Tuesday, 22 June 2021 00:00

ዝም- ጸጥ- እረጭ - ርግት

Written by  በስንታየሁ አለማየሁ
Rate this item
(0 votes)

  ትውስታ አድማስ

“--ዝምታ የተወጠረን ገመድ እንደ ማርገብ ነው፥ ዝምታ ከሩጫና ከውክቢያ ጋብ ብሎ ፋታ እንደ መውሰድ ነው፥ ፋታ ወስደን ስናበቃ ትላንት እንዴትና ምን እንደነበርን፥ ዛሬ የትና ምን ላይ እንዳለን ፥ ነገ ወዴትና እንዴት እንደምንጓዝ እናውጠነጥናለን።--”
                  
                  ስለ ኑሮው፣ ስለ ፖለቲካው፣ ስለ እምነቱ፣ ስለ መዝናኛው፣ ስለ ሀዘኑ፣ ስለ ደስታው፣ በዙሪያችን ስላሉ አጠቃላይ ተፈጥሮአዊም ሆኑ ሰው ሰራሽ ነገሮች በትክክል አስበን፣ ትክክለኛ መፍትሄ ማምጣት ይጠበቅብን ከሆነ፣ ለዚያ ትክክለኛው የህይወት ቁልፍ፣ ለራስ ጊዜ ሰጥቶ፣ በዝምታ ከራስ ጋር መነጋገር መቻል ነው:: በአዕምሯችን ላይ ተዘበራርቆ የተቀመጠው አለማችን፣ በልባችን ላይ ግን ሰላምና ፍቅርን ያገኛል፡፡ አዕምሮ የተቀነባበረና የተሰላ እውቀትን ሲሻ፣ ልብ ግን ህያው የእስትንፋስ ስሜትንና ፍቅርን ያቀዳጃል፡፡ እነዚህን ሁለት የአካለ ስጋ ሞተሮች ግብርና አካሄድ በውል አሰላስሎ ለማጥናት ዝም መሰኘት፣ ከራስ ጋር ስብሰባ መቀመጥ፣ የራስን ቃለ ጉባኤ በገዛ እግረ ህሊናችን ተጉዘን፣ በገዛ ነፍሳችን እጆች መፃፍ ያስፈልጋል፡፡
በፀጥታ ዝም፣ ቀስ ብሎ ምንም ሳያንሾካሹኩ፣ ዝም እንዳሉ እቃ ሳያጋጩ፣ ብረት ወይም ቆርቆሮ ነገር ሳይረግጡ፣ ሳልም ሳያስሉ፣ እሚያንሸራትት ነገር እረግጠው ድንገት ጧ ብለው ወድቀው ሰው ሳይረብሹ፣ ፀጥታ ሳያደፈርሱ፣ ፊሽካ ነገርም ሳያጮሁ ወይም እሚያለቅስ ልጅ ሳያዝሉ፣ መኪና ሳያንጋጉ፣ እሚነዳ መንጋም ሳያግተለትሉ፣ ታኮ ጫማም ሳይጫሙ ወይም እሚጮህ ከስክስ፣ እሚላመጥ ማስቲካም ቢሆን ወይም ከንፈር መምጠጥ --- ምንም ነገር ሳያደርጉ ዝም እንዳሉ ዝም ማለት፣ የሌላውንም ሆነ የራስን ሰላምና ፀጥታ ላለመበረዝ ወይም ላለማበላሸት ፀጥ ብሎ በዝምታ ቀስ እንዳሉ ዝም ማለት፤ ለዝምታ በዝምታ ከራስ ጋር ዝም እንዳሉ ተማክሮ፣ በፀጥታ ቀስ ብሎ ዝም ማለት፤ ሌላው ከገባበት አለምና ምሳጤ ነቅቶ በኛ ከንቱ ጩኸት እንዳይረበሽና ከነበረበት አውድ እንዳይሰናከል፣ በጥንቃቄ ዝም መሰኘትን መልመድ፡፡ በኛ በአንዳንዶች ዝም ማለት ምህኛት ብዙ ጩኸቶች እራሳቸውን ታዝበው ዝም ሲሰኙ መመልከት፣ ጩኸት እሚበረታው የበለጠ አጯጯሂ ሲያገኝ ነውና በዝምታ መበርታት፣ አጃቢ አልባ ብቸኛ ጩኸት የእብደት እንኳ ቢሆን ብቻውን መሆኑን ሲያውቅ ደንግጦ ዝም ወደ ማለት ይመጣል፡፡ ኳኳታን በመጥላት ብቻ ሳይሆን የውስጥን ሰላም ለመፈለግ ብሎም የከባቢውን አየር ላለመበረዝ ስንል ዝም ማለት፡፡ ዝም እንዳልን የአለምን ዝምታና ጩኸት ማሰስ፣ የዝምታን ዜማና ግጥም ዝም እንዳልን ማንጎራጎር፤ የውስጥን ዝምታ አውጥቶ በዝምታ የዘፈነ ከያኒም ያለ እንደሆነ፣ ያንን ዝም እንዳልን በዝምታ ውስጥ አብረን መዝፈን፡፡
የሸንበቆውና የዛፉ እንቅስቃሴ፣ የባህሩና የውቅያኖሱ ውዝዋዜ፣ የነፋሱ ሽውታና የበጋው ፀሐይ ሙቀት፣ የክረምት የጉም ጉዞና የደራሽ ጎርፍ ነገረ ስራ፣ የሰማዩ ጉርምርምታና የአካባቢው ቅዝቃዜ፣ የቀዬው ልምላሜና የከብቱ ፌሽታ ድንፋታ፣ የእረኞች ከብት የማገድ ተግባር፣ የገበሬው ባተሌነት፡፡ ወዲህ የከተሜው ዘናጭነት፣ ጎፈሬው፣ ቁንዳላው፣ ፍሪዙ፣ ባላቶሊው፣ መላጣው፣ ክብ ፂሙ፣ ባለ ከራባቱ፣ ባለ ጉልበት ቅድ ሱሪው፣ ባለ ሂውማን ሄሯ፣ ባለ ቦርሳው፣ ባለ ላፕቶፑ፣ ባለ መኪናው፣ ባለ ፎቁ፣ ነጋዴና ወዛደሩ፣ አስተማሪና አስተዳደሩ፣ ስፖርተኛውና አርቲስቱ፣ ፖለቲከኛውና የቤተ-እምነት ሰው ሁሉ፡፡ እንደ ሰው ሁሉ የቤት እንስሳት ይዞታና አኗኗር….ደግሞም የዱር እንስሳትና የሃገር ታሪካዊ ቦታዎች…. እነዚህ እና መሰል የህይወት አካሎች በሙሉ የጠቀስናቸውን ጎብኝተን ስናበቃ፣ የጉብኝታችንንና የእይታችንን ብሎም የመደመም የመናደዳችንን ስሜት የምናስቀምጠው በልቦናችን ጓዳ ውስጥ ነው:: ከልቦናችን አውጥተን በአዕምሯችን ሸምነንና አስልተን ስናበቃ መልካም ወደሆነው የጋራ የልብና የአዕምሮ ውሳኔ እናቀናለን፡፡ ይህንን ድርጊያ ለማሳመርና የእኛነት ስሪት ዛሬ ላይ ለተፈጠረውና ላፈጠጠው ገሃዳዊ እውነት ችግር መፍትሄ መሆኑን በውል ለማወቅ ስንል የዝምታ መረብ ውስጥ፣ የራስ አለም ምሳጤና ንጉደት ውስጥ መጥለቅ ያስፈልጋል፡፡
ከተሰለፍንበት ታክሲ ተራ፣ ከመርካቶ ገበያ ጫጫታ፣ ከዳንኪራ ቤት የወል ደስታ፣ ከስታዲዬም ሆይሆይታ፣ ከግርግርና ከስብሰባ ቦታ አንድምታ ተገልለን በየራሳችን ቤት፣ በየራሳችን የአዕምሮ ወለል፣ በየነፍሳችን ኮሪደር ላይ ብንሰበሰብ፤ አለምም እኛም በእፎይታና በሰላም አየር እንከበባለን፡፡
ደግሞስ በጫጫታ ውስጥ ልክ የኦዞን መስመር በተቃጠለ አየር እንደሚሸነቆረው ሁሉ ጩኸታችን የአሰተሳሰብን አየር ቢሸነቁር እንጂ ሌላ ምን ሊያተርፈን? የሙዚቃው ልሂቃን እነ ሞዛርት ሲናገሩ፤ Silence is the core part of Music ይላሉ። በእያንዳንዱ ሙዚቃ ውስጥ የሚያስፈልግ እረፍት አለ …ያ እረፍት ነው በሙዚቃ ውስጥ እንደ ዝምታ የሚቆጠረው።
ይህ የሚያሳየን እንግዲህ በጥድፊያው አለማችን መካከል፥ በነገሮቻችን መካከል እረፍት ወይም አንዳች ዝምታ እንደሚያስፈልገን ነው።
ዝምታ የተወጠረን ገመድ እንደ ማርገብ ነው፥ ዝምታ ከሩጫና ከውክቢያ ጋብ ብሎ ፋታ እንደ መውሰድ ነው፥ ፋታ ወስደን ስናበቃ ትላንት እንዴትና ምን እንደነበርን፥ ዛሬ የትና ምን ላይ እንዳለን፥ ነገ ወዴትና እንዴት እንደምንጓዝ እናውጠነጥናለን። ስለዚህ ይህንን ለማድረግ በሎሬቱ አንደበት እንዲህ እንበል……
ከሰው መንጋ እንገንጠል
ላንድ አፍታ እንኳን እንገለል
ዝም ብለን አብረን ዝም እንበል
እያልን በዝምታ ዝምተኛ ግለሰብ አባዝተን፣ ዝም የሚል ከጩኸት የራቀ ማህበረሰብ ወልደን፣ ዝም ጸጥ ረጭ ርግት ያለ፣ የራሱን ችግር በራሱ መፍትሄ የሚፈታ ሰላማዊ ሀገር እንፈጥራለን ብዬ አስባለሁ:: ቸር እንሰንብት!
**
( ምንጭ:-አዲስ አድማስ ድረ ገጽ ፤ሜይ 28, 2019)


Read 815 times