Print this page
Tuesday, 15 June 2021 18:24

ኢትዮጵያዊው የቦክስ አሰልጣኝ በአሜሪካ

Written by  ዘነበ ወላ
Rate this item
(0 votes)


           *ሃንጋሪዎች ቦክስ በዓለም ላይ የተጀመረው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ይላሉ
           *የቦክስ ሥልጠና ጠባይና ባህርይን ለማረምና ለማረቅ ይረዳል
                 
            ከዕድሜው ሶስት አስርቱን ያሳለፈው በቦክስ ስፖርት ነው፤ መጀመሪያ ተጫዋች ነበር፡፡ በኋላም የአሰልጣኝነት ኮርስ በጀርመንና ሃንጋሪ ወስዶ የተዋጣለት የቦክስ አሰልጣኝ ሆነ፡፡ ዛሬም በአገረ አሜሪካ በዚሁ ሙያ ላይ ተሰማርቶ ይገኛል። ከእንዳልካቸው አርጋው (ግምት) ጋር ከተለያየን ከ15 ዓመታት በኋላ በቅርቡ ወደ አገር ቤት መጥቶ ተገናኘን፡፡ ወደ “አንድነት ፓርክ” ከልጁ ጋር ይዤአቸው በመሄድም ፓርኩን አብረን ጎበኘን፡፡ እግረ መንገዴን ሻይ ቡና እያልን ታዲያ እንደሚከተለው ተጨዋወትን።  
እስቲ ስለ ቦክስ አጀማመርህ አጫውተኝ….?
የቦክስ  ጓንት በህይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ አጥልቄ መድረክ ላይ የወጣሁት አስመራ ውስጥ ነው፤ ስለዚህ ለኤርትራ ህዝብ ጥሩ ፍቅር አለኝ፡፡ አስመራ የማውቃቸው የአዲሱ ትውልድ አባሎች ባልተሟላ ሁኔታ የቦክስ ስፖርት ሲሰሩ በኢንተርኔት አየሁ፡፡ ይህ ልቤን ነካውና ለምን አንድ ነገር አላደርግም ብዬ ወሰንኩ፡፡ እንደምታየው ሀያ ጥንድ ጓንት፣ አንድ ፓድ፣ አንድ “ቦዲፓህ”፣ ሀያ የአዋቂዎች ባንዴጅ፣ አስር  የህጻናት ባንዴጅ፣ እንዲሁም ለሁለቱም የሚሆኑ የጥርስ መከላከያ ይዤ መጥቼ ለኢትዮጵያ ቦክስ ፌደሬሽን አስረክቤያለሁ፡፡ ግማሹ ለኤርትራ ቦክሰኞች የሚላክ ነው፡፡ ይህንን ለመሸመት በርካታ ገንዘብ አውጥቻለሁ። ይህንን ወጪ የሸፈንነው እኔና  ቤተሰቦቼ ነን፡፡ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌደሬሽን በእኔና በፌደሬሽኑ ስም አስመራ ወስዶ እንዲያስረክብልኝ ተስማምተናል፡፡ እኔ የምመለስበት ቀን በጣም ስላጠረ አስመራ በአካል ተገኝቼ ስጦታውን ማበርክት አልቻልኩም፡፡ ስለዚህ አንተ እኔን ወክለህ ትሄድልኛለህ፣ የቦክስ ፌደሬሽኑ  ከቻለ ሰው  ይወክል፤ ካልቻለም አንተ ትጥቁን ተረክበህ አድርስልኝ፡፡ ትጥቁን ወደ አገር ውስጥ ሳስገባ 18 ሺ ብር ቀረጥ ከፍያለሁ፡፡ ይህን ፌደሬሽኑ እንደሚመልስልኝ ቃል ገብቶልኛል፡፡ አንተ ግን በኤርትራ ላይ  መጻሕፍት ስለምትፅፍ፣ የጋራ አገራችንም ስለሆነች፣ በራስህ ወጪ አደራዬን ብታደርስልኝ ደስተኛ ነን፡፡
ቆዘምኩ፡፡ ግምት እንዳለው ኤርትራ አገሬ ነች፡፡  የወጣትነት ህይወቴን ያሳለፍኩባት ነች፡፡ እንዳለውም የመጻሕፍቶቼ ምንጭ ነች፡፡ ነገሩ እንዲህ ድንገት ሲሆን ብቻ ግር አለኝ፡፡ መጀመሪያ የተስማማነው አብረን ለመሄድና ትዝታችንን እያወጋን ለአንድ ሳምንት ያህል ቆይተን ለመመለስ ነበር። አሁን እንደሚነግረኝ፤ የእሱ አለመኖርና የእኔ ብቻዬን መሆን ግራ ቢያጋባኝም፣ “ቃል የእምነት እዳ ነው” እንደሚለው ፀጋዬ ገ/መድህን፣ በእሽታ ተቀበልኩት፡፡
ቦክስ አስመራ ውስጥ ጀምሬ ነበር፡፡ አዲስ አበባ ከመጣሁና ተጨማሪ ስልጠና ከወሰድኩ በኋላ ችሎታዬ አደገ፡፡ ጥሩ ተቧቃሽ ወጣኝ፡፡ የአዲስ አበባም ክለቦች ሻምፒዮና እንዲሁም የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ብዙ ጊዜ ሆኛለሁ፡፡ ቀደም ብሎ ስም አልባ የነበረው የባህር ኃይል  ቦክስ ክለብ፣ በ1980ዎቹ ገናና ተጠቃሽ ክለብ  እንዲሆን እኔና ጓደኞቼ ጠንክረን ሰርተን ዝነኝነትንም አግኝተናል፡፡
እኔ በ1978 ዓ.ም የጦር ኃይሎች ሻምፒዮና እንዲሁም የኢትዮጵያ ሻምፒዮና በመሆን የወርቅ ሜዳሊያዎችን ወስጃለሁ። በወቅቱ እኔና ሙጋቤ የሚባል የማዕከላዊ እዝ ቦክሰኛ ያሳየነው ጨዋታ ተአምር ነበር፡፡ ሁለት ዙር እኩል ብንቀጣቀጥም፣ ሶስተኛው ዙር ላይ እኔ በማየሌ አሸናፊ ሆኛለሁ፡፡ የሚገርመው ማሙሽ የሚባለው ጓደኛችን አስመራ እያለን “ግምት አዲስ አበባ ላይ ሙጋቤን ካልዘረርክ ወንድ አይደለህም!”   ይለኝ ነበር፤ እንዳለውም ሆነ፡፡ ከዚያ በኋላ ከፊቴ ቦክሰኛ ነኝ ያለ አይቆምም! ጥሩ የአካል ብቃት ላይ ነበርኩ፡፡ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እያለሁ ወደ ጀርመን ለአሰልጣኝነት ኮርስ ሄድኩ፡፡ እዚያም ሳለሁ በውድድር እሳተፍ ስለነበር፣ በጀርመን ሻምፒዮና ሆኜ፣ የአገሪቱ ትልቅ ጋዜጣ ስለ እኔ በሰፊው  በፊት ሽፋኑ ላይ ዘግቧል፡፡ ከጀርመን ከተመለስኩኝ በኋላ ባህር ኃይል ውስጥ በአሰልጣኝነት ማገልገል ጀመርኩ፡፡ አንድ አደረግሁት ብዬ የማስበው፣ የቦክሱን ውጤት ለመቀየር ጥሩ ምክንያት ሆኛለሁ፡፡ የባህር ኃይል ሻለቃ ክለብ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት እንዲሆን አድርጌያለሁ፡፡ ኢህአዴግ ሥልጣን እስከያዘበት ጊዜ ድረስ ይህ ውጤታችን እንደተጠበቀ ቀጥሏል፡፡ ምን አለፋህ፤ 75% የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች የባህር ኃይል ክለብ ነበሩ፡፡
ለመሆኑ ትክክለኛ ስምህ ማነው?
እኔ ወላጆቼ ያወጡልኝ ስም አለምሰገድ ገዛኸኝ ነው፡፡ ባህር ኃይል ልቀጠር ስል  “በፎርጅድ” ሰርተፊኬት “እንዳልካቸው አርጋው” ተብዬ ተቀጠርኩ፡፡ ግምት የሚለውን ቅጽል ስም አብረን የተቀጠሩት ልጆች ናቸው ያወጡልኝ፤ መጀመሪያ እንደውም “የሃምሳ ሰው ግምት ነበር!”  የሚሉኝ፤ በኋላ  አጥራ ነው “ግምት” የሆነችው፡፡ አሁን ሁሉም ሕጋዊ ዶክመንቶቼ በእንዳልካቸው አርጋው ነው የሚታወቀው።   አለምሰገድን የሚጠቀሙት ወዳጆቼ ብቻ ናቸው፡፡
ሀንጋሪ የሄድክበት ምክንያት ምን ነበር?
ኢንተርናሽናል የአሰልጣኝነት ኮርስ ለመሰልጠን ነበር የሄድኩት፡፡ መሄዱን አልፈልገውም ብዬ ለቦክስ ፌዴሬሽን ደብዳቤ ፅፌ ነበር፡፡ ከዛም የፌደሬሽኑ ፀሐፊ አቶ ጌታቸው ተረፈ አግባብቶኝ መስፈርቱንም እንደሟሟላ በመገመት፣ ሀሳቤን ቀይሬ እንድሄድ አደረገኝ፡፡ በወቅቱ እኔ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ደረጃ ላይ ነበርኩ፡፡ የኛ ቡድን ግሪክ ኦሎምፒክ ሲሄድ ነበርኩበት፡፡ ይህ ስልጠና ሲመጣ አንድ ኩባዊ አሰልጣኝ ከእኛ ጋር ይሰራ ስለነበር እድሉ ለእርሱ ተሰጠው፤ ግን ቦክሰኞቹ በእኔ መሄድ ላይ ተወያየን፡፡ ከሰውየው ጋር  አብረን ነው ቡድኑን የምናሰራው፡፡ በመላው አፍሪቃ ጨዋታዎች በናይጄሪያ ሁለት ልጆች አሸንፈውልናል፡፡ የሃንጋሪው እድል ለእኔ ሲሰጠኝ ተቀበልኩት፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ አሻጥሮችን አስተውል ስለነበር፣ ቦክስም ተቀባይነቱን በአገር ውስጥ ስላጣ፣ መከላከያ ሰራዊትም ቦክሰኛ ማጫወትን ስላቆመ፣ በአጠቃላይ ወደ  ሀገሬ መመለሴ እንደሌለብኝ ወሰንኩ፤ ውስጤም ቆረጠ፡፡
የሃንጋሪው ስልጠና የተሰጠን ለቻይና ኦሎምፒክ እንድንዘጋጅ ነበር፡፡ ሃንጋሪ የተሠጠኝን ስልጠና በጥሩ ውጤት አጠናቀቅሁ፤ እንዳልኩት ወደ ኋላ መመልከት አልፈለኩም፡፡ ሃንጋሪን ጥገኝነት ጠየቅሁ፤ ወዲያውኑ ተቀበሉኝ፡፡ ከእኔ በፊት ጥገኝነት ጠይቀው ዓመት ሁለት ዓመት የቆዩ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ የእኔን ጥገኝነት የተቀበሉኝ ግን በአምስት ወር ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ አንደኛ- ውጤቴንም ያውቃሉ፣ ሁለተኛ- ያለፈ ታሪኬንም ያጠናሉ፣ ሶስተኛ- እኔ የየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባል ባልሆንም ሲኮበለል ግን ይዋሻል፡፡ ስለዚህ በወቅቱ የነበረው የምርጫ 97 ግርግር ለእኔ ከለላ በጣም ጠቅሞኛል፡፡ የቅንጅት አባል መሆኔን ተናገርኩ፡፡ ያለ ብዙ ውጣ ውረድ ጥገኝነት ሰጡኝ፡፡
ሃንጋሪ ምን ያህል ጊዜ ቆየህ?
ሃንጋሪ ውስጥ ወደ ሰባት ዓመታት ያህል ቆይቻለሁ፡፡ እዚያ የመጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጅ ገባሁ፣ ተማርኩ፡፡ እዚያ የሚኖሩትን ፓስተሮች፣ አስተማሪዎችና ቤተሰቦቻቸውን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አሰራ ጀመር፡፡ ወጣቶቹ የቦክስ  አሰልጣኝ መሆኔን ስለሚያውቁ ቦክስ አሰራን አሉኝ። አሰራቸው ጀመር፡፡ ይህንን ያዩት ከፍተኛ ኃላፊዎቹ፣ ወደ አሜሪካን የምሻገርበትን ሁኔታ አመቻቹልኝ፡፡
የትዳርስ ነገር?
አዲስ አበባ እያለን ፍሬህይወት አለነህ የተባለች ፍቅረኛዬ ነበረች፡፡ ሐንጋሪ ጠራኋትና መጣች፡፡ ተጋብተን የመጀመሪያ ልጃችንን ወለድን፡፡ የሐንጋሪ ዋና ከተማ ቡናፔስት ነው፡፡ እኛ ግን ቫይካ በምትባል 1000 ሰዎች ብቻ  በሚኖሩባት ሚጢጢ ከተማ ውስጥ ነበርን፡፡ በሕይወቴ ለሰው ከፍተኛ ፍቅር ያየሁበት አገር ሐንጋሪ ነው፡፡ እናም  ሰው ለእነሱ እኩል ነው፡፡ ከመምህራኑ ውስጥ አሜሪካውያን ይበዙበታል፣ እንግሊዛውያንም አሉበት፣ ተማሪዎች ከሩሲያ ከቻይናም ነበሩበት፡፡ የሚበዛው የአገሪቱ ዜጋ ነው፡፡ የሚገርመኝን አንድ ነገር ልንገርህ፡፡ ሐንጋሪያን ቦክስ በዓለም ላይ የተጀመረው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ብለው አስተምረውናል፡፡ ይህ ያስደንቀኛል፡፡ ጀማሪ ከሆንን ታዲያ ዛሬ ለምን ወደ ኋላ ቀረን ስል ሁሌ አስባለሁ፡፡ እኛ ያለን መረጃ ከጣሊያን ወረራ በኋላ ይህ ስፖርት አንደተጀመረ ነው። ስለዚህ ይህ የሐንጋሪዎች መረጃ ለታሪክ ተመራማሪዎች ፍንጭ የሚሰጣቸው  ይመስለኛል፡፡ ይህንን ታሪክ የተማርኩት በኢንተርናሽናል የቦክስ አሰልጣኞች ኮርስ ላይ ነው፡፡ ይህንን ስሰማ አንድ የተደበቀና የጠፋ ታሪክ እንዳለ ተገንዝቤያለሁ፡፡
እሺ አሜሪካስ እንዴት ገባህ?    
ቀደም ብዬ እንዳልኩት እዚያ መጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጅ የስፖርት አሰልጣኝ ሆኜ ሳለሁ፤ አንድ ሰው አነጋገረኝ፡፡ “አንተ ቦክሰኛ ነህ፣ ይህ ስፖርት አሜሪካ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ነው፡፡ አሜሪካን ሄደህ እድልህን ብትሞክር?” አለና የምሄድበትን አካባቢ በፊልምም በመጻሕፍትም አስደግፎ አሳየኝ። “ደስ ይለኛል፣ ባለቤቴን ላማክር” አልኩና ተሰነባበትን፡፡ ከዚያም “ከወደድከው ሄደህ አይተህ እንድትመጣ ለ20 ቀን ሁሉንም  ወጪህን ችለን እንልክሀለን” አሉኝ - ተስማማሁ፡፡ ባለቤቴም ተስማማች፤ ግብዣውን ተቀብዬ አሜሪካን ሄድኩ፡፡
የሄድኩበት ሰፈር በጣም የሚያስፈራ ሰፈር ነው፡፡ አደንዛዥ ዕጽ (ድራግ) በመውሰድ የደነዘዙ ሰዎች  በብዛት አሉበት። ወጣቶቹን ብታያቸው በጣም ታዝናለህ፡፡ በጣም ሱሰኛ ሆነዋል፡፡ በአንዱ ጥግ ላይ ሰው ሞቶ ማየት የተለመደ ነው፡፡ እኔ ጎብኝቼ ከወደድኩት ወጣቶቹን እንዳሰለጥን የወሰዱኝ እዚያ ሰፈር ነው፡፡ በእነሱ አስተሳሰብ በቦክስ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በመስጠት፣ ወጣቶቹን ከገቡበት ድብርት ማውጣት ይቻላል፡፡ እኔም እንደገባሁ ነው ስራ የጀመርኩት፡፡ እየሰራሁ ጥናቴን አካሄድኩ። በቦክስ ስፖርት ወጣቶቹን ማዳን ከቻልኩ መሞከር እንዳለብኝ ወሰንኩ፡፡ አገር ቤት እያለሁም ይህ ልምድ በተወሰነ ደረጃ አጋጥሞኛል፡፡ አንዴ ከሀዋሳ አንድ ወጣት መጣ፣ አለባበሱ ጎስቋላ ነው፡፡ ያደረጋት ነጠላ ጫማ  አሮጌ ናት፡፡ የአልኮል መጠጥ ይጠጣል፣ ተደባዳቢ ነው፡፡ በቀጥታ መጥቶ ቦክስ አሰልጥነኝ አለኝ፡፡ ተቀበልኩትና፣ አስፈላጊውን እገዛ አደረግሁለት፤ ስልጠናውን ጀመረ፡፡ ይህንን ያዩት የአዋሳ ልጆች ማንነቱን ነግረው ተቃወሙ፡፡ እኔ ደግሞ አስተካክለዋለሁ ብዬ ተቀበልኩት። ስልጠናውን እየወደደው ሲመጣ፣ እኔ ደግሞ ለቦክሰኛ ከሱስና ከአንባጓሮ የፀዳ ፀባይ እንደሚያስፈልገው እመክረው ነበር። በዚህ መልኩ አስተካክየው ከኢትዮጵያ አልፎ ቱኒዝያ ደረስ ሄዶ ተወዳድሯል፡፡ እኔ አሰልጣኙ ነበርኩ፡፡ በአሜሪካንም እነዚያን በአደንዛዥ ዕጽ የደነዘዙ ወጣቶች፣ የቦክስ ስልጠና በመስጠት ከሱሳቸው ማውጣትና ማረቅ ነው የተፈለገው፡፡ ስፖርቱን ሰርተው እንዳጠናቀቁ የመፅሐፍ ቅዱስ ትምህርት ይሰጣቸዋል፡፡ ወደው ይከታተሉት ጀመር። እኔም ይህንን ሃላፊነት  ተቀብዬ መስራት ጀመርኩ፤ በዚህም ደስ የሚያሰኙ ውጤቶችን አግኝቻለሁ፡፡
ባለቤቴም ሐንጋሪ የወለድነውን የመጀመሪያ ልጃችንን ይዛ አሜሪካ  መጣች። የተቀሩት ልጆቻችን በአሜሪካ በተከታታይ ተወለዱ፡፡ እኔም በርካቶችን በቦክስ ስልጠና ከገቡበት አዘቅት ውስጥ እንዲወጡ ለማድረግ ከስራ ባልደረቦቼ ጋር በእጅጉ ጣርኩ፤ ተሳካልኝም፡፡ እውነቱን ለመናገር በጣም ፈታኝ ነበር፡፡ የቤተሰብ መፍረስ በአንድ ወላጅ ብቻ ማደግ ያለውን የኑሮ ጣጣ ስታየው…. አሜሪካ ያለህ አይመስልህም። ያም ሆነ ይህ በሺ የሚቆጠሩ ወጣቶችን ከዚህ ዘግናኝ ችግር እንዲገላገሉ አድርገናል፡፡
ማሰልጠኛው የማነው?
በአንድ ቤተ ክርስቲያን የሚረዳ ማሰልጠኛ ነው፡፡ መስራቹ ድሮ የብሔራዊ ቦክስ ቡድን ተጫዋች ነበር፡፡ ቦዲ ሐዝቦርን ይባላል፡፡ እሱ ራሱ በዚህ ችግር ምክንያት ለእስር ተዳርጓል፤ ተጎሳቁሏል፡፡ ስለዚህ ይህን አይነቱን ችግር ለመቅረፍ፣ ይህ አይነቱን ስልጠና መስጠቱን አምነውበት የመሰረቱት ስለነበር፣ የተፈለገውም ውጤት መጣ፡፡ ሐዝቦርን መጀመሪያ ወንጀለኛ ሆኖ የተሳሳተውን መንገድ በጥልቀት ሄዶበት፣ ተገቢውንም ቅጣት በማግኘቱ፣ አገሩን ለመካስ የመሰረተው ተቋም እንዳሰበው ውጤታማ ሆኗል፡፡ በእንዲህ አይነት ሁኔታ ለውጤት የበቁ ልጆችን ማፍራት ብዙ ጥረት ይጠይቃል፡፡ ትልቁ ተግባር  ግን ልጆቹ ዳግም የአደንዛዥ እጽ ሱሰኛ እንዳይሆኑ መጠበቅ ነው፡፡ ያም ሆኖ ለብሔራዊ ቡድን ደረጃም የደረሰ ልጅ አሰልጥኜ ነበር፤ ልጁ ወደ “ፕሮፌሽናል” ደረጃ አደገ። እናም በዝረራ ነው የሚያሸንፈው፡፡ ሜኒ ፑል ይባላል፡፡ ኢንተርኔት ውስጥ ገብተህ ብትፈትሽ ታገኘዋለህ፡፡
 ለቃለ ምልልሱ አመሰግናለሁ!
እኔም እግዜር ይስጥልኝ፡፡  ከልብ አመሰግናለሁ!Read 1460 times