Saturday, 19 June 2021 16:53

ምርጫ ቦርድና የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ተፋጠዋል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)


        - ኮሚሽኑ በምርጫው የሰብአዊ መብት ጉዳዮችን ለመታዘብ ያቀረበውን ጥያቄ ቦርዱ አልተቀበለውም
        - ቦርዱ ጥያቄውን ያልተቀበለው ኮሚሽኑ በታዛቢነት እንዲሳተፉ ከተፈቀደላቸው አካላት ባለመካተቱ መሆኑን አመልክቷል፡፡
               
          የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ላይ የሰብአዊ መብት ጉዳዮችን ለመታዘብ ያቀረበውን ጥያቄ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አልተቀበለውም፡፡
ቢቢሲ ከታማኝ ምንጮች አገኘሁት ባለውና ከቦርዱ እንደተጻፈ በተገለጸው ደብዳቤ፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በተሻሻለው የምርጫ ህግ አንቀጽ 123 መሰረት፤ መጪውን ምርጫ ለመታዘብ የሚያስችለው አግባብ የለም፡፡ ኢሰመሃ የታዛቢነት፣ የጋዜጠኝነት ወይም ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲና የግል እጩ ወኪልነት መብት ስለሌለው የይለፍ ካርድ ሊሰጠው አይችልም ያለው የቦርዱ ደብዳቤ፤ ለኮሚሽኑ የይለፍ ካርዱን የሚሰጥበት የህግ አግባብ ባለማግኘቱ ምክንያት ቦርዱ ጥያቄውን ተቀብሎ ለማስተናገድ እንደማይችልም አመልክቷል፡፡
ይህ የቦርዱ ውሳኔ አግባብ አለመሆኑን ያመለከተው የሰብአዊ መብቶች  ኮሚሽን፤ በተሻሻለው የኮሚሽኑ ህግ መሰረት ኮሚሽኑ ምርጫን የመታዘብ ተግባርና ኃላፊነት እንደተሰጠው አመልክቷል፡፡ ይህንን የኮሚሽኑን ስልጣንና ኃላፊነት እንደሚረዳ ያመለከተው ቦርዱ፤ ነገር ግን ይህ የመታዘብ ስራ ምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ እንዲገባ የሚያስችለው የይለፍ ካርድ ከሚሰጣቸው አካላት ውስጥ የምርጫ አዋጁ አያካትተውም ብሏል፡፡
የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በምርጫ ወቅት የሰብአዊ መብት ጉዳዮችን ለመታዘብ የሚችለው በምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት መሆኑን አመልክቶ፣ ይህንን የኮሚሽኑን የሰብአዊ መብቶች ክትትል ስራ ቦርዱ ሊያግዘውና ሊተባበረው እንደሚገባ አመልክቷል፡፡
ከዚህ ቀደም በተከናወነ ህዝበ ውሳኔ ላይ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባልደረቦች የይለፍ ካርድ ተሰጥቶአቸው ሂደቱን መታዘባቸውን ያስታወሰው የኮሚሽኑ ደብዳቤ፤ ሂደቱ የሰብአዊ መብቶች የተከበሩበት መሆኑን ተከታትዬ ማረጋገጥ አለብኝ ብሏል፡፡ በኮሚሽኑ የማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት፤ ማንኛውም ሰው ለኮሚሽኑ ስራ አስፈላጊውን ድጋፍ የመስጠት ግዴታ መቀመጡን ከግምት ውስጥ አስገብቶና ጥያቄውን ተቀብሎ ምላሽ እንዲሰጠውም ቦርዱን ጠይቋል፡፡
ቦርዱ ለኮሚሽኑ ደብዳቤ  የሰጠውን ምላሽ ለማወቅ ወደ ኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የስራ ኃላፊዎች በተደጋጋሚ ያደረግነው የስልክ ጥሪ  ምላሽ አላገኘም፡፡


Read 12851 times