Print this page
Tuesday, 29 June 2021 00:00

በእግዜር ችሎት ላይ መታደም

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(2 votes)

"--አዎ ከደመና ለመተቃቀፍ፣ ከጉም ለመሳሳም፣ ጨረቃን ለማሽኮርመም፣ ፀሐይን ለማሸሞር፣ በእግዜር ችሎት ላይ ለመታደም ከፍታውን እፈልገዋለሁ፡፡ ችሎቱ ምድራዊያን እንደሚሉት አገዛዝ አይደለም፡፡ ችሎቱ ለመበየን፣ ለመቅጣት ሳይሆን ለምህረት የተሰየመ ነው፡፡--"
 
ከሰሞኑ የሆነች እንደ ቅብጥብጥ ልጃገረድ አሳሳች ቅዳሚት ዕለት የእግዚአብሔር ተራራ ላይ ነበርኩ፡፡ Tegan Bennett Daylight የተባለች ደራሲ እንዲህ ትላለች፡- ‹‹If you scratch a writer you will get a walker.›› እኔ ራሴን እንደ ደራሲ ቆጥሬ አላውቅም፡፡ ደራሲ ያሉኝም እንደሁ ስሜን አሳስተው የጠሩት ያህል ስቅቅ ይለኛል፡፡ ቢሆንም ተቅበዝባዥ ነኝ፡፡ ዘመን አይሽሬው እንግሊዛዊ ገጣሚ ዊሊያም ወርድስ ወርዝ በሕይወት ዘመኑ ሦስት መቶ ሺህ ኪሎ ሜትሮች በእግሩ እንደተጓዘ ይነገራል፡፡ በሌላ አነጋገር፤ የተጓዘው ርቀት ቢቀጣጠል የምድርን መጠነ ዙሪያ አምስት ጊዜ ዞሮታል ማለት ይሆናል፡፡ እኔም ላለፉት አስራ ስምንት ዓመታት በቀን በአማካይ ከ7-10 ኪሎ ሜትሮች ሳካልል አሳልፌያለሁ። ለበርካታ ዓመታት የቀኑ አልበቃኝ ሲል ቢያንስ በሳምንት አንድ ቀን ከሌሊቱ  ስምንት ሰዓት እየተነሳሁ የአዲስ አበባን ከጓዳ ተርፎ ጎዳና ያደረ ችጋር፣ ነውር ሳስስ አሳልፌያለሁ፡፡
እነሆ በዚህች አሳሳች ቅዳሚት፤ የእግዚአብሔር ተራራ ላይ ቆሜ ነበር። ታላቁ ባለቅኔና ኢጅፕቶሎጂስ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን በጦቢያ መጽሔት ላይ በተደጋጋሚ በሰጣቸው ቃለ መጠይቆች፤ ‹ካ› ጥንታዊ የኩሽ የእግዚአብሔር መጠሪያ ስም ነው ይለናል፡፡ እናም የካ ሚካኤል ስንል ትርጉሙ የእግዚአብሔር ሚካኤል፣ የካቲት- የእግዚአብሔር ድርብ እውነት፣ የካ ተራራ - የእግዚአብሔር ተራራ መሆኑ ነው። የካ ተራራ አዲስ አበባን ዙሪያ ከከቡቧት መናገሻ፣ እንጦጦ፣ የረርና ጨርጨር የተራራ ሰንሰለቶች አንዱ ነው፡፡ ተራራው እስከ ዛሬ ካሰስኳቸው አዲስ አበባን የከበቡ ተራሮች ሁሉ ድንግልና መሳጭ እንደሆነ መናገር እችላለሁ፡፡ ይህ ግን ስንተኛው ጉብኝቴ ይሆን? እውነት ለመናገር መቁጠር ይቸግረኛል፡፡
እነሆ የእግዚአብሔር ተራራ ላይ ቆሜያለሁ፡፡ ግን ብቻዬን አይደለሁም። ሃሳብ አብሮኝ አለ፡፡ ስለ ሞቱት እንሰቀሰቃለሁ፣ ስለ ታገቱት እጨነቃለሁ፤ ስለ ተገፉት እትከነከናለሁ። ስለ ብቻ ትግሎቼ እቆዝማለሁ፡፡ ቢሆንም እጎብጣታለሁ እንጂ እምባዬን ለማንም አላሳይም፡፡ ወዲያው ግን ነፍሴ ከፊቴ በተዘረጋው ገር ገበርባራ፣ ደግሞ እንደገና  ጥሬ፣ እውነተኛ፣ ልሙጥ ገፀ  ምድር ስትነካ፣ በቅጠሎቹ ሽብሸባና ጭብጨባ ስትመሰጥ ከዓለማዊው ቅዝምዝም ለሰዓታት ነጻ ትወጣለች፡፡ Friedrich Neitszche ይሄንን ስሜቴን እንዲህ ይጋራዋል፡፡  “He who climbs upon the highest mountains laughs at all tragedies, real or imaginary.” Werner Herzog የተባለ ግለሰብ በበኩሉ፤ “እያንዳንዱ ሰው ቢያንስ  በሕይወት ዘመኑ አንድ ጊዜ ጀልባውን እየገፋ ወደ ተራራ ማውጣት አለበት፡፡” ይለናል፡፡  
ተራሮች ግን የእግዜርም ሆኑ አልሆኑ ወንድሞቻችን ናቸው፡፡ ትናንት ለአያቶቻችን ከጠላት መሸሸጊያ ነበሩ፤ ዛሬ ለእኔና እናንተ መተከዚያ ሆነዋል፡፡ ተራሮች የዘለዓለማዊነት አምሳያ ናቸው፡፡ የቆራጥነት መለኪያም ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡ ተራሮች ግን ብቻቸውን አይደሉም፡፡ ገታራ የሆኑ ረቂቅና ሁሉን አወቅ ዛፎችም አብረዋቸው አሉ፡፡ Harry J. Stead የተባለ እንደኔው ተቅበዝባዥ ደራሲ ስለ ዛፎች ሲፅፍ፡- ‹‹trees are in particular mysterious to me; they are like gods or mystics, infinitely wiser than humans, all knowing, all seeing, and we can only admire them from below.” ይላል።
ሕንዳዊው ሚስቲክ ገጣሚ ራቢንድራናዝ ታጎር ዛፎችን የተመለከተች ረቂቅ ግጥም አለችው፡፡
I asked the tree,
Speak to me of God,
And it blossomed.
እግዚአብሔርን ስትሹ ስለ ምን በድን ቤተ መቅደስና ቤተ መስጂዶች ውስጥ ብቻ ትፈልጉታላችሁ፡፡ እሱ በመፍካቱ ውስጥ፣ በመገርጣቱ ውስጥ፣ በማቆጥቆጥ በማበብ ውስጥ የሚገለጥ እውነታ ነው፡፡ ይህ እውነት እንደ ግብዞች፣ ወይ እንደ ቶማሳዊያን ካልዳሰስን አናምንም ለሚሉት የሚጨበጥ አይደለም፡፡ በቀና መንፈስ ከእያንዳንዷ ቢራቢሮ ጋር ለመቅበጥበጥ፣ ከእያንዳንዷ አበባ ጋር ለመሽኮርመም ስንዘጋጅ፣ በነፋስ በሚደንስ ሲሻው እንደ ሱባዔ በሚያረም የስነ ተፈጥሮ ውህድ ውስጥ በንቃት ስንቀዝፍ ብቻ የሚገለጥ እንጂ… ሰው የስነ ተፈጥሮ ጠባቂ ይሆን ዘንድ በመለኮቱ ቢሾምም፣ ለምድር ስነ ሕይወትን በሙሉ በጭካኔ የሚያወድም መርገምት፣ የአንበጣ መንጋ ሆኖባታል፡፡  
እናም ወደ ተራሮች የመሸሽ ምኞት ቅንጦት እንዳልሆነ እወቁት… በፍጹም! እዚያ ተፈጥሮ ነው፤ እዚያ ንጹህ ትንፋሽ፤ ወደ ተራሮች መውጣት የሚያርበተብት መሻት ነው። ወደ ተፈጥሮ የመመለስ ፍንደቃ፣ በኦና የብርሃን ንኝት የመስከር፣ ጸሐይ እንዳኮረፈች ልጃገረድ ከተራሮች ጀርባ ስትጋረድ፣ ጨለማ ከሸለቆዎች ጥልቅ እየዳኸ ወጥቶ መላውን ፍጥረት ሲቆጣጠር የመመልከት መቋመጥ… ተራሮች ወንድሞቻችን ናቸው። አዎ ከደመና ለመተቃቀፍ፣ ከጉም ለመሳሳም፣ ጨረቃን ለማሽኮርመም፣ ፀሐይን ለማሸሞር፣ በእግዜር ችሎት ላይ ለመታደም ከፍታውን እፈልገዋለሁ። ችሎቱ ምድራዊያን እንደሚሉት አገዛዝ አይደለም። ችሎቱ ለመበየን፣ ለመቅጣት ሳይሆን ለምህረት የተሰየመ ነው፡፡
እነሆ የእግዚአብሔር ተራራ ላይ ቆሜያለሁ፡፡ እውነትስ ግን ሼክስፒር ይሉት ምትሃተኛ ‹‹ልክፍቱ የጨረቃ ነው። አለቅጥ ዝቅ ዝቅ እያለች ከሚገባት በታች ወርዳ ሰውን ሁሉ አሳብዳዋለች፡፡›› ያለው የእግዚአብሔር ተራራ ላይ ሆኖ አይቷት ይሆን እንዴ?
ተራሮችን የመውጣት፣ በእግር የመንሸራሸር መሻት በተለይ ለደራሲያኑ ትርጉሙ ብዙ ነው፡፡ ከላይ ለአብነት የጠራነው ኒቼ Twillight of the Idols በሚለው መጽሐፉ እንዲህ ይላል፡- ‹‹All truly great thoughts are conceived while walking›› ፈንሳዊው ዣን ዣክ ሩሶ በበኩሉ፡- ‹‹I could meditate only when I am walking. When I stop I cease to think; my mind only works with my legs.›› ሌላም እንጨምር፡፡ ኤድዋርድ ሆግላንድ የተባለ ደራሲ ስለ ድርሰት ይትባህሉና የእግር ጉዞው ግንኙነት ቀጥሎ የማቀርበውን ጥቅስ ‘ዘ አትላንቲክ’ የተሰኘው መጽሔት ላይ ፅፎ ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡ ‹‹እያንዳንዷን ተጨማሪ ማይል በተራመድኩ ቁጥር የተሻለ ደራሲ እንደምሆን አውቃለሁ፡፡››
ጆርጅ ሳንድ በተባለው የብዕር ስሟ የምትታወቀው ፈረንሳዊት ደራሲ በበኩሏ፤ ‹‹የፓሪስን ከተማ ከአንደኛው ጫፍ ወደ ሌላኛው ጫፍ በእግሬ ብጓዝ አንድ ልብወለድ መፅሐፍ አውጠንጥኜ እንደምጨርስ አውቃዋለሁ፡፡›› ትላለች፡፡ ከቪትሆቨን፣ ኒቼ፣ ሔሰ እስከ ቤኬትና ካፍካ ኪነታዊያን በአብዛኛው የመራመድ ውል የለሽ መሻት የሚያክለፈልፋቸው ድንጉጦች ነበሩ፤ ናቸውም፡፡ ከፈለጋችሁ እኮ አንድ ሺህ ገጾች ወስጄ ስለ በእግር መጓዝ፣ ማሰብና ተራሮች እልፍ ነገሮችን ላወጋችሁ እችላለሁ፡፡ ግን ምን ያደርግላችኋል? ይልቅ ጫማችሁን አጥብቁ። በዚሁ ጉዳይ ብቻ ብዙ ሺህ ገጾችም ተጽፈዋል፡፡ ፈልጎ  እያነበቡ መራመድ ነው፡፡

Read 8582 times