Saturday, 26 June 2021 00:00

የምርጫ ታዛቢዎች በ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ምን ታዘቡ?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

ባለፈው ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም የተካሄደውን  6ኛ አገር አቀፍ ምርጫ የታዘቡ የሃገር ውስጥና የውጭ ሃገር ታዛቢዎች ባወጡት የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርታቸው፤ ምርጫው ሰላማዊና ህዝቡ በንቃት የተሳተፈበት እንደነበር ማረጋገጣቸውን ያመለከቱ ሲሆን በምርጫው ያስተዋሏቸውን ግድፈቶችም በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
በመላ ሃገሪቱ ከ2ሺ በላይ ታዛቢዎችን አሰማርቶ ነበረው የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ህብረት ባለፈው ረቡዕ ባቀረበው የመጀመሪያ ደረጃ የትዝብት ሪፖርቱ፤ የምርጫ ቁሳቁስ መጓደልና ምርጫው በአንዳንድ ቦታዎች በሰዓቱ አለመጀመሩን እንደ ዋነኛ ድክመት መመልከቱን  አስታውቋል፡፡
ከምርጫ ቁሳቁስ መጓደል ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ፣ ቤኒሻንጉል፣ ሲዳማና ጋምቤላ 138 ያህል ሪፖርቶች እንደደረሱት ህብረቱ አመልክቷል፡፡ ያልተፈቀደላቸው ሰዎች በምርጫ ጣቢያ የመገኘት ሁኔታን እንደ ድክመት የጠቀሰው ህብረቱ፤ ከዚህ ጋር በተያያዘም 30 ያህል ሪፖርቶች እንደደረሱት አስታውቋል፡፡ ለአብነትም፡- በአማራ ክልል የቀበሌ ሊቀ መንበሩን ጨምሮ ሰራተኞች በጣቢያ ውስጥ ተገኝተው መራጮችን የማስጨነቅ ተግባር መፈጸማቸው ተጠቅሷል፡፡
በ17 የምርጫ ጣቢያዎች ማስፈራራትና ማዋከብ ሲፈጸም ታዛቢዎች መመልከታቸውን፣ 12 በመቶ ወይም (በ256) የምርጫ ጣቢያዎች በድምፅ መስጫ ቀን ቅስቀሳ ሲደረግ መታዘባቸውን፣ 92 በሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች ደግሞ ህጉ ከሚፈቅደው ውጪ በፖሊስ ጣቢያዎች፣ ወታደራዊ ካምፖችና በፓርቲ ጽ/ቤት ህንፃ ስር መከፈታቸውን፣ እንዲሁም 40 ያህል የህብረቱ ታዛቢዎች ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እንዳይገቡ መከልከላቸውንም ከህብረቱ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት መረዳት ተችሏል።
በዚህ ምርጫ በህብረቱ እንደ ጠንካራ ጎን ከተጠቀሱት መካከል፡- ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለክፍተቶች ምላሽ ለመስጠት ጥረት ማድረጉ፣ ህዝቡ በምርጫው በንቃት መሳተፉ፣ እንዲሁም የሴቶች ተሳትፎ የጎላ መሆኑና ጣቢያዎች ለአቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞች አመቺ መደረጋቸው ይገኙባቸዋል፡፡
ከ1 ሺህ 100 በላይ ታዛቢዎችን በመላ ሃገሪቱ አሰማርቶ ምርጫውን መታዘቡን የገለጸው የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን በበኩሉ፤ በአብዛኛው የምርጫ ጣቢያዎች የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ በተቀናጀ መንገድ የተከናወነ መሆኑን ጠቁሞ፤ በአንዳንድ ጣቢያዎች የቁሳቁስ እጥረት ማጋጠሙን እንዲሁም ለመራጮች ተገቢውን ገለፃ ያለማድረግ ክፍተቶች መስተዋላቸውን አመልክቷል፡፡ ይሁን እንጂ የምርጫው ሂደት ከተፅዕኖ ነፃ የሆነና መራጩ ህዝብ የፈለገውን ፓርቲ እንዲመርጥ ያስቻለ መሆኑን ታዝቧል፤ ኮንፌዴሬሽኑ፡፡
ከ640 በላይ ታዛቢዎችን ያሰማራው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ (ኢሰመጉ)፤ ታዛቢዎቹ በምርጫው እለት ከ4ሺህ በላይ ምርጫ ጣቢያዎችን ተዘዋውረው መታዘባቸውንና የድምፅ አሰጣጡን ጠንካራና ደካማ ገጽታዎች መታዘባቸውን አመልክቷል፡፡
ኢሰመጉ በምርጫው ከታዘባቸው ጠንካራ ጎኖች መካከል፡- መራጮች በጽናት ተሰልፈው መምረጣቸው፣ የመራጮች ደማቅ ተሳትፎ፣ የኢንተርኔት አለመዘጋት፣ የጎላ የፀጥታ ችግር አለማጋጠሙ፣ ችግሮችን ለመፍታት ቦርዱ ያሳየው ተነሳሽነትና ትጋት፣ አብዛኛው ምርጫ አስፈጻሚ ለምርጫው ገለልተኛነት መረጋገጥ ጥረት ማድረጋቸው፣ የሚዲያዎችና የሲቪክ ማህበራት ተሳትፎ ጠንካራ መሆን ተጠቅሰዋል፡፡
በድምጽ መስጫው እለት በኢሰመጉ ከተስተዋሉ ዋና ዋና ድክመቶች መካከልም፡-፣ ታዛቢዎች ላይ ይፈጸሙ የነበሩ ማዋከቦች፣ ለአካል ጉዳተኞችና አቅመ ደካሞች አመቺ ያልሆኑ ምርጫ ጣቢያዎች መኖራቸው፣ የምርጫ ጣቢያዎች ዘግይቶ መከፈት፣ ምርጫው ከመጀመሩ በፊት ህጉን በተከተለ መንገድ ቃለ ጉባኤ አለመያዝ፣ በምርጫ ጣቢያዎች አካባቢ ቅስቀሳዎች መደረጋቸው፣ የጸጥታ አካላት ከምርጫ ጣቢያው 500 ሜትር እንዲርቁ ቢጠበቅም በቅርብ ርቀት መገኘታቸው ይጠቀሳሉ፡፡
በተጨማሪም የምርጫ ቁሳቁስ እጥረት ማጋጠም፣ እንዲሁም ታዛቢዎች በድምጽ ቆጠራ ላይ እንዳይሳተፉ የማድረግ ሙከራዎች እንደነበሩ በኢሰመጉ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ተመልክቷል፡፡
ምርጫውን ከታዘቡ የውጭ የምርጫ ታዛቢ ቡድኖች መካከል፣ በቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዚደንት ኦሊሴንጉ ኦባሳንጆ የሚመራው የአፍሪካ ሕብረት ምርጫ ታዛቢ ቡድን ይገኝበታል፡፡ ሕብረቱ፤ ምርጫው አንዳንድ ጉድለቶች ቢኖሩበትም፣ ሰላማዊና ተዓማኒ በሆነ ድባብ መካሄዱን አመልክቷል።   
የአፍሪካ ሕብረት ምርጫ ታዛቢ ቡድን የምርጫውን አካሄድ ከታዘበ በኋላ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱን ያወጣ ሲሆን የተካሄደው ምርጫ ከሎጂስቲክና የደህንነት እጥረቶች፣ ከፖለቲካ ተግዳሮቶችና የኮቪድ-19 ጥንቃቄ ጉድለቶች በቀር ቅድመ ምርጫውም ሆነ ምርጫው ያለ ችግርና በሰላማዊ መንገድ ተከናውኗል ብሏል፡፡  
ታዛቢ ቡድኑ፤በምርጫው 46 የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩዎቻቸውን ማስመዝገባቸውን አስታውሶ፤ በኦሮሚያ ክልል የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ በምርጫው ላለመሳተፍ በመወሰኑ፣ በክልሉ በርካታ ቦታዎች ፉክክር አልተስተዋለባቸው ብሏል። ከድምጽ መስጫ ቀን በፊት የነበረው የምረጡኝ ቅስቀሳ በተወሰነ መጠን የፖለቲካ ፓርቲዎች በጸጥታ ምክንያት እንቅስቃሴያቸው ቢገታም፣ በአመዛኙ ግን ሰላማዊ እንደነበር የታዛቢው ቡድን አስታውቋል።
የምርጫ ታዛቢ ቡድኑ፤ በምርጫው የሴቶች ተሳትፎን በተመለከተ ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገበው ጠቅላላ ቁጥር 45.7 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው ብሏል። በምርጫ ጣቢያዎች ከሚመደቡት አምስት የምርጫ ቦርድ አስፈጻሚዎች መካከል በአማካይ ሁለቱ ሴቶች መሆናቸውንም ታዝቤያለሁ ብሏል፤ የአፍሪካ ሕብረት ታዛቢ ቡድን በመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ።

Read 727 times