Saturday, 03 July 2021 20:22

የCR7 ሰባት ሁኔታዎች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 በዩሮ 2020 ላይ ፖርቱጋል የሻምፒዮንነት ክብሯን ለማስጠበቅ ብትቀርብም በጥሎ ማለፉ ተሰናብታለች፡፡ ዋና አምበሏ ክርስትያኖ ሮናልዶ ዶሳንቶስ አቪዬሮ በአውሮፓ ዋንጫው ላይ በነበረው ተሳትፎ አዳዲስ ክብረወሰኖችን በማስመዝገብ ተሳክቶለታል፡፡ በአውሮፓ ዋንጫ ላይ ለአምስተኛ ጊዜ በመሳተፍ እንዲሁም የጎሎቹን ብዛት 14 በማድረስ የምንግዜም ከፍተኛ አግቢ ለመሆን ችሏል። በዩሮ 2020 የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች ከመደረጋቸው በፊት 5 ጎሎችን በማስቆጠር ኮከብ አግቢነቱን እየመራም ነው፡፡
ከ846 ሚሊዮን ዩሮ በላይ  ገቢ ከእግር ኳስ
ክርስትያኖ ሮናልዶ በዓለም እግር ኳስ ከፍተኛውን ታሪክና ውጤት ያስመዘገበ ተጨዋች እየሆነ መጥቷል ፡፡ ከእግር ኳስ ስፖርት ከደሞዝ፤ ከስፖንሰርሸፕ፤ ከንግድ ማስታወቂያዎች እና ሌሎች የገቢ ምንጮች ከ846 ሚሊዮን ዩሮ በላይ (እስከ 1 ቢሊዬን ዶላር) ገቢ በማግኘት የመጀመርያው ተጨዋች ነው፡፡ ከ423 ሚሊዮን ዩሮ በላይ በሚገመተው  የሃብት መጠኑ በዓለም ላይ እጅግ ሀብታሙ የእግር ኳስ ተጫዋች ሆኗል፡፡
ከ300 በላይ ዋንጫ፤ ሜዳልያ እና ልዩ ልዩ ሽልማቶች
ባለፉት 18 ዓመታት በክለብና በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ያበረከተው አስተዋፅኦ እጅግ የላቀ ሲሆን ከታዳጊነቱ አንስቶ ከ300 በላይ ዋንጫ ፤ ሜዳልያ እና ልዩ ልዩ ሽልማቶችን  አሸንፏል፡፡ በፕሮፌሽናል የተጨዋች ዘመኑ ከ34 በላይ ግዙፍ የዋንጫ ሽልማቶችን የተቀዳጀ ሲሆን ሰባት ጊዜ የአውሮፓ ሊግ ሻምፒዮንነትና 5 ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎች ይገኙበታል፡፡በዓለም እግር ኳስ ከፍተኛ ደረጃ ያላቸውን ሽልማቶች በግሉ ለመሰብሰብም በቅቷል፡፡ የአውሮፓ የወርቅ ኳስ ሽልማትን 5 ጊዜ፤ የፊፋ ኮከብ ተጨዋች ሽልማትን 2 ጊዜ፤ የአውሮፓ የወርቅ ጫማን 4 ጊዜ፤ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ኮከብ ተጨዋችነትን 4 ጊዜ ተቀዳጅቷል፡፡ በፊፋ የፕሮፌሽናሎች ምርጥ 11 ቡድን  14 ጊዜ ከመካከከቱም በላይ የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች የዓመቱ ኮከብ ተጨዋች ሆኖ 4 ጊዜ ተመርጧል፡፡
1100 ጨዋታዎች 781 ጎሎች
ከ1,100  በላይ ጨዋታዎችን ካደረጉ ጥቂት ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች አንዱ ሲሆን 781 ጎሎችን በማስቆጠር የዓለም እግር ኳስ ከፍተኛ አግቢ ለመሆን በቅቷል። ፔሌ 757፤ ሮማርዮ 740 ጎሎችንን አስቆጥርዋል፡፡ በሪያል ማድሪድ ቆይታው የክለቡ የምንግዜም ከፍተኛ ግብ አግቢ ለመሆን የበቃው በ438 ጨዋታዎች 451 ጎሎች በማስቆጠር ሲሆን በማንችስተር ዩናይትድ በ118 ጨዋታዎች 292 ጎሎችን ከማስመዝገቡም በላይ አሁን በሚገኝበት ጁቬንትስ  በ106 ጨዋታዎች 84 ጎሎችን ከመረብ ያዋሃደ ነው፡፡ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ በ176 ጨዋታዎች 134 ጎሎችን በማስመዝገብ ከፍተኛው ግብ አግቢ ሲሆን በሁሉም ዓለም አቀፍ ውድድሮች በብሄራዊ ቡድን ደረጃ 109 ጎሎችን ከመረብ በማሳረፍ ዋናው ተጠቃሽ ሆኗል፡፡
ዓመታዊ ገቢ 102 ሚሊዮን ዩሮ ፤ 30 ሚሊዮን ዩሮው ከስፖንሰርሺፕ
ባለፈው አንድ ዓመት ከ102 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ገቢ በማግኘት የዓመቱን ከፍተኛ ገቢ ካስመዘገቡ ስፖርተኞች በሶስተኛ ደረጃ ላይ ነው። በ2021 ዓመታዊ ገቢው የበለጠው ብቸኛው የእግር ኳስ ተጨዋች ሜሲ ብቻ ነው፡፡ ከገቢው ግማሹን የሚያገኘው ከግዙፎቹ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ታግ ሄውር፤ ሃርብ ላይፍ እና ናይኪ  ጋር ባለው የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ነው፡፡ካስትሮል፤ ሳምሰንግና ኬኤፍሲ ሌሎቹ ስፖንሰሮቹ ናቸው።  በእግር ኳስ ረጅም የስፖንሰርሺፕ ስምምነቶች በማድረግም የሚተወቅ ሲሆን ከአሜሪካው የትጥቅ አምራች ኩባንያ ናይኪ ጋር ያለው የዕድሜ ልክ ስምምነት በዓመት 16.9 ሚሊዮን ዩሮ የሚያገኝበት እና  እስከ 73 ዓመቱ ለኩባንያው በተለያየ መንገድ በመስራት እስከ 1 ቢሊዮን ዩሮ ሊያገኝበት ይችላል፡፡  ከእግር ኳስ ሜዳ ውጭ ከዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር በስፖንሰርሺፕ እና በንግድ ማስታወቂያ በዓመት የሚያገኘው ከ30 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ነው፡፡
ከ500 ሚሊዮን በላይ ተከታይ በማህበራዊ ሚዲያ
ከስፖርቱ ዓለም ተነስቶ በኢንተርኔት ማህበራዊ ሚዲያዎች በሁሉም ዘርፍ ተወዳዳሪ ያጣም ሆኗል፡፡ በፌስቡክ ፣ በኢንስታግራም እና በትዊተር ከ500 ሚሊዮን  በላይ ተከታታዮችን ያገኘ የመጀመሪያው ሰው ሲሆን በሚያገኘው ገቢ የሚወዳደረው አልተገኘም፡፡ በኢንስታግራም 244 ሚሊዮን፤ በፌስቡክ 125 ሚሊዮን በትዊተር 91 ሚሊዮን ተከታዮችን አፍርቷል፡፡ በ1 የኢንስታግራም ፖስት እስከ ከ845 ሺህ ዩሮ በላይ የሚከፈለው ሲሆን ከኢንስታግራም ብቻ  ዓመታዊ ገቢው ከ40 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ነው፡፡
ከእግር ኳሷ ውጭ በኢንቨስትመንት
በልብስ ምርት፤ በሆቴሎች፤ በፀጉር ውበት ጥበቃ፤ በሽቶ እና ሌሎች የውበት እቃዎች አምራችነት ኢንቨስት አድርጓል፡፡  በሆቴል፤ በጂምናዚየም፤ በልብስ እና በኮስሞቲክስ የተሰማራባቸው ኢንቨስትመንቶች በተለይ በየዓመቱ ከፍተኛ ገቢ የሚያገኝባቸው ናቸው፡፡ CR7 በሚል ከሚያመርተው የልብስ ፋሽን በተጨማሪ በፖርቹጋል ውስጥ ፔስታና CR7 የተባሉ ሆቴሎችንም ያንቀሳቅሳል፡፡  በስፔን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚሰራባቸው ጂምናዚዬሞች የፀጉር ንቅለ ተከላ የሚሰራ ክሊኒክም ከፍቷል ፡፡

19 ውድ መኪናዎችና ሁለት የግል ጀቶች
በቅንጡ አኗኗሩ የሚታወቅ ሲሆን እጅግ ውድ ዋጋ ያላቸው 19 መኪናዎችን የራሱ ንብረት አድርጓል፡፡ አዘውትሮ የሚነዳት 269 ሺ ዩሮ የምታወጣውን ላምበርግኒ አቬንታደር መኪናውን ቢሆንም  ከ845ሺ ዩሮ በላይ ዋጋ ያላት ቡጋቲ ቬይሮን ፤  ከ1 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ያጣባቸው ሁለት ፌራሪዎች ፤ ቤንትሊ ጄት ስፒድ  እንዲሁም አስተን ማርቲን ከስብስቦቹ ይጠቀሳሉ፡፡ ሁለት የግል ጀቶች አሉት የመጀመርያው Gulfstream G650 የተባለ በ28 ሚሊዮን ዩሮ ሲሆን stream G200 በ20 ሚሊዮን ዩሮ የገዛቸው ናቸው ፡፡


Read 204 times