Tuesday, 22 June 2021 00:00

የ120 ዓመቱ አዛውንትና አቅመ ደካሞች ከአጣዬ ጥቃት እንዴት ተረፉ?

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 ከወራት በፊት በሰሜን ሸዋ ዞን በአጣዬና አካባቢው በደረሰው ጥቃትና ውድመት በርካቶች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ
ዜጎች ቤት ንብረታቸውን አጥተው ተፈናቅለዋል፤ ጥንታዊቷ አጣዬም ወደ ፍርስራሽነት ተቀይራለች፡፡ከዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ የ120 ዓመቱ አዛውንትና አቅመ ደካማ ጓደኞቻቸው ተዓምር በሚመስል መልኩ ተርፈው በደብረብርሃን ከተማ መጠለያ ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ ለመሆኑ እኒህ አዛውንት እንዲሁም አይነ ሥውራንና አቅመ ደካሞች እንዴት ከጥቃቱ ተረፉ? በምን ሁኔታስ ደብረ ብርሃን ከተማ መጠለያ ውስጥ ገቡ? አሁንስ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ እኒህን ተፈናቃዮች በመጠለያው ተገኝታ አነጋግራቸዋለች፡፡ ሃሳባቸው እንዲህ ተጠናቅሮ ቀርቧል፡፡

                 “እኔስ ቀብሬ የተማሰ ነኝ የማስበው ለወጣቱ ነው”
                      አቶ ሳህለ አመንሸዋ

         ሳህለ አመንሸዋ እባላለሁ፤ የተወለድኩት መንዝ ነው፤ መንዝ  ልወለድ እንጂ ከልጅነት እስከ እውቀት የኖርኩት ኤፌሶን የሚባል የአጣዬ አካባቢ ነው፡፡ እድሜዬ 120 ዓመት ነው፡፡ ወደ ሁለተኛው የጣሊያን ጦርነት ሲዘመት የ25 ዓመት ልጅ ነበርኩ፡፡ ጣሊያን መጣ፤ ጃንሆይ ሸሽተው ወደ ውጪ ሄዱ፡፡ ጣሊያን አምስት አመት አገራችን ውስጥ ቆይቶ ሄደ፡፡  ወደ ጦርነቱ ሲዘመት 25 ዓመቴ ነበር፤ ጣሊያን የቆየበትን አምስት አመት ስትደምሪው 30 ዓመት ይሆናል፤ ከዚያ በኋላ ጣሊያን ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን አመት ስታሰይው ዕድሜዬ 120 ዓመት ይሆናል፡፡
በዛን ጊዜ እኔ አልዘመትኩም፤ ገና ልጅ ነበርኩኝ፤ ብቻ የገጠር ኑሮ እርሻውንም ከብት ጥበቃውንም እያልኩ ነበር ያደግኩት፡፡ ከዚያ በኋላ አጣዬ መጣሁ፡፡ ንግድ ፈቃድ አውጥቼ ናፍጣ እነግድ ነበር፤ በሬ ፍየልና በግ እያረድኩ ስጋ እሸጥ ነበር፤ ብቻ ብዙውን ጊዜዬን በንግድ ነበር ያሳለፍኩት፡፡ ንግድ የጀመርኩት የአስም በሽታ ታማሚ ሆንኩና አፈር መንካት እርሻ ማረስ ሳቆም ነው፡፡ መቼም ባልንጀሮቼ ይወዱኛል፤ እርሻዬን እነሱ ያርሱልኛል፤ ያመርቱልኛል፤ እንዲህ እያልኩ ነው የኖርኩት፡፡
እርግጥ አንዲት ልጅ አዲስ አበባ አለችኝ፤ በፊት ትጠይቀኝ ነበር፤ አሁን አልተመቻትም፤ ጊዜውም እንደምታዩት እንዲህ ያለ ሆነ፡፡ ይሄው እንደምታይው እኛም አቅማችን ደክሞ እሰው እጅ ላይ ወድቀን ነው ያለነው፡፡
አቅመ ደካሞች ሆናችሁ እንዴት ተጥቃት ተረፋችሁ ያልሽው ትልቅ ጥያቄ ነው፡፡ ያ ሁሉ ውርጅብኝ፣ ያ ሁሉ እሳት እከተማዋ ላይ ሲዘንብ፣ እኛ በአረጋዊያን መጠለያ ውስጥ ነበርን፡፡ ያው አረጋዊያን መጠለያ እየተረዳን ነበር የምንኖረው፡፡ ከዚያ መጡና ያንን መጠለያችንን ኩሽናውን እሳት ለኮሱት፡፡ ተመልከቺ፤ በዚያ መጠለያ ውስጥ ከሰባት በላይ አቅመ ደካሞች ነበርን፡፡ እያቸው አብዛኛዎቹ አይነ ስውራን ናቸው፡፡ (በመጠለያው ያሉ ጓደኞቻቸውን በእጃቸው እየጠቆሙኝ)፡፡ ያው ጉልበት ያለው እየሮጠ አመለጠ፤ ግማሹም እየተመታ ወደቀ፡፡ እኛ ሰባታችን ጭብጥ ብለን በየአልጋችን ላይ ተኝተናል፡፡ ኩሽናውን ለኮሰና ጥይት መተኮስ ሲጀምር ፤”ኧረ እባካችሁ አይነ-ስውራን ነን፤ አቅመ ደካሞች ነን ማረን እባክህ ስለ ፈጣሪ” ብለን ተማጸንነው፡፡ እግዚያሔር ይስጠው ራራልን መሰለኝ፤ ኩሽናውን ለኩሶ አቃጥሎ እኛን ትቶን ሄደ፡፡ ጩኸታችንን ባይሰማና ዋናውን መጠለያ ቢያነደው ሮጠን አናመልጥ፣ የሚደርስልን የለ፣ እዛው ነደን ከሰል ሆነን እንቀር ነበር፡፡ አሁንም ያ የማረን ሰው እግዚያሔር ይስጠው፤ እንደዛ ዙሪያችንን ተከበን ምን ይውጠን ነበር! ያው አትሙቱ ብሎን … አፋፍሰው እዚህ መጠለያ ከተቱን፡፡ ከአንድ ወር በላይ ሆኖናል፡፡ በተቻላቸው አቅም እየተንከባከቡን ነው፡፡
እኔ አሁን ትንሽ ያቃተኝ ብርዱ ነው፡፡ ብርዱን አልቻልኩትም፡፡ እርግጥ እነሱ ብርድልብሱን ምኑን ያመጣሉ፤ ግን እኔ ብርዱን አልቻልኩትም፡፡
በደንብ እየተንከባከቡን ነው፤ ጧት ማታ ምግብ ያቀርባሉ፤ እየበላን እየጠጣን ነው፤ እዚህ ያመጡን ከግለሰብም ከሁሉም እየለመኑ እያመጡ (እነሱ የሰው ፊት አዩ እንጂ) ይንከባከቡናል፤ እኛ አልተጎዳንም፡፡
የአጣዬ ጉዳይ መላ ምንድን ነው አልሽኝ? እኔ ምኑን አውቄው ልጄ፤ እዛ እግርጌያችን ተቀምጠው በየጊዜው ይጠቀጥቁናል፡፡ መጨረሻውን እግዚያሔር ነው የሚያውቀው፡፡
ሁሉ ነገር ተተስተካከለማ ወደ አጣዬ ወደ ቀያችን ብንመለስ እንደሰታለን፡፡ መጠለያችሁ እየተሰራ ነው፤ ትሄዳላችሁ ብለውናል፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ምን ይታይዎታል ላልሽኝ፤ እኔ ከእንግዲህ ምን ይታየኛል፤ መቃብሬ የተማሰ ነኝ፤ ዛሬ ልጠራ ነገም ልጠራ እችላለሁ፡፡ እኔ የማስበው ለወጣቱ ነው፡፡ ለወደፊቱ ቀን በወጣና፣ ወጣቶቹ በሰላም በኖሩ ብዬ ነው የምመኘው እንጂ እኔማ ያው የተፈቀደልኝን ያህል ኖሬያለሁ፡፡ ነገም ልጠራ እችላለሁ፡፡ ለሀገሬ ህዝብ ለወጣቱ ሰላም እንዲመጣ ነው ምኞቴና ፀሎቴ፡፡

______________________________


                 “ስርቆትም እንኳን ቢሆን በአገር ነው አሁንም በልጆቼ አጥንት ነው የምጦረው
                                ወ/ሮ ሮማን አበረ ታዬ፤  የ80 አመት አዛውንት


          አጣዬ መኖር ከጀመርኩኝ ከ50 ዓመት በላይ ይሆነኛል፡፡ በጃንሆይ ጊዜ ነው አጣዬ ከተማ የገባሁት፡፡ የተወለድኩት ግን ኤፍራታና ግድም የሚባል የአጣዬ ዙሪያ አካባቢ ነው፤ ያደግኩት ግን የትም ነው መኪና እየጋለብኩ፡፡ ኑሮ የትም ስለሆነ ብዙ ቦታ ተዘዋውሬ ከዚያ በኋላ ነው አጣዬ ከተማ መኖር የጀመርኩት፡፡ ትዳር ነበረኝ፤ ልጆችም ወለድኩ፤ ተማሩ፤ ሁሉም ስራ ከያዙ በኋላ ሞቱብኝ፡፡ ይህ እንግዲህ እግዜር ባይፈቅድ ነው፡፡ የተበደርኩትን ለራሱ ለእግዜሩ መለስኩለት፡፡ አሁን ላይ የልጆቼ ጓደኞች ይረዱኛል፡፡ እዚህ ድረስ መጥተው ይጠይቁኛል፣ ፍራንክ ስፈልግም ይልኩልኛል፡፡
የአጣዬ ጉዳይ እንዲያው ዝም ነው፡፡ እላያችን ላይ ጥይት ሲዘንብብን እንደ ጎበዞቹ ዘልዬ ወጣሁ፤ ዘራፍ! እያልኩ፤ መቼስ ልብ አይሞት፡፡ እንደገና ነገሩን ሳየው እማሆይን ነው፤ መለስ አልኩና “እኛ ዕውሮች ነን፤ አንካሳዎች ነን፡፡ እኛ ምን እንሰራላችኋለን? ኧረ እባካችሁ ጡረተኞች ነን፤ ተውን” ብለን ስንለምን፣ ማዕድ ቤታችንን ለኩሰው እኛን ጥለውን ሄዱ፤ ተረፍን፡፡
እዚህ ያመጣን ጥሩሰው መኮንን የሚባል፣ የዚህ አረጋዊያን ማህበሩ ሀላፊ ነው፡፡ ሌላም ሰለሞን አረጋኸኝ የሚባል አለ፡፡ እነሱ ናቸው የያዙን፡፡ ብርቄ ደምሴ የምትባል አለች፤ አብስላ የምታበላን፤ እናታችን ማለት ናት፡፡ ብቻ ደብረ ብርሃንን ጥይት ሳይሆን ወርቅ ይዝነብባት፡፡ የደብረ ብርሃን ሰው፤ ሰው ወዳድና ሃይማኖተኛ ነው፡፡ እስከ ዛሬ የጎደለብን የለም፡፡ ከዚህ በኋላ ካልደከማቸውና ካልሰለቹን በስተቀር፡፡ መቼም ሰው ይሰለቻል፤ ይደክመዋል፤ የማይሰለቸውና የማይደክመው ፈጣሪ ብቻ ነው፡፡
 የጎደለ ነገር  መቼም አይጠፋም፤ እስከ ዛሬ ችግር አልነካንም ነበር፡፡ ይህን ሰሞን ችላ ብለውናል ፤ ቢቸግራቸው ይመስለኛል፡፡ እዚህ ከመጣን ሁለተኛ ወራችንን ይዘናል፡፡ ሚያዚያ 27 ነው የመጣነው፡፡ ብቻ አለን፡፡ ቀናችሁ ገና ነው ቢለን ነው የተረፍነው፡፡
አገራችን ለምን እንዲህ ሆነች አልሽኝ የኔ ልጅ? እንዲህማ ያደረገን ጥጋብ ነው፡፡ እስከ ዛሬ አብረን በልተን፣ አብረን ጠጥተን፣ በለቅሶ በሰርጉ በሁሉም ነገር ተደጋግፈን የኖርን፣ የምንተዋወቅ የምንጠያየቅ ነበርን፡፡ ነገር ግን  ከተማችንን ከእነንብረቱ አቃጥለው፣ እሳቱን ሞቁት፡፡ በከተማው ፍራሽ ላይ ሸለሉበት፤ እኛው አቅፈን ያሳደግናቸው ልጆች፡፡ ምን ታደርጊዋለሽ! የኔ ልጅ ተይኝ እስቲ፤ ተይኝ እስቲ! ከተማውን አወደሙት፤ ሰውን ጨፈጨፉት ንብረት ወደመ፡፡ በአሁኑ ወቅት ሰባራ እንስራ እንኳን ያገለግላል፤ እንኳን ሌላው ደህናው ንብረት፡፡ ከየት መጥቶ ይለማል ይሄ ሁሉ፡፡ በአበበ ገመዳ ጊዜ እንኳን እንዲህ አልሆነም፡፡
“አበበ ገመዳ ማን መሰሉሽ? ቀደም ብለው በጃንሆይ ዘመን  የነበሩ ሰው ናቸው፡፡ በዛን ጊዜ ሰው በአደባባይ ይሰቀል ነበር፡፡
አበበ ገመዳ የእግዜር ታናሽ ወንድም
የዛሬን ማርልኝ ሁለተኛ አልወልድም” የተባለላቸው ናቸው፡፡ ይህን ያለችው ልጇ ሲሰቀልባት የነበረች አንዲት እናት ናት፡፡ ይህንን  ስትል ፈቱና ለቀቁላት፡፡ በዚያን ሰዓት እንኳን አንዲህ ርህራሄ ያሳዩ ነበር፡፡
ጨካኝ የሚባሉት ሳይቀሩ፡፡ አሁን መዓት ነው የመጣብን፡፡ እርሱ ቁጣውን ይመልስልን እንጂ ሁላችንም የአንድ አዳምና ሄዋን ልጆች ሆነን እንዲህ የምንባላበት ነገር አይገባኝም፡፡ እድሜዬን አላውቅም፡፡ ሀኪም ቤት ሄጄ “የ77 ዓመት  ከሆኑ እንዴት ሪፈር ተፃፈልዎት?” አለኝ ሀኪሙ፡፡ እኔ ሁለት መቶስ ብታደርገው ምን ቸገረኝ እድሜ ይጠገባል ወይ አልኩት፡፡ መቼም ወደ 80 ይሆነኝ እንደሆነ እንጃ፡፡
የልጆቼን የተወለዱበትንም የሞቱበትንም እድሜ አስታውሳለሁ፡፡ ትንንሾቹ ወዲያው   በትንሽነታቸው ነው የሞቱብኝ፡፡ ሁለቱ ባለዲግሪም ባለ ማስተርስም ነበሩ፡፡ ባለማስተርሱ አሰብ ተመድቦ ሲሰራ ጭንቅላቱ ተነካብኝ፤ አጣዬ አመጡት፤ ሲመጣ ራሱን አያውቅም፡፡ እንዲሁ እንዲሁ ሲል አቦከር የሚባል ጴንጤዎች የሚቀበሩበት ተቀበረ፡፡ አንዱም ከጋምቤላ ነው አስክሬኑ ተጭኖ የመጣው፤ አጣዬ አማኑኤል ተቀበረ፡፡ ዞሮ ዞሮ ልጅ አልሆነልኝም፡፡ ስማቸው አልሞተም፤ በአጥንታቸው በስማቸው እጦራለሁ፡፡ እስካሁን አልራበኝም፡፡ ከአጣዬ ስንመጣ ድንጋይ ላይ ነበር የወደቅነው፡፡ የዚህ ቤት ጌታ ፀሀይ ፅድቅ ይባላሉ፡፡ ይህን ቦታ ፈቀዱልን፡፡
ይኸው እየኖርን ነው ኑሯቸውን ፀሀይ ያድርግላቸው፣ የደብረ ብርሃን ሰው ወርቅ ይዘንብበት፡፡ አንድዬ ያመጣውን ቁጣ ያብርድልን፡፡ ሰላም ያድርገው አገሩን እኛስ መቼም ተቃርበናል እንዲያው ለቀሪው ለአገሩ ሰላም ያውርድ፤ ሌላ የምለው የለኝም፡፡ ሰማሽ የኔ ልጅ፤ ልመናም ሰርቶ ማግኘትም ሌላው ቀርቶ ስርቆትም በአገር ነው፡፡ አገር ከሌለ ምንም የለም፡፡ ለሃገራችን ሰላም ይስጣት! የልጄ ጓደኞች፤ አሸናፊ ደሳለኝንና መስፍን ከበደን እንደምትጠይቁኝ እንደምትንከባከቡኝ፣ ፈጣሪ ብድራታችሁን በምድር በሰማይ ይክፈላችሁ፤ ተከበሩ በይልኝ፡፡

______________________________________


               “ልጄን መኪና ድጦብኝ ዙሪያው ገደል ሆነብኝ”
                      (ወ/ሮ አስናቀች ሰይድ)



            ተወልጄ ያደግኩት ወሎ ወረባቦ አካባቢ ተውለደሬ የሚባል ቦታ ነው፡፡ ለብዙ ጊዜ የኖርኩት አጣዬ ነው፡፡ ብዙ ልጆች ወልጄ አልቀውብኝ አንድ ልጅ ነበር የቀረኝ፡፡ እሱ ነጋዴም ቄስም ነው፡፡
እኔም ፏጭሬ ለፍቼ፣ እሱም ያቅሙን እየሰራ እንኖር ነበር፡፡ ደሃ የምንባል ብንሆንም ሳንበላ አናድርም ነበር፡፡ ያን የቀረኝን አንዱን ልጄን ጎስም፣ መኪና ድጦብኝ ዙሪያው ገደል ሆነብኝ፡፡ ከዚያም በኋላ ስራ በማጣት፣ በድህነትና በመጉላላት ጤናዬ ተቃወሰ፡፡ መንግስት አፍሶ አረጋዊያን ማቆያ ዶለን፤ ደህና እንኖር ነበር፡፡ ያው ዕዳ ቻያችን አጣዬ ነበር እንዳይሆን ሆነ፤ ሁሉን ነገር እንዳይሆን አደረጉት፡፡ መቼስ ድሃና አቅመ ደካማ ምን መላ አለው ብለሽ ነው!
መቼም ፈጣሪ  አላልኩም ብሎ አንድ ቤት ከሰል ሆነን ተማለቅ አዳነን ይሄው አለን፡፡ እንዲህ ያለ ነገር በአገር ላይ ሲመጣ ምን ይያዛል፤ ምን ይጨበጣል! እዚህ መቼም ያላቸውን አልነፈጉንም፤ እየበላን እየጠጣን ነው፡፡ እስከ መቼ እንዲሀ እንደምንዘልቅ መድኃኔዓለም ነው የሚያውቀው፡፡ እኔ መቼም ልጄን መኪና ተዳጠብኝ ወዲህ ኑሮዬ ኑሮም አይደል፡፡ እግዜር አይከሰስ፤ እኔ ከእግዜር አልበልጥ ሀዘኔን እሳቴን ታቅፌ ሞቴን እጠብቃለሁ፤ ተይኝ እስኪ (ለቅሶ…)
ወደ አገሬ አልሄድ አይኔ ደክሟል፤ መሬት የለኝ ቤት መጠለያ የለኝ፤ እንዲያው ዝም ነው አንቺው፡፡ አንድዬ እንደወደደ እንደፈቀደ ያድርግ፡፡ እሱን ማን ይከስሳል፤ ማንስ ይወቅሳል፡፡ ይኸው ያለንበትን ሁኔታ ተመልከቺ እኛ ከምንናገረው በላይ ወዛችን ይናገራል፤ ሁኔታችን ይመሰክራል፡፡
_______________________________________

                    “እኛን አላህ ነው የደረሰልን፤ ሰው ጨክኖብን ነበር
                           (ወ/ሮ ዘውዴ ከማል)


             እኔ አይነ ስውር ነኝ አላይም፤ በአረጋዊያን ማህበርም ያሉት እንደኔው አቅመ ደካማና አካለ ጎደሎ ናቸው፡፡ አላህ ባይደርስልን ምን እንሆን ነበር፡፡
 አሁን ለጊዜው እዚህ ያመጡን ሰዎች፣ ተየትም ተየትም ብለው እያበሉን እያጠጡን ነው፤ አልጨከኑብንም፡፡ ግን እስከ መቼ ነው እንዲህ ሰው አስቸግረን የምንኖረው እያኩ እጨነቃለሁ፡፡
አሁን እኔና ይቺ አጠገቤ ያለች ሴት ተደጋግፈን ተያይዘን ነው ደጅ ወጥተን የምንገባው እንጂ የአይን ብርሃን እንኳን የለንም፡፡ እኔ አሁን አምስት ልጆቼን ቀብሬ ብቸኛ ሆኜ አነጋጋሪ እንኳን አጥቼ፣ በብቸኝነትና በድህነት ስማቅቅ፣ እዛው አጣዬ አረጋዊያን መጠለያ አስገቡኝ፡፡ እዛ በቀዬአችን በለመድነው ቦታ እየተጦርን ባለንበት፣ እንዲህ ያለ መዓት ወረደብን፤ አላህን ምን እንዳስቀየምነው እንጃ፡፡
እርግጥ ልጆቼን አላህ ነው የወሰደብኝ፤ በጦርነት አይደለም የሞቱብኝ፡፡ ከአምስቱ አንድ ሁለቱን እንኳ አላህ ቢያስቀርልኝ ጧሪ አላጣ፤ ሰውም አላስቸግርም ነበር፡፡ አሁን ይኸው አለን፤ መቼስ ምን እናደርጋለን፡፡ ተሞት ያተረፈንን፤ እነዚህን ተንከባካቢዎች የሰጠንን ፈጣሪን እያመሰገንን ነው ያለነው፡፡
እናንተን ያሳን ጌታ እሱ ያውቃል፡፡ መቼስ እናንተ መጥታችሁ ባትጠይቁን ለማን እንተንፍሰው ነበር፤ በረካ ሁኑ፤ ልጆቻችሁ ይጡሯችሁ፡፡ መጣታችሁ “እንዴት ሆናችሁ፤ ተምን ወደቃችሁ” ማለታችሁም ለኛ ትልቅ ተስፋ ነው፡፡ በረካ ሁኑ፤ አላህ ያቆያችሁ፡፡ እናንተ ታያችሁን አገር አየን ማለት ነው፡፡ ለቀረው ነገር አላህ ያውቃል፡፡

Read 9225 times