Saturday, 03 July 2021 20:13

ኢትዮጵያ ለከፍተኛ የምግብ እጥረትና የኑሮ ውድነት ከተጋለጡ ቀዳሚ ዓለም ሀገራት አንዷ ሆነች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

ኢትዮጵያ በዓለም ለከፍተኛ የምግብ እጥረትና የኑሮ ውድነት ከተጋለጡ ቀዳሚ ሶስት ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗ ተገለፀ፡፡
አለማቀፍ የረሃብ አደጋዎች ቅድመ ማስጠንቀቂያ ተቋም ከትናንት በስቲያ ሃሙስ ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ፤ በዓለም ላይ በግጭት ምክንያት ለከፍተኛ የምግብ  እጥረት የተጋለጡ ሃገራት፡- ኢትዮጵያ፣ደቡብ ሱዳንና የመን መሆናቸውን ጠቁማል፡፡ ኢትዮጵያ በዋናነት በትግራይ ክልልባለው ግጭት ሳቢያ ለምግብ እጥረት ከተጋለጡ ሃገራት በቀዳሚነት እንድትቀመጥ አድርጓታል ሪፖርቱ፡፡
በትግራይ ክልል ያለው ቀውስ ከ5.2 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለምግብ እጥረት እንደዳረገ፣ ከ30 ሺህ በላይ ህፃናትን ለረሃብ እንዳጋለጠ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ህፃናትና እናቶች በአልሚ ምግብና ህክምና እጥረትም ለሞት እየተዳረጉ መሆናቸውን አስታውቋል።
በትግራይ የተፈጠረው ቀውስ የኮቪድ ወረርሽኝ፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪና  ሌሎች ምክንያቶች ደግሞ በተለይ በከተሞች የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ በኑሮ ውድነት እየፈተነ መሆኑን፣ ይህም በሃገሪቱ ማይክሮ ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ተፅዕኖ ማሳረፉን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
በኢትዮጵያ በአብዛኛው ማህበረሰብ ለምግብነት የሚውሉት ጤፍ፣ ማሽላ፣ ገብስና በቆሎ ዋጋቸው በእጅጉ ማሻቀቡን፣ የዛሬ 5 ዓመት ከነበረውም በሁለት እጥፍ መጨመሩን ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት የሸቀጦች የዋጋ ግሽበት ምጣኔ 12 በመቶ እንደነበር ያስታወሰው ሪፖርቱ፤ በአሁኑ ወቅት የዋጋ ግሽበት ምጣኔው 19.2 በመቶ መድረሱን በዚህም ሳቢያ የሸቀጦች ዋጋ በእጅጉ እያሻቀበና በተለይ የከተማ ነዋሪዎችን ህይወት እየፈተነ መሆኑን አመልክቷል፡፡
በሁለተኛነት በሪፖርቱ የተጠቀሰችው ጎረቤት ደቡብ ሱዳን፤ በአሁኑ ወቅት አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት ውስጥ እየገባች ቢሆንም፣ ካለፉት የቀውስ ጊዜያቶች የዞረ ድምር በሃገሪቱ ሚሊዮኖችን ለምግብ እጥረት አጋልጧል ተብሏል፡፡
የሃገሪቱ መንግስት አፋጣኝ መፍትሔ የማይሰጥ ከሆነ በተለይ የምግብ እጥረቱ በበረታባቸው በፓይቦር፣ ጆንግሌ፣ ዋራና ታላቁ አኬቶር አካባቢዎች ረሃብን ሊያስከትል እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
ከምግብ እጥረቱ ባሻገር በደቡብ ሱዳን ከጊዜ ወደ ጊዜ የሸቀጦች ዋጋ ንረት እያጋጠመ መሆኑን  ያመለከተው ሪፖርቱ፤ የጥራጥሬ ምግቦች ዋጋ ከጥቂት ወራት በፊት ከነበረው ከ400 እስከ 500 መቶ በመቶ ድረስ አስደንጋጭ ጭማሪ ማሳየቱ ተመልክቷል፡፡
በተመሳሳይ በግጭት ውስጥ ባለችው የመን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝቦች ለከፋ ረሃብ መጋለጣቸውንና ከሚያዚያ ወር ጀምሮ መደበኛ የምግብ ሸቀጦች ዋጋም የ65 በመቶ አማካይ የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
ዓለማቀፍ የረሃብ አደጋዎች ቅድመ ማስጠንቀቅያ ተቋሙ፤ በሶስቱ ሀገራት ያለው ችግር ተባብሶ ቀጠናዊ አለማቀፋዊ ቀውስ ከመፈጠሩ በፊት አለማቀፉ ማህበረሰብ በልገሳው እንዲረባረብ ጥሪ አቅርቧል፡፡

Read 4993 times