Print this page
Saturday, 19 June 2021 17:36

ሃሌሉያ ሆስፒታል የስም ማጥፋት ወንጀል እንደተፈፀመበት ገለፀ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

 ከኮቪድ ህክምና ክፍያ መብዛት ጋር በተያያዘ የተነሳው ወቀሳ አግባብነት የለውም ብሏል
        -የጤና ሚ/ር በክፍያ ደረጃ ከ5 ሆስፒታሎች በ4ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጦታል
       -እስከ አሁን ከ700 በላይ ለሚሆኑ የኮቪድ-19 ታማሚዎች ህክምና ሰጥቷል
            
                 ሃሌሉያ አጠቃላይ ሆስፒታል፤ ከኮቪድ-19 ህክምና ክፍያ ጋር በተያያዘ የስም ማጥፋት ወንጀል እንደተፈፀመበት ገለፀ፡፡ ሆስፒታሉ ሰሞኑን የህክምና ማዕከሉን አደረጃጀትና የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ለጋዜጠኞች አስጎብኝቷል፡፡
ላለፉት 12 ዓመታት በተለያዩ የህክምና ዘርፎች አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው ሃሌሉያ አጠቃላይ ሆስፒታል፤ ከኮቪድ-19 በሽታ ህክምና አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የስም ማጥፋት ወንጀል ተፈፅሞበኛል፤ ሆስፒታሉ ከሚታወቅበትና ከሚሰጠው ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት በተቃራኒው ስሜ ያለአግባብ እንዲጠፋ ተደርጓል ሲል ወቅሷል፡፡
የሆስፒታሉ አስተዳደር በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳስታወቀው፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወደ አገራችን መግባቱን ተከትሎ ከመንግስት ጎን በመቆምና ወገኖቹን በመታደግ ሆስፒታሉ ቀዳሚ እንደነበርና አራት ኪሎ የሚገኘውን የሆስፒታሉን ቅርንጫፍ ከነሙሉ አደረጃጀቱና ከህክምናው ባለሙያዎቹ ጭምር መንግስት እንዲገለገልበት በመስጠት፣ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ሲወጣ የቆየ ሲሆን፤ በመቀጠልም ሆስፒታሉ የኮቪድ-19 ህክምናን እንዲሰጡ ፈቃድ ከተሰጣቸው  የግል ተቋማት መካከል ቀዳሚው በመሆን የመንግስትን ሸክም በማቅለሉ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሲያደርግ መቆየቱ ተነግሯል፡፡
ሆስፒታሉ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎቱን ከሌሎች አቻ ተቋማት ጋር ሲነፃፀር ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ሲሰጥ መቆየቱን የገለፁት የሆስፒታሉ ባለቤትና ቺፍ ክሊኒካል ኦፊሰር ፕሮፌሰር ጌታቸው አደራዬ፤ የጤና  ሚኒስቴር በኮቪድ-19 ህክምና ላይ በተሰማሩ 5 ሆስፒታሎች ላይ በቅርቡ ባደረገው ጥናት፣ ሃሌሉያ ሆስፒታል በብዙ መልኩ  የተሻለ መሆኑንና በክፍያ መጠኑም ከ5 ሆስፒታሎች በአራተኛነት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የሚገልጽ መረጃ እንደሰጣቸውም ተናግረዋል፡፡ አንድ የሚዲያ ተቋም ሆስፒታሉ ለኮቪድ ታማሚዎች የተጋነነ ዋጋ ያስከፍላል በሚል ያቀረበብን ዘገባና ለዘገባው የተጠቀማቸው መረጃዎች ፈጽሞ የጋዜጠኝነትን ስነ-ምግባር ያልተከተለና የሆስፒታሉን ስም ሆነ ብሎ ለማጉደፍ የተደራጀ የሚያስመስለው ነው ብለዋል፡፡
የሚዲያ ተቋሙ ለሆስፒታላችን ምንም ዓይነት ቅሬታ ያልቀረበባቸውን ጉዳዮች በማንሳት የእኛን ምላሽ ሳያካትትና ስለ ጉዳዩ የምንሰጠውን መረጃዎች ሳያገናዝብ በሚያሳዝን ሁኔታ ስማችንን አጉድፎታል፡፡ ዘገባው  የእኛንም ምላሽ ማካተትና ሚዛናዊ መሆን ሲገባው፣  ፕሮግራሙን በወገንተኝነት ማስተላለፍ እንደማይቻል የሚገልፅ የፍ/ቤት የእግድ ትዕዛዝ ወጥቶበት እያለ፣ እግዱን ጥሶ ፕሮግራሙን አስተላልፎታል፤ በዚህም ሆስፒታላችን ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል ሲሉ ፕሮፌሰር ጌታቸው ተናግረዋል፡፡
ጉዳዩ በፍርድ ሂደት ላይ መሆኑን በመጠቆም፤ መገናኛ ብዙኃን ህብረተሰቡን የሚያገለግሉ ተቋማት ላይ የሚሰሯቸው ሚዛናዊነት የጎደላቸው ዘገባዎች፣ የገንዘብ ብቻ ሳይሆኑ  ከፍተኛ የሞራል ኪሳራም የሚያደርሱ በመሆናቸው ሊያስቡበት ይገባል ብለዋል የሆስፒታሉ ባለቤት፡፡
በመንግስት የጤና ተቋማት የሚሰጡ የኮቪድ ህክምናዎች ለታማሚው በነፃ ቢሰጡም መንግስት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ወጪ በየወሩ እንደሚያደርግባቸው የገለፁት በጤና ሚኒስቴር የህክምና ዳይሬክተር ጄነራል ዶ/ር ያዕቆብ ተሰማ፤ በመንግስት አቅም ብቻ ይህንን ወረረርሽኝ መዋጋት ባለማቻሉ የግሉ ዘርፍም ተሳታፊ እንዲሆን መደረጉን ተናግረዋል፡፡
አንዳንድ መገናኛ ብዙኃን መንግስት ቁጥጥር የሚያደርግበትን ጉዳይ በመረጃ ላይ ያልተመሰረቱ ዘገባዎችን በማሰራጨት የግሉ ዘርፍ የሚያደርገውን አስተዋፅኦ የሚያሳንስ ተግባር በፈፀማቸው አሳዝኖናል፤ ይህ ዓይነት ተግባር የግሉ ዘርፍ ወረርሽኙን በመዋጋቱ ረገድ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ የሚያደናቅፍ ነው ብለዋል፡፡
የመንግስት የጤና ባለሙያዎች በኮቪድ ህክምና ሥራ ላይ እያሉ ሲታመሙ የሚታከሙበት ቦታ ባለመኖሩ ብዙ በተጨነቅንበት በዚያ በከባድ ወቅት ሆስፒታሉ የአራት ኪሎ ቅርንጫፉን ከነሙሉ ማቴሪያሉና የሰው ሃይሉ መንግስት እንዲጠቀምበት መስጠቱ ሊያስመሰግነው የሚገባና ለህዝብ ወገንተኝነቱን የሚያሳይም ነው ሲሉም ተናግረዋል፤ ዶ/ር ያዕቆብ፡፡
ሆስፒታሉ ከኮቪድ-19 ህክምና ጋር በተያያዘ በስፔሻሊስት ሃኪሞች የታገዘ ህክምና የሚሰጥ፣ ታማሚዎች ሁሉንም ዓይነት ህክምና በአንድ ቦታ እንዲያገኙ በማድረግ ህይወታቸውን ለመታደግ ከፍተኛ ጥረት የሚያደርግ መሆኑ ይታወቃል ያሉት የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ የትናየት እሸቱ፤ ከታካሚዎቻችን መካከል በርካታዎቹ በሆስፒታሉ በሚያገኙት የህክምና  እርዳታና ጥራት ያለው አገልግሎት እጅግ መደሰታቸውን በተደጋጋሚ ነው የሚገልፁልን፤ ሆኖም ከዚህ በተቃራኒው ፍፁም ሆስፒታሉን ሊገልፅ የማይችልና  ከእውነት የራቀ ዘገባ በመገኛና ብዙኃን በመተላለፉ እጅግ ሞራላችን ነክተውታል ብለዋል፡፡
ድርጊቱ ሆስፒታሉን በአገራችን ብሎም በአፍሪካና በዓለም ደረጃ ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት የሚታወቅ እንዲሆን እያደረግን ያለውን ጥረት ለማደናቀፍ የታለመ ቢሆንም፣ ዓላማችንን በእንዲህ አይነት ሃሰተኛ ዘገባ ለመስበር የሚደረገውን ሙከራ በመቋቋም፣ ሃሳባችንን ከግብ ለማድረስ እንሰራለን” ሲሉ ተናግረዋል፤ ዋና ስራ አስፈፃሚዋ፡፡
ሃሌሉያ ሆስፒታል ከ33 በላይ የተለያዩ የህክምና አገልግሎቶችን በዘመናዊና ጥራቱን በጠበቀ መልኩ እየሰጠ መሆኑን የተናገሩት የሆስፒታሉ ምክትል ዋና ስራ  አስፈፃሚ አቶ ይድነቃቸው ስሜ፤ 118 አስተኝቶ ማከሚያ አልጋዎችና ጥራቱን የጠበቀ ላብራቶሪ ያለው መሆኑንና እስካሁንም ከ735 በላይ ለሚሆኑ የኮቪድ ህሙማን ህክምና መስጠቱን ተናግረዋል፡፡ ሆስፒታሉ ከ450 በላይ ለሚሆኑ ባለሙያዎችና ሠራተኞች የሥራ ዕድል የፈጠረ መሆኑ ታውቋል፡፡

Read 2144 times