Saturday, 03 July 2021 20:18

በትግራይ ታጣቂዎች ጥቃት ከመፈፀም እንዲቆጠቡ አምነስቲ አሳሰበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

   ባለፈው ሰኞ የመከላከያ ሰራዊት ከትግራይ  መውጣቱን ተከትሎ፣ በታጣቂዎች እጅ በወደቀችው የትግራይ መዲና መቀሌ የሠብአዊ መብቶች ጥሰት ሊፈፀም ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት እንዳደረበት ያመለከተው አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ ታጣቂዎች የጦር ወንጀሎችን በሰው ልጅ ላይ ከመፈፀም እንዲቆጠቡ አሳስቧል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የመከላከያ ሠራዊቱን ከመቀሌና ከተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ማስወጣቱን ተከትሎ፣ ታጣቂ ሃይሎች በአካባቢው የቂም በቀል እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳደረበት አምነስቲ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡
መንግስትና ታጣቂ ሃይሎች በተለይ የሠብአዊ ድጋፎችን ዝውውር እንዳያደናቅፉ ጥሪ ያቀረበው የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ፤ በክልሉ የቴሌኮም እንዲሁም የመረጃና መገናኛ አውታሮች በሙሉ ክፍት እንዲሆኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡
መንግስት በአፋጣኝ የኢንተርኔት፣ ስልክና፣ የመገናኛ ብዙኃን መረጃ አቅርቦት እንዲያቀላጥፍ የጠየቀው አምነስቲ፤ እነዚህ መሰረተ ልማቶች መሰረታዊ የሰብአዊ መብት ጉዳዮች ከመሆናቸውም ባለፈ ለሰብአዊ ድጋፎች ወሳኝ ሚና አላቸው ብሏል፡፡
በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ቅድሚያ ለሰብአዊነት እንዲሰጡና ጨርሶ ከማጥቃት እንዲቆጠቡ አምነስቲ አሳስቧል፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽል፤ የትግራይን ሁኔታ በቅርበት እንደሚከታተልና በተለይ በንፁሀን ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን  እንደሚያጋልጥ አመልክቷል  በመግለጫው፡፡

Read 12007 times