት ማመንጫ ብቻ እንዲገለገሉበት፣ ከዚያም በማድረግ ውኃቸውን አከማችተው ለእርሷ እንዲሰጧት ትሻለች፡፡ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ለሱዳንና ለግብጽ የውሃ ማጠራቀሚያ ባንክ ለማድረግም ፅኑ ፍላጎት አላቸው፡፡ በውኃ አሞላሉና በአስተዳደሩ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር አሳሪ ስምምነት መዋዋል አለብን ብለው የሚወተውቱትም ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ አሳሪ ውል ትግባልን የሚለው ጩኸትም የህዳሴውን ግድብ፣ ኢትዮጵያ በራሷ ወጪ ሰርታ ለግብጽና ለሱዳን የውሃ ማጠራቀሚያ ሆኖ እንዲያገለግል ለማድረግ ከማሰብ የመነጨ ነው፡፡ ለዚህ ሴራ እጇን መስጠት የማትፈልገው ኢትዮጵያ፤ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ፊቷን ወደ ምሁሮቿ አዙራ በዩኒቨርሲቲ ልሂቃን በሚቀርቡ ሃሳቦች ለመደገፍ ቆርጣ የተነሳች ሆናለች፡፡ ልዮ ልዩ ጥናቶችን በመጠቀምም ያለመችውን ከግብ ለማድረስ እየተጋች ነው። እየተንቀሳቀሰች መሆኑ እየታየ ነው፡፡ “ህዳሴ ግድቡን እውን ለማድረግ  የዜጎችና የምሁራን ድርሻ” በሚል ርዕስ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደ ጉባኤ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። በዚህ ጉባኤ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ የውሃና የመስኖ  ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፤ “አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ በንጹህ ውሃ መጠጥ እየተቸገረ እያለ በቢሊዮን ሜትር ኪዩብ የሚቆጠር ውሃ ከኢትዮጵያ  ከድንበሯ የምታስወጣበትን መንገድ ለመለወጥ መንግስት እየሰራ ነው” ሲሉ ያደረጉት ንግግር የሚያመለክተው አዳዲስ ሕዳሴዎች የሚመጡት ሰሜን ብቻ ሳይሆን በመላ ኢትዮጵያ መሆኑን ነው፡፡
አቦ ይህን ሃሳብ መሬት ወርዶ ለማየት ፈጣሪ ያብቃን!

Read 1297 times