Print this page
Saturday, 19 June 2021 16:34

አስር የመንገዶች ባለስልጣን ሠራተኞች በታጣቂዎች ተገደሉ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

  በኦሮሚያ  ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ሜታ ወልቂጤ ወረዳ ሎያ ጎዳኔ ቀበሌ ውስጥ  ባለፈው ረቡዕ ሰኔ 9 ቀን /2013 ዓ.ም አመሻሽ ላይ በመንገድ ግንባታ ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ አስር የፌደራልና የኦሮሚያ መንገዶች ባለስልጣን  ሰራተኞች በታጣቂዎች መገደላቸው ተገለፀ፡፡
በታጣቂዎቹ ጥቃት የተገደሉት የፌደራልና የኦሮሚያ መንገዶች ባለስልጣን ባለሙያ የሆኑ ዘጠኝ ሰዎችና የቀበሌው ነዋሪ የሆነች አንዲት ሴት ሲሆኑ በጥቃቱ አስሩም  ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ሠራተኞቹ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የዓለም ገና ዲስትሪክት ባልደረቦች ሲሆኑ   በዞኑ መኡርጋ በሚባል ወንዝ አካባቢ ያለ የመንገድ ሥራ ላይ ውለው  አመሻሽ ላይ ጎሮ ወደሚባል ቦታ ሲመለሱ መኪናቸው በታጣቂዎች እንዲቆም ተደርጎ ጥቃቱ እንደተፈጸመባቸው ምንጮች ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡
 ታጣቂዎቹ  ጥቃቱን በፈጸሙበት ወቅት  አንድ ሰው ለማምለጥ  ሙከራ ማድረጉንና  በአቅራቢያው ወዳለ ገደል ዘሎ መግባቱን  የጠቆሙት ምንጮች፤ ግለሰቡ በህይወት መትረፍ አለመትረፉ እስከአሁን አለመረጋገጡን ተናግረዋል፡፡ በጥቃቱ የተገደሉት ሰዎች አስከሬን አዲስ አበባ ወደሚገኘው ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ተልኮ ምርመራ ከተደረገ በኋላ በትላንትና እለት ለቤተሰቦቻቸው ተሰጥቷል፡፡
ጥቃቱን የፈጸመው “ኦነግ-ሸኔ” የተባለው ቡድን እንደሆነ ቢነገርም  እስካሁን  ከቡድኑ በኩል ድርጊቱን ስለመፈፀሙ የተገለጸ ነገር እንደሌለና ማንም  ለጥቃቱ ኃላፈነቱን እንዳልወሰደ  ታውቋል፡፡


Read 859 times