Tuesday, 15 June 2021 19:32

ሁለት ሰአት ከሩብ...

Written by  ሞሃ
Rate this item
(3 votes)

 ሰው የብዙ ቀናቶች ድምር ነው፡፡ የብዙ ተሞክሮዎች ውጤት አንድን ሰው ሰው ያደርጉታል ወይ ይሰብሩታል፡፡ የልጅነት ጓዴ የሆነችውን ሴት ለመጠየቅ ሳመራ ባይተዋርነት ልቤን ሞልቶት ልክ የምጓዘው ወደ ራስ ቅል ተራራ ይመስል የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማኝ ነበር፡፡ ከሰቃዮቹ መካከል የሆንኩ ያህል ለምን እንደሚሰማኝ አላውቅም፡፡
(ይህን ትውልድ የህይወት ሽርፍራፊዎች ዋጋ አስከፍለውታል፡፡ ለያንዳንዱ መኖር እሱ ዋጋ ይከፍላል፡፡ ደሙን ይገብራል አጥንቱን ይከሰክሳል ላቡን ያለመታከት ይሰጣል። አሁን ዋጋ ከፍሏል፣ ትናንት ዋጋ ከፍሏል ነገም እንዲሁ ይቀጥላል. . .ያልታሰበው የኑሮ ውድነት - ጦርነት - የእርስ በርስ መጠፋፋት ...የህይወት “አብዘርድ”ነት ላይ አድርሶታል)
ይህን አንድ ምሁር በራድዮ ሲያወሩ ነው የሰማሁት “ይህ ትውልድ ለራሱ ባይተዋር ሁኗል”
እዚያ ቤተመንግስት ውስጥ የሚሰራው ደባ ያንድን ምስኪን ወጣት ህልምና ተስፋ የሚያጨልም ሊሆን ይችላል፡፡ የራቀ ይመስላል አይደል አልራቀም
ከዚህ መሃል የጥንት ወዳጄ ዛህራ አንዷ ናት፡፡ እሷ ከሽርፍራፊ ህይወት መሃል ከቁልሉ መሃል ያለች አንዲት ምስኪን ሴት ናት፡፡  ከተለያየን ቢሰነባብትም ቅሉ ስለሷ የምሰማው ብዙ ብዙ ነገር እንዳልረሳት አድርጎኝ ነበር፡፡ ለምሳሌ አንድ የተሳካለት ነጋዴ እንዳገባች ሰምቻለሁ፡፡ ልክ እንዳገሬ ፖለቲካ ነው ትዳር. ... በማግስቱ ነገሮች ይቀየራሉ፡፡ ሰው አይቀመስ መቼስ ደግደጉን ማሰብ እንጂ፡፡ እንደተፋታች ሰማሁ ልጠይቃት አመራሁ ...አንድ ከባለስልጣን በተረፈች ኮንዶሚንየም ቤት ውስጥ መኖር ከጀመረች ሶስተኛ ቀኗን ይዛለች። ተጣደፍኩ፡፡ እንደደረስኩ . . . ምናይነት ሴት ሁና ይሆን ምንስ ትመስል ይሆን ስል በር ላይ ቆሜ ማሰላሰል ጀመርኩ ምንም ምስል ሊከሰትልኝ አልቻለም አንኳኳሁ፡፡ አንዲት በመጠኑ ፊቷ ጠየም ያለ ሴት ከፈተችልኝ። ያቺ የቀይ ዳማ ጠይማለች፡፡ ትላልቅ ሌባ አይኖቿ ጉድጓዳቸው ውስጥ ተደብቀዋል። እሷ ተቀይራለች የማውቃት ሴት ያልሆነች ያህል ፈዝዤ ቀረሁ ሰው ምስኪን ፍጡር ነው- ሰው ርኩስ ነው . . .”ሰውም ርኩስነትን እንደምሳሌያችን እንፍጠር አለ” ሰው በመሆን አለመሆን ሳይሆን ያለበትን በማስጠበቅ አለማስጠበቅ ጦርነት ላይ ያለ ፍጡር ነው፡፡ አይኖቼ እምባ አጋቱ። ላለቅስ አልችልም፡፡ ለምን አለቅሳለሁ እንደ ልጅ ተቃቀፍን፡፡ ልጅ ሆንን ዳግመኛ፡፡ሲጃራ ሱጃራ ትሸታለች፡፡ ተቀምጣ የነበረው ባዶ ክፍል ውስጥ መስኮት ስር ሲጃራ እያጤሰች ነበር፡፡ ቤቱ ጭል ጭል በምትል አምፖል (የትጋ እንዳለች አላውቅም) ብርሃን በመጠኑ ወገግ ብላለች፡፡ ማንም ጠያቂ ያሌለበት ህይወት እየገፋች ነው፡፡ ዙርያዬን በመገረም ለማየት ሞከርኩ፡፡ መገረሜን ከሁኔታዬ ያወቀች ይመስል እንዳዲስ ቤቱን ተመለከተች፡፡ እጄን ይዛ ወደ መስኮቱ ከወሰደችኝ ቡሃላ ባዶ ወንበር አጠገብ ትታኝ ትይዩ ካለ ፊቱን ወደ መስኮቱ ካዞረ ወንበር ላይ ተቀመጠች፡፡እንግዳ ሆንን . . .
“ደህና ነሽ” አልኩ ዝምታውን ለመስበር፡፡ አሽትሬው ላይ የሚጤስ ሲጃራ ተቀምጧል
ከጭጋጋም ቀኖቿ አንዱን መዝዛ ትተርክልኝ ጀመር፡፡
“መሰበር ይሰማኛል-  ማንም ሰው ያንን ማወቅ አይችልም እኔ ብቻ ስብራቴን ይዤዋለሁ፡፡ እንዳመመኝ የሚያውቁት ካቃሰትኩ ብቻ ነው እኔ ደግሞ ማቃሰት አልችልም፡፡ በሁለት ግድግዳዎች መካከል ያለሁ እና መተንፈስ የማልችል ሁኛለሁ” አለች፡፡ ከሲጋራው አንድ ሁለት ግዜ መጣለት አሽትሬው ላይ አስቀመጠችው እናም መስኮቱን አሻግራ እየተመለከተች “ህመምህን የሚጠይቁህ ላንተ ሊታመሙ አልያም በህመምህ ሊያዝኑ አይደለም። ታውቃለህ . . . እኔም ለካ ታምሜያለሁ እላለሁ ከኔ የባሰ አለ- ብለው ራሳቸውን ሊያፅናኑ ነው፡፡ ጥፍሬ ተነቀለ ብትል ቁርጭምጭሚታቸው እንደተጎዳ ይነግሩሃል - ላንተ ሃዘን መጥተው ከሞተ ለቆየ ዘመዳቸው አንብተው ይሄዳሉ”
የግድግዳው ሰአት ከምሽቱ ሁት ሰአት ከሩብ ላይ ቆሟል፡፡ ህይወት የቆመች መሰለኝ በቤቱ ውስጥ ምንም ህይወት ያለው ነገር አይታይም፡፡ ከሰአቱ ስር አንድ ጥቅስ በትላልቅ ፊደላት “አላህ ሆይ እንዳለህ ማወቄ ነው አለመኖርህን እንዳስብ ያደረገኝ” የሚል ጥቅስ ተጠቅሶ ተንጠልጥሏል፡፡ ጥቅሱ አጠገብ ልትጠፋ ጭልጭል የምትል የራስጌ መብራት ከእንጨት በተሰራ ሶስት ማዕዘን እቃ ላይ ከተሰካ ማቀፊያ ላይ ተሰክታለች፡፡
ግን ስንት ሰአት ነው የትኛው ሁለት ሰአት ከሩብ ነው የጠዋት ነው የምሽት ሁለት ሰአት ከሩብ አላውቅም ያገሬ ሰማይ እምባ ማርገፍ ከጀመረ ቆይቷል - ተራሮች ጭጋግ ለብሰው ሜዳዎች ፅልመት ተከናንበዋል፡፡ አላውቅም ቀን ይሁን ምሽት . . . አላውቅም ባውቅም እንዳላወቅኩ ነው ለራሴ የምነግረው፡፡ ቀና ብዬ አየሁዋት አሻግራ ትመለከታለች የምትመለከተውን ለማየት ሞከርኩ- ከመስኮቱ  ባሻገር ሰፊ ግድግዳ አለ ከግድገድዳው ባሻገር ምናልባትም ሰፊ ግድግዳ ይኖራል፡፡ እንደመታፈን ያለ ደረትን ጫን የሚያደርግ ስሜት . . . ሊሰማኝ ሞከረ። አይኖቼን ከመስኮቱ ወደሷ ጣል አድርጌ
“ዛህራ” አልኩ
“አጭስ” አለች አሽትሬው ላይ በስሱ የሚጤሰውን ሲጃራ እያመለከተች፡፡ ለጥሪዬ የተሰጠ ምላሽ ነበር
“ለቀላል ነገሮች ነፍሴ አትሳብም”
“ያ ምን ማለት ነው”
“ምን ማለት እንደሆነ አላውቅም ግን ሲጃራ ከማጨስ ደረቅ አልኮል መርጣለሁ” አልኩ፡፡ ላንዲት ሙስሊም ሴት ይህን ማለቴ ለራሴ ግራ አጋባኝ እና የተናገርኩትን ለማስተባበል “ያው በናንተ ሃራም ነው” አልኩ “ለኔ በህይወት መኖር ነው ሃራም” አለች ሲጃራውን እያነሳች ዝም አልኩ፡፡ ካንዱ መስጂድ አሰጋጅ የሆኑት አባቷ እጇን እየያዙ ወደ መስጂድ ይዘዋት እንደሚሄዱ አስታስኩ፡፡ ሁሉም በምድር ላይ ያለ ነገር ከመብል እና መጠጥ ከዚያ ከፍ ሲል ሃራም ነው ይሉ እንደነበር ትነግረኝ ነበር፡፡ እቤታቸው ውስጥ ቴሌቪዥን አልነበረም። “ባንድ ሳጥን አለምን አጠፉ” ይላሉ ሲበሳጩ፡፡ ከዚያ ሁሉ ግዜ ቡሃላ አንዲት ልጃቸው “መኖር ሃራም ሆነባት” ሲጃራውን በሃይል ስባለት ስታበቃ ጢሱን በቀጭኑ እየለቀቀች “ለቆሰለ እግርም ይሁን ለቆሰለ ነፍስ የምትሰጠው መድሃኒት ልዩነት አይኖረውም፡፡ ብዙ ያልታመሙ ሰዎች የፍርድ ወንበር ላይ መቀመጣቸው ነው ህመምህን የሚያብሰው፡፡ አጭስ አታጭስ ጠጣ አትጠጣ እርግጥ ሰውየው ግድ አይሰጠው ይሆናል . . . እውነቱ ግን መኖር አለመኖርህም ግድ አይሰጠውም” በትልቁ ስባ በትልቁ ለቀቀችው “እስከ ፅርዓ አርያም የሚዘልቅ ይመስል . . . ከንቱ . . . ከንቱ ብቻ ነው” ደጋግማ ሳበች “ለኔ መኖር ነው ሃራም” አለች ረገጥ አድርጋ ቁሬዋን ተቀብዬ እስኪጎመዝዘኝ ድረስ ሳብኩለት፡፡ ፊትለፊቷ ላለማሳል ታገልኩ፡፡ በድንግዝግዙ ውስጥ የፊቴን መለዋወጥ ስታስተውል ቆይታ “አትጨነቅ ማሳል ትችላለህ”
“እሺ” . . . የተለያዩ ሃሳቦች ይመላለሱብኝ ጀመር፡፡ በልጅነት እየተለዋወጥን ያነበብናቸው መፅሃፍት ሀሳቦች፡፡ ልክ የህይወት እንዴትነት አይነት ጨዋታ. . .በዚህ ሁኔታ ጨዋታ ላስብ አልችልም፡፡ አእምሮዬ በኒኮቲኑ ሰበብ ይሁን ብቻ አላውቅም አንድ ነገር ላይ ሙጭጭ አለብኝ እኔና አንቺ የት ነን ልበላት እዚህ ነን ብትለኝ ምን ለውጥ ያመጣል፡፡ አዎን እዚህ ነን፡፡ ለምንድን ነው አራት ግድግዳዎች መካከል ያለነው?
“ታውቃለህ . . . ባለቤቴን ስፈታው ስለ ትዳር ቅዱስነት የነገሩኝ ሰዎች ትዳር ያልያዙ ትዳራቸውን የፈቱ አልያም ያንድን ባለትዳር ሴት አልጋ የሚሻሙ ወንዶች ናቸው፡፡እኔ አልጋ ላይ ያለኝን ኑሮ እነሱ መች ያውቃሉ? አያውቁም! ሳሎኔ ማማሩን ብቻ ተመልክቶ አንድ ሰው እንዴት ስለትዳር ጥሩነት ሊያወራ ይችላል? የነሱ ግን ይለያል! እነሱ ናቸው ፈራጆች እነሱ ናቸው” ይህን ካለች ቡሃላ ወንበሯን በይበልጥ ወደ መስኮቱ አስጠጋች ከዚያም ቀስ እያለች እንዲህ ተረከችልኝ ባለቤቴን እወደው ነበር፡፡ ስለምወደውም ነው የተጋባነው ግን መጋባት ብቻውን ፍቅርን አያስቀጥልም እንዲያውም በተቃራኒው ፍቅር በራፍ ላይ ቆሞ የሚቀር ይመስለኛል። ትዳር አንዲት ሴት እና ወንድ በጋራ ሊኖሩበት የሚያስፈልግ አስቀያሚ ጥምረት ነው፡፡ ግን . . . ታውቃለህ ይህን አይነት አመለካከት ነበረኝ ግን አመለካከት ብቻውን ምን ይሰራል? . . . ተጋባን፡፡ አፈቅረው ነበር ብዬሃለሁ አይደል? አዎን ብዬሃለሁ ያላልኩት ማፍቀር ብቻውን ጥቅም የለውም ነው፡፡ ፍቅር ብቻውን ለትዳር መሰረት አይደለም፡፡ ሰው ብዙ አመል አለው፡፡ ሃያ እና ሰላሳ አመት በወላጆች ቤት ኑረህ ከማታውቀው ሰው ጋር መተቃቀፍን ያህል ለሰው ልጅ እንግዳ ነገር የለም፡፡ ትዳር ደግሞ ይህን እንግዳ ነገር የማታመልጥበት እስር ቤት ነው፡፡
አምላኬ . . . ከአክስቶቼ እጅ ፈልቅቆ ከወሰደ ቡሃላ ከቤት እንኳ መውጣት ከባድ ሆነብኝ፡፡ ሁለት ሰአት ከሩብ ከሆነ ወደ አልጋ እንሄዳለን፡፡ ምንም ሊሰማኝ አይችልም ነበር፡፡ ለኔ የሚሰማኝን ህመም ማድመጥ አይፈልግም፡፡ ይባስ ብሎ መውጫና መግቢያዬን የሚቆጣጠሩ እናቱን አምጥቶ ከኛ ጋር ይኖሩ ጀመር፡፡ ማንም አይሰማኝም ነበር፡፡
በስተመጨረሻ ፈታሁት- እወደው ነበር ግን ሊያደምጠኝ አይችልም፡፡ አዎን ሊያደምጠኝ አይፈልግም፡፡ በራሴ ፍላጎት ፈታሁት፡፡ ህይወቴ ከሁለት ሰአት ከሩብ ቡሃላ አልጋ ላይ የሱን ስሜት መሙያ ባዶ ነገር መስላ ታየችኝ፡፡ አንድ ነገር ለሁሉ እኩል ቅዱስ አይሆንም አይደል? ትዳር ለኔም ቅዱስ አልነበረም፡፡ አላህ- አለ ብለውኛል- ሁሉን የሚያገባ እና የሚወልድ አድርጎ መቼም አይፈጥርም፡፡ ሃሃ የቼዝ ጠጠሮች አንድ አይነት ሊሆኑ አይችሉም ጨዋታው ያሰለቻል”
በቃ ይህ ነው ምክንያትሽ ልላት አሰብኩ ግን ህመም ለባለቤቱ ነው ከባድ፡፡ ዝም አልኩ፡፡ “ሁሌም የምንኖረው በግድግዳዎች መካከል ነው” ያለችኝ ጭንቅላቴ ውስጥ አቃጨለ፡፡
“አሁን ነፃ ነሽ?”    
“አይ በትናንት እስር ቤት ውስጥ ነኝ፡፡ በስጋዬ እንጂ በነፍሴ እስር ቤት ነኝ”
“ሁላችንም እስር ቤት ውስጥ ነን”
“ማስተዛዘን መልካም ነው - ሁላችንም ህመምተኞች ነን የሚል ሃኪም እጁ ላይ ያሉ ህመምተኞች ላይ ይፈርዳል፡፡ የሆነው ሁኖ ስለምታደምጠኝ አመሰግናለሁ፡፡  ግን ይህ ሁሉ ግዜ የት ከርመህ ነው እንዴትስ አገኘኸኝ”
“አፈላልጌ አገኘሁሽ- መቼስ ሰው ከልቡ ከፈለገ እግዚአብሄርንስ ያገኝ የለ አይደለም እዚህ ምድር ላይ ያለን ሰው ይቅርና። እውነቱ ግን የሁለታችን የጋራ ወዳጅ የሆነሰው ነው አድራሻሽን የጠቆኝ”
“አይ ጥሩ”
“እንደ ዱሮው ሙዚቃ ትሰሚያለሽ?”
ሰው እንዲህ አይነት ጥያቄ ለምን እንደሚጠይቅ አይገባኘም፡፡ በምላሹ ምን ላገኝ እችላለሁ? ያኔ በልጅነት “ህይወት ያለ ሙዚቃ ደባሪ እንደምትሆን እንደምትናገር አውቃለሁ፡፡ አንድ ቀን ግን ቀይ እና ሰማያዊ ሸንተረር ያለበት ፌስታል ካሴት ሞልታ ቤት ድረስ እንዳመጣችልኝ እና ዳግመኛ ሙዚቃ እንደማታዳምጥ እንደነገረችኝ አልረሳም፡፡
አባቷ ገርፈዋት ነበር “ጥላሁን ጀነት ያስገባሽ እንደሆን እናያለን” ብለው ጂኒ ሰፍሮባት ይሆናል ተብሎ ቁርአን እንደተቀራባት ነግራኛለች፡፡ ምንም አይነት ጂኒ ሲያጡ ሰልችተው ተዉት፡፡
ከሰፈር እና ከጫዎታ ለሳምንታት ቀረች፡፡
“ከዚያን ቀን ቡሃላ አዳምጬ አላውቅም” ፓኮውን ከመስኮቱ ደፍ ላይ አነሳች “ግን ግጥም ማንበብ ጀመርኩ ነብይ መኮንን እና ገብረ ክርስቶስ ደስታን ጮህ ብዬ አነባለሁ፡፡ ሃሃሃ ከኔ እኩል የቆሰሉ ይመስለኛል፡፡ ደግሞ ልምጭ ያሌለው ግርፊ ነበር ካሴቶቼን ሰብስቤ እንድሰጥህ ያደረገኝ”
“ነፃ ነሽ ነው ያልከው፡፡ ምንም ነፃ አይደለም ሁሉም ሰው በግድግዳዎች መካከል ነው የሚኖረው፡፡ ልዩነቱ ግድግዳውን ባጠነከረው ቁጥር ራሱን ከጠላት የሚጠብቅ ይመስለዋል እንጂ ሰው ራሱን ነው ከራሱ መጠበቅ ያለበት፡፡ አሁን ነፃ አይደለሁም እንዴ?. . . ከባለቤቴ ነፃ ነኝ የከበደኝ ከራሴ ነፃ መውጣት ነው” አንድ ሲጃራ መዝዛ አፏ ላይ ሰካች “አየህ ስጎረምስ እናቴም አባቴም ባንድ አውቶቡስ አዳጋ ህይወታቸው አለፈ፡፡ ዝም ብለው ሞቱ፡፡ በዚህ አስቀያሚ አለም ላይ ስላመጡኝ እንኳ ይቅርታ አልጠየቁኝም፡፡ ግን ይቅር አልኳቸው፡፡ እዚህ ሰው እጅ ላይ መውደቄን ሳስብ ግን ሁሌ እንደረገምኳቸው ነው” ሲጃራውን ለኩሳ እንደነገሩ መሳብ ጀመረች፡፡ዝም አልን፡፡ ከተቀመጥኩበት ተነስቼ መስኮቱጋ ጠጋ አልኩ፡፡
“ምናልባት አንድ ቀን ሁሉም ነገር የተሻለ ይሆናል” አልኩ ዝምታውን ለመስበር። በደብዛዛው የክፍሉ ብርሃን ውስጥ ያየችኝ አስተያየት አስፈሪና አሳዛኝ ተስፋ የማይታይበት ነበር፡፡ የጥፋተኝነት ስሜት ተሰማኝ፡፡ ላንድ ሰው ከባዱ ላንዱ ህመም የጋራ ተመጣጣኝ ምላሽ መስጠት አለመቻል ይመስለኛል፡፡ ምን እንደምላት ሳወጣና ሳወርድ ባንድ ልቦለድ ላይ ያነበብኩት ጥቅስ ትዝ አለኝ “ሰው ሰውም ሰይጣንም ነው። የገዛ ስፍራውን አሳልፎ ሰጥቷል- ግዛቱ የጭካኔ ነው፡፡ ፈጣሪ አንድ ቀን የተሸለውን ያደርጋል፡፡ አገር ስትረጋጋ ሁሉም ነገር የተሻለ ይሆናል” ስል በውል ያላመንኩበትን ነገር ተናገርኩ፡፡ ዳግም በመሰልቸት ተመለከተችኝ “ይቅርታ” አልኩ፡፡
“ተወው ይቅርታ የሚያስጠይቅ ነገር አልተናገርክም፡፡ ልክ በህመሜ ያንተን ቁስል መጠገን የምትፈልግ አይነት እየተሰማኝ ነው”
እንዲያ አላሰብኩም፡፡ እንዲያ ላስብም አልችልም፡፡
“መሄድ አለብኝ” አልኩ ትከሻዋን በእዝነት እየዳበስኩ
“ወዴት ነው የምትሄደው?”
“አላውቅም ግን መሄድ ብቻ እንዳለብኝ ነው የሚሰማኝ”
“የሚሰማህን ብቻ ተከተል”
ከደብዛዛው ክፍል ወጥቼ ድንግዝግዙ ህይወት መካከል ተቀላቀልኩ፡፡  በየጥጋጥጉ የተጋደሙ ሰዎችን ኩርፊያ እያደመጥኩ ፀጥ ረጭ ያለውን ጎዳና በዝግታ አዘገምኩ . .


Read 1776 times