Print this page
Saturday, 03 July 2021 20:28

ከአለማቀፉ የኮሮና ክትባት 40 በመቶ የተሰጠው በቻይና ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች መሰጠት ከጀመሩበት ያለፈው ታህሳስ ወር አንስቶ እስከ ሳምንቱ መጀመሪያ ድረስ በመላው አለም የተሰጡ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች ቁጥር ከ3 ቢሊዮን ማለፉንና ከአጠቃላይ ክትባቶች ውስጥ 40 በመቶ ያህሉ ወይም 1.2 ቢሊዮን ክትባቶች የተጠሱት በቻይና ውስጥ መሆኑን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
329 ሚሊዮን ክትባቶችን ለዜጎች መስጠት የቻለችዋ ህንድ ብዛት ያላቸው የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን በመስጠት ከአለማችን አገራት የሁለተኛነትን ደረጃ ስትይዝ፣ አሜሪካ በ324 ሚሊዮን ክትባቶች በሶስተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝም ዘገባው አመልክቷል፡፡ በአለማችን የኮሮና ክትባቶች በይፋ በዘመቻ መልክ መሰጠት በጀመሩበት 20 ሳምንታት ጊዜ ውስጥ አንድ ቢሊዮን ክትባቶች መሰጠታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ይህ ቁጥር በቀጣዮቹ 6 ሳምንታት ሁለት ቢሊዮን፣ በ3 ሳምንታት ደግሞ 3 ቢሊዮን መድረሱን አመልክቷል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ዜና ደግሞ፣ የተለያዩ አይነት የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ቀላቅሎ መስጠት የበለጠ ውጤታማ መሆኑን በብሪታኒያ የተካሄደ አንድ ጥናት ማረጋገጡን ቢቢሲ የዘገበ ሲሆን፣ የፋይዘርና የአስትራዜኒካ ክትባቶችን ቀላቅለው የሰጡት ተመራማሪዎች ክትባቶቹ የበለጠ ውጤታማና የበሽታ የመከላከል አቅምን የሚያዳብሩ መሆናቸውን ለማረጋገጥ መቻላቸውንም አመልክቷል፡፡
ስፔንና ጀርመንን ጨምሮ አንዳንድ የአለማችን አገራት በተመሳሳይ መልኩ የተለያዩ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ቀላቅለው መጠቀም መጀመራቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ያም ሆኖ ግን መሰል የተቀላቀሉ ክትባቶች በአንዳንድ ሰዎች ላይ አልፎ አልፎ የደም መርጋት ችግር ማስከተላቸውንም አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2020 ብቻ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ 2.4 ትሪሊዮን ዶላር ያጣው የአለማችን ቱሪዝም፤ ይህ ቁጥር በዘንድሮው አመት መጨረሻ ከ4 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተመድ አስታውቋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቱሪዝም ድርጅትና የንግድና ልማት ማዕከል በጋራ ባወጡት መግለጫ እንዳሉት፣ ምንም እንኳን ዘርፉ ባደጉት አገራት ሊያገግም እንደሚችል ቢጠበቅም በድሃ አገራት ግን ክፉኛ እንደሚጎዳ ይጠበቃል፡፡


Read 11150 times
Administrator

Latest from Administrator