Saturday, 03 July 2021 20:17

መንግስት የትግራይን ችግር በውይይት የመፍታት እቅድ እንዳለው ተገለፀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

መንግስት በትግራይ ያለውን ችግር ከሲቪል ማህበረሰቡና ከሃገር ሽማግሌዎች ጋር ውይይት በማድረግ መፍትሄ ለማበጀት እቅድ እንዳለው ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ ምክትል ጠ/ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተለያዩ ሃገራት አምባሳደሮች ገለፁ፡፡
በትግራይ ለተፈጠረው ችግር መነሻው የሕውሐት ቡድን መሆኑን ለአምባሳደሮቹ ያስረዱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ሕውሐት ከፌደራሉ መንግስት ጋር ያለውን ልዩነት በሠላም እንዲፈታ የቀረበለትን ተደጋጋሚ ጥሪ አለመቀበሉን አስገንዝበዋል።
መንግስት በሽብርተኝነት የፈረጀው የሕውሐት ቡድን በጦርነቱ ወቅት ብሔርን መሰረት ያደረገ ጥሪ በማድረግ ወጣቶች በስሜታዊነት የጦርነቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረጉን ያብራሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ አዝማሚያው ያሳሰበው መንግስት ህዝቡ የጥሞና ጊዜ እንዲያገኝና አርሶ አደሩ የክረምቱ የእርሻ ተግባር እንዳይስተጓጎልበት በማሰብ የተናጠል የተኩስ አቁም እርምጃ መውሰዱን ገልጸዋል።
በጦርነቱ ሕውሐት ድልድዮችን፣ የቴሌኮምና ኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶችን ሆን ብሎ በተደጋጋሚ ማውደሙን ጠቁመው፤ በአንፃሩ መንግስት እነዚህን የወደሙ መሰረተ ልማቶች ጠግኖ ወደ ስራ ለማስገባት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል- የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፡፡
በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ድጋፍ ለሚሹ ሰዎች የሰብአዊ እርዳታ እንዲደርሳቸው የፌደራሉ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ያስገነዘቡት ምክትል ጠ/ሚኒስትሩ አለማቀፉ ማህበረሰብ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Read 11559 times