Print this page
Saturday, 03 July 2021 20:24

የስነተዋልዶ ጤና ግንዛቤ ማስጨበጫ ድረገጽ

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

በአለምአቀፍ ደረጃ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ጥያቁ እያነሱ መልስ ለማግኘት ሲባል ባለሙያን ለማግኘት ሲባል ከቦታ ቦታ ሳይንቀሳቀሱ ባሉበት ቦታ ሆነው ለፈለጉትን ጥያቄ መልስ ለማግኘት የሚያስችሉ በርካታ ድረገጾች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ በተለይም በጤና ጉዳይ ስለምንም አይነት ሕመም መንስኤ እና ክትትል እንዲሁም መፍትሔውን ጭምር በዝርዝር ለመረዳት የሚያስችሉ ባለሙያዎች ትኩረት ሰጥተው መልስ የሚሰጡባቸው እንዲሁም ይህንን ተግባር በከፍተኛ ሁኔታ  የሚያስፈጽሙ አካላት መኖራቸውን ድረገጾቹ ያስረዳሉ፡፡ ይህንን በሚመለከት ለዚህ እትም የምናነሳውን ጉዳይ ያብራሩልን አቶ አዲሱ ደረሰ በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ፕሮግራም ኮሙዩኒኬሽን ኦፊሰር ናቸው፡፡   
አቶ አዲሱ እንደገለጹት የኢትዮጲያ የጽንስና ማህጸን ሃኪሞች ማህበር (ESOG) ከአለም አቀፉ የጽንስና ማህጸን ሃኪሞች ፌደሬሽን (FIGO) ጋር በመተባበር አዲስ ድረ ገጽ ሊያስተዋውቅ ነው፡፡ በባለፉት ሁለት አመታት በሁለቱ ተቋማት ውስጥ በሚገኙ ባለሞያዎች በተቋቋመ ቡድን በምክክር ሲበለጽግ የነበረው ድረ ገጽ ወደ ስራ ሲገባ የወጣት ወንዶችን እና ልጃገረዶችን የስነተዋልዶ ጤና ግንዛቤ ከማሳደግም ባሻገር ጥያቄዎችን ለመጠየቅ እና መልስ ለማግኘትም እንደሚረዳ ይጠበቃል፡፡
በአፍሪካም ሆነ በሌሎች የአለም ክፍሎች የስነጾታና የስነ ተዋልዶ ርዕሰ ጉዳዮች በግልጽ በቤተሰብም ሆነ አገልግሎቱን በሚፈልጉ ሰዎች እና በጤና ባለሞያዎቻቸው መካከል በግልጽ ውይይት የሚደረግበት እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ እንደ ኢትዮጲያ ባሉ የባህል እና የሃይማኖት ሚና በጎላባቸው አገራት ውስጥ ደግሞ ይህ ልምድ እምብዛም የሚበረታታም አይደለም፡፡ ይህ ሁኔታ ግን ዜጎችን ጤንነታቸውን በማስረጃ በተደገፈ ሁኔታ እንዳይጠብቁ ሲያደርጋቸው ቆይቷል፡፡
ጽንስ ማቋረጥ የሚፈልጉ ልጃገረዶች ህጉ ቢፈቅድላቸውም በሃይማኖታዊ ምክንያቶች ለህክምና ባለሞያዎቻቸው ቀርበው ማማከር ባለመቻል በባህላዊ መንገድ ጽንሱን ለማቋረጥ እየሞከሩ ህይወታቸውን የሚያጡበት ሁኔታ አለ፡፡
ጤንነቱን ባልጠበቀ ሁኔታ የግብረ ስጋ ግንኙነት ያደረጉ ወጣቶች በአባላዘር በሽታ እንደተጠቁ ቢጠረጥሩ ሚስጥራቸውን ጠብቀው ምክር እንዴት ያገኛሉ?
ለመጀመሪያ ጊዜ የወር አበባ የታያት ልጅ አገረድ ስለሁኔታው ለመረዳት የምታዋየው ባይኖራት ምን ታደርጋለች?
የማህጸን ጫፍ ካንሰር ምን እንደሆነ ማወቅ ፈልጋ ካጠገብዋ መረጃው ያለው እና የምታዋየው ሰው ባይኖርስ?
እርጉዝ ሴት ስለእርግዝናዋ የመጀመሪያ ደረጃ መረጃን ማግኘት ቢያሻትስ?
የቤተሰብ ምጣኔ መጠቀም አስባ ምን መንገዶችን መከተል እንዳለባት የመጀመሪያ ደረጃ መረጃ እየፈለገች ቢሆንስ?
ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎች የተለያዩ ስነተዋልዶ ነክ ጥያቄዎች ያሏቸው ዜጎች ወደጤና ተቋም ሳይሄዱ ነገር ግን ሚስጥራቸው ተጠብቆ ጥያቄዎችን የሚጠይቁበት ድረ ገጽ በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበርና በአለም አቀፉ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ፌደሬሽን ተቋቁሞ ስራ ሊጀምር ነው፡፡ በዚህ ጽሁፍ የምናስታዋውቃችሁ አዲሱ ድረ ገጽ Ask Dr. FIGO ወይንም በግርድፉ “ሃኪም ፊጎን ያማክሩ” የተሰኘው ድረ ገጽ ነው፡፡  
ድረ ገጹ ሲለቀቅ በአማርኛ የጎብኚዎችን ጥያቄዎችን መቀበል እና መልስ አዘጋጅቶ መመለስ ይችላል፡፡ በቅርቡም በኦርምኛ ቋንቋም ጥያቄዎችን ተቀብሎ ማስተናገድ ይጀምራል፡፡ የድረ ገጹ ጽንሰ ሃሳብ ምንም እንኳን በሌሎች በኢኮኖሚ ባደጉ አገራት ውስጥ ሲሰራበት የቆየ ቢሆንም በኢትዮጲያ ግን በአገር ውስጥ ቋንቋ መቅረቡ ብዙዎችን ተጠቃሚ እንደሚደርግ ተገምቷል፡፡
በአሜሪካን አገር ከሚገኝ እና ተመሳሳይ አላማ ካለው ድረገጽ ላይ ሲጠየቁ የነበሩ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ተመርጠው እና ወደ አማርኛ ቋንቋ ተተርጉመው ድረ ገጹን ለማስጀመር ተዘጋጅተዋል፡፡ በዚህም አንድ ኢትዮጲያዊ ጥያቄው/ዋ በድረገጹ የመረጃ ቋት ውስጥ ከሚገኙ ጥያቄዎች ጋር ተመሳሳይ ከሆነ በፍጥነት በአማርኛ ቋንቋ አውቶማቲክ ምላሽ ያገኛል/ ታገኛለች ማለት ነው፡፡
ጥያቄዎቻቸው ደግሞ በመረጃ ቋት ውስጥ ካሉት ጋር የማይመሳሰሉ ከሆነ ደግሞ ጥያቄዎቻቸውን ጽፈው በድረ ገጽ ላይ ያስቀመጣሉ፡፡ በዋናነት የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር አባላት የሆኑ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያዎች በራሳቸው አካውንት ወደ ድረ ገጹ ሲገቡ የተደረደሩ ጥያቄዎችን ይመለከታሉ፡፡ ከእነዚህ ወደ ድረገጹ በመጡ ዜጎች ከተጠየቁ ጥያቄዎች መካከል ለጊዜው መመለስ የሚችሉትን ያህል ይመልሱና መልሶቻቸውን እዛው ድረ ገጹ ላይ አስቀምጠው ይወጣሉ፡፡
ጠያዊዎቹ ከአንድ አሊያም ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ተመልሰው ወደ ድረ ገጹ ሲመለሱ ለጠየቋቸው ጥያቄዎች መልሶቻቸውን ያገኛሉ፡፡ ጠያቂዎች ጥያቄዎቻቸውን ሲያቀርቡ የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች መልሶቻቸውን ለማዘጋጀት የሚረዱ ጥያቄዎችን እንዲመልሱ ይደረጋል፡፡
ጠያቂዎች ስማቸውን፤ አሊያም ማንነታቸውን ሊያሳውቁ የሚችሉ ማናቸውንም መረጃዎችን አይጠየቁም፡፡
ስልክ ቁጥር አሊያም የሚኖሩበትን አከባቢም ሆነ ሌላ የግል መረጃ እንዲያስገቡ አይጠየቁም፡፡
የጠያቂዎች ማንነት ምላሹን የሚሰጡት ሃኪሞች የሚያውቁበት ምንም አይነት ሁኔታን ድረገጹ ስለማይፈቅድ ጠያቂዎቹ በፍጹም ነጻነት ጥያቄዎቻቸውን መጠየቅ ይችላሉ፡፡
የጠያቂዎቹ እድሜ፤ ጾታ፤ የእድሜ ደረጃ፤ ጠያቂዋ እርጉዝ መሆን አለመሆኗ፤ ወይም ከዚህ በፊት የነበሩ የጤና ሁኔታዎች እንዳስፈላጊነቱ መረጃን እንዲያስገቡ ሊጠየቁ ይችላሉ፡፡ እነዚህ መረጃዎች የጥያቄዎቹን መልሶች ለማዘጋጀት ብቻ የሚረዱ እንጂ የጠያቄዎቹን ማንነት ለማወቅ የሚያስቸሉ እንዳይሆኑ ተደርገው የተዘጋጁ ናቸው፡፡
የድረ ገጹን አጠቃቀም ቀላልነት፤ የቋንቋ አጠቃቀም እና ጥቅም ላይ መዋል መቻሉን ለማረጋገጥ ከተመረጡ ትምህርት ቤቶች ከተውጣጡ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ጋር የሙከራ ስራ የተሰራ ሲሆን፤ ከተማሪዎቹ በተገኘ ግብረ መልስም ድረ ገጹ አጅግ ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል ግምት ተይዟል፡፡  
አቶ አዲሱ እንዳብራሩት የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር እና የአለም አቀፉ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ባለሞያዎች ፌደሬሽን በጋራ ያስተዳድሩታል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ድረ ገጽ ለመጀመሪያው አመት በሙከራ ደረጃ የሚተገበር ሲሆን፤ ከዚያ በኋላ በኢትዮጲያና በሌሎች የአፍሪካና የአለም አገራት ሙሉ በሙሉ ስራ ላይ እንደሚውል ታውቋል፡፡ ድረ ገጹ በቅድሚያ በአማርኛ ቋንቋ ጥያቄዎችን ለመጠየቅና መልስ ለማዘጋጀት ሲውል፤ ከሁለተኛው አመት በኋላ ኦሮሚኛ ቋንቋን እንደሚጨምር ታቅዷል፡፡
በቅርቡ በኢትዮጲያ እያደገ የመጣው የኢንተርኔት አገልግሎት ስርጭትም ለድረ ገጹ ጥቅም ላይ መዋል አመቺ ሁኔታዎችን ይፈጥርለታል ተብሎ ይገመታል፡፡ በአዲስ አበባና በክልሎች ባሉ ትላልቅ ከተሞች ውስጥ እየተስፋፋ የመጣው ገመድ አልባ የኢንተርኔት አገልግሎት ዋንኛው ጠቃሚ ሁኔታ ነው፡፡ ሌላው በአገሪቱ ተጨማሪ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ድርጅት ወደገበያ ይገባል የሚል ግምት መኖሩ ሌላኛው የድረ ገጹን ጥቅም ላይ መዋል በከፍተኛ ሁኔታ ሊያሳድጉ የሚችሉ ሁኔታዎች ናቸው፡፡    
ድረ ገጹን በዋናነት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች፤ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፤ ወጣት ሰራተኞች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ጥቅም ላይ ሊያውሉት እንደሚችሉ ይገመታል፡፡ ምንም እንኳን ስለ ስነተዋልዶ ጤና እና ስነጾታ ጤና ርዕሰ ጉዳዮች ጠቃሚ ግንዛቤን ይሰጣል ተብሎ ቢታሰብም፤ ድረ ገጹ የህክምና ክትትልን፤ የጤና ባለሞያዎችን በቀጥታ ማማከርንም ሆነ ወደጤና ተቋማት መሄድ ባስፈለገ ጊዜ መሄድን ይተካል የሚል የተሳሳተ ግንዘቤ እንዳይወሰድ የድረ ገጹ አበልጻጊዎች አጽኖት ሰጥተው ይናገራሉ ብለዋል አቶ አዲሱ ደረሰ በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ፕሮግራም ኮሙዩኒኬሽን ኦፊሰር፡፡

Read 11764 times