Tuesday, 15 June 2021 19:51

የተዘነጉት የዜግነት እሴቶችና የኢትዮጵያ ቀጣይ ጉዞ

Written by  አብርሃም ገብሬ
Rate this item
(1 Vote)

  አድማስ ትውስታ

              "--በዜግነት ዕሴቶች ላይ መሰረቷን ባደረገች አገር ውስጥ፣ በዜጎች መካከል አንዳችም የመብት መበላለጥ አይኖርም፡፡ ሁሉም ዜጋ እኩል የሆነ የፖለቲካ መብት ይኖረዋል እንጂ፡፡ አገሬ ብሎ በሚጠራት አገሩ ላይ ዜጋው እኩል የመወሰን ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትም ነው፡፡--"
 
           ኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረው የለውጥ ሂደት ማሳረጊያው ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መመስረት ከሆነ፣ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመዝለቅ በየትኛው መንገድ ነው መጓዝ የሚያስፈልገው? የዲሞክራሲ መዳረሻ መንገዱ የሚመረጥበት መስፈርትስ ምን መሆን አለበት? ከሁኔታዎች ጋር እራሱን እያደሰ የሚሄድ፤ ቀጣይነት ያለው ዲሞክራሲያዊ ስርዓትስ እንዴት መመስረት ይቻላል? የሚሉትን ጥያቄዎች በአግባቡ መመለስ ከተቻለ፣ ለዛሬዋ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ ለመጪው ትውልድ የሚሆኑ መልካም እሴቶችን በጽኑ መሰረት ላይ አኑሮ ማለፍ ይቻላል፡፡
ዲሞክራሲያዊ ስርዓት በመተግበር ሰፊ ልምድ ያዳበሩ አገራት፣ ከነገድ ጋር የተያያዙ ማንነቶችንና ሌሎችንም ፈርጀ-ብዙ ልዩነቶቻቸውን አስታርቀው የሚጓዙበትን መላ ይዘይዳሉ፡፡ መልከ-ብዙ ልዩነቶቻቸውን ለማቻቻል ካስቻሉዋቸው ዘዴዎች መካከል አንዱ የ“ዜግነት” (Citizenship) ስርዓተ ማህበር ነው፡፡ በተለይም የግለሰብንና የነገዳዊ ስብስቦች መብትን ለማረቅ የዜግነት ዕሴቶች አስፈላጊነት አጠያያቂ አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥም የነገድና የግለሰብ መብትን አሰናኝቶ ወደፊት ለመጓዝ የሚያስችል ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ዕውን ማድረግ በእስካሁኑ ጉዞ አልተቻለም፡፡ ለነገዳዊ ስብስቦች እውነተኛ የሆነ ራስን በራስ የማስተዳደር መብቶቻቸውን በማረጋገጥ፣ የሃገሪቱን ዋነኛ አስተሳሳሪ ማንነትን ግን በዜግነት መሰረት ላይ በማቆም የሁሉም መብት የሚከበርበት ስርዓት ለመዘርጋት አልተሞከረም፡፡ ስለዚህ እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ኢትዮጵያ ውስጥ አብቦ ፍሬ እንዲያፈራ፣ የዜግነት ዕሴቶችን ማዕከል ያደረገ ስርዓት ማቆም ያስፈልጋል፡፡ ዜግነትን ማዕከል የሚያደርግ ስርዓትን ተመራጭ የሚያደርገው፣ መልከ-ብዙ ልዩነቶችን የማስተናገድ አቅም ስላለው ነው፡፡
ዜግነት፤ ግለሰቦች አገሬ ብለው ከሚጠሯት አገር ጋር ህጋዊ ትስስር የሚፈጥሩበትና ለአገራቸው ወገንተኝነት የሚያሳዩበት ስርዓት ነው ይላሉ - የዘርፉ ምሁራን፡፡ የትስስሩ ፍጥጥም ደግሞ በህግ ውል የሚቋጭ ነው፡፡ ይህ ህግ፤ ዜጎች ሉዓላዊነታቸው እንዳይደፈርና የዜግነት መብታቸው በመንግስትም ሆነ በሌላ አካል እንዳይጣስ ጥበቃ የሚያደርግ ተቋም ጭምር ነው - የዜግነት አስተሳሳሪ ማንነት፡፡ በዜጎች ይሁንታ የሚመሰረተው መንግስትም፣ የዜጎችን መብት የማክበርና የማስከበር ግዴታ ይኖርበታል ማለት ነው፡፡ ዜጎች መብቶቻቸውን እንደሚጠቀሙ ሁሉ ግዴታዎቻቸውንም ይወጣሉ፡፡
የነገዳዊ ማንነት (ethnic identity) የሁሉ ነገራችን መስፈርያ በሆነበት በኢትዮጵያ የፖለቲካ አውድ ውስጥ፣ ወደ ዜግነት ፖለቲካ ለመሸጋገር እንቅፋቶቹ ብዙ ናቸው፡፡ ነገር ግን የተረጋጋና ቀጣይነት ያለው የዲሞክራሲ ስርዓት ለማቆም፣ በዜጎች የጋራ እሴቶች  ላይ ከሚመሰረተው የዜግነት ፖለቲካ ውጪ ዕውን ማድረግ አዳጋች መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው የጻፉ ምሁራን አሉ። ከነዚሁ መካከል የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከግማሽ ምዕተ-ዓመት በላይ በቅርበት የተከታተሉትና የጻፉት አቶ ዩሱፍ ያሲን አንዱ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ውስጣዊ የፖለቲካ ችግሮችን በጥልቀት በመመርመር፣ “የዜግነት መብቶችን ማዕከል ያደረገ አሰባሳቢ ማንነት” ዋንኛ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግሮች መፍቻ መንገድ ነው ይላሉ - አቶ ዩሱፍ ያሲን፡፡ አቶ ዩሱፍ፣ “ኢትዮጵያዊነት፤ አሰባሳቢ ማንነት በአንድ አገር ልጅነት” በተሰኘው መጽሐፋቸው (ገጽ 414) ላይ እንዳሰፈሩት፣ “…የዜግነት መብቶችን ማዕከል ያደረገ አሰባሳቢ ማንነት ብቻ ነው አነታራኪ የሆኑትን የቅርንጫፍ ማንነቶቻችንን ሁላ አዋህዶ ሊያስተሳስረን ብቃት ያለው። …እሱም በአንድ አገር ልጅነት አቅፎ ደግፎ የሚያኗኑር ዜግነትን መነሻ ያደረገ ተጋሪዮሾችን ጠበቅ፤ ሌሎች ግልገል የዘር፣ የቋንቋ፣ የወንዝ፣ የፖለቲካ አመለካከት ተጋሪዮሾችን ለቀቅ በማድረግ ነው” በማለት የወደፊቷ ኢትዮጵያ፣ የዜጎችዋ መብትና ጥቅም የተከበረባት አገር እንድትሆን፣ ዜግነትን ማዕከል ያደረገ ስርዓት መፍጠር አስፈላጊ እንደሆነ ነው የሚያሳስቡት፡፡
በዜግነት ዕሴቶች ላይ መሰረቷን ባደረገች አገር ውስጥ፣ በዜጎች መካከል አንዳችም የመብት መበላለጥ አይኖርም፡፡ ሁሉም ዜጋ እኩል የሆነ የፖለቲካ መብት ይኖረዋል እንጂ። አገሬ ብሎ በሚጠራት አገሩ ላይ ዜጋው እኩል የመወሰን ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትም ነው፡፡ በዜግነት አስተሳሳሪ ማንነቶች ላይ በታነጸች አገር ውስጥ፣ በዜጎች መካከል የሃብት፣ የዘር፣ የነገድ፣ የጾታ፣ የሃይማኖትና የተወለዱበትን ስፍራ ተተግኖ የሚደረግ ምንም አይነት ልዩነትና አድሎኣዊነት የለም። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሚታዩትን ፈርጀ-ብዙ ተቃርኖዎች አስታርቆ ለመሄድ፣ የዜግነት ፖለቲካ እንዲጎለብት፤ የዜጎች ተጋርዮሻዊ ማንነቶችን ማጉላት አስፈላጊ የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡
ማሞ ሙጬ (ፕ/ር) “Re-Imagining and Revisiting Ethiopiawinet and Ethiopianism for our Time?” በተሰኘው ጽሁፋቸው፤ እየዳከርንበት ካለው የፖለቲካ ውጥንቅጥ መውጫው መንገድ፣ የአያት ቅድመ አያት ደምና አጥንት ከምንቆጥርበት የነገዳዊ ማንነት ብያኔዎች በመሻገር… በሰብዓዊ መብት፣ በሰው ልጆች ነጻነት፣ እኩልነት፣ የጋራ አገራዊ  እሴቶች ላይ በሚመሰረቱ ብያኔዎችና ብልጽግናዎች…ላይ ማተኮር ሲቻል ነው ይላሉ፤ “…primordially and biologically defined ethnically fractured citizen must be fully liberated to emerge as the Ethiopian citizen par excellence with full human rights, self-worth, dignity, independence, agency and with the freedom to self-organize, self-express, self-define… as an Ethiopian citizen without diminishing any and all the human rights regardless of language, ethnic origin, religion, gender and any other varieties and diversity.” በማለት ያብራራሉ፡፡ ማሞ ሙጬ (ፕ/ር)፤ ከላይ የዘረዘሯቸውን የሰው ልጅ መሰረታዊ እሴቶች ተግባራዊ ለማድረግ፣ ከዜግነት ፖለቲካ ውጪ ማሰብ ያዳግታል፡፡ ስለዚህ የዜጋዊ ብሄርተኝነት (civic nationalism) መሰረታዊ ዕሴቶች እንዲዳብሩ የማስቻሉ ነገር አጠያያቂ አይደለም። በዜግነት አስተሳሳሪ ማንነቶች ላይ ተመርኩዞ የሚገነባ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ አስተሳሳሪ ማንነቶች፡- ነገድ፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት ጾታ… አይደሉም፡፡ በግለሰብ መብት ላይ የሚመሰረቱት የዜግነት ካስማዎች፡- ነጻነት፣ እኩልነት፣ ወንድማማችነት ናቸው እንጂ፡፡
በእርግጥ የዜግነት ፖለቲካ ማዕከል ወዳደረገ ስርዓት ለመሸጋገር ጉዞው ቀላል አይደለም። ውጣ ውረድ የበዛበትና የሚያደክም ነው - መንገዱ፡፡ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ወደ ዜግነት ለሚደረገው ጉዞ የአደናቃፊነት ሚና ሊጫወቱ የሚችሉ ሃይላት ደግሞ መልከ-ብዙ ናቸው። ከሁሉም በላይ ግን በተለያዩ ጎራዎች የተቧደኑ፤ ዛሬን እንጂ ነገን አሻግረው የማይመለከቱ፤ መሐለኛውን መንገድ ከመምረጥ ይልቅ ጠርዘኝነትን የሚመርጡ ልሂቃን ጉዳይ አንዱ ሊሆን ይችላል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የተገኙ የለውጥ ዕድሎችን እንዲመክኑ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ይኸው የጠርዘኝነት ልማድ አንዱ ነው። ይህ ጠርዘኝነት፣ በስልጣን ወንበር ላይ በአቋራጭ ወጥቶ ለመቀመጥ ከሚደረገው እሽቅድድም ጋር ይዛመዳል፡፡  የዚህ አይነቱ ጠልፎ ለመጣል የሚደረግ እሽቅድድም ግቡም አንድ ነው - ስልጣን፡፡ በዚህ ምክንያት ነገን አሻግሮ ከመመልከት ይልቅ፣ የዛሬውን ጠባብ ጥቅም በማሳደድ፣ ከለውጥ ሂደቱ ‘እኔ ምን ላተርፍ እችላለሁ?ʼ በሚል ስሌት ስለሚጓዝ፣ ወደ ዜግነት ለመሸጋገር ለሚደረገው ረዥሙ ጉዞ መሰናክል ሊሆን ይችላል፡፡
ሌላው ደግሞ የመንግስትን ስልጣን በጨበጡ ባለ ጊዜዎች ከዚህ ቀደም የተረቀቁት ህጎች ናቸው። እነዚህን ህጎች ህዝብ አልተወያየባቸውም፡፡ ህጎቹን በማርቀቅና በማጽደቅ ሂደት እውነተኛ የህዝብ ወኪሎች ተሳትፈዋል ማለትም አይቻልም፡፡ ሌላው ቀርቶ የህጎች ሁሉ አውራ የሆነውን ሕገ መንግስት እንኳ ብንወስድ ከዚሁ ችግር የተላቀቀ አይደለም።
ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን በስራ ላይ ያለውን ህገ መንግስት ጨምሮ አራት ህገ መንግስቶች ጸድቀው ስራ ላይ ውለዋል። እነዚህም በአጼ ኃ/ሥላሴ ዘመነ መንግስት በ1923 ዓ.ም እና በ1948 ዓ.ም የተሻሻለው ህገ መንግስት፣ ደርግ  በ1980 ዓ.ም አርቅቆ ያጸደቀው ህገ መንግስት እና በ1987 ዓ.ም  ጸድቆ አሁን በስራ ላይ ያለው ሕገ መንግስት ናቸው። አራቱም ሕገ መንግስቶች የሚጋሯቸው መሰረታዊ ባህርይ አለ ይላሉ - የታሪክ ምሁሩ ባህሩ ዘውዴ (ፕ/ር)። ከዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማህበር ባዘጋጀው መድረክ ላይ “ምን አለምን? የት ደረስን? ወዴትስ እያመራን ይሆን?” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሁፋቸው፣ “….ሥርዓታዊ አስተዳደርን፣ በተለይ ህገ መንግስታዊ አገዛዝን ስናይ… ሁሉም ከታች [ከሕዝብ] የመነጩ ሳይሆን ከላይ የተደነገጉ፣ የህዝብና የመንግስት ቃል ኪዳን ሳይሆኑ፣ የድል አድራጊዎች ቻርተሮች መሆናቸውን ነው፤” በማለት ነበር - አሁን በስራ ላይ ያለው ሕገ መንግስትና የቀድሞ ሕገ መንግስቶች ከላይ ወደ ታች የተደነገጉ መሆናቸውን የገለጹት፡፡ በሌላ አነጋገር፤ ህዝብና መንግስት የተዋዋሉባቸው ሰነዶች አይደሉም ማለት ነው፡፡ እንደዚህ አይነት አካሄዶች ደግሞ ዜግነት ላይ ከሚመሰረት ስርዓተ ማህበር ጋር አይጣጣሙም፡፡
በዜግነት ላይ የተመሰረተች ዲሞክራሲያዊት አገር ዕውን የማድረግ ሂደት ሲታሰብ፣ አሁን በስራ ላይ ያለውን ሕገ መንግስት ጊዜው ሲፈቅድ ለውይይት ማቅረብ ያሻል ማለት ነው፡፡ የአሁኑ ሕገ መንግስት በተለይ ስምንተኛው አንቀጽ፤ ዜጎችን የኢትዮጵያ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነት መብትን ይነፍጋቸዋል። ይሄ ደግሞ በዜግነት መሰረት ላይ የቆመ ስርዓት ለመገንባት ትልቁን እንቅፋት ይጋርጣል፡፡
የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ለዜግነት ሳይሆን ለብሄር የተሰጠበትን አግባብ አጥብቀው ከተቹት ምሁራን መካከል አንዱ አለማየሁ አረዳ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ “ምሁሩ” በተሰኘው መጽሐፋቸው(ገጽ 198)፤ “…ዜግነት ቋሚ ክስተት ሲሆን ብሔር ግን መሸጋገሪያ ማህበረ ፖለቲካዊ ስብስብ ነው። እናም ስለ ምን ሉዓላዊነትን ቋሚ ባልሆነ ማህበራዊ መሰባሰብ ላይ መመስረት አስፈለገ? በሁሉም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ተግባሮችና እንቅስቃሴዎች ውስጥ ብሄርነት ከዜግነት በላይ ቅድሚያ በተሰጠበት አድሎኣዊ  ስርዓት ውስጥ ምን አይነት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው ሊመሰረት የሚችለው?” በማለት ይጠይቃሉ። አለማየሁ አረዳ (ዶ/ር) በዚሁ መጽሐፋቸው፣ ሉዓላዊነትን አስመልክተው የሕገ መንግስቱን ስላቅ ሲገልጹት፤ “…ሉዓላዊነትን ለብሔር/ብሔረሰቦች የሰጠ ሕገ መንግስት፣ የዜጎች መብቶችም ይከበራል ይላል፡፡ይህ የፖለቲካ ድራማ፣ ትራጀዲውን ከሃያ አምስት አመታት በኋላ እያሳየን በመሆኑ፤ኮሜዲው የሚቀርብበትን ዕለት በጉጉት እንጠብቃለን፤” በማለት የሕገ መንግስቱ ተቃርኖዎችን ለማመላከት ይጥራሉ፡፡
ሌላው ደግሞ የሚሻሻሉ የሕገ መንግስት አንቀጾች አሉ ብሎ ብዙሃኑ ቢስማማም እንኳ፣ ሕገ መንግስቱ የሚሻሻልበት መንገድ ክርችም ተደርጎ የተዘጋ ነው። በአጭሩ ሕገ መንግስቱ እንዲሻሻል ተደርጎ የተቀረጸ አይደለም፡፡ “ሕገ መንግስቱን ስለማሻሻል፤” የሚለውን የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 105ን መመልከት ይቻላል፡፡ 
ስለዚህ የዜግነት ፖለቲካን ስናስብ፣  የተለያዩ ‘ተቋማት’ የተመሰረቱባቸውን ህጎች እንደገና መፈተሽና መከለስ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ህጎች ዘለቄታዊ ህልውና እንዲኖራቸው የተለያዩ አካላት ከሂደቱ ጀምሮ ተሳታፊ መሆን ይኖርባቸዋል። የዜግነት ፖለቲካ ስር እንዲሰድድ ትልቁ ድርሻ የሚወስዱትን የዴሞክራሲ ተቋማትን ገለልተኛ አድርጎ መመስረት ሲቻል ነውና፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ አሃዳዊ ስርዓት ምን እንደሚመስል አይተናል፡፡ ይሄ አሃዳዊ ስርዓት ብዙሃኑን የሚያገልል ነው በሚል - በነገዳዊ ማንነት ላይ የተመሰረተ የለበጣ “ፌዴራላዊ ስርዓት” ተዘርግቶም ተመልክተናል፡፡ ምንም እንኳን ፌዴራሊዝምን ያለ ዲሞክራሲ ተግባራዊ ማድረግ የማይቻል ቢሆንም። በዚሁ የዘውግ ፌዴራሊዝም ጦስ፣ ያለፉት ሶስት አስርት ዓመታት፣ ለሃገርም ሆነ ለህዝብ የስጋትና የሰቆቃ፤የመፈናቀልና የህልፈት መንስኤ ሆኖ መክረሙን በተጨባጭ  ኖረነዋል፡፡ የተዘረጋው  ዘውጋዊ ስርዓት፣ በህብረተሰቡ ውስጥ ከመተባበር ይልቅ የመከፋፈል ድባብ ፈጥሯል። ከወንድማማችነት ይልቅ በጎሰኝነትና በዘረኝነት አየሩን እንዲበከል አድርጓል፡፡ ከእኩልነት ይልቅ ‘እኛ ቀድመን እንብላʼ የሚሉ ተስገብጋቢ ድምጾችን አንግሷል፡፡በጥቅሉ በእስካሁኑ የኢትዮጵያ የታሪክ ጉዞ፣ ሁሉንም ሊያስጠልል የሚችል ስርዓት መፍጠሩ ላይ አልተሳካልንም፡፡ ባለቅኔ ጸጋዬ ገ/መድህን “የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ” በሚለው ሥራው፤
“…ያለፈ ጥረታችንን፣ ሳስታምመው ትዝ ሲለኝ ከሞከርነው ነገር ይልቅ፣ ያልሞከርነው ነው እሚቆጨኝ።” ብሎ እንደከየነው…በኢትዮጵያ የፖለቲካ ከባቢ ውስጥም የዜግነት ፖለቲካ አልተሞከረም። የአገራቸውን ጉዳይ፣ ጉዳዬ ብለው በዚህ ዙርያ የጻፉና ያሳሰቡ ኢትዮጵያውያን ቢኖሩም ሃሳባቸው  ግን ተቋማዊ መደላድል መያዝ አልቻለም፡፡ ግን አልረፈደም፡፡
ዛሬም ቢሆን የዜግነት ስርዓተ ማህበር መመስረት ይቻላል፡፡ የዜግነት እሴቶች እንዲጎለብቱ ደግሞ ማህበራዊ ፍትህን ማረጋገጥ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ለዜግነት ፖለቲካ እርሾ ሊሆኑ የሚችሉ እሴቶች ለመቀመር ወደ ራሳችን ባህሎች መመልከትም  ፋይዳው የጎላ ነው፡፡
ባህል እንደሚታወቀው ብዙ ፈርጆች አሉት። ወግ፣ ልማድ፣ እምነት፣ ሃይማኖት ...ሃገርን እንደ ሃገር፤ ህዝብን እንደ ህዝብ ደግፈው የሚያቆሙ ካስማዎች ናቸው። ይብዛም ይነስም ነጽረተ ዓለማችን (world- view) የሚቀረጸው ከባህል በሚቀዱ ፈርጀ-ብዙ ዕሴቶች አማካይነት ነው። ስለሆነም ባህላችንን መመርመር፣ ማጥናት፣ መተቸት ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ይህን ሂደት በመከተል ለዜግነት እሳቤ አስፈላጊ የሆኑ ዕሴቶችን አንጥሮ ማውጣት ይቻላል፡፡ ይህን ማድረግ ሲቻል ደግሞ የዜግነት እሴቶች በሂደት እንዲያብቡ ጥርጊያውን ያመቻቻል።



Read 1898 times