Saturday, 03 July 2021 20:36

ወላጆች ልጆቻቸው ከመቀሌና አክሱም ዩኒቨርስቲዎች እንዲወጡላቸው እየተማፀኑ ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 “በስልክ እንኳ ድምፃቸውን ብንሰማ እፎይ እንላለን” “መንግስት ስለ ልጆቻችን አንድ መፍትሔ ይስጠን” “በመንግስት እምነት ጥለን ነው     ልጆቻችንን የሠጠነው”


             መንግስት ሰሞኑን ያወጀውን የተናጠል ተኩስ አቁም ተከትሎ፣ የመከላከያ ሰራዊት መቀሌን ለቅቆ መውጣቱ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ከተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች ልጆቻቸውን ወደ አክሱምና መቀሌ ዩኒቨርስቲ የላኩ ወላጆችና ቤተሰቦቻቸው ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ገብተዋል፡፡ እነዚህ ወላጆች በክልሉ ስልክና መብራት መቋረጡን ተከትሎ ስለ ልጆቻቸው ደህንነት ማወቅ እንዳልቻሉ  በሃዘን ይገልፃሉ፡፡ ባለፈው ዓርብ ተሲያት  ላይ ወደ አራት ኪሎ ቤተ መንግስት ተሰብስበው የመጡትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ከልጆቻቸው ጋር የሚገናኙበትን ወይም ልጆቹ ያሉበትን ወቅታዊ ሁኔታ የሚያውቁበትን መንገድ እንዲፈልጉላቸው ለመማፀን ነበር፡፡  የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ለአቤቱታ ከመጡት ወላጆች ጥቂቶቹን  አነጋግራቸዋለች፡፡


                    “መንግስትን አምነን ነው የላክናቸው፤ ከጭንቀታቸን ይገላግለን”
                             ወ/ሮ መዓዛ አስፋው (ወላጅ)


            ልጄ ሳምሪ አለም ትባላለች፡፡ መቀሌ ዩኒቨርስቲ ኩይሃ ካምፓስ የአራተኛ ዓመት የኢንጅነሪንግ ተማሪ ናት፡፡ በኮቪድ ምክንያት ትምህርት ተቋርጦ፣ እዚሁ ከእኛ ጋር ነበረች፡፡ ነገር ግን የካቲት መጀመሪያ ላይ ትምህርት ተጀምሯል በሚል ዩንቨርስቲው ጥሪ ሲያደርግ ላክናት፡፡
“የባለፈውን ዓመት ሴሚስተርና፣ የአራተኛ ዓመትን የመጀመሪያ ሴሚስተር በጥሩ ሁኔታ እየተማርን ነው፤ በ3 ወር ያልቃል” ብላኝ ነበር፡፡ ሁሌም በስልክ ስንገናኝ “በፌደራል እየተጠበቅን ያለ ስጋት ነው የምንማረው አትስጉ ነበር የምትለን፡፡ አሁን ከዚህ ስጋት በላይ ሌላ አስከፊ ስጋት ነው የገጠመን፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ በስልክ ሰኞ ሰኔ 21 ቀን ረፋድ 4 ሰዓት ነው ያገኘኋት፡፡ ህወሃት ከተማውን ተቆጣጥሮታል ተብሎ ህዝቡ ደስታውን እየገለፀ መሆኑን ከመቀሌ ከተማ ልጆች ደውለው ነገሩን አለችኝ፡፡ ምክንያቱም ኩይሃ ከመቀሌ ትንሽ ወጣ ያለ ነው፡፡
“እናም ስልክም ኔትዎርክም ቢቋረጥ እንዳትጨነቁ” አለችኝ፡፡ ከዚያ በኋላ እኛም እንደ ማንኛውም ሰው መንግስት የተኩስ አቁም ስምምነት አድርጓል፤ ወታደሩን እያስወጣ ነው የሚል ነገር ሰማን፡፡ በጣም ግራ ተጋባን፤ ምክንያቱም ወታደር ከወጣ፣ ልጆቻችንን ማነው የሚጠብቃቸው? የሚለው ጉዳይ  የበለጠ ስጋት ውስጥ ከተተን፡፡ ይኸው ከሰኞ ጀምሮ ሰማይ ምድሩ እንደዞረብን በጭንቀት አለን፡፡
ሀሙስና አርብ ይሄው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማነጋገርና መፍትሔ ለመጠየቅ ቤተ መንግስት ደጅ እየጠናን ነበር፡፡ ተወካይም መርጠን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅ/ቤት ልከን ነበር፡፡ “ትንሽ ጠብቁ ታገሱ፤ ልጆቹ እንዲያውም በጣም ሰላም ናቸው፤ ፈተና እየተፈተኑ ነው፤ እርግጠኛ ነን”፡፡ ብለውናል፡፡ “ተረጋጉ” አሉን- የወከልናቸው ሰዎች፡፡ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ የሚሰጡበትን መንገድ አመቻችተን እንነግራችኃለን” “ተረጋጉ አሉን” ብለው ነው የወከልናቸው ሰዎች የተመለሱት፡፡ እኛ እንግዲህ መንግስትን አምነን ልጆቻችንን ልከናል፡፡ እነዚህ ልጆች ተምረው ተመርቀው ነገ አገራቸውን የሚረከቡ፣ ቤተሰባቸውንና ወገናቸውን የሚያግዙ ናቸው፡፡ ከ19-21 ዓመት የእድሜ ክልል ያሉ ገና ወጣት ልጆች ናቸው፡፡ እኛ ፖለቲካውን አናውቅም፤ የተደረገውን ስምምነትም አናውቅም፡፡
ስለዚህ መንግስትም ሆነ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተባብረው አንድ ነገር ያድርጉ፡፡ ምክንያቱም መንግስት ራሱ የመደባቸው ተማሪዎች እዛ እያሉ ወታደሮቹን  ሲያስወጣ፣ ለእነሱ ምን እንዳሰበላቸው እንቆቅልሽ ሆኖብናል፡፡ ይሄው አምስት ቀን እያለቀስን፣ ያለ እንቅልፍ ስላለን አንድ መፍትሔ አንዲሰጠን በእግዚአብሔር ስም እንማጸናለን፡፡ መንግስት በምርጫው አሳብቦ ወደ ወላጆቻቸው ሊልካቸው ይችል ነበር፤ እኛም ግራ ገብቶናል፡፡ አንድ መፍትሄ ከመንግስት እንጠብቃለን፡፡ ሌላው ቢቀር በስልክ አንኳን ድምፃቸውን ብንሰማ  እፎይ እንላለን ስለ እግዚአብሔር ብሎ መንግስት ይድረስልን፡፡
______________________________                “ይሄ ፖለቲካዊ ውሳኔ ሲወሰን ትምህርት ሚኒስቴር ልጆቼን አውጡልኝ ማለት ነበረበት”
                             አቶ አበበ አወቀ (አያት)


              የተማሪ በመንፈስ ዳንኤል አያት ነኝ፡፡ መቀሌ ያለው  የልጅ ልጄ ነው፡፡ ነገር ግን እኔው ዘንድ ነው ያደገው፤ ያስተማርኩትም እኔ ነኝ፡፡ መቀሌ ዩኒቨርስቲ የኮምፒዩተር ሳይንስ የ3ኛ ዓመት ተማሪ ነው፡፡ ለፋሲካ መጥቶ እኛው ጋር ነበር፡፡  እኔም ታምሜ ስለነበር እኔን ለመጠየቅ ፋሲካንም አብሮን ለመዋል መጣ፤ ደስ ብሎን በዓልን አክብረን ወደ ትምህርቱ ተመለሰ፡፡ “በሰላም ያገናኘን” ብሎ ተሰነባብቶን ሄደ፡፡
በሰላም ትምህርቱን ቀጥሎ ነበር፡፡ ሁልጊዜ  እሁድ እሁድ በስልክ እንገናኛለንና ባለፈው እሁድ ሰኔ 20 ቀን ደውልኩለት፡፡ “አባዬ አንተ እንዴት ነህ? እቴቴስ እንዴት ናት? እኔ ምንም ችግር የለም፤ አታስቡ ደህና ነኝ፤ አንተስ ተሻለህ ወይ? አለኝ “አዎ ደህና ነኝ” ተባባልን፡፡ በሰላም እንደ ማንኛውም ጊዜ ተሰነባበትን፡፡
ሰኞ ማታ ቁጭ ባልኩበት ደወለ፡፡ እኔ ስኳርና ደም ግፊት ስላለብኝ፣ ብነግረው ደንግጦ አንድ ነገር ይሆናል ብሎ ፈራና ካሱ የምትባል እህቱ አለች፤ “ካሱን አቅርብልኝ” አለኝ፡፡ እሷን አገናኘሁት፤ ለእሷ “በአካባቢያችን ጥይት እንደጉድ እየፈላ ነው፤ ችግር ሳይፈጠር አይቀርም፤ አባዬ እንዳይሰማ እናቴም እንዳትሰማ” ብሎ ተናገረ፡፡ ከዚያ በኋላ እኔም ሰማሁ፡፡ ስልክ ብንደውልም ስልክ አይሰራም፤ ይሔው እስካሁን በለቅሶና በጭንቀት አለን፡፡
አሁን የምንለው መንግስት ሆደ ሰፊ ነው፤ ብዙ ነገር ማድረግ ይችላል፤ አንድ መላ ይዘይድልን፡፡ እኔ የገረመኝ መንግስት ይህን ፖለቲካዊ ውሳኔ ሲወስን፣  ትምህርት ሚኒስቴር ያሰማራቸውን ተማሪዎች ያውቃል።
መጀመሪያ ልጆቼን አውጡልኝ ብሎ ሀላፊነቱን እንዴት አልተወጣም? የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ይሄ አልሆነም፤ ምን ይደረጋል? አሁን እኛ የምንፈልገው ልጆቻችንን በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ፤ ከታማኝ ወገን እንድሰማ ነው፡፡
ወይ  ይመጡላችኋል ይበሉን፡፡ በቀይ መስቀል በኩልም ይሁን በራሱ በመንግስት ችሎታም ቢሆን አንድ መፍትሔ እንዲሰጠን እንማጸናለን፡፡ ይህ በሆነበትና ቤተሰብ እየተላቀሰ ባለበት፣ መንግስትም ሆነ ትምህርት ሚኒስቴር ዝም ማለቱ ይበልጥ አሳስቦናል፡፡
ቀይ መስቀል ሄደን አቤት ስንል “መንግስት ሽፋን ከሰጠን ልጆቹን እናመጣለን፤ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ከባድ ነው” ብለውናል፡፡ መቀሌም ሆነ አክሱም ያሉት የቀይ መስቀል ቢሮዎች ስራ ላይ እንዳልሆኑ ነግረውናል። በዚህ የተነሳ ቤተሰብ እየተላቀሰ ስራም መስራት አልቻልንም፣ ድርጅታችንን ዘግተን ነው ያለነው፡፡ እባካችሁ እናንተም ይህንን አስተላልፉልን፡፡
ወክለን የላክናቸው ወላጆች “እስከ ማክሰኞ ታገሱ፤ መንግስት መግለጫ  ሊያወጣ ይችላል” ይሉናል። እንዴት እንታገስ? በምን አንጀታችን? እስኪ እናንተው ፍረዱን፡፡ እኛ በመንግስት እምነት ጥለን ነው ልጅ የሰጠነው፡፡ አሁንም ዋስትናችን መንግስት ነው፤ አንድ መፍትሔ በአፋጣኝ ይስጠን፡፡ ሌላ የምለው የለኝም፡፡
___________________________
                     “ተይ ይቅርብሽ አትሂጂ እያልኳት ነው የሄደችው”
                            (ወ/ሮ ብርቱካን አሸብር፤ ወላጅ)


            የተማሪ ቤዛ አሰፋ ወላጅ እናት ነኝ። ልጄ የአክሱም ዩኒቨርስቲ የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ተማሪና የዘንድሮ ተመራቂ ናት። በዚህ ዓመት ተመራቂ ስለሆነች ቮልቮ ካምፓኒ አፓረንት ወጥታ ነበር፡፡ አፓረንት እንደወጣች ኮሮና ገባ ተባለና አቁመውት ነበር፡፡
እንግዲህ ኮሮናም  ዓመት ሞላው፤ ሁሉም ወደ ነበረበት እየተመለሰ ሲሄድ ተመራቂ ስለሆኑ የግድ መግባት አለባቸው ተባለ፡፡ መጀመሪያ መንገድ ተዘግቷል ተብሎ አስቀርቻት ነበር፡፡
በድጋሚ “አትሂጂ ሁሉም ይረጋጋ” አልኳት “አይ ይሄንን ሁሉ ዓመት ለፍቼ ልፋቴ መና መቅረት የለበትም መሄድ አለብኝ” አለችና የካቲት 21 በአውሮፕላን እስከ መቀሌ ላክናት ከዚያም አክሱም በሰላም ገባች፡፡ ትምህርት ጀመረች በስልክ እንገናኝ  ነበር፡፡
በመሀል ደግሞ ኔትወርክ ተቋረጠ። ኔትወርኩ ከ15 ቀን በላይ ተቋርጦ ከዩኒቨርስቲው እየወጡና ሳንቲም እየከፈሉ የግል ቦታ እየሄዱ ይደውሉ ነበር፡፡ ስትደውል ነገሩ እንዴት ነው ስንል እኛ በፀጥታ ሀይሎች እየተጠበቅን ነው የምንማረው፤ ምንም ስጋት አይግባችሁ” እያለችን፤ በዚህ ተስፋ አድርገን ቁጭ ብለን ነበር፡፡
ለመጨረሻ ጊዜ  ሰኔ 14 የምርጫው ቀን ተደዋወልን፡፡ ከዚያ በኋላ ስልኳ ተቋርጧል። ተመልከቺ ገና የ22 ዓመት ልጅ ናት፤ የዘንድሮ ተመራቂ ነበረች፡፡ መስከረም 22 እመረቃለሁ ብላኝ ነበር፡፡
እኛ መንግስትን የምንጠይቀውና የመጀመሪያ ፍላጎታችን የምናደርገው፤ ልጆቻችንን በእጃችን እንዲያስገባል ነው። ይሄ ለጊዜው የማይቻል ከሆነ፣ በስልክም ሆነ ብቻ ባለው አማራጭ  የመገናኛ ዘዴ፣ የልጆቻችንን ድምጽ ያሰማን፡፡ ምክንያቱም “ፌደራል ይጠብቀን ነበር” ብለዋል።
ፌደራልና መከላከያ ከዚያ ከወጣ ልጆቻችንን የተረከበው አካል ማን ነው? ትላንትና ጠዋት (ሀሙስ) የወጣን ማታ ነው የገባነው፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር ሄድን፤ ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርም ሄደን እዛ ገባን፡፡
16 ሰው ተመርጦ ከገቡት ውስጥ እኔም አንዷ ነበርኩኝ ገባን፤ ልጆቻችሁ በደህና ሁኔታ ላይ ነው ያሉት፤ ይመጣሉ  አታስቡ፤ እኛም ጉዳዩ ላይ እየሰራን ነው” አሉን፡፡ ከዚያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ እንሂድ ተባብለን ሄድን፡፡ የተወሰኑት ገቡ፣ ለዛሬ ተቀጥረን (አርብ) መጣን “ልጆቻችሁ ደህና ናቸው፤ አታስቡ ድምፃቸውን እናሰማችኋለን” አሉን።
ይሄው ፈጣሪን ተስፋ አድርገን እያለቀስን አለን፡፡ እኔ አሁን መንግስት ልጄን ቢቻል በአካል ያስረክበኝ፤ ምርቃቱም ይቅርብኝ። ምርቃቱም እሷ ስትኖር ነው፡፡ ካልሆነ ግን በስልክም ቢሆን ድምጽ እንስማ። ይሄ ሁሉ በመቶ የሚቆጠር ወላጅ ደጅ የወጣው፣ የልጆቻችን ድምፅ ስለጠፋብን ነው፡፡ ደህንነታቸውን ካወቅን ድምፃቸውን ከሰማን፣ የግድ አምጡ ብለን መንግስትን አናስጨንቅም፡፡ ብቻ ያሉበትን ሁኔታ እንወቅ፡፡ ሌላም ጊዜ እኮ እዛው ነው ያሉት። ስለዚህ ወይ ድምፃቸውን ያሰሙን፤ ካልቻሉም በአካል ያምጡልን  ስንል እንጠይቃለን፡፡_____________________________
                          “አንድ ልጄ ናት ጎዳና ላይ እያደርኩ ነው እዚህ ያደረስኳት”
                                  ወ/ሮ ሙሉ ታሪኩ፣ (ወላጅ እናት)


            ልጄ እየሩሳሌም ታደሰ አንድ ብቻ ናት፡፡ ከእርሷ በላይም በታችም ሌላ ልጅ የለኝም፡፡ የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ ናት፡፡ ነገ ሰው እሆናለሁ ብላ ጎን ለጎን የርቀት ትምህርት ትማራለች የካቲት 20 ነው ከዚህ ተነስታ አክሱም የሄደችው፤ በስልክ እንገናኝ ነበር። በመሃል ኔትወርክ ተቋርጦባቸው እንኳን ከየትም ብላ በስልክ ድምጿን ታሰማኝ ነበር።
የ22 ዓመት ልጅ ናት፡፡ ከልጅነት  እስከ አሁን ጎዳና ላይ ነበርን ቤት የለንም። አሁንም ቴሌ ገራዥ አካባቢ የማይሆን መጠለያ ሰጥተውኝ እዛ ነው ያለሁት፡፡ ተይኝ የኔ ችግር ተነግሮ አያልቅም፡፡ ቴሌ ጋራዥ 32 ቀበሌ ከጀርባ ሽንት በሚወርድበት ቦታ ላይ  ሆኜ እያስተማርኳት ነው ከ8 ወደ 9ኛ ክፍል ያለፈችው፡፡  ከዚያም በኋላ እኔም እሷም ተስፋ ባለመቁረጥ በችግር አልፈን ነው ዩኒቨርስቲ የደረሰችው፡፡
ከአሁን አሁን ትምህርቷን ጨርሳ ሰው ልትሆንልኝ ነው ብዬ አይን አይኗን ሳይ ዛሬ ጭራሽ ድምጿም እራቀኝ፤ ዙሪያው ገደል ሆኖብኛል (ለቅሶ….) በስንት መከራ መጠለያ አገኘሁና ገባሁ። ለማጥናት እንኳን እየረበሿት ከጠዋት እስከ ማታ ነው ስታለቅስ የምትውለው።
“ማጥናት አልቻልኩም እማዬ፤ ወዴት ልሂድ” ስትል የአካባቢውን የህግ ሰዎች ባማክርም እንደ ሰው ቆጥረው አይሰሙኝም። ይሄው ይሄ ሁሉ ታልፎ ነው ዩኒቨርስቲ የሄደችው። ይሄን የአካባቢው ሰው በሙሉ ያውቃል። የሚገርምሽ ዩኒቨርስቲ ሄዳ ሰው 20 እና 25 ብር ሲልክላት እንኳን መልሳ ለእኔ ትልክልኛለች፡፡
እኔ ኪንግስ ሆቴል ነበር የምሰራው። ከዚያ የማገኘውን ትንሽ ብር ስቀበል የሆነ ነገር ሳደርግላት እንኳ “እማ በርቺ ነገ እኔ ሰው እሆናለሁ፤ ላንቺ ቀርቶ ለሀገር እተርፋለሁ አይዞሽ” ትለኝ ነበር፡፡ አክሱም ዩኒቨርስቲ ሲደርሳት  በምናባቴ እልካታለሁ፤ እዚሁ የርቀት ትምህርቷን ትቀጥል እንጂ ብዬ ስወስን፣ ጋዜጠኛ ክብሬ ተስፋዬ ሰምታ፣ “በየወሩ 500 ብር እረዳታለሁ” አለች፡፡
በእርሷ እርዳታ ነው አክሱም ዩኚቨርስቲ አትቀርም ብላ የላከቻት፡፡ በዚሁ እሷን አመስግኚልኝ፡፡ ባለፈው ሰኔ 20 ቀን ማታ ደውላ “እስኪ ከመጠሊያ ወጣ ብለሽ አነጋግሪኝ” ብላ ደወለች፡፡ እኔ ግን ጎረቤቶች ብቸኛነቴን ስለማያውቁና ስለሚደበድቡኝ ፈርቼ ወጥቼም አላናገርኳትም፡፡ ከዚህ ቀደምም ደብደበውኛል፡፡
በነጋታው ሰኞ ለወንድሜ ልጅ ደውላ “ኔት ወርክ ስለተቋረጠ አትጨነቂ ለመድሃኒዓለም ለገብርዔል ፀልይ አይዞሽ” ብላ  መልዕክት ተወችልኝ። ድምጿን ሳልሰማ ይሔው ስንት ቀኔ! አንድ ልጄ ናት፤ አይኔ ማለት ናትና እግዚአብሔር ይድረስልኝ፡፡
እኔ ልጄን መንግስት ያምጣልኝ፡፡ የኔን ልጅ ብቻ አይደለም፤ ሁሉንም ልጆች ይምጡልን፡፡ እዛ ያሉት ሌሎችምኮ እህት ውንድሞቿ ናቸው፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ዘዴ ያውቃል፤ አንድ መፍትሔ ያምጣልን።
Read 3096 times