Saturday, 19 June 2021 17:21

የመጨረሻው የሕዝብ ዐመፅ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ንጉሡ ወደ ሮም ሃይማኖት ቀንበር ያልገቡትን ሊተዋቸው ይችላል፡፡ እነርሱን እሺ ለማሰኘት የሚበቃ በቂ ዐቅምም ላይኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን
የሮምን ሃይማኖት የተቀበሉትን ወደ ተውት የስህተት መንገድ መመለስ ፈጽሞ ትክክል አይደለም፡፡




            በ1623 ዓ.ም የገበሬዎች ዐመጽ በላስታ ተጀምሮ እስከ ደምቢያ ደረሰ፡፡ በትግራይም ዐመጹ ከንጉሡ ቁጥጥር ውጭ ወጣ፡፡ አልፎንዞ ሜንዴዝ በስዕለ ክርስቶስ እየተመራ ንጉሡ የኃይል ርምጃ እንዲወስድ ይጫነው ነበር፡፡ የንጉሡ የእንጀራ ልጅ የትግራዩ ገዥ ተክለ ጊዮርጊስ በኃይል ካቶሊካዊነትን ለማሥረጽ የሚደረገውን ተግባር ተቃወመው፡፡ የወታደሮች ካህን የሆነውን ካቶሊካዊውን ያዕቆብንም ገደለው፡፡ ንዋያተ ቅድሳቱንም አቃጠላቸው፡፡ ከዚያም ዐመፀ፡፡ የሠርጸ ድንግል የልጅ ልጅ የሆነው ዘወልደ ማርያምም አብሮት አመጸ፡፡ በበጌምድር ታዋቂው ባላባት ላእከ ማርያምም ዐመፀ፡፡
ንጉሥ ሱስንዮስ ከፍተኛ ድንጋጤ ላይ የወደቀው ላስታ በመልክዐ ክርስቶስ መሪነት ሲያምፅ ነው፡፡ መልክዐ ክርስቶስ የዐፄ ዳዊት ልጅ የንጉሥ ሕዝብ ናኝ ተወላጅ ነው፡፡ ቀደምት ቤተሰቦቹ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን ብዙ መከራ ደርሶባቸዋል፡፡ ዐፄ ሱስንዮስ ካቶሊክነትን ሲቀበል በላስታ የነበሩት የሕዝብ ናኝ ተወላጆች በንጉሡ ላይ ዐመፁ፤ እንዲያውም ዙፋኑ ይገባናል አሉ፡፡ የዚህ ዐመጽ መሪ መልክዐ ክርስቶስ ነበረ፡፡
በላሊበላ ቤተ ገብርኤል የሚገኘው ወንጌል እንደሚገልጠው፤ መልክዐ ክርስቶስ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ከካቶሊክ ለመጠበቅ ነው የተነሳው፡፡ መልክዐ ክርስቶስ ከ1622 ዓ.ም ጀምሮ በአካባቢው ወታደር ማሰባሰብና ንጉሡን በካቶሊክነቱ ምክንያት መቃወም ጀመረ፡፡ ከትግራይ፣ ከበጌምድርና ከአምሐራ ካህናት፣ ገበሬዎችና ታላላቅ ሰዎች ጋር ቅንጅት መፍጠርም ጀመረ፡፡ የዐመፁ ዋና ማዕከል እመኪና የተባለው አምባ ነው፡፡ ሱስንዮስ በ1625 ዓ.ም በተደጋጋሚ ወደ ላስታ በመሄድ አምባውን ለመስበር ሞክሮ ነበር፤ ግን አልተሳካለትም፡፡ በዚሁ ዓመት መጨረሻ የላስታ የአምሐራ፣ የበጌምድርና የጎጃም 25,000 የሚሆኑ ገበሬ በመልክዐ ክርስቶስ መሪነት ወደ ደምቢያ ሆ እያለ መጣ፡፡ ዋግ ሹም ርቱዓ አምላክና ራስ ቢሆኖ መስፍነ ዋድላ ዋናዎቹ አዝማቾች ነበሩ፡፡
ጦሩ መጣሁ መጣሁ ሲል አቤቶ ፋሲለደስ ከሚመጣው ቁጣ እንዲያመልጥ አባቱን መክሮት ነበር፡፡
#አስቀድሞ ከዋና ከተማቸው ከደንቀዝ ከመነሣታቸው በፊት ያን ጊዜ የስሜን ደጃዝማች የነበረው ልጁ አቤቶሁን ፋሲል ቀረበና አባቱን ንጉሡን እንደዚህ አለው፡- ጌታችን ንጉሥ ሆይ፣ ባላየነውና ባልሰማነው፤ በአባቶቻችንም መጽሐፍ ላይ በሌለው የፈረንጆች ነገር የተነሳ እነሆ ሁሉም ዐመፀ፣ ሁሉም ታወከ፡፡ እኛም አንተን ፈራን፤ፊትህንም አፈርነው፡፡ ስለዚህም ከአንተ ጋር የምንነጋገረው በአፋችን ነው እንጂ በልባችን አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በጠላትህ ላይ ድል ማድረግን ቢሰጥህ የእስክንድርያን ሃይማኖት ለመመለስ ለእግዚአብሔር ተሳል; አለው፡፡ ንጉሡም እሺ አለ፤ ይላል፡፡
ሥልጣናቸውንና መሬታቸውን በሱስንዮስ ወንድሞችና በፈረንጆች የተነጠቁ መኳንንትም ከዐማፅያኑ ጋር ተባብረዋል፡፡ በ1623 ዓ.ም  ንጉሥ ሱስንዮስ ነገሮችን እያላላ ቢመጣም እጅግ በጣም ዘግይቷል፡፡ ሜንዴዝ የነገሮችን መለሳለስ ሊቀበል ፈልጎ ነበር፡፡ ማንም ሊያምነው ግን አልቻለም፡፡ በዚሁ ዓመት ትንሣኤ በኢትዮጵያውያን የዘመን አቆጣጠር መሰረት ተከበረ፡፡
ግንቦት 23 ቀን 1624 ዓ.ም ጦሩ እስከ ወይናደጋ መምጣቱ ተነገረ፡፡ ሱስንዮስ አማራጭ አልነበረውም፤ ጦሩን አስከትቶ ዘመተ፡፡ ሰኔ 3 ቀን 1624 ዓ.ም በተደረገው ጦርነት ርቱዓ አምላክና ራስ ቢሆኖ ሞቱ፡፡ መልክዐ ክርስቶስ ግን አመለጠ፡፡ በዕለቱ 8,000 የገበሬ ጦር ዘለቀ፡፡ ምድሩም በሰው አስክሬን ተሞላ፡፡ የሱስንዮስ ዜና መዋዕል ግን “የሞቱትን ቁጥር እንዳንቆጥር አይቻለንም” ይላል፡፡ በዚያ ቀን የሞተው ሕዝብ እጅግ ብዙ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ሜንዴዝም በጦርነቱ ዋዜማ የነበረውን ሁኔታ ለፓፓው በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ይገልጠዋል፡፡
መጀመሪያ ውሳኔ ከማሳለፍ ተቆጥቦ ነበር፡፡ ነገር ግን ዐመፀኛው ወደ ከተማው መጠጋት ሲጀምርና ሕዝቡ እርሱን መከተል ሲቀጥል፣ አንዳንድ መኳንንትም ከዐማፂው ጋር ሲቆሙ፤ ወደ ጦርነቱ ለመግባት ተገደደ፡፡ ዐመፀኞቹ በቁጥር ብዙ ነበሩ፡፡ ንጉሡም በፈረሰኛ ጦሩ ይበልጥ ነበር፡፡ ዐማፅያኑን በፈረሰኛ ጦር ገጠማቸው፡፡ ድልም አደረጋቸው፡፡ ከእርሱም ወገን የሞተበት ሁለት ወይም ሦስት ሰው ብቻ ነበረ፡፡ ከ5000-6000 የሚሆን ሰው ከጠላቶቹ ወገን ተገድለዋል፡፡ የዐመፁ መሪም አመለጠ፡፡ ንጉሡ እግዚአብሔርን የሚያመሰግንበት ዕድል አግኝቶ ነበር፡፡ ነገር ግን እጅግ የሚያስከፋ ነገር ፈፀመ፡፡;
ሜንዴዝ ከጦርነቱ በኋላ የሆነውን ነገር እንዲህ ይገልጠዋል፡-
በጥባጮችና የካቶሊክ እምነት ጠላቶች ንጉሡ የወደቀውን የአስክሬን መዓት እንዲመለከት አደረጉት፡፡ የዐማፅያኑ ደም ገና ትኩስ ነበር፡፡ “ተመልከት፤ ከእነዚህ ዐፅማቸው ሜዳውን ከሞላው ሰዎች መካከል አንድም የውጭ ሀገር ሰው የለም፡፡ ገዳዮቻቸውም የውጭ ሰዎች አይደለንም፡፡ ወንድሞቻችንንና የቅርብ ዘመዶቻችንን አጣን፡፡ ብናሸንፍም ብንሸነፍም ያው ነው፡፡ በሁለቱም ተሸናፊዎች ነን፡፡ ምንም ዓይነት መሳሪያ ሳናገኝ ይሄው አምስት ዓመት ሆነ፡፡ አሁን ግን ጊዜም ብርታትም ከእኛ ጋር አይደሉም፡፡ ለፈረሶቻችን ሣር የሚያጭድ ወንድ አናገኝም፡፡ በቅሎዎቻችንም ጠባቂ የላቸውም፡፡ መሣሪያ የሚሸከም አይኖርም፡፡ የዚህ ሁሉ ጣጣ መነሻ የሮም ሃይማኖት የሚባል ነገር ነው፡፡ ለእነዚህ ገበሬዎችና ያልተማሩ ሰዎች የትላንት ልማዳቸውን ካልመለስክላቸው በቀር መንግሥትህን አንተም የልጅ ልጆችህም ታጣላችሁ; አሉት፡፡  በዚህ ተደናግጦ፣ ብዙ ሰዎችም ተገድለው በዓይኑ ፊት ወድቀው ስለአየ ለእምነቱ ያለው ክብር ወረደ፡፡ ጽናቱንም አጣ ይላል፡፡
ሜንዴዝ እንደሚለው ንጉሡ በዚህ ንግግር ደነገጠ፡፡ ሜንዴዝ ንጉሡን ለማበረታታትና ወደ ቀድሞ መንፈሱ ለመመለስ ደጋግሞ መሞከሩን በደብዳቤው ላይ ይገልጣል፡፡ እርሱ፣ ጳጳሱና አምስት ኢየሱሳውያን እየተመላለሱ ሞክረዋል፡፡ ንጉሡ ግን ወደ ቀድሞ መንፈሱ መመለስ አልቻለም፡፡ ሜንዴዝ ሁኔታውን እንደዚህ ይገልጠዋል፡፡
መጀመሪያ እርሱና የሀገሩ ሰዎች መሰላቸታቸውን ነገረኝ፡፡ “ወታደሮቼ እንዲሸሹና የጦርነቱ ጊዜ እንዲራዘም የሚያደርግ ጊዜ መስጠት የለብኝም” አለኝ፡፡ ሃይማኖቱን ጥያቄ ውስጥ መክተት ሳይሆን የተወሰኑ ሥርዓቶችን መተው ነው ሲል በተደጋጋሚ ነገረኝ፡፡ እኔ ግን “ለእኔ ጉዳዩ የሥርዓት እንዳልሆነ ግልጽ ሆኖልኛል፡፡ ነገር ግን የሃይማኖቱ ምሶሶ ነው የተጠቃው፡፡ በስርዓት ጉዳይ አጨቃጫቂ ነገር ካለ፣ ለመስማማት ዝግጁ ነኝ፡፡ እርሱ መለኮታዊ ሕግ አይደለምና፡፡ የተወሰኑ አባቶችን ልከህ ልንፈታው እንችላለን” አልኩት፡፡ እርሱም ያንን እንደሚያደርግ ቃል ገባልኝ፡፡
ነገር ግን ሰዎቹን አልላካቸውም፡፡ ወይም ደግሞ የእርሱን ሐሳብ አልገለጠልኝም፡፡ እኔ የላክኋቸው መልእክተኞች ሲጠይቁትም አልመለሰላቸውም፡፡
በዮሐንስ መጥምቅ ልደት ቀን በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው አለቆች ወደ ቤቴ መጡና “ንጉሡ ዙፋኑን ለመጠበቅ የእምነት ነጻነትን (ሰው የሮምን ወይ የኢትዮጵያን እንዲመርጥ) ከማወጅ የተሻለ ዕድል የለውም” ሲሉ በንጉሡ ስም ተናገሩ፡፡ እኔም ንጉሡ ይህንን ለሁሉም ለመስጠት ሐሳብ እንዳለው ጠየቅኳቸው፡፡ የሮምን ሃይማኖት ላልተቀበሉትና ለተቀበሉት፡፡
እነርሱም “ዓላማው ለሁሉም እኩል ነጻነት መስጠት ነው” አሉኝ፡፡ እኔም “ንጉሡ ወደ ሮም ሃይማኖት ቀንበር ያልገቡትን ሊተዋቸው ይችላል፡፡ እነርሱን እሺ ለማሰኘት የሚበቃ በቂ ዐቅምም ላይኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን የሮምን ሃይማኖት የተቀበሉትን ወደ ተውት የስህተት መንገድ መመለስ ፈጽሞ ትክክል አይደለም፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሰዎች እምነታቸውን በነጻነት እንዲመርጡ መደረጉ ቀርቶ ሁሉም ወደ አባቶቻቸው እነት እንዲመለሱ ታወጀ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በተደጋጋሚ የሮም ሃይማኖት ለጦርነትና ለግድያ ምክንያት ነው ብለው ስለሚከሡ ነው፡፡--
**
ምንጭ፡- (ከዲያቆን ዳንኤል ክብረት ከእቴጌ ዕሌኒ እስከ ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ፤የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ግንኙነት;፤ግንቦት 2013 ዓ.ም፤ የተቀነጨበ)

Read 1456 times