Sunday, 27 June 2021 17:27

በአዲስ የቢዝነስ ዘርፍ የመጡት ዶ/ር ፍሰሀ እሸቱ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 - በቢዝነስ ፕሮጀክት የጥቁር ህዝብን ክብር ማስመለስ እንችላለን
- “ፐርፐዝ ብላክ” ፕሮጀክት በ54ቱም የአፍሪካ አገራት ይጀመራል
- “የፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ” አክስዮን ሽያጭ ሃምሌ 17 ይጀምራል
 
 ላለፉት 10 ዓመታት በአሜሪካ የስደት ህይወት ሲመሩ የቆዩት ዶ/ር ፍስሃ እሸቱ፤ ከጥቂት ሳምንት በፊት አዲስ የቢዝነስ ፕሮጀክት ይዘው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡ የጥቁር ህዝቦችን መብትና ክብር ለማስመለስ ዋናው ጉዳይ የፖለቲካ ትግል ማድረግ ሳይሆን የጥቁሮችን የኢኮኖሚ አቅም ማጠናከር ነው የሚሉት ዶ/ር ፍስሃ፤ ይሄን ለማሳካትም #ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ;የተሰኘ አዲስ ኩባንያ በኢትዮጵያ  መመሥረታቸውን፡፡ የኩባንያው የአክስዮን ሽያጭም ሃምሌ 17 እንደሚጀምር ዶ/ር ፍስሃ አስታውቀዋል፡፡   
በአገሪቱ የመጀመሪያውን የግል ኮሌጅ-ዩኒቲ- ያቋቋሙት ዶ/ር ፍስሃ፤ የመጀመሪያውን የግል ዕለታዊ ጋዜጣ በመጀመርም ስማቸው ይነሳል፡፡ የዛሬ አስር ዓመት ገደማ ድርጅቶቻቸውን ሁሉ ሸጠው ወደ አሜሪካ የተሰደዱት ዶ/ር ፍስሃ፤ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ወደ አገራቸው የተመለሱት፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ዶ/ር ፍስሃ ጋር ሰፊ ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡ እነሆ፡-  


         የዛሬ 10 ዓመት ምን ቢያጋጥሞዎ ነው ድርጅትዎን ሸጠው ወደ ባዕድ አገር የተሰደዱት?
እንደሚታወቀው ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ፤ ዲጂታል ቴክኖሎጂው በሀገራችን ገና በማይሞከርበት ጊዜ፣ በኦንላይን በይው በኢ-ኮሜርስ … “ዲጂታል ኢትዮጵያ” በሚል እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቶ ነበር። የዛሬ 16 እና 17 ዓመት ማለት ነው፡፡ ነገር ግን በተደጋጋሚ በዩኒቨርስቲው ላይ የሚደርሰው ጫና ከፍተኛ ነበር፡፡ የተለያዩ ነገሮችን ለመስራት ስንቀሳቀስ መንገዶች ይዘጋጉብናል፡፡ በግልም ሆነ በተቋም ደረጃ በእኔ ላይ የደረሰው ጫና እንደ ሰው ተስፋ የሚያስቆርጥ ነበር፡፡ አስታውሳለሁ “My Fashion” በተሰኘው መፅሔት ውዝግብ ሳቢያ ሁለት ዓመት ሙሉ ነው  ፍርድ ቤት የተመላለስኩት፡፡ ጫናው ሲበዛና በተለይ አንቺ ኢላማ መደረግሽን ስታስቢ ያለሽ ምርጫ ወይ ራስሽን መስዋዕት ማድረግ ነው ወይ ደግም ከድርጅቱ ጋር ተያይዘሽ ገደል መግባቱን ነው፡፡ በዚያን ሰዓት እኔ የመረጥኩት  ተቋማቱን አስተላልፌ መውጣት ነበር፡፡
እርስዎ የቢዝነስ ሰው እንጂ ፖለቲከኛ አልነበሩም፡፡ ኢላማ የተደረጉበት ምክንያት ምንድን ነው?
እንዳልሽው እኔ የፖለቲካ ሰው አይደለሁም፤ ነገር ግን የሚገዳደራቸው ሰው ስለማይወዱ እኔ ለእነሱ እብሪተኛ ነኝ፡፡ ይሄ የእነሱ አስተሳሰብ ነው፡፡ የምታስታውሺ ከሆነ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በየቦታው ጭቅጭቅ ከም/ጠቅላይ ሚኒስትሩና  ከተለያዩ የመንግስት ሀላፊዎችም ጋር ውዝግብ ውስጥ ነበርኩ፡፡ በአጠቃላይ ሰዎቹ ስትገዳደሪያቸው አይወዱም ነበር፡፡ ሌላው ደግሞ ገንዘብ አለሽ ብለው ካሰቡና ደጋፊ ካልሆንሽ ጠላት ነው የምትሆኚው፤ በእነሱ አስተሳሰብ፡፡ ነገር ግን ይህ ከፖለቲካ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ የእነሱ ደጋፊ ካልሆንሽ፣ በየጊዜው የምትግዳደሪያቸው ከሆነና ገንዘብ አለሽ ብለው ካሰቡ አይመቻቸውም፡፡ በሁሉም ነገር መንገድ እየዘጉ እንድትማረሪ ነው የሚያደርጉሽ፡፡ ሌላው ጉቦ እየሰጠ ዝም ብሎ ዲግሪ እያተመ ሲሰጥና ዕድሉ ሲለቀቅለት፣ እኛ ትምህርት ላይ ቀልድ አናውቅም ነበርና እንዴት ያሰቃዩን እንደነበር፤ እኔ ነኝ የማውቀው። የጀመርናቸው ትልልቅ ፕሮጀክቶች ሆን ተብሎ እንዲቆሙ ይደረጉ ነበር፡፡ ትታገሽ ትታገሺና ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ተስፋ ትቆርጫለሽ፡፡ አገርሽ ራሱ እንዲያስጠላሽ ነው የሚያደርጉት፡፡ በዚህ የተነሳ በቃኝ ብዬ አገሬን ጥዬ ወጣሁ፡፡
እንዴት ነው አዲስ አበባ አልተለወጠችብዎትም?
አዲስ አበባ ሙሉ ለሙሉ ተቀይራለች። የማውቃቸው ቦታዎች ሁሉ ጠፍተው ሌላ ሆነዋል፡፡ በእርግጥ ስለመቀየሯ  እዛም ሆነን እንሰማ ነበር፡፡ ሰው ሲነግረን የተጋነነ ነበር የሚመስለን እንጂ በዚህ ደረጃ ተቀይራለች ብለን አናስብም ነበር፡፡ ወደ ዚህ ስመጣ መኪና እነዳለሁ ስላቸው “በፍፁም እንዳትነዳ ትጠፋለህ” ነበር ያሉኝ። ልክ ስገባ እንኳን መኪና ልነዳ ሁሉ ነገር ተቀያይሮ መንገዱንም መለየት አልቻልኩም፡፡ የአዲስ አበባ በዚህ መጠን መቀየር በጣም  ያስደንቃል። ሌሎቹም የሀገራችን ትልልቅ ከተሞች ተቀይረዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
እዚህ ሳሉ አቅደውት ባለማሳካትዎ የሚቆጭዎት ነገር አለ?  
የሚያሰራ ሁኔታ ቢኖርማ፣ ለእኔ 10 ዓመት ብዙ የምሰራበት ጊዜ ነበር፡፡ አሁን ይዘን የመጣነው የኢ-ኮሜርስ ስራ እኮ የዛሬ 17 ዓመት እዚህ ጀምረነው ነበር፡፡ አስቢው አማዞን  ሥራ ከጀመረ 20 ዓመቱ ነው፤ ዛሬ የ1ትሪሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ነው። የኦንላይን ትምህርት አሁን ተስፋፍቷል፡፡ እኛ ከ16 ዓመት በፊት ስንጀምረው ማንም እዚህ አገር አያውቀውም ነበር፡፡ የኦንላይን ትምህርቱን ያን ጊዜ እንደ ጀመርነው የሚያሰራን ሁኔታ ተፈጥሮና ድጋፍ አግኝተን ቢሆን ኖር፣ አሁን ላይ ከቡና ያልተናነሰ ገቢ ያስገባ ነበር፡፡ ምክንያቱም እኛ በዚያን ሰዓት ከዓለም ዙሪያ በሙሉ በሶስት ዲግሪ ፕሮግራሞች ማለትም በኢኖሚክስ፣ በዚዝነስ አድሚንስትሬሽንና (አንዱ በማርኬቲንግ ይመስለኛል) በኦንላይን ትምህርት ተማሪ ተቀብለን ነበር፡፡ ሁለተኛ ፎቅ ላይ ያለው ቢሯችን በሙሉ በአይቲ ቴክኖሎጂና በሙያተኞች የተደራጀ ነበር፡፡ ያንን ኦንላይን ትምህርት ሲከለክሉን ነው እንደገና ወደ ኖርማሉ ያዞርነው፡፡ ያንን “ዲጂታል ኢትዮጵያ” ብለን የተነሳንበትን ብንቀጥል ኖሮ ዛሬ የት በደረስን ነበር፡፡
ሌላው “ናሽናል ፔይመንት ጌትዌይ” ብለን የጀመርነውም ያን ጊዜ ነበር፡፡ የስልክ የመብራት የውሃና ሌሎች ክፍያዎችን በተቀናጀ መንገድ በኦንላይን እንዲከፈል የማድረግ ስራ የጀመርነው እኛ ነበርን። ያን ጊዜ ተፈቅዶልን ብንቀጥል ዛሬ የት በደረስን ነበር፡፡ “ፓን አፍሪካ ውሜን ኢጁኬሽን” በሚል የሴቶች ፕሮጀክት ጀምረን ብዙ ሂደት ታልፎ፣ 29 የአፍሪካ አገሮች ተስማምተውና ፈርመው ዲዛይኑ ተሰርቶ ወደ ትግበራ ልንገባ ስንል ነው የተከለከልነው፡፡ ያ ተግባራዊ ቢሆን ኖሮ አሁን ላይ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ኢትዮጵያ ታገኝ ነበር፡፡ ተመሳሳይ ብዙ ነገር ልቆጥርልሽ እችላለሁ፡፡ እዚህ ብኖር ኖሮ ዛሬ እንደ አዲስ የሚወሩት ነገሮች የዛሬ 15 ዓመት ነበር ስራ ላይ የሚውሉት። ያው ሁሉም የሚሆነው  ግን ፈጣሪ የፈቀደ ጊዜ ነው፡፡ ከሚዲያም ጋር በተገናኘ “ፓን አፍሪካ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን” ለማቋቋም ብዙ ርቀት ተጉዘን ነበር፡፡ በሌላ በኩል፤ የጋዜጠኛን መብት በማስከበር ቀዳሚው ዩኒቲ ነው፡፡ እነ “ዕለታዊ አዲስ” በሚታተሙበት ወቅት በጋዜጠኛ ደሞዝ ደረጃ ተሰምቶ የማይታወቅ 5 ሺ እና 6 ሺህ ብር ደሞዝ ነበር የምንከፍለው፡፡ እና እዚህ ብኖር ኖሮ፣ የዘረዘርኩልሽ ሁሉ ይተገበር ነበር፡፡ አስር ዓመት የባከነ ጊዜ ነው ለኔ፡፡ የሆኖ ሆኖ አሁንም ተስፋ አልቆረጥንም ፡፡
አሁን ይዘው ስለመጡት አዲስ ፕሮጀክት “ብላክ ፐርፐዝ” ይንገሩኝ እስቲ?  ምንድነው ሀሳቡ?
ወደ ኋላ ሄደን ስንመለከት “ብላክ ፐርፐዝ” የተባለው ፕሮጀክት ዝም ብሎ የተቋቋመ ግንጥል ቢዝነስ አይደለም፡፡ ከቢዝነስ በላይ ነው፡፡ ተልዕኮም ጭምር አለው፡ ዓላማውም ትልቅ ነው፡፡ ለምን ዓላማ ተመሰረተ ካልሽኝ፣ ቁጭት ነው የመሰረተው፤ ጥቁር የመሆን ቁጭት፡፡   እንግዲህ አንድ ሰው በአገሩ ላይ  የቢዝነስ ሰው ሆኖ ካሳለፈ በኋላ ጥሩ ህይወት ከኖረና ብዙ ነገር ካሳለፈ በኋላ አሜሪካ ሲገባ ምንም ነው፤ ያ ሰው በጥቁርነቱ ብቻ በቃ ምንም ነው ምንም!! ያን ሁሉ ትምህርት ተምረሽ ዲግሪ ተሸክመሽ፣ የካበተ የስራ ልምድሽ ሁሉ ገደል ገብቶ መልክሽ ብቻ ማተር የሚያደርግበት አገር ነው አሜሪካ፡፡ አሜሪካ የእኩልነትና የነፃነት ሃገር ነው ይባላል አንጂ ውሸት ነው፡፡ የፖሊስ መኪና ከኋላሽ ሲመጣ ገና ለገና ጥቁር ስለሆንሽ ብቻ  እታሰራለሁ ብለሽ ትፈሪያለሽ፡፡ ብቻ ብዙ ብዙ ነገር አለ። በተለይ ዘረኝነት በአሁኑ ጊዜ በጣም እየባሰ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ብትወስጂ እንኳን በከፍተኛ ሁኔታ የተጠቃው ጥቁሩ ህዝብ ነው፡፡ እንዴት እንደተገለሉ ስታይ፣ በተለይ ከትራምፕ ጋር በተያያዘ የነጮቹ ዘረኝነት ጎልቶ ሲወጣ ስትመለከቺ፣ ይሄ ነገር እስከ መቼ ነው ትያለሽ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስታይው ከእኛ ከኢትዮጵያውያን ጀምሮ በየሀገሩ ሲሰዱ በየባህሩ ሰጥመው ሲቀሩ፣ ሌላውንም ስንመለክት እስከ መቼ ነው አፍሪካ እንደዚህ ሆና የምትቀጥለው የሚለው ጥያቄ እረፍት ይነሳል፡፡ በተለይ እነጩ ባህር ውስጥ ገብቶ ላየውና ጥቁር ለሆነ ሰው ይታወቀዋል፡፡ እዛ አገር ውስጥ ዜግነት እንኳን ብታገኚ እኩል አይደለሽም፡፡
መዝገብ እንኳ ከጠረጴዛ በላይና ከጠረጴዛ በታች እንደሚቀመጥ ነው የሰማሁት…
እውነት ነው፡፡ ይሔ ሁሉ እስከ መቼ የሚለውን ነገር እንድታሰላስይና  እንድትብሰለሰይ ያደርግሻል፡፡ እኔ ለሁለት ዓመት በዚህ ሀሳብ ተጠምጄ ነበር፡፡ እኔ “አንድ ኢትዮጵያ” እንቅስቃሴ ላይ እያለሁ ስናገር የነበረው ከፖለቲካ ይልቅ የሰውን ልጆች ሊቀይር የሚችለው ኢኮኖሚ ነው እያልኩ ነው፡፡ ፖለቲካ ትልቅ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር ጠፍቶኝ አይደለም፡፡ ልብ ካልነው ኢኮኖሚ ፖለቲካውንም ተፅዕኖ ያሳድርበታል፡፡ ስለዚህ ኢኮኖሚ ላይ መተኮር አለበት፡፡ ገንዘብ ካለ ሀይል ይኖርሻል፡፡ ከዚያም ክብርም ይኖርሻል ብዙ ጊዜ ጥቁሮች የሚሄዱበት መንገድ የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት ነው፡፡  አሜሪካ ውስጥ “black lives matter”  ለብዙ ዓመታት ያለ እንቅስቃሴ ነው፡፡
ስለዚህ ኢኮኖሚው ላይ ማተኮር ነው ያለብን፡፡ ይህንን ካደረግን ብቻ ነው ለውጥ ማምጣት የምንችለው በሚል “Black Economy Excellenc” የሚባል ትልቅ ድርጅት ከአንድ ዓመት በፊት ሜይ 2020 ዓ.ም ላይ አቋቋምን፡፡ በኢኮኖሚ መፍትሄ የጥቁሮችን ችግር እንፍታ ጥቁሮችን እናስከብር፣ የጥቁሮችን ተፅዕኖ ፈጣሪነት በዓለም ላይ እናረጋግጥ፤ ለውጥ እናምጣ፣ በተለይ ለልጅ ልጆቻችን የኢኮኖሚ ደህንነት ልህቀትን እናምጣ በሚል ቁጭት ነው የተፈጠረው፡፡ ስለዚህ ከፖለቲካ መፍትሔ ይልቅ ኢኮኖሚያዊ መፍትሔ ላይ እናተኩር፤ “ተጠቅተናል እንደዚህ ተደርገናል” እያለን ሌሎችን እየወቀስን ከምንቀጥል ይልቅ በራሳችን ሰርተን ለውጥ እናምጣ፤  ባለን እንመካ የሚል ሃሳብ ነው፡፡
ተመልከቺ ከዓለም ህዝብ 1.3 ቢሊዮኑ ጥቁር ህዝብ ነው ይሄ ቀላል አይደለም። ጥቁር ህዝብ ደግሞ  ምንም የሌለው ደሃ አይደለም፡፡ አሜሪካ ውስጥ ብቻ ጥቁሮች 1.1 ትሪሊየን ዶላር በየዓመቱ ያወጣሉ፡፡ ነገር ግን ችግሩ ምንድን ነው? ገንዘቡን እናወጣና ለሌላው እናስረክባለን፤ አላወቅንበትም፡፡ የጥቁር ህዝብ ገንዘብ በአንድ ላይ ቢሰባሰብ በዓለም ላይ ምርጥ 10 ከሚባሉ ኢኮኖሚዎች አንዱ ይሆናል፡፡ ገንዘብ አጥተን አይደለም፤ እንደ አፍሪካ ያለ ትልቅ ሀብት ያለው አህጉርም የለም፡፡ ስለዚህ ለምንድን ነው ደሃ የምንሆነው? ከፈለግን “መብት ስጡን፤እኩል አድርጉን እያልን እየጮኽን መቀጠል እንችላለን፡፡ ከዛ ይልቅ አንደኛ ራሳችን ልንሰራቸው የምንችላቸው ነገሮች ሁሉንም ያካተተ፣ ሁለተኛ ከትንሽነት አስተሳሰብ ወጥተን ሁልጊዜ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ማሰብ አለብን፡፡ ምክንያቱም የ1.3 ቢሊዮን ህዝብ እጣ ፈንታ ለመወሰን ትንሽ ፕሮጀክት የትም አያደርስም፡፡ ብልህ በመሆን ብዙ ተሞክረው የሰሩትን ለእኛ በሚመች መልኩ አድርገን መስራትና መተግበር ይኖርብናል፡፡ ለዚህም ሞዴል ዘርግተናል፡፡
ምን የሚባል ሞዴል ነው የዘረጋችሁት?
“ዘ ግሎባል ብላክ  ኮሌክቲቭ ፐርፔቹዋል ዌልዝ ጀኔሬሽን” ይባላል፡፡ ይህ ማለት ስማርት በሆነ መንገድ በመሄድ የጥቁርን ሀብት ወደ አንድ ቦታ በማምጣት አቅም መገንባት ነው፤ ዋነኛው ጉዳይ፡፡ በዚህ ደግሞ አራት ዋና ዋና ዓላማዎችን ለማሳካት ይውላል። ይህ በአንድ የተከማቸ ገንዘብ አንደኛ፤ በሚቀጥሉት  15 ዓመታት ውስጥ 1 ቢሊዮን ጥቁር ህዝቦችን ኢምባክት የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን መዘርጋት፣ ሁለተኛ በዚህ ሂደት ውስጥ 1 ሚሊዮን ጥቁር ሚሊኒየነሮችን መፍጠር፣ ሶስተኛ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ውስጥ 1.5 ትሪሊዮን የአሜሪካን ዶላር ያለው የጥቁር ህዝብ የጋራ ሀብት መፍጠር ሲሆን አራተኛው ለጥቁር ህዝብ ከራሱ በላይ ሊናገርለት የሚችል ማንም የለም ብለን ስለምናምን የጥቁር ህዝብ ሚዲያ ድርጅት ማቋቋም ነው፡፡ “ብላክ ናሬቲቭ ሚዲያ ኦርጋናይዜሽን” ይባላል፡፡ እነዚህን አራት ግቦች ለማሳካት የሚችል ሞዴል ነው የዘረጋነው፡፡ እኛ  ኮሌክቲቭ ሀብት የምንፈጥረውም ሆነ ሁሉን የምናሳካው ለምነን ወይም በሌላ መንገድ ሳይሆን ቢዝነስ በመስራት ነው፡፡ ማንም ላይ ጥገኛ አንሆንም፡፡ እኛ ይህንን ለሰዎች ስናስረዳ “ለምን አውሮፓ ህብረትን አትጠይቁም? ለምን የተባበሩት መንግስታትን አታናግሩም? ምናምን” ይሉናል በፍፁም! ይሄ ነው እኛን ደሀ አድርጎ ያስቀረን፡፡ ይሄ ነው የልመና አስተሳሰብ የጫነብን፡፡ ስለዚህ የራሳችን ቢዝነስ በመስራት ነው ግባችንን የምናሳካው፡፡
አሁን እኛ አባይን የገደብንበትና ከሌሎች ተፅዕኖዎች የወጣንበትን  አይነት አካሄድ ማለት ነው…..?
ኤግዛክትሊ! ትክክል ነሽ አመሰግናለሁ። የማንም እጅ ጥምዘዛና ተፅዕኖ በሌለበት መንገድ ሰርተን ነው አላማችንን የምናሳካው። በራስ ላይ መተማመን ማለት እሱ ነው፡፡ ስለዚህ ምን ዓይነት ቢዝነስ እንፍጠር ሲባል፣ አሁን ኢትዮጵያ የመጣንበት “ፐርፐዝ ብላክ” የሚባለው ተወለደ ማለት ነው፡፡ 135 ያህል ሰዎች አሉበት፤ አብረው ለዚህ ፕሮጀክት ለፍተው ደክመዋል፡፡
ከሁሉም የአፍሪካና የአሜሪካ ጥቁሮች የተወጣጡ ናቸው ወይስ ኢትዮጵያውያን ብቻ ናቸው?
አሁን  ያሉት በአብዛኛው ኢትዮጵያን ናቸው፡፡ በዚህም በጣም  ኩራት ይሰማናል።  እኛ ይህንን ፕሮጀክት ዳግማዊ አድዋ ነው የምንለው፡፡ የአድዋ ድል ለመላው ጥቁር ህዝብ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፤ ያለመገዛት ነፃ ሆኖ የመኖር ስነ ልቦና አትሞብናል። ስለዚህ በዚህ ፕሮጀክት የጥቁር ህዝብን ታሪክ መቀየር ከቻለን፣ የጥቁር ህዝብን ክብር እናስመልሳለን ብለን ነው የምናስበው።
እቅዳችሁና ሀሳባችሁ ትልቅና አጓጊ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ጥቁር ህዝብን ከፍ የማድረግ የማንቃት ስራ ሲሰራ ነጮቹ ደስተኛ አይሆኑም፡፡ የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት ሲተባበሩ፣ አንድ ሲሆኑና ጠንከር ሲሉ ምዕራባዊያን የሚበተኑበትን አጀንዳ በመፍጠር፣ እንቅፋቶችን በማበጀትና በቀጥታም ይህን በተዘዋዋሪ እጃቸውን በማስገባት ሂደቶችን ያበላሻሉ፡፡ በዚህ ፕሮጀክታችሁ መሰል ችግር ቢገጥመን ምን ማድረግ አለብን ብላችሁ አስባችኋል?
እውነትሽን ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ ሳናስበው አልቀረንም፡፡ “ብላክ ኢኮኖሚ ኤክሰለንስ” ብለን ስንነሳ ራሱ በመሃላችን ብዙ ፍትጊያ ነበር፡፡ ለምን ብላክ ብለን እንነሳለን። በውስጠ ታዋቂነት እንሂድና ለውጥ ካመጣንና ካደግን በኋላ እንቀይረዋለን የሚል ክርክር ሁሉ ነበር፡፡ ግን የለም፤ በዚሁ አቋማችን እንግፋ፤ በተቻለ መጠን እነሱ ላይ ጥገኛ የማይሆን ሲስተም እንፍጠር በሚል ነው የተስማማነው፡፡ እነሱ ላይ ጥገኛ የሆነ ሲስተም ከሆነ እንዳልሽው በአንድም በሌላም መንገድ  ችግር ሊፈጥሩ ይችላሉ። አሁን ይሄ ፕሮጀክት በማንኛውም መንገድ ሌላውን ማህበረሰብ የሚነቅፍና የሚወቅስ አይደለም፡፡ በቃ ጥቁር ህዝብ ያለውን አቅም ሀብትና እውቀት አስተባብሮ ኢኮኖሚያዊ ደህንነት መፍጠር ላይ ብቻ ነው ትኩረታችን፡፡ ሌላው ነገር የምንፈጥረው ሲስተም የሚያገልና የሚለይ አይደለም፤ ነጮችም ገብተው ኢንቨስት ማድረግ ይችላሉ፡፡ ከፈለጉ የእኛን ምርት ገዝተው ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ የእነሱም ምርት መጥቶ አፍሪካ ሊጠቀምበት የሚችል አሰራር ነው የሚዘረጋው፡፡
እስኪ ወደ  ኢትዮጵያ የመጣው “ብላክ ፐርፐዝ” የሚሠራውን ይንገሩኝ?
“ብላክ ፐርፐዝ” የ”ብላክ ኢኮኖሚ ኤክሰለንስ” አንዷና ትንሿ ፕሮጀክት ናት፡፡ “ብላክ ፐርፐዝ” አሁን ያለንበትን የዲጅታል ኢኮኖሚ ዘመን በመከተል የተገለለውን ጥቁር ህዝብ ለመሳብ “ኢ-ኮሜርስ ፕላት ፎርም” መዘርጋት ነው፡፡ ለምሳሌ አማዞን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለነጩ ማህበረሰብ ይሰራል፡፡ አሊባባን ስትመለከቺ የኢስያ ነው፤ ቢጫውን ማህበረሰብ የሚያገለግል ነው። ለጥቁር ማህበረሰብ ማን አለው? ማንም የለውም ስለዚህ ለጥቁሩ ይህ ፕላትፎርም መፈጠር አለበት አልን፡፡ ግን ደግሞ
ቴክኖሎጂ ይዘን ብቻ እንግባ ብንል የትም አያደርሰንም፡፡ ምክንያቱም መሰረተ ልማት በአፍሪካ የተሟላ ባለመሆኑ አስቸጋሪ ነው። እንግዲህ 1 ቢ. ጥቁር ህዝብ የሚያገለግል ኢኮኖሚ እንገንባ ነው ያነው፡፡ ይሄ 1 ቢ. ህዝብ አብዛኛው የት ነው ያለው? አፍሪካ ነው፡፡
ከአፍሪካ አብዛኛው ህዝብ ያው ደግሞ ገጠር ነው፡፡ ስለዚህ ወደድንም ጠላንም ያንን ህዝብ ኢምፓክት እናድርግ ካልን ከገበሬው ጋር መስራት አለብን፡፡ ከገበሬው ጋር ሰራን ማለት ገበሬው በየቀኑ የሰው ልጅ የሚበላውን የሚጠጣውን የሚያመርት ነው፡፡ ገበሬውን ስታገለግይ ተጠቃሚውንም ታገለግያለሽ፡፡ ስለዚህ ከገበሬው ጋር መስራት አለብን፡፡ N to N PTC ይባላል ሞዴሉ፡፡ ገዢና ሻጭን በማገናኘት ደላላን ከመሃል ታስወጫለሽ፡፡ ይህ ሲሆን አንደኛ ገበሬው ምርቱን በተሻለ ዋጋ ይሸጣል፡፡ ሁለተኛ ተጠቃሚው ተገቢ በሆነ ዋጋ ይገዛል ማለት ነው፡፡
የኑሮ ውድነቱን በማረጋጋት ረገድ የምትጫወቱት ሚና ይኖራችኋል ማለት ነው?
 ትክክል ነሽ፤ ገብቶሻል፡፡ ሰው እየተማረረ ያለበት የኑሮ ውድነት ይረጋጋል፡፡ ገበሬውም ተጠቃሚ ይሆናል፤ ማለት ነው፡፡ ኢኮኖሚው ያድጋል፡፡ ለወጣቱም ብዙ የስራ ዕድል ይፈጠራል ማለት ነው፡፡ ይሄ እንግዲህ በፐርፐዝ ብላክ ፕሮጀክት “ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ” ነው ይሄ አሁን የምንነጋገርበት ቢሮ የተከፈተው፡፡ በቀጣይ  በ54ቱም የአፍሪካ አገራት ሞዴሉ ይከፈታል፡፡ እኛ ደስ የሚለን እንደ መጀመሪያ በኢትዮጵያ መከፈቱ ነው፡፡ ከገበሬው ጋር ስንሰራ 10 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር ለመሰብሰብ ነው ያቀድነው፡፡ ይሄ “ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ” ደግሞ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀብት እንዲሆን ነው የምንፈልገው፡፡ “ለምን ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ” ተባለ? የሚገኘውን ሀብት መልሰን ማህበረሰቡ ላይ ኢንቨስት ስለምናደርግ ገንዘቡ እየተሽከረከረ ለህዝብ ይሰራል ማለት ነው፤፡ ስለዚህ ካምፔይናችንም  “”ኑ በጋራ አብረን እንስራ” በሚል መሪ ቃል ነው የሚሰራው፡፡
አክሲዮን ለመሰጥ ነው ያሰባችሁት? ከሆነ መቼ ነው መሸጥ የምትጀምሩት?
ሀምሌ 17 ለህዝቡ አክስዮን መሸጥ እንጀምራለን፡፡ ገንዘቡን እንዳገኘን መንግስት መሬት እስኪሰጠን አንጠብቅም፡፡ በኪራይ  ስራ እንጀምራለን፡፡
በአሁኑ  ሰዓት ስራውን ለመስራት ከወጣቶች ፌደሬሽንና ከሌሎች ዘጠኝ ድርጅቶች ጋር ተፈራርመናል። ከወጣች ፌዴሬሽን ጋር ስልጠናም ተጀምሯል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት እናስመዘግባለን፡፡ ሁሉም የዚህ ፕሮጀክት ባለቤት እንዲሆን ጥሪ እናቀርባለን፡፡

Read 4281 times