Saturday, 03 July 2021 20:21

የተጨዋቾች ዝውውር በ2021

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች የተጨዋቾች ዝውውር ገበያ የተከፈተ ቢሆንም በCOVID-19 ወረርሽኝ ሳቢያ ገበያው ያን ያህል የተሟሟቀ አይደለም፡፡  በአውሮፓ እግር ኳስ ላይ የተጨዋቾች ዝውውር ገበያውን ለመከታተል የጀርመኑ ትራንስፈርማርከት ግንባር ቀደም አማራጭ ነው፡፡ ድረገፁ  በዝውውር ገበያው ላይ የተጨዋቾች እና የቡድኖችን ዋጋ የሚተምን፤ የዝውውር ዜናዎች እና ታሪኮችን የሚያቀርብ፤ የገበያውን አጠቃላይ ሁኔታ በመገምገምና በማጥናት አኃዛዊ መረጃዎች የሚሰጥ፤ ዜናዎች፤ መረጃዎች እንዲሁም ውጤቶችን በማሰራጨት ይሰራል፡፡
በትራንስፈርማርከት ድረገፅ በቀረበው መረጃ መሰረት በአሁኑ ወቅት በዓለም እግር ኳስ ከፍተኛውን ዋጋ  የሚያገኘው ተጨዋች ለፓሪስ ሴንትዥርመን የሚጫወተው የ22 ዓመቱ ኪሊያን ምባፔ ሲሆን በ160 ሚሊዮን ዩሮ ዋጋው ነው፡፡ አርኒንግ ሃላንድ ከቦርስያ ዶርትመንድ በ130 ሚሊዮን ዩሮ እንዲሁም ሃሪ ኬን ከቶትንሃም በ120 ሚሊዮን ዩሮ ዋጋቸው ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ አላቸው። ሰሞኑን ከቦርስያ ዶርትመንድ ወደ ማንችስተር ዩናይትድ የተዛወረው ጃዶን ሳንቾ፤ መሃመድ ሳላህ ከሊቨርፑል፤ ሮሜን ሉካኩ ከኢንተር ሚላን ፤ ኬቨን ደብርዋይኒ ከማን ሲቲ እንዲሁም ኔይማር ከፓሪስ ሴንትዥርመን በ100 ሚሊዮን ዩሮ የዋጋ ተመናቸው እስከ 8ኛ ደረጃ አከታትለው ይይዛሉ፡፡ ፍሬንኪ ዲጆንግ ከባርሴሎና እንዲሁም ቡርኖ ፈርናንዴዝ ከማንችስተር ዩናይትድ በ90 ሚሊዮን ዋጋቸው እስከ 10ኛ ደረጃ ይቀመጣሉ፡፡
በዓለም እግር ኳስ በተጨዋቾች የዝውውር ገበያ ላይ የተመዘገቡ የክፍያ ሪከርዶችን ከትራንስፈርማርከት ገፅ መመልከት ይቻላል፡፡ በከፍተኛ የዝውውር ሂሳብ ክብረወሰኑን የያዘው የብራዚሉ ኔይማር ሲሆን ከባርሴሎና ወደ ፓሪስ ሴንትዠርመን ሲዛወር በተከፈለው 222 ሚሊዮን ዩሮ  ነው፡፡ ኪሊያን ምባፔ ከሞናኮ ወደ ፓሪስ ሴንትዥርመን በ180 ሚሊዮን ዩሮ፤   ፍሊፕ ኩቲንሆ ከሊቨርፑል ወደ ባርሴሎና በ145 ሚሊዮን ዩሮ፤  ኦስማን ዴምበሌ ከቦርስያ ዶርትመንድ ወደ ባርሴሎና በ135 ሚሊዮን ዩሮ እንዲሁም  ጆአ ፊሊክስ ከቤነፊካ ወደ አትሌቲኮ  ማድሪድ በ127 ሚሊዮን ዩሮ የዝውውር ሂሳብ እስከ አምስተኛ ደረጃ ይወስዳሉ፡፡
ከአውሮፓ ክለቦች በተጨዋቾች ስብስቡ ከፍተኛ የዋጋ ተመን በማስመዝገብ የመጀመርያውን ስፍራ የሚይዘው የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊጉ  ማንችስተር ሲቲ በ1.03 ቢሊዮን ዩሮ ነው፡፡
ሊቨርፑል በ929 ሚሊዮን፤ ቼልሲ በ916 ሚሊዮን፤ ሪያል ማድሪድ በ886.50 ሚሊዮን እንዲሁም ባርሴሎና በ832 ሚሊዮን ዩሮ የዋጋ ተመናቸው እስከ 5ኛ ደረጃ ይቀመጣሉ። ፓሪስ ሴንትዠርመን በ804.95፤ ባየር ሙኒክ በ773.3፤ ማንችስተር ዩናይትድ በ763.25፤ ኢንተር ሚላን በ757.95 እንዲሁም አትሌቲኮ ማድሪድ በ689.5 ሚሊዮን ዩሮ  እስከ 10ኛ ደረጃ ተይዘዋል፡፡
በተጨዋቾች የዝውውር ገበያ ታሪክ ከአሰልጣኞች ከፍተኛውን ወጭ በማውጣት የሚታወቁ አሰልጣኞችም በትራንስፈርማርከት ደረጃ ወጥቶላቸዋል። በማንችስተር ሲቲ የሚገኘው ፔፔ ጋርዲዮላ በአሰልጣኝነት ዘመኑ በ3 የተለያዩ ክለቦች 21 ዋንጫዎችን ያሸነፈው  51 ተጨዋቾች ከዝውውር ገበያው በመግዛት ሲሆን በድምሩ 1.19 ቢሊዮን ዩሮ ወጭ በማድረግ የመጀመርያውን ደረጃ ይዟል፡፡ ጆሴ ሞውሪንሆ በ4 የተለያዩ ክለቦች ሰባት ዋንጫዎችን ለማሸነፍ በነበራቸው ቆይታ ለ46 ተጨዋቾች ግዢ  1.06  ቢሊዮን ዩሮ፤ ዲያጎ ሲሞኔ በ2 ክለቦች 8 ዋንጫዎች ሲያሸንፍ ለሰበሰባቸው 58 ተጨዋቾች 977.72 ሚሊዮን ዩሮ፤ ማሲሚላኖ አሌግሪ በሁለት ክለቦች 12 ዋንጫዎች ለመቀዳጀት 76 ተጨዋቾች ከገበያው ሲገዙ 972.62  ሚሊዮን ዩሮ እንዲሁም አንቶኒዮ ኮንቴ በ3 የተለያዩ ክለቦች 8 ዋንጫዎች ለመሻነፍ 73 ተጨዋቾችን ሲገዙ 935.69 ሚሊዮን ዩሮ ወጭ አድርገው እስከ አምስተኛ ደረጃ ተሰጥቷቸዋል፡፡

Read 1282 times