Monday, 05 July 2021 20:18

ሴቶችና ጋሼ ስብሃት በድርባቦ

Written by  ዘነበ ወላ
Rate this item
(1 Vote)

   ዛሬ ላስበው ነው፤ እሱ እንዳለው በሚወዱት ሰዎች ዘንድ ዘላለማዊ ነው። የካቲት 12 ቀን 2004 ዓ.ም ተቀበረ:: እኔ ከእረፍቱ እለት ጀምሮ እነሆ እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ አንዲትም ቀን ሳላስበው አላለፈችም። ባለፉት ዘጠኝ አመታት ሁሉ.። የቅርቡን ላስታውስ፡፡ ሰሞኑን አልበርት አንስታይን የመጨረሻውን ቃል ምን እንዳለ ሳስብ፣ ጋሼ በሃሳቤ መጣና "ልክ ነህ የመጨረሻውን ቃል ተናግሯል። የተናገረው በጀርመንኛ ነው። አጠገቡ ያለችው አስታማሚው እንግሊዘኛ የምትናገር ስለነበረች ምን እንዳለ ብትሰማውም አልገባትም’’ አለኝ። ለዘመኑ ቴክኖሎጂ ምስጋና ይግባውና ኢንተርኔት ውስጥ ገብቼ ጠየኩ። ጋሼ እንዳለው ሃሳቡን ደግሞልኝ ሌሎች መላምቶችን ደረደረልኝ።
እሱ ቢኖር ኖሮ ምንም አትጠራጠሩ እጠይቀው ነበር። ሳነብ አንድ ጠጣር ያልገባኝ የእንግሊዝኛ ቃል ሲያጋጥመኝ ‘’ጋሼ ይህ ምን ማለት ነው?’’ እልና እጠይቀዋለሁ። አዘውትሮ እንደሚያደርገው ማስታወሻ ደብተሬን ይቀበለኝና ይጽፍልኛል። ተጨማሪ ቢያውቀው የሚለውንም ያክልልኛል። አሁን ግን ሞባይሌ ላይ ቢያንስ ሶስት መዝገበ ቃላት ስላሉ አንዱን ከፍቼ እጠይቀዋለሁ። ምላሽ አገኛለሁ። አንዳንዴ መዝገበ ቃላቱ ከነጭራሹ ላያውቀው ይችላል። የሚደንቀው ጋሼን ማሰቤ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
አንዳንዴ ክፍለ ሃገር በአውቶቡስ ስጓዝ በምናቤ ቀድሞ የሚከሰተው ጋሼ ስብሃት ለአብ ነው። ወሬ እንጀምራለን አልያም ቀደም ብሎ በህይወት እያለ በአያሌው የተከራከርንበት ርዕስ በሃሳቤ ይመጣል። ትዝ እንደሚለኝ፤ ጋሼ ስብሃት ለአብ ሴቶችን 100% ቅዱስ ፍጥረታት አድርጎ ነው የሚያየው። መቶ በመቶ በጋሼ ስብሃት ለአብ ነብስ ውስጥ ሴቶች ሁሉ ቅዱስ ናቸው። ይህ  ለእኔ አይዋጥልኝም። እንደ ዴስቲዮቪስኪ "ሴት ልጅ ሰው ነች አይደለችም" ቅጥ ያጣ ድፍረት አይዳዳኝም፡፡ እንደ ጎርኪ "ሴት ልጅ ሁለተኛ ነብስህ ናት" ይስማማኛል። የእኔ መከራከሪያ፤ "እንደ ማንኛውም ሰው ሴቶችም አስተዋይ፣ አርቆ አሳቢ የሆኑትን  ያህል፣ ነውረኞችም ሞልተውባቸዋል፤" የሚል ነው፡፡ እሱ ግን ይህንን ‘አይኔን ግንባር ያድርገው’ ይልና ሊያስበው  አይፈልግም፤ ንትርኩ ይቀጥላል።
 “ምነው አንተ ለሴት ልጅ እጅህን ሰጠህ?’’ እለዋለሁ።
እሱ ደሞ ቆጣ ብሎ “ለሴት እንጂ ላንተኮ እጄን አልሰጠሁም?!” ብሎ ያፈጥብኛል። ሲቆጣና ሲያፈጥ ያስፈራል። ሴት አላዋቂዎች ህይወቱ ላይ ቢከሰቱም አስውቦ ነው የሚገልጻቸው፡፡
በዘጠናዎቹ አካባቢ ከእኔ ጋር ቂርቆስ አንድ ክፍል ቤት ተከራይቶ ጎረቤቴ ሆኖ  ይኖር ነበር፡፡ ሲያሻቸው ልጆቹ ዜናም ሆነች ኩኩሻ ይመጡና አብረውት ይኖሩና ሲያሻቸው ወደተለያየ ቦታ ተመልሰው ይሄዳሉ። እንዲህም ቢሆን ብቻውን አይደለም። እኔ ከስራ ሰአት ውጪ ሁልግዜም አብሬው ነኝ። እርሱም በሚጽፍበትና በሚያነብበት ጊዜ ብቻውን መሆን ይመርጣል። የእኛ ቤት የልጆች ሞግዚት - አጸዱ፤ በጣም ስለምትወደው በፍቅር ትንከባከበዋለች።
ጋሼ ስብሃት፤ አዲስ አበባን ዙሪያዋን የመክበብ ያህል የተለያዩ ሰፈሮች ኖሯል። አፈር የቀመሰው ቂርቆስ ውስጥ እየኖረ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ እኛ ሰፈር መጥቶ ከእኔ ጋር መኖር ስንጀምር፤
"ይኸውልህ ጋሼ ስብሃት፤ አዲስ አበባ ውስጥ ስትኖር የትም ሰፈር ጨዋ የመኖሩን ያክል ዱርዬም አለ። ስለዚህ አታምሽ፤ ካመሸህ በዱርዬዎቹ  ልትመታ ትችላለህ‘’ አልኩት።
"እስከ ስንት ሰአት ነው የሰአት እላፊው?’’
‘’እስከ ሁለት ሰአት” አልኩት፡
አሁን የሆነ ጓደኛችን ቤት አምሽተን ወደ ቤት እየተጨዋወትን እየሄድን ነው። እንዲያውም አንድ ካቲካላ ቤት በር ላይ ደርሰናል። ከአንድ አስር እርምጃ በኋላ ቤት እንገባለን።
‘’አሁን ስንት ሰአት ነው?”
“ለሁለት ሰአት ሃያ ጉዳይ!”
“ሃያ ደቂቃ እየቀረን ነው እንዲህ አይነት ሆረር የምትነግረኝ። ሃያ ደቂቃ አለን ወንድ የሆነ አይነካንም!”
ተሳሳቅን። እንዳበቃን ‘’ጋሼ ይቺ ቤት ካቲካላ ይሸጥባታል፣ ጥሩ ሽሮ ወጥ በሶስት ብር መብላት ይቻላል። ገንዘብ ካለህ ክፈል ከሌለህ ግን ዘነበ ይከፍላል ብለህ ብላ ዘና በል፤ እኔ ምሽት ስመጣ አብረን ወደ ቤት እንገባለን” አልኩት፡፡
"እሺ’’ አለኝ። በህይወቱ የመጀመሪያ ካቲካላ ቤት ጠቋሚው እኔ ሳልሆን አልቀርም። ከዜና ጋር ስንጫወት "አባዬ ሁሌም አዲስ ሰፈር ስንገባ ካቲካላ ቤቱ የት እንዳለ በደንብ ያውቃል’’ ያለቺኝ ትውስ አለኝ።
በበነጋታው እዚያው ካቲካላ ቤት ሄደና ምግብ አዝዞ በላ፣ ካቲካላውን አስቀዳና ፉት እያለ ማንበብ ጀመረ። በየመሃሉ የሚያስቅ ነገር ሲያጋጥመው የኮረኮሩት ያህል ነው የሚስቀው። እኔ በህይወቴ ከወረቀት ጋር መሳቅ የሚችሉ ሁለት ሰዎችን ብቻ ነው የማውቀው፤ አንድ ጋሼ ስብሃት ለአብ፣ ሁለተኛ አሰፋ ጎሳዬን ነው። ይሄ ሳቅ ከጢሙ መንዠርገግ ጋር ያወካት የካቲካላ ቤቷ ባለቤት በጣም ደንግጣ ‘’በህግ አምላክ አንቱ ሰውዬ ዳዊቶትን አይድገሙብኝ፤ ይቺም ኑሮ ሆና ይደግሙብኛል!’’ ብላ ጮኸችበት። ደነገጠና ቀስ ብሎ መጽሐፉን ዘግቶ ቀና ብሎ አያት፤ ተሸብራለች። ባላሰበው መንገድ በመተርጎሟም ተገርሟል። የሃገራችንን የአፍዝ አደንግዝ ገበያን መዝጋት፣ ከባሰም እንደርቢ እንዲሆን የሚያደርጉ የደብተራ አካሄዱንም ያውቀዋል። ስለዚህ በብልሃት ሴትየዋን ማረጋጋት ነበረበት፡፡  
"እሜቴ! እያነበብኩት ያለሁት ዳዊት ሳይሆን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ነው" አለና ገልጦ አሳያት፤ ባታውቀውም  እንድትረጋጋ። ከዚያ መጽሐፉን አጠፈና ኪሱ ከተተ። ካቲካላውን ጨረሰና ሂሳቡን ከፍሎ ወደ ቤት መጣ። የቀን ውሎዋችንን መጨዋወት ጀመርን። ስለ ሴትየዋ ሲያወጋኝ፣ እኔ ምን እንደነካኝ አላውቅም ብልጭ ብሎብኝ "ዝም አልካት?’’ አልኩት።
"ለምን ዝም አልላትም፣ እሷ እኮ ያየቺኝ በተሰጣት ብርሃን ልክ ነው!’’
ጋሼ ስብሃት ሴቶችም ይወዱታል፣ አንዴ በህይወቱ ከተከሰቱ በፍቅር ምንጊዜም ያስቡታል። መውደድ ስል ከስጋ ፍላጎት ጋር ካያያዛችሁት ተሳስታችኋል፤ እኔ ያልኩት መንፈሳዊ ዘላለማዊ ፍቅር ነው። አያሌዎች አሁንም ድንገት ሲያገኙኝ፣ ያ ዘላለማዊ ፍቅራቸው ይቀሰቀስና ያስታውሱታል። እኔም እንዳልኳችሁ እነሆ ባለፉት ዘጠኝ አመታት እንዲሁ እንደተጨዋወትን፣ እንዳወጋን፣ እንደተከራከርን አለሁ። ይህን የምናብ ጨዋታ እጽፈዋለሁ እላለሁ እንጂ በእጄ የያዝኩት ማስታወሻ የለም። ሃሳቡም የሚመጣው ረጃጅም መንገድ ላይ ነው። በእንዲህ አይነት ሁኔታ ማስታወሻ መያዝ አይቻልም። መዳረሻዬ ላይ ስደርስ ደግሞ ደክሞኛል፣ በዚያን ጊዜ የቅድሙ እኔ ሳልሆን ሌላ ሰው ነኝ። እንዲህ አይነቶቹን ሃሳቦች በደምብ አሰናድቼ መድረክ ላይ "ጋሼ ስብሃት ለአብና ሴት...’’ ማሰቤን አስታውሳለሁ።  "አንዱ ‘ፖየቲክ ጃዝ’ ላይ እደሰኩርበታለሁ" እላለሁ፤ ይሁን እንጂ ልክ እንደ ፈጠራ ስራ አለቦታው እየመጣ ስለሚያስቸግረኝ የተጨበጠ መረጃ የለኝም። አሁን ይህቺን ማስታወሻ ለመያዝ ቀን መንሸራሸር፣ መንቆራጠጥ እያልኩ ጠረጴዛዬ ዘንድ ሳልደርስ ከመሸ በኋላ ሃሳብ ሲያጣድፈኝ እዚያው ቆም ባልኩበት መከተብ ጀመርኩ።
ጋሼ ስብሃት ለአብ ዛሬ እንዳስታውሰው ያደረገኝ ጉዳይ አንዲት ድንቅ መታሰቢያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሙዚየም ውስጥ ስለቆመለት ነው። ይህ መታሰቢያ እንዲቆምለት መጀመሪያ ስልክ ደውሎ ጉዳዩን ያበሰረኝ የጋራ ወዳጃችን አቶ ደረጀ ገብሬ ነው። ደረጄ እዚያው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መምህር ስለሆነ አንዴ ደወለልኝና ‘’ዘነበ እዚህ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ባለ ሙዚየም ሃላፊዎቹ ለደራሲያን ክፍል አዘጋጅተዋል። አቶ ሃዲስ አለማየሁ፣ አቶ መንግስቱ ለማ፣ አቶ አቤ ጉበኛ፣ አቶ ጳውሎስ ኞኞ፣ አቶ ማሞ ውድነህ-- ቤተሰቦቻቸው ደራሲያኑ በህይወት በነበሩ ጊዜ የተጠቀሙበትን ቁስ፣ የእጅ ጽህፈታቸውን፣ መጻህፍቶቻቸውን ወዘተ... አምጥተው አስቀምጠውላቸዋል። አሁን በሙዚየሙ ውስጥ ጎብኚዎች ያስቧቸዋል ይጎበኟቸዋል። አንተም የስብሃት ጉዳይ ስለሚያገባህ የእርሱን ቁስ በእጅህ ያለውንም ወይም ከቤተሰቦቹ ጠይቀህ አንድ ነገር አድርግ’’ አለኝ። ወዳጄ ደረጄን ከልብ አመስግኜ በቅርቡ እንደምከውነው ቃል ገብቼለት ተሰነባበትን።
እኔ በወቅቱ አዲስ መጽሐፍ እየጻፍኩ ነበር። ይህ መጽሐፍ ምናልባትም ከአስር ጊዜ በላይ እየተጻፈ፣ እየዳበረ፣ እየታረመ ሳዘጋጀው የነበረ ‘’የምድራችን ጀግና’’ የተሰኘው መጽሐፍ ነበር። ይህ መጽሐፍ ከእድሜዬ ሃያ አመታት እንዳስበው እንድሰራው አድርጎኛል። ይሁን እንጂ ከላይ እንዳልኩት አንዱ ከአንዱ ስጎትት እጄ ላይ ከራርሞ በሚወጣበት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል፤ በጥድፊያ ከቅድስት የሺጥላ ጋር እየሰራን ነበር።  ቅድስት የሺጥላ የስራ ባልደረባ ብቻ ሳይሆን በጣም ሽርክ ነን። የእኔን ብቻ ሳይሆን የበርካታ ደራሲያንን ስራዎች፣ የመመረቂያ ጽሁፎች  ጽፋለች። ከማስታውሰው የጋሼ ሳህለ ስላሴ ብርሃነ ማርያምን፣ የሙሉጌታ ሉሌን፣ የዶክተር በድሉ ዋቅጅራን፣ የእንዳለጌታን... እያልን ስንቆጥር ከአንድ ደርዘን በላይ ደራሲያን በእርሷ በኩል አልፈዋል። ቅድስት ባለትዳር ነች፤ የአንድ ወንድ ልጅ እናት፣ ባለቤቷ ባዕድ አገር ነው የሚኖረው።  ለፋሲካ፣ ለቅዱስ ዮሃንስ ሲሆን አገር ቤት ይመጣል። በዚህ ጥድፊያ ላይ እንዳለሁ ከጋራ ወዳጃችን ዮናስ ታረቀኝ ጋር ሻይ ቡና ተባብለን ስንጨዋወት "ባለቤቷ እዚህ አዲስ አበባ ነው እንዴ  ያለው?’’ አለና ጠየቀኝ፤ እኔም አፍታ ሳልቆይ "ምን ይሰራል እዚህ?’’ አልኩ ቆጣ ብዬ።
የጋሼ ሳህለ ስላሴ ብርሃነ ማርያምን ‘የክርስቶስ ህይወት’ የተሰኘ መጽሐፍ እየጻፈችለት ሳለ ወንድ ልጇን ድንገት ወልዳ ስራው ተቋረጠ። የዮናስ አጠያየቅ "ባሏ እዚህ ከሆነ ቢዚ ስለሚያደርጋት ፍጠን!" እያለኝ ነው። አጣራሁ፡፡ ባለቤቷ አዲስ አበባ መጥቶ ሄዷል፡፡ ጉድ ሆኛለሁ። ቅድስት ጸንሳ ይሆን ስል ሃሳብ ገባኝ፡፡ በጣም ስለምንቀራረብ ወጣ ብለን ዘና ማለት እንዳለብን ሳነሳላት "አይቻልም!’’ አለቺኝ።
"ምንድነው!’’
"ጸንሻለሁ!”
‘የፈሩት ይደርሳል የጠሉት ይወርሳል’ እንዲሉት ሆነብኝ። ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ላይ አንድ የሚጨምረው ህጻን ከመምጣቱ በፊት በጥድፊያ ሥራዬን ማቀላጠፍ  ጀመርኩ፤ እሷም በሚያስደንቅ ሁኔታ ብዙ ጊዜዋን ሰጥታኝ መጽሐፉን ለማጠናቀቅ ቻልን፡፡ ልጇን ከመውለዷ ሃያ ቀን ቀድመን ጨረስን፡፡ ተመስገን! አልኩኝ፡፡ በእንዲህ አይነት ጥድፊያ ውስጥ ሆኜ፣ ከኤፍኤም ራዲዮ ጣቢያ (የትኛው እንደሆነ የዘነጋሁት) ደውሎልኝ "ስለ ጋሼ ስብሃት እናውራ" ብለውኝ፣ አልችልም አልኳቸው። በስልክ ሊያስገቡኝ ፈለጉ፤ እርሱንም አይሆንም አልኳቸው፤ እርግጠኛ ነኝ ተቀይመውኛል። ያለሁበትን ሁኔታ የማውቀው እኔ፣ እግዚአብሄርና ቅድስት ብቻ ነን። በህይወት ቢኖርና ይህንን እንቢታዬን ጋሼ ቢሰማ “ልክ ነህ!” እንደሚለኝ እርግጠኛ ነኝ።
ጥድፊያው ከቅድስት ጋር ብቻ አይደለም፣ ባለ ታሪኩ ዶክተር ተወልደም አርጅቷል፣ በአዛውንትነት እድሜ ላይ ነው ያለው፡፡ እኔም ከዚህ ስራ ወይም ከክብደት መጨመር ጋር ተያይዞ የደም ግፊት ያጣድፈኝ ጀምሯል። ስለዚህ ከሁለት አንዳችን ይህ ስራ ዳር ሳናደርሰው እንዳንሰናበት ከፍተኛ ስጋት ነበረብኝ። በአጠቃላይ ከቅድስት ጋር ህይወትን መቅደም ሲሆን፣ ከዶክተር ተወልደብርሃን ጋር ደሞ ሞትን መቅደም ነበርና ተሳካልኝ። እርግጠኛ ነኝ እነዚያ "ሞቼ እገኛለሁ አላናግራችሁም" ብዬ እምቢ ያልኳቸው ጋዜጠኞች እንዲህ አይነቱ ነብስ ግቢ፣ ነብስ ውጪ በሚያሰኝ ጥድፊያ ላይ መሆኔን ቢያውቁ፣ ‘’ይቅር ለእግዜር’’ ይሉኛል። የጤናዬን መክፋት በአንድ ማስረጃ ላስደግፍ። በሃምሌ ወር አጋማሽ በ 2011 አ.ም መገናኛ አካባቢ አርሾ ክሊኒክ ሄጄ የጤና ክትትል አድርጌያለሁ። ምርመራውን ያካሄደልኝ ዶክተር ብስል ቀይ፣ ሙሉ በሙሉ የሸበተ ሃኪም ተቀበለኝ። ከላቦራቶሪ የመጣውን ውጤት አይቶ ህመሜን ነግሮኝ መዳኒት እንደሚያዝልኝ አስረዳኝ። እኔ ደሞ በሚያዝልኝ መድሃኒት ላይ መጠነኛንባብ ስላለኝ ‘’ይሄ የምታዝልኝ መድሃኒት ህይወትን በሙሉ የሚወሰድ ነው። ሳይንሱ አድጓል ሌላ መድሃኒት ልታዝልኝ አትችልም?’’ አልኩት።
‘’ለየትኛው እድሜህ ነው!’’ አለና ተቆጣኝ። ጸጥ ብዬ አፍጥጬ አየሁት። ይህ የተናገረው ቃል ካንድ ባለሙያ አንደበት የሚጠበቅ አይደለም። ምናልባትም ከመጀመሪያው ዲግሪው በላይ የጨመረው እውቀት ያለ አይመስለኝም። ችሎታውን ተጠራጠርኩ። እርሱ ዘንድ ቀርቤ ይህንን አይነት መስተንግዶ ለማግኘት ከሁለት ሺህ ብር በላይ አውጥቻለሁ። የሚያዝልኝን እንዲያዝልኝ ካጻፍኩ በኋላ ወረቀቱን ይዤ ወጥቼ ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ጥዬው፣ እያብሰለሰልኩ ወደ ቤቴ ሄድኩ። በበነጋው ወደ ሸገር ክሊኒክ ዘልቄ ከዶክተር ዳዊት በመምከር የተሻለ ጤና እንዲኖረኝ ሆነ። ይሄን መራር ትዝታዬን ሳወጋ አንባቢያን በወቅቱ የነበረው ምስል በቅጡ ተከስቶ እንዲታያቸው ነው።
አሁን ፋታ ኖረኝና ወዳጄ ደረጀ ገብሬ የሰጠኝን የቤት ስራ ለማከናወን ባለፈው ሰኔ ወር ላይ ተነሳሁ። በ እጄ ያሉትን ማስረጃዎች ካስቀመጥኩበት አንስቼ አየሁ። የትምህርት ቤት ሰርተፊኬቶቹን፣ "እፎይታ" ሲሰራ የተገለገለበትን ቦርሳ፣ በመንግስት ስራ ላይ እያለ የተጠቀመባቸው መታወቂያዎቹን... ወዘተ ሰበሰብኩ። ያሳደገው ልጁ ደምሰው ሃይለሚካኤል በህይወቱ መጨረሻ የተጠቀመበትን ብዕር፣ ቄንጠኛ ኮፍያውን፣ የእጅ ጽሁፉን ወዘተ አመጣ። እድሜ ለዘመናችን ቴክኖሎጂ፣ ይህንን የሰበሰብኩለትን ለሙዚየሙ ማስረከቤን ፌስቡክ ገጼ ላይ ጻፍኩ። ይህንን ተስፋልደት ገብረሚካኤል የተባለ ጓደኛችን አሜሪካ ሆኖ አይቶት ኖሮ እሱ ዘንድ ያስቀመጠውን ልብሱን እንድወስድ ትእግስት በላይ በምትባል እመቤት ላከልኝ። ልብሱን የማውቀው ነው፤ ቶሎ ላውንደሪ አስገባሁት፤ ሸሚዙን ቤቴ ውስጥ አጠብኩት። ኪሶቹን ስፈትሽ አዘውትሮ ጢሙን የሚያበጥርበት ማበጠሪያ፣ በህይወቱ መጨረሻ አካባቢ ጣቱ ላይ አያት የነበረች አርቴፊሻል ቀለበት አገኘሁ። እነሱንም የቅርሱ አካል እንዲሆኑ አደረኩ። አዘውትሮ ከሚይዛቸው ፌስታሎች አንዱን አከልኩ። አስር ብር ብቻ ያለባት የባንክ ደብተሩም አብራ አለች። ስለሷ ለጋሼ አንስቼለት ‘’ትጠራቀምልኝ አንድ ቀን ብዙ ብር ስትሆን እንጠቀምባታለን’’ ያለኝን አስታውሳለሁ። ይህ ቁስ በቅጡ ተደራጅቶ የሚቆምበትን ቁምሳጥን በማሰራት ረገድ ወዳጄ አሊ ጃዕፋር አግዞኛል። ይህ ቁምሳጥን በገበያ ሲገመት ሃያ ሺህ ብር ያወጣል፤ ግማሹን ስላገዘኝ እኔ የመስታወት ወጪውን ሸፍኜ የምንፈልገው ቁስ ባሰብነው ጊዜ ደርሶ 85ኛ ዓመት የልደት በአሉን በፍቅር አሰብን።
የሙዚየሞቹ ሃላፊዎች በቅርቡ በቅጡ እቃውን አደራጅተው ለተመልካች ክፍት አድርገውት አየሁ። ይህ በጣም አስደስቶኝ የምስራቹን በፌስቡክ ገጼ ላይ ለወዳጆቼ አበሰርኩ።
በሚያስገርም ሁኔታ የወዳጆቼ ብዛት በአያሌው ጨመረልኝ፤ በእለቱ ስልኬ መትረየስ ነበር የሆነው፤ የገባው ጥሪ በርካታ ነበር። ጋሼ ስብሃት ለአብን በተመለከተ የወደፊት እቅዴ፣ ይህቺኑ መታሰቢያ የምትሆነውን ስፍራ ውብና ዘላቂ በሆነ ሁኔታ ማጠናከር ነው። ወደፊት ትንሽ ደርጀት ስል ለስሙ በሰም ሃውልት አሰራለታለሁ። ይህ አይነቱ ጥበብ ለንደን ውስጥ ማዳም ቱሶ ተቋም እንደሚሰራ አውቃለሁ። አቅሜ የሚፈቅድ ከሆነ ከወዲሁ አጣራለሁ፤ ካልሆነም ጊዜ ይፍቀድ እንጂ አንድ ቀን ይህን የሰም ሃውልት አቆምለታለሁ። አሁንም ይህንን ጽሁፍ አንብቦ የወደደው አንድ ወዳጃችን ደውሎልን ‘’አጣራና ንገረኝ እኔ አሰራለታለሁ!’’ ቢለኝስ? ማን ያውቃል? በራሱ በጋሼ አባባል ልደምድም፡፡ ‘’ኢንሻ አላህ!”

Read 3153 times