Wednesday, 16 June 2021 00:00

ባለሃብቱን ለመመረቅ ደጅ የጠኑት አዛውንት

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

  እጅግ ግዙፍ የሆነውና 5.2 ቢ.ብር የፈጀው WA ኢንዱስትሪያል የዘይት ፋብሪካ የምረቃ ዝግጅት የተጀመረው ከሳምንት ቀደም ብሎ ነው፡፡ የምርቃቱ ዋዜማ ደግሞ እሁድ ግንቦት 29 ቀን 2013 ነው፡፡ የተጀመረውም ለበርካታ መገናኛ ብዙሃን የዘይት ፋብሪካው ባለቤት አቆ ወርቁ አይተነው ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠት ነበር፡፡ በእርግጥ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውን፣ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከነቤተሰቦቻቸው ጨምሮ በርካታ ድምፃዊያን ተዋንያን፣ ባለሃቶች በደብረ ማርቆስ ከትመው ነበር፡፡
ከዚህ ሁሉ ሰው ለዚህ ፅሑፍ አዘጋጅ አንድ ቀልብ የሳበ ልዩ እንግዳ ዕሁድ በፋብሪካው የምረቃ ዋዜማ ፋብሪካው በር ላይ አስገቡኝ አናስገባም ከጥበቃዎች ጋር ክርክር ገጥመዋል፡፡ ቁመተ ረጅም፣ መልከ መልካምና አለባበሰ ሸጋ ናቸው፡፡ አዛውንቱ ለምን በዚያ ቦታ ተገኙ፣ ከየት አካባቢ ነው የመጡት? ለመሆኑ እኚህ ሰው ማን ናቸው? ለስራ ደብረማርቆስ ከተማ የነበረችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከነዚህ ልዩ እንግዳ ጋር
ቆይታ አድርጋለች- እነሆ፡፡


                 እንተዋወቅ አባቴ?
አንጋፋው አርቲስት ስማቸው ዘመረ እባላለሁ፡፡
ትውልድና እድገትዎ የት ነው?
ክልል ሶስት ምስራቅ  ጎጃም ዞን፣ ሁለት እጁ እነሴ ወረዳ፣ ሞጣ ቀራኒዮ ደብረ ጉባኤ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ገንገርታ ነው ነዋሪነቴ፡፡
ራስዎን ሲያስተዋውቁኝ “አንጋፋው አርቲስት” ነኝ ብለዋል፡፡ አንጋፋ የሚያሰኝዎት ምን ምን ስራ ሰርተዋል?
በብዙ ነገር  ታፍኜ ነው እንጂ ለምሳሌ ግጥም በመግጠም አጠገቤ የሚደርስ የለም። ለምሳሌ ከአበበ ብርሃኔ ጋር ተወዳድረን  በፈጠራ ቀድሜዋለሁ፡፡
መቼ ነበር ይሄ የሆነው?
ኧረ ቆይቷል፡፡ ያን ጊዜ ካሴቱን እንዳወጣሁት በ1998 ዓ.ም ነው፡፡
ምን የሚል ካሴት ነበር ያወጡት?
“ሌፎ ለፎ” የሚል ካሴት አውጥቼ ነበር። ያንን ወስደው ለሌላ አርቲስት ለዳኜ ዋለ ሸጡብኝ፡፡ እኔ አዳማጭም የለኝ፣ ለማን ልክሰስ? ታፍኜ ነው ያለሁት፡፡
ምን ማስረጃ አለዎት የእርስዎ ዘፈን ለዳኜ ዋለ ለመሸጡ?
እስከ ግጥሙ እስከ ክሊፑ ድረስ እኔ የሰራሁት ነው፡፡ አንቺ የጋገርሽው እንጀራ ይጠፋሻል እንዴ? የራሴ ስራ እንዴት ይጠፋኛል፡፡ ተይ እንጂ፡፡ ብጮህ ብጮህ የሚሰማኝ አጣሁ´ኮ፡፡
አሁን ያገኘህዎት ደብረ ማርቆስ WA የዘይት ፋብሪካ በር ላይ ነው፡፡ ከየት ነው የመጡት? ለምንስ ነው የመጡት?
የመጣሁት ከሞጣ ነው፡፡ አመጣጤ አቶ ወርቁ አይተነውን ለመመረቅና ለማመስገን ነው?
አቶ ወርቁ አይተነውን ያውቋቸዋል ማለት ነው?
አዎ አውቀዋለሁ፡፡ ወጣት ወርቁ  አይተነው ማለት የአገር መብራት ማለት ነው፡፡ አንድ ጊዜ አንዳንድ ቦታ ስንዘዋወር አግኝቼው ግጥም ገጠምኩለትና ሸለመኝ፡፡ ይህንን ግጥም አብረሽ ብታስተላልፊው ደስ ይለኛል፡፡ ግጥሙ ይቅደምና ከዚያ በላይም ትጠይቂኛለሽ፡፡
እሺ ግጥሙን ይቀጥሉ አጠር አድርገው…?
ተመስገን ጌታዬ በተወለድኩበት
ባደግኩበት ሞጣ
አንክብክቡ ወርቁ በሊኮፍተር መጣ
መስጠት እንደ ወርቁ ማን አውቆ ማን   
አውቆ
ይሞታል ባላገር በድሪቶ ታንቆ…
እንደምነው ጎጃም እንደምነው ጎንደር
እንዴት ነው በጌምድር
እየከዳ እምቢ አለ ወዳጅና ምድር
መሬቱም እምቢ አለ ማዳበሪያ ለምዶ
ትንሽ ባሳንሰው አከረመኝ ባዶ፡፡
ዝናብ እንኳ አልጣለ ምንድን ነው
መብረቁ
ለስሜ ሸልመው እንክብክቡ ወርቁ፡፡
…አልኩት ሸልሞኛል፤ እድሜው ይርዘም።
ምን ሸለመዎት?
100 ሺ ብር ሸለመኝ፡፡ ይሄውልሽ የሶስት ዓመት የመሬት ክርክርና ሙግት የተሟገትኩበት ብዙ ብድር ነበረብኝ፡፡ ሶስት ሚኒዎል (ሚሊዮን ማለታቸው ነው) ብር የሚያወጣ መሬት ተቀምቼ የወያኔ ጁንቶይ (ጁንታዎች ማለታቸው ነው) በልተውብኝ  እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ብሄድም ተስፋ ሳላገኝ ስልክ ቁጥር ተሸክሜ ብዞርም፣ ዶ/ር ዐቢይን በአካል አላገኘው አልኩኝ፡፡ ከዚያም እነ አንተነህ ተሻገር (አገኘሁ ተሸገር ለማለት) ብጮህ አይሰሙኝ፡፡ ብዙ ተሰቃይቻለሁ፤ ታፍኛለሁ፡፡
እኮ ምንድን ነው በዋናነት ችግርዎ?
አምስት ገመድ መሬት ነበረኝ፤ ካቢኔዎች ከቀበሌ ጋር ተመሳጥረው ለዘመድ እዝማድ ሸጠው በሉብኝ፡፡
እዚያው ሞጣ ውስጥ ነው?
አዎ ሞጣ ሁለት እጁ እነሴ ወረዳ ውስጥ ይሄንን ባመለክት፣ በአስራት የቴሌቪዝን ጣቢያ ለምን ተናገርክ ብለው እግሬን ሰበሩኝ። ተመልከች (የተጎዳ እግራቸውን የሚያሳይ ፎቶ እያሳዩኝ) ተመልከች ይሄ ፊቴን… አልሞት ስላቸው በሽጉጥ አፈ ሙዝ መቱኝ። አልሞት አልኩኝ፡፡ ታፍኜ ነው ያለሁት፡፡ እነሱ ያመኑትን ብር እንኳን እንዳይሰጡኝ ዞኑ ጭምር አልተባበረኝም፡፡ አሁን እንኳን እዚህ ፋብሪካ እንዳትገባ የምባለው አንዳንድ ነገር ለባለስልጣናት እንዳልናገር ነው፡፡ በደል ካልተነገረ ዴሞክራሲ የታለ? አንድ አገር የሚስተካከለው እንደኔ ያለ አዛውንት ሲመርቅና ሲናገር ነው እኔ አሁን የ83 ዓመት አዛውንት ነኝ፤ እንድመርቅ እንድናገር መፈቀድ ነበረበት፡፡
አሁን እዚህ የፋብሪካ ጥበቃዎቹ “አሁን አቶ ወርቁ የሉም፤ የፋብሪካው ምረቃም ነገ ነው” እያሉዎት ነው፡፡ መቼ ነው ከሞጣ ደብረማርቆስ የመጡት?
ትላንትና ነው (ቅዳሜ መሆኑ ነው) የመጣሁት፡፡ እኔ እንደውም ቀደም ብዬ ሀሙስ ነበር ለመምጣት ያሰብኩት፡፡ የሚገርምሽ ከሸለመኝ ወዲህም እንዲሁ አንድ ቦታ ከሊኮፍተር ወርዶ አግኝቸው፣ ከወጣት ወርቁ ጋር አብሬው በልቼ ጠጥቻለሁ፡፡
ለመሆኑ የመሬትዎ ጉዳይ ምን ደረሰ? የሸለመዎትን 100 ሺህ ብርስ ምን ሰሩበት?
የሶስት ዓመት የመሬት ሙግት ብድር ነበረብኝ፣ ያንን ብድር ዘጋልኝ፡፡ ሁለት ቤት ነበረኝ፤ የድርጅትና የአስፋልት መስመር ላይ ያለ ሊሸጥብኝ ነበር፤ ተሟገትኩና ያንንም አስቀረልኝ፡፡ እኔ 12 ልጆች አሉኝ፤ ያ ገንዘብ ጠግኖ፣ ችግራችንን ቀርፎ፣ አጥናንቶ አኑሮናል፡፡ ወጣቱን እንክብክቡን ወርቁን ዘላለም በጤና ያቆየው፡፡
ስለዚህ እዚህ የመጡት አቶ  ወርቁን ሊያመሰግኑት ነው አይደለ?
አዎ እሱን ለማመስገንና ለመመረቅ ነው፡፡ ቀረርቶም አለኝ፤ እንዴ ልቅደደው?
ይቀጥሉ… (በጣም ውብና ማራኪ ድምጽ ነው ያላቸው)
ልጅ አሳዳጊና ሳር ቤት ውስጥ ያለ ሰው ደካማ ሩግ ያለው
ሁልጊዜ እንደ ጊደር ሲጠቁ መኖር ነው
ኧረ ወርቁ አይተነው ያ በላይነህ ክንዴ
አንበሳው በጎንደር እያጉረመረመ
ጎጃምን አህያ የበላይን አገር ሲግጠው
ከረመ
ኧረ ጀግና ጎበዝ አንት በላይ ዘለቀ
ቀና ብለህ እየው አማራው አለቀ
አብይ ግፋ ዶክተር አብይ ግፋ
እኔ አግዝሃለሁ ብቻህን አትልፋ
ወደ ሽለላ ልግባ…?
ይቀጥሉ…
አሸከፈከፈኝ እንደ ቄብ ዶሮ
የሚሆን ነገር አለ ዘንድሮ
ልከህ ስደደኝ ጮቄ ለጮቄ
ላምጣው ክላሹን ከእጁ መንጭቄ
እንቆቆው  ወርቁ እሱ ባይኖር
እኔም እስከዛሬ የለሁም ነበር
እረኛ እረኛ በጣም እረኛ
ያለ ክላሺንኮቭ የለውም ዳኛ
እረኛው መጣ እረኛው መጣ
ሳይናገሩት እየተቆጣ
የመነኩሴ ልጅ የፀሎተኛ
የገበሬ ልጅ የጅራፈኛ
ልክስክስ ነገር አንወድም እኛ
ቅደደውና አገር ያውሰው
ለስንቱ ሌባ ይጨነቃል ሰው
ሰው መግደል እንደሁ ቀላል ሙያ ነው
ትልቁ ሙያ እንደነ ወርቁ ሰርቶ መብላት ነው… ይሄው ነው፡፡
በጣም አመሰግናለሁ፡፡ አዝናንተውኛል፡፡ ነገ ምርቃቱ ላይ ይገኛሉ ታዲያ?
ታስገባችሁኝ ደስታዬ ነው ለዚሁ ነው የመጣሁት፡፡ ግን የሚያስገቡኝ አይመስለኝም፡፡
ድንገት አቶ ወርቁን በስራ ብዛት ካላገኙት እዚሁ ላይ ይመርቁት እስኪ?
ወጣቱ ወርቁ አይተነው ማለት እናቱ ሰኞ ለማክሰኞ የፀነሰችው ወርቅ ልጅ ነው። እናንተም ልጆቼ ፍጥረት ስትፈጥሩ ሰኞ ለማክሰኞ ወይም ረቡዕ ለሀሙስ ይሁን ቅዳሜ ለእሁድ የተወለደ እንኳን ዶክተር ሊሆን፣ እንኳን አውሮፕላን አብራሪ ሊሆን፣ እኳን ልማት ሊያለማ የሰው አጥፊ ነው የሚሆነው፡፡
እንዴት ማለት?
ህጉ አይፈቅደውማ!
እኮ የትኛው ህግ?
ፈጣሪያችን ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአርብ ጀምሮ እስከ ቅዳሜና ሰንበት ያለውን ቀን የጸሎት ነው ያደረገው፡፡ ስለዚህ ይሄም ልጅ ወርቁ አይተነው በሙሉ ቀን በመፈጠሩ ሞጣ ላይ ሙስሊምና ክርስቲያን የሚያጣላ ሌባ ሞክሮን ነበር፡፡ እናም ወርቁ እዛ መጥቶ ሳያዳላ አረጋግቶ፣ ትክክል ስራ ሰርቶ በመመለሱ አይኑን ቢያሳየኝ ብዬ ደብረ ወርቅ ገብርኤል አከብር ነበር ብሄድ ሰራዊቶቹ እንዳሁኑ አባረሩኝ፡፡ እሱን ለማግኘት ስለፋ ስለፋ እግዜር ባለው ቀን ተገናኝተናል። ዘሩ ይባረክ፣ ያቆየው፣ የረገጠው መሬት ሁሉ ለምለም ይሁን፡፤ ይሄ ሁሉ ልማት ለአገር ነው፡፡ ለወርቁ አይተነው የሚበቃው አንድ እንጀራ ነው፡፡ አስር እንጀራ የሚበላ ባለስልጣንም የለም፡፡ ግን ይህ ልማት ለእኛ ለህዝቡ ነው፡፡ በጎንደርም እየሄደ ወጣቱን እያረጋጋ፣ እንዳይራበሽና ወደ ውዥንብር እንዳይገባ ትልቅ ስራ እየሰራ ነው፡፡ ወርቁ አይተነውን መርቁልኝ፡፡ የሚሆንልኝ ተሆነ እስተ አራት ሰዓት ለመግባት እሞክራለሁ። አንቺ ይሄንን ታስተላለፍሽው ሊያስገቡኝ ይችላሉ፡፡ ግጥምም፣ ዘፈንም ሆነ ቀረርቶ እችላለሁ አሰምቸሻለሁ፡፡ እና ይሄንን ቶሎ  አስተላልፈሽ እንዲያስገቡኝ ሙከራ አድርጊ፡፡ አየሽ ቂጡ ላይ ቁስል ያለበት ሰው እንደልቡ አይቀመጥም፡፡ አሁን  ቢገባ ለዶ/ር ዐቢይና ለሌላውም ጉዳያችንን ይነግርብናል ብለው ነው የሚከለክሉኝ፡፡
ይሄ ደግሞ ምን መሰለሽ? እግርን ቢሸፍኑት ራስ ብቅ ይላል፤ ይታያል፡፡ ራስሽን ብትሸፍኚው መልሶ እግርሽ ይታያል። ሁሉንም ሸፍኖ አይቻልም፡፡ ይሄው ነው ያለኝ ሀሳብ፤ በደንብ አስተላልፊልኝ አደራ። እማልገባና እማይሆን ተሆነ የያዝኳት ፍራንክ ሳታልቅ፣ ነገ ተሳፍሬ ወደ ሀገሬ ወደ መጣሁበት እመለሳለሁ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡ እገዜር ይስጥልኝ የኔ ልጅ፡፡

Read 3886 times