Sunday, 27 June 2021 16:40

በወላይታ የተካሄደው ምርጫ ውድቅ እንዲደረግ ፓርቲዎች ጠየቁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

 በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን የተካሄደው ምርጫ በገዥው ፓርቲ ተጭበርብሯል ያሉት “አብን” እና “ኢዜማ”ን ጨምሮ 8 ተወዳዳሪ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ባለፈው ሰኞ ሰኔ 14 የተደረገው ምርጫ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ እንዲደረግላቸው ጠየቁ፡፡
ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶቹ በምርጫው ሂደት የተፈጠሩ ችግሮችን አስመልክቶ በጋራ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባቀረቡት  የቅሬታ አቤቱታ፤ በምርጫው ሂደትና በድምጽ መስጫው እለት በገዥው ብልፅግና ፓርቲ ተፈጽመዋል ያሏቸውን ችግሮች በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
በምርጫው ሂደት ፓርቲዎቹ ሲያቀርቧቸው ለነበሩ ቅሬታዎች በቦርዱ በኩል አዎንታዊ ምላሽ እየተሰጠ መቆየቱን ያስታወሱት ፓርቲዎቹ፣ ዋናው ችግር በድምፅ መስጫ ቀን የተፈፀሙት ድርጊቶች ናቸው ብለዋል፡፡
በድምጽ መስጫ ቀን ካጋጠሙ ችግሮች መካከልም ታዛቢዎቻቸው የቅድመ ምርጫ ቃለ ጉባኤ እንዳይፈርሙ መደረጉን፤ ድምፅ ቆጠራ ላይ ታዛቢዎች እንዳይሳተፉ በፖሊስ መከልከላቸውንና ቆጠራው ከተከናወነ በኋላ በጉልበት ተደብድበው እንዲፈርሙ መደረጉን፤ በዚህ ድብደባም አንዳንዶቹ ላይ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው፤ የተወሰኑትም በፖሊስ ታፍነው ተወስደው እስካሁን የደረሱበት አለመታወቁን ፓርቲዎቹ በአቤቱታቸው አመልክተዋል። በተጨማሪም የተፎካካሪ ታዛቢዎች እምቢ ብለው በወጡባቸው ጣቢያዎች በሙሉ በተጭበረበረ የምርጫ ውጤት ላይ አስፈፃሚዎች አስመስለው ፈርመው ሳጥኑን እንዲታሸግ አድርገዋል ብለዋል- ፓርቲዎቹ።
በዞኑ በሚገኙ 3 የምርጫ ክልሎች ውስጥ የፌደራልና የክልል እጩዎች ስም ፎቶግራፍና የምርጫ ምልክት የሌላቸው እንዲሁም የተሰረዙ እጩዎች ምትካቸው ሳይስተካከል የታተመ የተሳሳተ የድምጽ መስጫ ወረቀት ጥቅም ላይ እንዲውል ተደርጓል ያሉት ፓርቲዎቹ በህገ-ወጡ የድምፅ መስጫ ወረቀት ምክንያት ከውድድር ውጪ ተደርገናል ብለዋል፡፡
ፓርቲዎቹ ካቀረቧቸው በርካታ ተጨማሪ አቤቱታዎች መካከል ዕድሜያቸው ያልደረሰ ህፃናት ታዳጊዎች እንዲመርጡ መደረጉን፣ ድምፅ መስጠት ከመጀመሩ በፊት ድምፅ የተሰጠባቸው ወረቀቶች በምርጫ ሳጥን ውስጥ ተከተው መገኘታቸውን፣ አንድ ግለሰብ በርካታ የመራጭነት ካርድ ይዞ በተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወረ እንዲመርጥ መደረጉን፣ ካድሬዎች የምርጫ  ቦርድ አስፈጻሚዎችን ተክተው ምርጫውን ማስፈፀማቸውን የሚገልፁት ይገኙባቸዋል። በተጨማሪም አቅመ ደካሞችን ለማገዝ በሚል መራጮች የአምፖል ምልክት ላይ እንዲመርጡ በቀጥታ መታገዛቸውን፣ በአንድ ምርጫ ጣቢያ የተመደበው 1500 ድምፅ መስጫ ወረቀት ሆኖ ሳለ 2500 ድረስ የተገኘባቸው ጣቢያዎች መኖራቸውን እንዲሁም በምርጫው እለት የገዥው ፓርቲ ካሬዎች የቤት ለቤት ቅስቀሳን ጨምሮ  የምርጫ ቅስቀሳዎችን ሲያደርጉ ፓርቲዎቹ በአቤቱታቸው አቅርበዋል፡፡
በወላይታ ዞን የተደረገው ምርጫ ሙሉ ለሙሉ የተጭበረበረ ነው ያሉት ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ፤ በዞኑ የተካሄደው ምርጫ ሙሉ ለሙሉ እንዲሰረዝና ድጋሚ ምርጫ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡
ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም  በወላይታ ዞን ምርጫ የተደረገው ዞኑ ካሉት 13 የምርጫ ክልሎች በ7 ያህሉ ላይ ሲሆን ቀሪዎቹ 6ቱ በሁለተኛው ዙር ጳጉሜ 1 የሚካሄድባቸው ይሆናል፡፡
ፓርቲዎቹ አክለውም፤ በ7ቱ የምርጫ ክልሎች የተደረገው  ምርጫ ካልተሰረዘ  በ6ቱ  የምርጫ ክልሎች ላይ እንደማይሳተፉ ለቦርዱ ባቀረቡት አቤቱታ አስታውቀዋል፡፡
ለምርጫ ቦርድ ቅሬታቸውን ያቀረቡት ተፎካካሪ ፓርቲዎች፡- እናት ፓርቲ፣ የወላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ (ዎብን)፣ የወላይታ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ግንባር፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፣ ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ፣ ህብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ  ፓርቲ የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራሲ ፓርቲ እና የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) ናቸው፡፡


Read 9992 times