Saturday, 19 June 2021 18:15

ማንቶ ኢንዱስትሪያል የከተማ ግብርና መሳሪያዎችን ማምረት ጀመረ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

የመጀመሪያዎቹን ምርቶች ለ250 የከተማ አርሶ አደሮች በስጦታ አበርክቷል ለም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጀነሬተር ሸልሟል
                   
            አዲስ አበባ ተወልደው ባደጉት ሁለት ወጣቶች የተመሰረተውና 550 ሚ.ብር የወጣበት ማንቶ ኢንዱስትሪያል ግንባታው ተጠናቅቆ የከተማ ግብርና መሳሪያዎችን ማምረት ጀመረ፡፡ የመጀመሪያዎቹን ምርቶች አዲስ አበባ ለሚገኙ 250 የከተማ ግብርና ላይ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች በስጦታ አስረክቧል፡፡
ማንቶ ኢንዱስትሪያል ባለፈው ሰኞ ሰኔ 7 ቀን 2013 ዓ.ም አመሻሽ ላይ በሀያት ሬጀንሲ ሆቴል ባዘጋጀው ስነ-ስርዓት ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ም/ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ተገኝተው ወጣቶቹን ያበረታቱ ሲሆን ለአርሶ አደሮቹ የተበረከተውን የግብርና መሳሪያም ለሁለት ተወካዮች አስረክበው ለራሳቸውም በኢንዱስትሪው የተመረተውን ድምፅ አልባ ጀነሬተር ተሸልመዋል፡፡ ምክትል ከንቲባዋ ሽልማታቸውን ከተቀበሉ በኋላ ባደረጉት ንግግር “ሽልማቶቹ በመብራት መጥፋት ስራ እንዳልፈታና 24 ሰዓት እንድሰራ አደራ እንደተጣለብኝ ገብቶኛል” በማለት ወጣቶቹን አመስግነው በቀጣይ ሥራቸው ከጎናቸው እንደሚሆኑ ቃል ገብተዋል፡፡የማንቶ ኢንዱስትሪያል ዋና ስራ አስኪያጅ ወጣት አብራር ሙራድ ሙክታር በዕለቱ ባደረገው ንግግር ኢንዱስትሪያቸው የሚያመርታቸውን የግብርና መሳሪያዎች ቀደም ሲል በውድ የውጪ ምንዛሬ አገራችን ታስገባ እንደነበር ገልፀው፣ እነዚህን መሳሪያዎች አገር ውስጥ በማምረት የውጪ ምንዛሬን ከማዳናቸውም በላይ በፋብሪካው ለ400 ወጣቶች ስራ እድል መፍጠራቸውንም ገልፀዋል፡፡
 ፋብሪካው በቀጣይ በፀሃይ ብርሃን የሚሰሩ “SNK Power” የተሰኙ መሳሪያዎችን ለማምረት በዝግጅት ላይ መሆናቸውንም ገልፀው ለተጨማሪ የሰው ሀይል የስራ እድል እንደሚፈጥሩም አስታውቀዋል፡፡


Read 2040 times