Monday, 05 July 2021 20:13

የኢኮኖሚ መዋዠቅ፤ የዋጋ መናር መውረድ?

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  "ለህግ ተገዢ ያሆኑ ፈርጣማ ክንድ ያላቸው ነጋዴዎች ከተበራከቱ አደገኛ ነው"

         የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስ ከሀሮማያ ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል፡፡ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን  በማስተርስ ኦፍ ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን፣ ያገኙ ሲሆኑ በኢንተርናሽናል ቢዝነስ ዘርፍም ስፔሻላይዝ እንዳደረጉ ይገልፃሉ፡፡ የዛሬው እንግዳችን የኢኮኖሚ ባለሙያው  አቶ ሀሮን ጋንታ፤ በአሁኑ ወቅት በጠቅላላ ቢዝነሶች ላይ በማማከር፣ በአዋጭነት ጥናትና በቢዝነስ ፕላን ስራ ላይ ተሰማርተው እየሰሩ ሲሆን የአገራችንን የኢኮኖሚ ሁኔታ፣ የዋጋ ግሽበትን፣ የብር የመግዛት አቅም መውደቅን እንዲሁም፣ ለችግሩ መንስኤ ያሏቸውን ፖሊሲዎችና የመፍትሔ አቅጣጫዎች “የኢኮኖሚ መዋዠቅና የስትራቴጂ አቅጣጫዎች በኢትዮጵያ” በሚል ባወጡት በጥናትና ምርምር ላይ ያተኮረ መፅሐፍ ለንባብ አብቅተዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ሀሮን ጋንታ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡ እነሆ፡-

                በአሁኑ ሰዓት የሶስተኛ ዲግሪ (PHD) ትምህርት መጀመርዎን ሰምቻለሁ፡፡ ምንድን ነው የሚያጠኑት?
እውነት ነው ሶስተኛ ዲግሪዬን መማር ጀምሬያለሁ፤ እያጠናሁ ያለሁት “ዶክተር ኦፍ ቢዝነስ ኢኮኖሚክስ” ነው፡፡ ያው ከ1ኛና ከሁለተኛ ዲግሪዎቼ ጋር ግንኙነት ያለው ትምህርት ነው፡፡
በቅርቡ “የኢኮኖሚ መዋዠቅና ስትራቴጂ አቅጣጫዎች በኢትዮጵያ” የተሰኘ መፅሐፍ ለንባብ አብቅተዋልና፡፡ እስኪ ስለመጽሐፉ ጠቅለል አድርገው ቢያብራሩልኝ?
አመሰግናሁ፡፡ እውነት ለመናገር እኔ ገና የሀይስኩል ተማሪ ሆኜ እነዚህን በመፅሐፌ ያካተትኳቸውን ዋና ዋና ነገሮች አጤናቸው ነበር፡፡ ምክንያቱም ተማሪ ሆኜ የሸቀጣሸቀጥ ምርቶችን እራሴ እየገዛሁ ነበር የምጠይቀው
እንዴት ማለት?
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ  በሚሽን ት/ቤት ውስጥ ነበርኩና ደሞዝ እየተሰጠኝ ራሴ እየገዛሁ ነው የምጠቀመው፡፡ ከ1992 እስከ 1995 ዓ.ም ድረስ የሚያስተምረኝ ድርጅት በወር 200 ብር ይከፍለኝ ነበር፡፡ በዛ ጊዜ በ200 ብር ምን ምን ገዝቼ ምን ያህል ብር ይተርፈኝ እንደነበር አስታውሳለሁ። ለዚህ መፅሐፍ መታተም መነሻዬም ይሄ ጉዳይ  ይመስለኛል፡፡ “በዛን ጊዜ የነበረው የብር የመግዛት አቅም ከአሁኑ ጋር ሲነፃፀር ምን ይመስላል? አሁን ላለው የብር መውደቅ፣ የኢኮኖሚ መዋዠቅ መንስኤው ምንድን ነው? ምንስ መደረግ አለበት?” በሚል ከ1990-2012 ዓ.ም ያለውን የ22 ዓመት የኢኮኖሚ ሁኔታ ነው ያጠናሁት። በዚያን ጊዜ በወር የሚከፈለኝ 200 ብር የቤት ኪራይ፣ ምግብ፣ አልባሳትና ሌሎች ወጪዎቼን ችሎ 20 እና 30 ብር ይተርፈኝ ነበር፡፡ ተመልከቺ!...
በዚያ ጊዜ ጥብስ ሲያምረኝ በ5 ብር በልቼ እመለስ ነበር፡፡ ጥራጥሬ ምስር በይው አተር ወይም በኪሎ በ2 ብር ከሃምሳና ከ3 ብር አይልጥም ነበር፡፡ በአጠቃላይ እስከ 1997 ያለው የብር የመግዛት አቅም በጣም ጠንካራ ነበር፡፡ በተለይ ከ1997 ምርጫ በኋላ ግን የሸቀጦች ዋጋ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ተደረገ፡፡ እኔ እስከማውቀው ከ1990-1997 ዓ.ም አንድ ኩንታል ነጭ ጤፍ ከ300-350 ብር ድረስ ይሸጥ ነበር፡፡ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ አንድ ኩንታል ጤፍ በአንድ ጊዜ ወደ 700 እና 800ብ አሻቀበ፡፡ በዚያን ጊዜ ትዝ የሚለኝ ነገር ባንኮች ለጥበቃ የሚቀጥሯቸው ሰራተኞች፣ የፖሊስ ሰራዊት አባላት ደሞዝ 400 እና 450 ብር ነበር፡፡ ከ1997 ምርጫ በፊት ማለቴ ነው፡፡ የሚገርምሽ በዛ ጊዜ ፖሊስ ሆኖ ለመቀጠር የማይጓጓ አልነበረም። ለምን ካልሺኝ… የ450 ብር ደሞዝተኛ መሆን ትልቅ ነገር ነበር፡፡ ተመልከች ቤት በ50 ብር ይከራያል፣ ለተለያዩ ወጪዎች 200 ብር ቢያወጣ፣ 200 እና 250 ብር እጁ ላይ ይተርፈዋል፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየው በወቅቱ የኢኮኖሚ መዋዠቅ አልነበረም፣ የሸቀጦች ዋጋ የተረጋጋና  ሚዛኑን የጠበቀ ነበር፡፡
ከ97 ምርጫ በኋላ ኢኮኖሚው የዋዠቀበት፣ የብር የመግዛት አቅም የወደቀበትና በሸቀጦች ላይ የዋጋ ማሻቀብ የታየበት ምክንያት ምንድን ነው?
በጥናቱ ውስጥ ብዙ ነገሮች ተገኝተዋል። አንዱ ምክንያት ጋጠ-ወጥ የግብይት ሥርዓት መፈጠሩ ነው፡፡ ይሄ ማለት ጋጠ-ወጥ ነጋዴዎች ገበያው ላይ ተፈጠሩ ማለት ነው፡፡ ከ1997 ዓ.ም በፊት ጋጠ-ወጥ ግብይት አልነበረም፡፡ አንዳንዴ በምርት እጥረት ጤፍን ጨምሮ አንዳንድ ሸቀጣሸቀጦች ላይ ዋጋ ቢጨምር እንኳን የተሻለ ምርት ሲመረት ዋጋው መልሶ ይወርድ ነበር። አሁን የትኛውም እቃ ዋጋው ከተሰቀለ ተሰቀለ ነው፡፡ ይህንን ያመጣው የተዝረከረከ የመንግስት ንግድ አሰራርና ቁጥጥር መላላት ነው፡፡ በመፅሐፉ ከገፅ 44 ጀምሮ ከ1990-2012 የተደረገው ጥናት በሶስት ሰሌዳ የተከፈለ ነው፡፡ ከ1990 - 1997፣ ከ1998-2003 ዓ.ም እና ከ2004-2012 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት የሸቀጣሸቀጥ ዋጋ እንዴት እንደነበር፣ እንዴት እየጨመረ እንደሄደ… በቤት ኪራይ፣ በምግብ፣ በመጠጥ፣ በአልባሳትና መሰረታዊ በሚባሉ ፍጆታዎች ላይ ከፍተኛ ለውጥ መጥቷል፡፡ ደግሞም ለዚህ ጉዳይ ከጥናትም ባሻገር እኔ የአይን ምስክር ነኝ፡፡ በዚህ ሕይወት ውስጥ ኖሬ እዚህ ደርሻለሁ፡፡
እስኪ በምግብ ዋጋ ላይ የመጣውን ልዩነት በአሃዝ ያስረዱኝ…?
በጣም ጥሩ! ከ1990-97 ዓ.ም በነበረው ጊዜ በአንድ መለስተኛ ወይም መካከለኛ ምግብ ቤት ጥብስ አምሮሽ ልመገብ ብትይ ከ5-8 ብር ነበር፡፡ አሁን ጥብስ ከ120-130 ብር ነው- በመለስተኛና መካከለኛ ምግብ ቤት ማለት ነው፡፡ በዛን ጊዜ ለምሳሌ 3 በ4 የሆነ አንድ ክፍል ቤት ከ35-70 ብር ይከራይ ነበር፡፡ ከከተማ ወጣ ያሉ ለምሳሌ ካራ ፣ ኮተቤ፣ ፈረንሳይ ያሉ አካባቢዎች ከከተማ ወጣ ያሉ ናቸው ይባሉ ነበር፡፡ አሁን እንኳን መሃል እየሆኑ ነው፡፡ ቦሌ፣ ፒያሳና መሃል የሚባሉ አካባቢዎች 3 በ4 የሆነ አንድ ክፍል ቤት-ከ40-120 ብር ይከራይ ነበር፡፡ ይህ ዓይነቱ ቤት በአሁን ሰዓት የትም… ይሁን የትም ስንት ብር ይከራያል ነው ጥያቄው? የዛን ጊዜ የነበረው የገንዘብ የመግዛት አቅም ጠንካራ ነበር፡፡
ከ1998-2003 ዓ.ም ደግሞ ያለውን ስንመለከት፣ የአንድ ጥብስ ዋጋ ከ5-8 ብር የነበረው ከ12 ብር እስከ 35 ብር መሸጥ ጀመረ፡፡ የአትክልት የጥራጥሬና ፍራፍሬ ዋጋ በእጅጉ ማሻቀብ ጀመረ፡፡ ከ1998-2003 ዓ.ም ጤፍ ከ1 ሺህ ብር አላለፈም ነበር፡፡ አምና በ2012 ከ4 ሺህ በላይ ነው፡፡ አሁን በምንነጋገርበት ጊዜ የ1 ኩንታል ጤፍ ዋጋ ከ5 ሺህ ብር አልፏል፡፡ 1 ክፍል ቤት 4 ሺህ ብር ድረስ እየተከራየ ነው፡፡
እውነት ነው አሁን ላይ 5 ሊትር ዘይት 600 ብር 1 ሊትር ዘይት 150 ብር ነው። የበርካታ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችም አሻቅቧል እርሶ በመፅሐፉ ለዚህ ሁሉ መንስኤው የተዝረከረከ የንግድ ስርዓት፣ ልብ ያልተባሉና ያልተጤኑ በርካታ ፖሊሲዎች አሉ ብለዋል፡፡ እስኪ በተለይ ያልተጤኑ ያሏቸውን ፖሊሲዎች ይንገሩኝ?
በኢህአዴግ መራሹ መንግስት በደንብ ያልተጤኑ ዘጠኝ ፖሊሲዎች በዚህ መፅሀፍ ተዳስሰዋል፡፡ እነዚህም ፖሊሲዎች ለዚህ ሁሉ የኢኮኖሚ መዋዠቅ፣ ለተበላሸ የንግድ ስርዓት መፈጠር፣ ለብር የመግዛት አቅም መውደቅ፣ ለሸቀጦች ዋጋ መኖርና ለኑሮ ውድነት… ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል የሚል ድምዳሜም አለ፡፡
እስኪ ፖሊሲዎቹን እንያቸው?
አንዱ የትምህርት ፖሊሲ ነው፡፡  ዚህ ላይ ፖለቲካዊ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ከህግም አንፃር በመጽሐፉ ትንተና ሰርቻለሁ። በኢትዮጵያ የ10ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና መስጠት ተጀመረው ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡ እርግጥ ከዘንድሮው የትምህርት ዓመት ጀምሮ ወደ ቀድሞው 12ኛ ክፍል ተመልሷል-የብሔራዊ መልቀቂያ ፈተናው። በመጽሐፉም ብልፅግና ይህንን በማድረጉ አድናቆቴንና ምስጋናዬን ገልጫለሁ፡፡ ይሄ ከ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የመስጠት ተሞክሮ የመጣው ከአውሮፓ ነው፡፡ በተለይ ከእንግሊዝ፡፡ እነዚህ አገራት በቴክኖሎጂ በመሰረተ ልማት፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካ ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ የደረሱ ናቸው፡፡
የእኛ አገር ባለችበት ተጨባጭ ሁኔታና ደረጃ በአማካይ ዕድሜያቸው 16 ሲደርስ ነው የ10ኛና ክፍል ብሔራዊ ፈተና የሚወስዱት፣ ውጤት ከመጣላቸው ወደ መሰናዶ ይገባሉ፡፡ ካልተሳካ ደግሞ ወደ ቴክኒክና ሞያ ማሰልጠኛ ት/ቤቶች ይሄዳሉ። በዚህን ጊዜ አንድ ሰው ድራፍቲንግ፣ ቅየሳ ወይም ደስ ያለውን መማር ይፈልጋል። በቅየሳ ወይም በድራፍቲንግ ኮታ የለም፣ አልቋል መማር ያለብህ የግንባታ ቴክኖሎጂ ነው ይባላል፡፡ ተመልከቺ፤ ልጁ መማር የሚፈልገው ሌላ እንዲማር የሚደረገው ሌላ ነው፡፡ አንድ ሰው ውጤታማና ምርታማ የሚሆነው የሚፈልገውንና የመረጠውን ሲማር ሆኖ ሳለ፣ የሚማረው ግን ካሰበውና ከመረጠው ውጪ ይሆናል፡፡ በተግባርም ሆነ በንድፈ ሀሳብ ደረጃ የመረጠውን ያልተማረ ተማሪ በአብዛኛው ውጤታማ አይሆንም። ትምህርቱን ይጠላዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ከሚማርበት ይባረራል ወይም ራሱ አቋርጦ ይወጣል፡፡ ከዚያ በኋላ ይህልጅ ወዴት ይሄዳል? የሚለው በአሉታዊ ተፅዕኖ ትንታኔ ውስጥ በመፅሀፉ  ተቀምጧል፡፡ የማይሰራ ነገር ግን  የሚበላ  ትውልድ እንድናመርት የትምህርት ፖሊሲው አስተዋፅ አድርጓል ማለት ነው፡፡ ሴት ተማሪዎችስ በዚህ ካለፉ በ16 ዓመት ዕድሜያቸው ወዴት ይሄዳሉ? ይህም ተተንትኗል፡፡ ወደ ሴተኛ አዳሪናት፣ ወደ ጎዳና ተዳዳሪነትና ወዳልተፈለገ ተግባር ሰማራሉ፡፡
ወይ አረብ አገር ይሄዳሉ፤ ካልሆነም ሳይማሩና ራሳቸውን ሳይችሉ  ያገባሉ፡፡ ሌላ ማህበራዊ ቀውስ ይፈጠራል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በቴክኖሎጂ፣ በመሰረተ ልማት፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካ ካደጉ የአውሮፓ ሀገራት የተኮረጀው የትምህርት ፖሊሲ ፈጽሞ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ድሃ  ሀገራት ሊተገበር ቀርቶ  ሊታሰብ አይገባውም ነበርና፡፡
እስቲ ሁለተኛውም ፖሊሲ እንመልከት?
ሁለተኛው የኮንስትራክሽን ፖሊሲ ነው፡፡ ወቅቱ በሀገራችን የግንባታ ነው። ለግንባታው ሲሚንቶን ጨምሮ በርካታ ግብአቶች ይገባሉ፡፡ ገቢ ግብአት ከወጪ ንግዳችን በጣም የበለጠ ነው፣ በዚህ ላይ በዘርፉ የተዝረከረከ፣ ለብክነት የተጋለጠ፣ ግምገማና ክትትል የማይደረግበት ሥለነበር ለዶላር እጥረትና ለኢኮኖሚ መዋዠቅ አንዱና ከፍተኛው የግንባታ ፖሊሲ ነው። በመፅሀፉ ተተንትኗል፡፡ አጠር አጠር እያደረግኩ ነው የምነግርሽ፡፡
ግንባታን በተመለከተ ይልቅ መንግስት በብዛት ሲወቀስበት የኖረው፣ ምግብና ዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎችን ከማስፋፋት ይልቅ ግንባታ ላይ በማተኮሩ፣ በርካታ የምግብ ሸቀጦችን እያስገባን፣ ለዶላር እጥረት ተጋለጥን የሚል ነው ትክክል ነው?
እውነት ነው፡፡ ይህም ልብ ያልተባለበት የኮንስትራክሽን ፖሊሲው ክፍል ነው፡፡ እንዳልኩሽ ለግንባታው የሚገባው ግብአት ብዙ ዶላር ይፈስበታል፡፡ የምግብ ምርት የሚያመርቱትን ብናስፋፋ ኖሮ… የዋጋ ንረቱም፣ የዶላር እጥረቱም፣ የኑሮ ውድነቱም አይመጣም ነበር፤ ቢመጣም በዚህ ልክ አይሆንም ነበር፡፡ ስለዚህ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የኮንስትራክሽን ፖሊሲው ክፍተት ለአሁኑ ኢኮኖሚ መዋዠቅ አበርክቶ አለው፡፡ ሌላው ይህ ፖሊሲ ለባለሀብቶችም ምቹ አልነበረም፡፡
እንዴት?
አንድ በግንባታ ላይ የተሰማራ ኢንቨስተር በሊዝም ይሁን በሌላ መንገድ ቦታ ገዝቶ ወደ ግንባታ ሲገባ የህንጻው አገልግሎት “ቅይጥ” ይላል- (Mixed use) ይህ ምን ማለት ነው? በአንድ የአስፋልት ዳር በሚነባ ህንፃ ላይ ከስር ባንክ ወይም ኢንሹራንስ ሊከራይ ይችላል፡፡ ከፍ ብሎ ካፊቴሪያ ይኖራል፣ ከፍ ብሎ ሬስቶራንት መኖሩ ግድ ይሆናል፡፡ ከዚያ ደግሞ ከፍ ብሎ የመኝታ አገልግሎትን ያካትታል፡፡ ይሄ በጣም የተበላሸና ለአንድ ከተማ መዘበራረቅ የራሱን አስተዋፅኦ የሚያበረከተ አሰራር ነውና ሊጤን ይገባል። ይህንንም ከእነምክንያቱ በመፅሐፉ ተንትኛለሁ፡፡
ግን ይሄ ከኢኮኖሚ መዋዠቅ ጋር ምን ያገናኘዋል?
በጣም ጥሩ ጥያቄ! ለምሳሌ በአንድ የንግድ ሞል፣ ጫጫታ በበዛበት፣ የመኝታ አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት ካለ፣ ሰው ጫጫታና እረብሻ ባለበት ቦታ አልጋ ይዞ መተኛት ወይም ማረፍ አይፈልለግም፡፡ ያ ነጋዴ ውድ አልጋ ገዝቶ፣ አንሶላ ግዝቶ በርካታ ከመኝታ ክፍል ጋር መሟላት ያለበትን ቁሳቁስ አሟልቶ አልጋውን የሚከራይ ከሌለ፣ የኢኮኖሚ ቀውስ ይመጣል አይመጣም? አልሚውንም አያበረታታም፡፡ ያሉት የመኝታ አልጋዎች አመታዊ የመያዝ አቅማቸው ለአመቱ ሲካፈል፣ ውጤታቸው 30 እና 40 በመቶ አይሞላም፡፡ ይሄ ኪሳራ ነው፡፡ በዚህና በመሰል ጉዳዮች ፖሊሲው መታየት አለበት፡፡ ሌላው የሰራተኛ ቅጥር ፖሊሲ ነው ያልተጤነው፡፡ በአሁን ሰዓት በ2ሺህ ብር ተቀጥሮ የሚሰራ አንድ ሰራተኛ ምን ከምን ሆኖ ነው የሚኖረው? ኑሮው እየናረ ሁሉ ነገር እየጨመረ ሲሄድ፣ መንግስት እየፈተሸና ፖሊሲውን እየመረመረ ካልሄደ፣ አሁንም የኢኮኖሚ ቀውስ አደገኛ ነው፡፡ 2 ሺህ ደሞዝተኛ ተራራ ወጥቶ ከከተማ ርቆ ብዙ ሰው ወደሌለበት ቦታ ሄዶ አንድ ክፍል ቤት 1 ሺህ 500 ብር ሊያገኝ ይችላል፡፡ ከዚያስ ቀለብ፣ ትራንስፖርት፣ አልባሳት፣ የልጆች ት/ቤት… እንዴት እንዴት ነው የሚሆነው? ሊታይ ይገባል፡፡
መንግስት እኮ የዛሬ 20 ዓመት ያወጣውን የሰራተኛ ቅጥር ፖሊሲ ከኢኮኖሚ ጋር አዛምዶታል፡፡ ሸቀጦች በሚጨምሩበት መጠን ተሰልቶ ነው የደሞዝ እርከን መሰራት ያለበት፡፡ አሁን ባለው የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት፣ እንዴት የ2 ሺህ ብር የደሞዝ እርከን ይኖራል፡፡ ይሄ ብዙ የሚያነጋግር ነው፡፡ ሁሉም በመፅሐፉ ተተንትኗል፡፡
የልማት ተነሺዎች የካሳ ፖሊሲም በመፅሐፉ ሊጤኑ ይገባል ብዬ ካነሳኋቸው ዘጠኝ ፖሊሲዎች አንዱ ነው፡፡ በአጠቃላይ መፅሐፉ በቀጥታ የህብረተሰቡን በር እያንኳኩ ባሉ ችግሮች ዙሪያ፣ ፖሊሲ አውጪዎችን የሚያነቁ፣ መንግስት አካሄዱን እንዲስተካክል የሚያደርጉ ቁምነገሮች በስፋት ይዟል፡፡
ለነዚህ ሁሉ ችግሮች የህገ-ወጥ ነጋዴዎች መበራከት፣ የመንግስት የተዝረከረከ አሰራርና የቁጥጥር መላላት እንደ መንስኤ በተደጋሚ በመፅሐፉ ተነስተዋል፡፡ መፍትሔውስ?
በአንድ አገር ላይ ፈርጣማ ክንድ ያላቸው፣ ለህግ ተገዢ ያልሆኑ ነጋዴዎች ከተበራከቱ አደገኛ ነው፡፡ አሁን ለዚህ ሁሉ ችግር መፈጠር ዋነኞቹ እንደነዚህ አይነት ነጋዴዎች ናቸው። አሁን አሁን መንግስት ትንሽ ቁጥጥሩን ጠበቅ ሲያደርግና በመጋዘን የተቆለፈ በርካታ ዘይት፣ ጤፍ፣ በርበሬ እየተገኘ ነው። ተፈጥሯዊ የምርት እጥረት ሳይኖር በሰው ሰራሽ የምርት እጥረት ነው ማህበረሰቡ እየተሰቃየ ያለው፡፡ በነዚህ አይነት ስርዓት አልበኛ ነጋዴዎች ላይ መንግስት ቁጥጥሩንና ክትትሉን ማጥበቅ አለበት፡፡ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የሸቀጥ ዋጋ መናር በሁለት ዋና ዋና ምክንቶች ይከሰታል ብለው  ያምናሉ። አንደኛው፣ ምርትና ምርታማነት ሲቀንስ ነው፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት 110 ሚ ከሆነ፣ በአመቱ የሚመረተው ጥቅል ምርት በነፍስ ወከፍ ስንት ነው የሚለውን መመለስ ካልተቻለ፣ ግሽበት አለ ማለት ነው፡፡ ሸቀጥ ይወደዳል፤ ብር ይረክሳል። ብር ሲረክስ፣ የመግዛት አቅሙም አብሮ ይወርዳል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ምርትና ምርታማነት በበቂ ሁኔታ እያለ፣ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች በሚፈጥሩት ሰው ሰራሽ እጥረት ምርት ከገበያ ላይ ይጠፋና ያለችዋ በውድ ዋጋ ትሸጣለች፡፡ በዚህን ጊዜ ለመንግስት ሌቦች ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል፡፡
እነማን ናቸው የመንግስት ሌቦች?
ይህን የማረጋጋት ስራ በቀጥታ የሚመለከታቸው ሆነው፣ ነገር ግን ከስግብግብ ነጋዴዎች ጋር በመመሳጠር፣ ቁጥጥሩንና ፍተሻውን ሆን ብለው በማላላትና አይቶ እንዳላየ በመሆን ከነዚህ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ጋር የጥቅም ተጋሪ የሚሆኑ ናቸው፡፡ ይሄ ሁሉ በጥናቱ የተካተተ ነው፡፡ ስለዚህ ይሄንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት “ምርት ገበያን የማረጋጋት ፕሮጀክት ፅ/ቤት” ቢቋቋም አዋጪ ነው የሚል የመፍትሄ ሀሳብም በመፅሐፉ ጠቁሜያለሁ፡፡ ይህ የፕሮጀክት ፅ/ቤት ህገ-ወጥ ነጋዴን ከመሃል ነቅሎ አውጥቶ፣ አምራችና ሸማችን በቀጥታ የሚገናኝና ሁለቱንም አካላት ተጠቃሚ የሚያደርግ  ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ነው በጥናቱ የደረስኩበት፡፡ ይህንን ማቋቋም ያለበት ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሆኖ፣ በስነ-ምግባር የታነፀና ለሀገራቸው ተቆርቋሪ የሆኑትን ዜጎች በመመልመል ይህን ፕሮጀክት ጽ/ቤት፣ የሚመራ አደረጃጀት ከፌደራል እስከ ክልል፣ እስከ ዞንና ወረዳ  ድረስ የተጠናከረ  ሲስተም ቢዘረጋ፣ ህዝቡም እፎይ ይላል፡፡ ገበያውም ይረጋጋል፡፡ አምራቾቹም በተሻለ ዋጋ ምርቱን ለሸማቾች ያቀርባል፡፡ ህገ-ወጥና ስግብግብ ነጋዴዎችና ደላሎች ከጨዋታ ውጪ ይሆናሉ አራት ነጥብ፡፡ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ምርት ገበያም´ኮ ጉዳዩ በቀጥታ ይመለከተዋል፡፡ ግን እስካሁን ችግሩ አልተቀረፈም፡፡
1. የምግብ ዋጋ በአማካይ ዝርዝር (ከ1998-2003)
የምግብ ዓይነቶች    የምግብ ቤቶች ደረጃ    ዋጋ (በብር)
ጥብስ    መለስተኛ እስከ መካከለኛ    12-35
ቀይ ወጥ    መለስተኛ እስከ መካከለኛ    12-35
ቅቅል    መለስተኛ እስከ መካከለኛ    12-30
ሚስቶ    መለስተኛ እስከ መካከለኛ    12-35
ክትፎ    መለስተኛ እስከ መካከለኛ    25-70
ጥሬ በኪሎ (ቁርጥ)    መለስተኛ እስከ መካከለኛ    40-90


2. የመጠጥ ዋጋ በአማካይ ዝርዝር (ከ1998-2003)
የመጠጥ ዓይነቶች    የመጠጥ ቤቶች ደረጃ    ዋጋ (በብር)
ድራፍት (ጃምቦ)    መለስተኛ እስከ መካከለኛ    3-7
ቢራ    መለስተኛ እስከ መካከለኛ    3-11
ወይን ትንሹ (ጉደር)    መለስተኛ እስከ መካከለኛ    12-20
ወይን ትንሹ (አክሱማይት)    መለስተኛ እስከ መካከለኛ    15-25
ወይን ትልቁ (ጉደር)    መለስተኛ እስከ መካከለኛ    22-30
ወይን ትልቁ (አክሱማይት)    መለስተኛ እስከ መካከለኛ    30-50
አዋሽ    መለስተኛ እስከ መካከለኛ    20-30
ለስላሳና አምቦ ውሃ    መለስተኛ እስከ መካከለኛ    2-4


3. የትኩስ መጠጥ ዋጋ በአማካይ ዝርዝር (1998-2003)
ትኩስ ነገሮች    የቤቶች ደረጃ    ዋጋ (በብር)
ማኪያቶ    መለስተኛ እስከ መካከለኛ    2-3.50 ሳ
ወተት    መለስተኛ እስከ መካከለኛ    2.25ሳ-4
ሻይ    መለስተኛ እስከ መካከለኛ    1.25ሳ-2.50
ለውዝ ሻይና ሌሎች    መለስተኛ እስከ መካከለኛ    2-3.50ሳ


4. የዳቦና ኬክ ዋጋ በአማካይ ዝርዝር (ከ1998-2003)
ኬኮች    የቤቶች ደረጃ    ዋጋ (በብር)
ደረቅ ተቆራጭ    መለስተኛ እስከ መካከለኛ    1.75ሳ-4
ዶናት    መለስተኛ እስከ መካከለኛ    2-5
ቦምቦሊኖ መለስተኛ    መካከለኛ    1.75ሳ-4
ዋይት ፎረስት    መለስተኛ እስከ መካከለኛ    2-5
ብላክ ፎረስት    መለስተኛ እስከ መካከለኛ    2-5
ጮርናቄ (ብስኩት)    መለስተኛ እስከ መካከለኛ    1.50ሳ-2
ሳንቡሳ (1ፒስ)    መለስተኛ እስከ መካከለኛ    1-2


Read 1356 times