Tuesday, 22 June 2021 00:00

ኮቪድ-19 የልጆች የጉልበት ብዝበዛን አባብሶታል

Written by  ብርሃኑ በላቸው አሰፋ
Rate this item
(1 Vote)

 “በምንምና በማንም የማይተኩ ልጆቻችንን ልንጠብቃቸው ይገባል”
                    
          የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ ) እ.ኤ.አ በ2020 ሪፖርቱ መሰረት፤ በመላው አለም 152 ሚሊዮን ልጆች ለጉልበት ብዝበዛ ተዳርገዋል፡፡ ይህ ቁጥር ካለፉት አራት አመታት ጋር ሲነፃፀር በ8 ነጥብ 4 ሚሊዮን ይልቃል፡፡  
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፣ ኮቪድ-19 መቀስቀሱን ተከትሎ፣ 9 ሚሊዮን ተጨማሪ ልጆች ለጉልበት ብዝበዛ ተጋልጠዋል፡፡ እንደ ዩኒሴፍ ሪፖርት፤ ከ5-17 የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ልጆች መካከል ግማሹ ለከባድ ስራ በመዳረጋቸው የጤናቸው፣ የደህንነታቸውና የሞራል እድገታቸው አደጋ ላይ ወድቋል፡፡
በአፍሪካ ከአምስት ልጆች አንዱ ለጉልበት ብዝበዛ ይጋለጣል፡፡ በተለይም በአህጉሩ የጦርነትና የግጭት ቀጠናዎች ውስጥ ችግሩ ይባባሳል፡፡ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ከአለምአቀፉ የስራ ድርጅት ጋር ባቀረቡት የ2015 ሪፖርት፤ በኢትዮጵያ የልጆች ጉልበት ብዝበዛ 42 ነጥብ 7 በመቶ ይደርሳል፡፡
ልጆች በአካልም ሆነ በአእምሮ ብስለት ያልዳበሩ በመሆናቸው ለጥቃት የተጋለጡ ናቸው። በተለይም የልጆች ጉልበት ብዝበዛ በስውርም ሊፈጸም ይችላል፡፡ የልጆች የጉልበት ብዝበዛ አይነቶችን  በዋናነት በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው የቤት ውስጥ የጉልበት ብዝበዛ ሲሆን  ሁለተኛው ደግሞ ባርነት ወይንም የግዴታ ስራ ነው፡፡
በቤት ውስጥ የሚፈፀሙ የልጆች ጉልበት ብዝበዛዎች በአብዛኛዉ ከማህበረሰቡም ሆነ ከመንግስታዊ አካላት እይታ የተሰወሩና በግልጽ የማይከናወኑ በመሆናቸው የልጆች ስቃይ በጣም የከፋ ነው። በዚህም የተነሳ በአንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች የችግሩ መኖር እንኳን ሳይታወቅ ታፍኖ ይኖራል።
ሁለተኛው አይነት የልጆች ጉልበት ብዝበዛ ደግሞ የባርነት ወይም የግዴታ ስራ ነው፡፡ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፤ 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ልጆች በአስገዳጅ ሁኔታ የጉልበት ብዝበዛ ይፈጸምባቸዋል፡፡ እነዚህ ልጆች በአብዛኛው ከብድር እዳ ፣ ባርነትና ከፆታዊ ጥቃት ጋር ተያይዞ ነው የጉልበት ብዝበዛ የሚካሄድባቸው፡፡  በዚህ  የጉልበት ብዝበዛ ልጆች ሳያውቁ  በገንዘብ ይሸጣሉ።
በሌላ በኩል፤ ልጆች  የወላጆቻቸው እዳ መያዣ ሊሆኑ ይችላሉ። ይኸውም ወላጆች ያለባቸውን እዳ መክፈል ሲያቅታቸው ልጃቸውን አሳልፈው ይሰጣሉ። በዚህ ሁኔታ ልጆች ከአቅማቸው በላይ ምንም አይነት ትምህርትም ሆነ እንክብካቤ ሳያገኙ እንደ ባሪያ ይሰራሉ። ለልጆች ጉልበት ብዝበዛ የተጋለጡት  አብዛኛውን ጊዜ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ደላሎች አማካኝነት ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው ከገጠር ወደ ከተማ እንዲኮበልሉ ይደረጋሉ፡፡
የልጆች ጉልበት ብዝበዛ መንስኤ ከሚባሉት መካከል በዋናነት ድህነት ፣ ስራ አጥነት ፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ፣ የትምህርት እድል እጦት ፣ ጦርነትና ግጭት  ይጠቀሳሉ፡፡  የልጆች ጉልበት ብዝበዛ ለከፍተኛ አካላዊ፣ ስነልቦናዊና ማህበራዊ  ጉዳቶች ያጋልጣል፡፡ ለብዝበዛ ሰለባ የሆኑ ልጆች  ከቀላል የአካል ጉዳት እስከ ሞት ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡ ለአብነትም አካላዊ ቁስለት ፣ መድማት ፣ መቃጠል አልያም  እድሜ ልክ የማይሽር አካላዊ ጉዳት ይገኝበታል።
እነዚህ ልጆች የፍርሃት ፣ የብቸኝነት ፣ ራስን የመጥላትና የተስፋቢስነት ስሜት ይሰማቸዋል፡፡ በራስ የመተማመን ስሜታቸው ይሸረሸራል፡፡ በማህበራዊ መስተጋብራቸው ላይም አሉታዊ ተፅኖ ያሳድራል፡፡ እነዚህ ተደራራቢ ችግሮች ደግሞ ለአደንዛዥ እፆችና ለተለያዩ ሱሶች እንዲጋለጡ ያደርጋቸዋል፡፡
በመሆኑም ልጆች ገና በጨቅላ እድሜያቸው የሚደርስባቸውን የጉልበት ብዝበዛ ለመከላከል ሁላችንም የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል፡፡ በተለይም ቤተሰብ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት በምንምና በማንም የማይተኩ ልጆቻችንን ልንከባከባቸው፣ ልንጠብቃቸውና ልናበረታታቸው ይገባል፡፡ በልጆች ጉልበት ብዝበዛ ዙርያ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እንዲኖሩ ይመከራል፡፡ ከመንግስት በኩል ጠንካራ ህግ ማፅደቅና ለተፈፃሚነቱም መትጋት ይጠበቃል፡፡  የሲቪክ ማህበረሰብ ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና መገናኛ ብዙኃን በልጆች ጉልበት ብዝበዛ ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል፡፡ ሠላማችሁ ይብዛ!!
**
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 903 times