Saturday, 19 June 2021 17:40

ድምጼን የምሰጠው ለማነው?

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

  ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ፣ በስድስተኛ ዓመቱ  በመጪው ሰኞ፣ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በሚደረገው የድምጽ መስጠት ተግባር በአመዛኙ ይጠናቀቃል፡፡ ሁለተኛው ዙር የድምጽ መስጫ እለት ጳጉሜ 1 ቀን 2013 እንደሚሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
በምርጫው፤ በክልልና በአገር አቀፍ 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች ለውድድር የቀረቡ ሲሆን ጎላ ብለው እየታዩ ያሉት ሰባት ያህል ፓርቲዎች ናቸው፡፡ “ጎላ ብለው” የሚለው ገለጻ የሚያመለክተው ለክልልና ለተወካዮች ምክር  ቤት ያቀረቡትን የእጩ ተወዳዳሪ ብዛት መመዘኛ መስፈርት በማድረግ ነው፡፡ ከሰባቱ ውስጥ  ዝቅተኛ የተወዳዳሪ ቁጥር ያቀረበው የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ነው፡፡ ፓርቲው በዘመነ ሕውኃት/ኢሕአዴግ በተካሄዱ ምርጫዎች ሲሳተፍ የቆየ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በ2011 ዓ.ም የወጣው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ-ምግባር አዋጅ፣ የዳግም ምዝገባውን መመዘኛ ከፍ በማድረጉ፣ ብዙ ፓርቲዎች ረግፈው ሲቀሩ፣ ፓርቲው  ህልውናውን በማትረፉ እንደ ሌሎቹ ሁሉ እድለኛ ያደርገዋል፡፡
የፈረሱት  ፈርሰው፣ አንዳንዶች እራሳቸውን በትነውና በአዲስ መንገድ አደራጅተው ወደ ፖለቲካው  እንደ ገቡት ሁሉ፣ በርካታ አዳዲስ ፓርቲዎችም ተፈጥረው ወደ ትግል መስኩ ተቀላቅለዋል፡፡
ለብዙ ዓመታት የዳር ተመልካች የነበሩ ምሁራን በርከት ብለው ወደ እጩ ተወዳዳሪነት የመጡ በመሆኑ በአንዳንድ የምርጫ ክልሎች “ማንን መርጠን ማንን እንተዋለን” የሚያሰኝ ሁኔታ ፈጥረዋል፤ በተለይም ለተወካዮች ምክር ቤት፡፡
በዚህ አጋጣሚ በሰላማዊ ትግሉ ውስጥ፣ ሲደርስባቸው የነበረውን ልዩ ልዩ ጫና፣ እስራትና መንገላታት ችለው አገራችንን ለዚህ ወቅት ላበቁ ወገኖች ምስጋና ማቅረብ አክብሮትን መግለጽ የተገባ ነው ብዬ ስለማምን፣ ምስጋናና አክብሮቴን እነሆ ብያለሁ፡፡ በወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ወደ ሚመራው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንመለስ፡፡ ቦርዱ ነፃና ገለልተኛ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩም የቦርዱ ሰብሳቢዋ ወይዘሪት ብርቱካንም ደጋግመው ተናግረዋል፡፡ ገለልተኛ አልሆነልንም የሚሉ ስሞታዎች መኖራቸው ግን የሚካድ አይደለም፡፡ እንደ ቀደመው ሁሉ ተቃናቃኝ ፓርቲዎች፣ ጽ/ቤቶቻችን ተዘጋብን አባሎቻችን ሰበብ እየተፈለገ ታሰሩብን የሚሉ አቤቱታዎች ወደ ቦርዱ ሲያቀርቡ ከርመዋል፡፡ ቦርዱም ቢሆን አሌ የሚለው ጉዳይ አይደለም፡፡ የብልፅግና ሹማምንት የተቀናቃኝ ፓርቲዎችን ስም ማጥፋታቸውን እንዲያቆሙ እንዳደረገው ሁሉ በዚህም ጊዜ እጃችሁን ሰብስቡ ማለት ነበረበት፡፡  
በውድድሩ ላይ የሚገኙት ፓርቲዎች እምብዛም ከቀደመው የተሻለ ነገር እንዳልጠበቃቸው በአደባባይ እየተናገሩ ነው፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ክልል፣ ከብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ በስተቀር ሌላው ፓርቲ  ትንፍሽ እንዳይል እገዳ ተደርጓል የሚለው ክስ ተደጋግሞ ተሰምቷል፡፡ ነገሩ ለምርጫ ቦርድም አዲስ እንዳልሆነ የታወቀ ነው፡፡ የራሱን ክልል ለሌላው ፓርቲ የተዘጋ በማድረጉ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በላይ መወቀስ ያለበት በአቶ ሽመልስ አብዲሳ የሚመራው የክልሉ መንግሥትና የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ነው፡፡ በአካባቢው እንዳይደርሱ የተገፉ ፓርቲዎች ጉዳዩን ወደ ፍ/ቤት ወስደው ፍትሕ ሲጠይቁ ግን አልታዩም፡፡
ቦርዱን የፈተነው ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የሐረሪና የባልደራስ ጉዳይ ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡ ሀረሪዎች እስከ ሰበር ድረስ  ተጉዘው ከዚህ ቀደም በነበረው መንገድ የድምፅ አሰጣጡ እንዲቀጥል ሲያስወስኑ፣ ባልደራስ በጥርጣሬ ተይዘው የሚገኙ አባላቱ፣ እጩ ተወዳዳሪ ሆነው በምርጫው እንዲሳተፉ ያቀረበው ጥያቄ በፍ/ቤት ተቀባይነት አግኝቶ፣ እነ አቶ እስክንድር በእጩ ተወዳዳሪነት እንዲመዘገቡ አስወስኗል፡፡ በመሆኑም ቦርዱ ለከፍተኛ የገንዘብ ወጪና ለተጨማሪ ሥራ ተዳርጓል፡፡ በአንፃሩ ይህ ተግባር በእርግጥም የፍትሕ ሥርዓቱ በለውጥ ሂደት ላይ ነው የሚያሰኝም ሆኗል፡፡
ቦርዱ የማያውቃቸው የሰባ ዘጠኝ የምርጫ ጣቢያዎች መፈጠርና የሶማሌ ክልል የድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ የተሰራው ወንጀል፣ ቦርዱ እስከ ምን ድረስ ራሱን ለማጥራትና ምርጫውን ታማኝ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ሊመሰገንበትም ይገባል፡፡
ይህ ሁሉ ታልፎ አሁን ከድምፅ መስጫው እለት ደርሰናል፡፡ ለመራጭነት የተመዘገብን ሰዎች ለድምፅ መስጠት ስንነሳ ማንን ልምረጥ ዋና ጥያቄ ይሆንብናል፡፡  ማንን ልምረጥ  የሚለው ጥያቄ መልስ የሚያገኘው በየምርጫ ጣቢያችን ለውድድር ከቀረቡት ሰዎችና ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ነው፡፡ ለውሳኔያችን መነሻና መድረሻ መሆን ያለበት እጩውን ያቀረበው ፓርቲ  ነው ወይስ የፓርቲው እጩ ተወዳዳሪ? ይህም ጥያቄ ነው፡፡
ለእኔ ያለ ሰው ፓርቲዎች ባዶ ቀፎዎች ናቸው፡፡ የተነሳሁት ሰው  ለመምረጥ ነው፡፡ ድምጼን የምሰጠውም ለሰው ነው፡፡ ከሰውም ለሰው፤ በተግባር ለሚፈተን!

Read 4181 times