Saturday, 19 June 2021 16:33

ፌስቡክ በኢትዮጵያ ሃሰተኛ ናቸው ያላቸውን 176 አካውንቶች ዘጋ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 በኢትዮጵያ የተዛቡ መረጃዎችን ሲያቀርቡ ነበር ያላቸውን 176 ሃሰተኛ የፌስቡክ አካውንቶች መዝጋቱን ፌስቡክ ኩባንያ በድረገፁ ባሰራጨው መረጃ  አመልክቷል፡፡
በዓለም ላይ ተፅኖ ፈጣሪ ከሆኑ ማህበራዊ የትስስር ገፆች በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ፌስቡክ፣ ማንነታቸውን ሰውረው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ በአማርኛ ቋንቋ ሲሰሩ ነበር ያላቸውን 65 የግለሰብ አካውንቶችን ጨምሮ 52 ገጾች፣ 27 የቡድን አካውንቶች እንዲሁም 32 የኢንስታግራም አካውንቶችን መዝጋቱን ነው ያስታወቀው፡፡
እነዚህ አካውንቶች በተለይ የተዛቡና አሳሳች መረጃዎችን የሚያሰራጩ እንደሆኑ የጠቆመው ኩባንያው፤ በአገር ውስጥ ዜናና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ አተኩረው የሚሰሩ ናቸው ብሏል፡፡ በተቀናጀ ሁኔታ የሚንቀሳቀሱትን እነዚህን አካውንቶች የሚያንቀሳቅሱት ግለሰቦች ምንም እንኳን ማንነታቸውንና ትስስራቸውን ለመደበቅ ቢሞክሩም፣ ፌስቡክ አደረግሁት ባለው ምርመራ፣ ግለሰቦቹ ከመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ለማወቅ መቻሉን አመልክቷል፡፡
 እነዚህ አካውንቶች በአመዛኙ የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ላይ የጣሉትን ማዕቀብ በመቃወም የሚታወቁ፣ ራሳቸውን ከምርጫው ያገለገሉትን ኦፌኮ እና ኦነግን ጨምሮ ከመንግስት ጋር ግጭት ውስጥ የገባውን ህወኃትን  የሚነቅፉና የሚያጥላሉ ናቸው ብሏል፤ ኩባንያው፡፡
ፌስቡክ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ፣ ከኢትዮጵያ አገር አቀፍ ምርጫ ጋር ተያይዞ ሐሰተኛና ጥላቻን ያዘሉ መልዕክቶች በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኩ በኩል እንዳይተላለፉ ለመከላከል አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን ማስታወቁ  ይታወሳል።


Read 868 times