Wednesday, 07 July 2021 19:02

ኦ…ፍትህ ሆይ ወዴት ነሽ?

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ (singofbird@gmail.com)
Rate this item
(1 Vote)

"--እውነት ነው፡፡ ከጥንት እስከ ዛሬ ለነጻነትና ለፍትህ የተከፈለው ዋጋ ሊገለጽ የሚችል አይደለም፡፡ ከጋንዲና ከማንዴላ ሰቆቃ
በኋላም እንኳን ዛሬም በህንድና በደቡብ አፍሪካ ዘግናኝ ማህበረሰባዊ ክፍፍሎች አልተወገዱም፡፡ ሰቆቃው ቀጥሏል፡፡--"
                         
               ማህተመ ጋንዲ የኖረባት ህንድ በሚዘገንን ሁኔታ የተከፋፈለች ነበረች፡፡ በህንድ የማህበረሰብ አወቃቀር ለሺህ ዓመታት አይነኬ (untouchables) ተብለው የተገለሉ ህዝቦች ነበሩ፡፡ በህንዳዊያን እምነት መሰረት አይነኬዎቹ የነኩትን ማንኛውም ነገር መንካት ያረክሳል፡፡ ጋንዲ ግን አንድ አይነኬ ቤተሰብን ተቀበለ፡፡ አብሮ ከመብላት አልፎ ልጃቸውን በጉዲፈቻ እንደ ራሱ ልጅ ማሳደግ ጀመረ፡፡ የመረረ ተቃውሞው የጀመረው ከባለቤቱ ነው፡፡ ቢሆንም አልተበገረም፡፡ መላው ሂንዱስታኖች ይህን ለሺህ ዓመታት የዘለቀ አስነዋሪ ልማድ እንዲሽሩ ቀሰቀሰ፡፡ አንድ ጊዜ እንዲህ አለ፡-
‹‹እኔ በድጋሚ መወለድ አልፈልግም፡፡ በድጋሚ መወለድ ካለብኝ ግን አይነኬ ሆኜ መወለድ ነው የምፈልገው፡፡ ህመማቸውን መታመም፣ መገለላቸውን መቅመስ እፈልጋለሁ፡፡ የህይወታቸውን የስቃይ ጥልቀት ኖሬ ላየው እፈልጋለሁ፡፡›› በዚህ አባባሉ ብቻ ጋንዲ በሞራል ደረጃው “ባሪያ ሳልሆን ነፃ፣ ሴት ሳልሆን ወንድ አድርገህ ስለፈጠርከኝ አመሰግናለሁ” ካለው ከአርስቶትል ብዙ እንደሚልቅ አሳይቷል፡፡
ለመጨረሻ ጊዜ አውሮፓን ጎብኝቶ ከተመለሰ በኋላ ደግሞ፤ ‹‹በአውሮፓ ጥቂት ጎንበስ ብለህ ሰላም ብትለው ሁሉም ሰው ጎንበስ ብሎ አጸፋውን ይመልስልሃል፡፡ እኔ ግን የሀገሬን ልጆች አይነኬዎቹን መሬት ላይ ወድቄ የእግራቸውን አቧራ ብጠርግ እንኳን ለሺህ ዓመት የደረሰባቸውን በደልና መገፋት የሚክስ አይሆንልኝም፡፡›› ብሏል። ስንቶቻችን ማህተመ ጋንዲ በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ወቅት ከኢትዮጵያዊያን ጎን ቆሞ በየጋዜጦቹ ላይ ስለ ኢትዮጵያ ነጻነት ይጽፍ እንደነበረ እናውቃለን?  
ጊዜው ትንሽ ቆይቷል፡፡ ምናልባት በ1992 ወይም 93 ዓ.ም ይሆናል፡፡ ወጣቶቹ እየታፈሱ ነው፡፡ እዚህም እዚያም የኦነግ አባላትን አደኑ ቀጥሏል፡፡ በዚህ መሀል ማንም የማያውቀው ግን ለኦሮሞ ህዝብ ነጻነት ‹ሞቲ ቢያ› በሚል የብዕር ስም የሚጽፈው ትንታግ ጋዜጠኛ መታሰሩ በሹክሹክታ ይወራ ጀመር። በዚያው ሰሞን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያዎች በአንዱ፣ በአንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ ሁለት እስረኞች ለብቻቸው ታስረው ነበር፡፡ ድንገት አንደኛው ታሳሪ ማንም እንደማይሰማቸው ካረጋገጠ በኋላ ከዚህ በፊት ወደማያውቀው ታሳሪ ጆሮ ጠጋ ብሎ፤
‹‹አልሰማህም እንዴ ሞቲ ቢያን እኮ አሰሩት አሉ፡፡›› አለው፡፡ ይሄው ወደ ጆሮው ጠጋ ብሎ የነገረው ታሳሪ ራሱ ሞቲ ቢያ እንደሆነ ፈጽሞ አልጠረጠረም ነበር፡፡ ሞቲ ቢያ (ገመቹ መልካም) ለምስኪኑ እስረኛ ስለ ማንነቱ ምንም አላለውም፡፡ ቆይቶ ግን አሁን ፈርሶ የአፍሪካ ህብረት ሕንጻ በተገነባበት ቦታ ላይ የአለም በቃኝ ወህኒ ቤት ውስጥ ተገናኝተው የሞቲ ቢያን ማንነት ራሱ ደርሶበታል፡፡ ይህን የምነግራችሁን ታሪክ ያነበብኩት ሞቲ ቢያ፣ በቅርቡ ለንባብ ባበቃው ‹‹ነጻነት በነጻ የለም!›› መጽሐፉ ላይ ነው፡፡ ሞቲ ቢያ በዚሁ መጽሐፉ ላይ ‹‹የአንዷን ቀን የእስር ቤት ጉስቁልና ከኖራት ሰው ውጭ ማንም በሺህ ገጾች እንኳን ሊረዳው አይችልም›› ይላል፡፡
እውነት ነው፡፡ ከጥንት እስከ ዛሬ ጠዋት ለነጻነትና ለፍትህ የተከፈለው ዋጋ ሊገለጽ የሚችል አይደለም፡፡ ከጋንዲና ከማንዴላ ሰቆቃ በኋላም እንኳን ዛሬም በህንድና በደቡብ አፍሪካ ዘግናኝ ማህበረሰባዊ ክፍፍሎች አልተወገዱም፡፡ ሰቆቃው ቀጥሏል፡፡
ኢትዮጵያዊ፤ ‹‹ንጉስ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ›› የሚል የሻገተ ብሂል አለው፡፡ የግብጻዊው ደራሲ ተውኔት "The sultan’s dilemma" ግን ለፍትህ ሲባል፣ ለህግ ሲባል ንጉስ እንደሚከሰስ ሰማይ እንደሚታረስ የተመለከትኩበት ግሩም ተውኔት ሆኗል፡፡ እንዲህ ሆነላችሁ፡- በጥንት የማምሉካዊን አገዛዝ ዘመን፣ አንድ አስቀድሞ ባሪያ የነበረ፣ ነጻነቱ በይፋ ሳይታወጅ ለንግስና የበቃ ንጉስ ለፍትህ ሲባል፣ ለህግ የበላይነት ሲባል ለሽያጭ ቀረበ፡፡ ወዲያው የዚህ ገናና ንጉሥ ዕጣ ፈንታ፣ በንግስናው የመቀጠል ወይም ወደ ባርነት የመጋዝ አጣብቂኝ በአንዲት የተናቀች ሴተኛ አዳሪ እጅ ወደቀ፡፡ ህግ፣ ለፍትህ ሲባል ገናናውን ንጉሥ በሰንሰለት አስሮ በአንዲት ሴተኛ አዳሪ እግር ስር ሸበለለው፡፡ ይህች የተናቀች ሴተኛ አዳሪ፣ በአንድ ጀግና ንጉሥ ዕጣ ላይ መወሰን ትችል ዘንድ ህግ በሰጣት ዕድል ነፍሷ ተደስታ በሲቃ ስታነባ አየን፡፡
ሆኖም የምንኖረው ሕይወት እንደ ተውፊቅ አል ሀኪም  "The sultan’s dilemma" (መንታ መንገድ) የቀለለ አይደለም፡፡ በእርግጥ ፍትህ፣ ነጻነት በነጻ የለም፡፡ ፍትህ ያለ ዋጋ የሚገኝ አይደለም። ሲግመን ፍሮይድ፤ ያለ ፍትህ ስልጣኔ የሚታሰብ አይደለም ይላል፡፡ በቅርቡ በአንድ የድምጽ ማሰባሰቢያ ድረ ገጽ ላይ ያየሁት አሃዛዊ መረጃ አስደንቆኛል፡፡ ነገሩ ከገበሬና ከነጋዴ የሚል የአራተኛ ክፍል ክርክር ይመስላል፡፡  በዚህ ድረ ገጽ ላይ "ከፍቅርና ከፍትህ የቱ ለሰው ልጅ የበለጠ አስፈላጊ ነው?" የሚል ጥያቄ ነው የቀረበው። ከመላሾቹ መካከል 67% ያህሉ ፍትህን መርጠዋል፡፡ ሶቅራጥስም በዘመኑ ስለ ፍትህ በተጠየቀ ጊዜ እንዲህ ብሎ ነበር፡- ‹‹ፍትህ የሁሉም መልካም ነገሮች እናት (ምንጭ) ነች፡፡›› ፍቅር፣ ሰላም፣ አንድነት የመሳሰሉት ነገሮች ሁሉ ምንጭ ፍትህ ነች እንደ ማለት፡፡
ሌላም አንድ ትዝብት እነሆ… እኔ የቃና ቴሌቪዥን አድናቂ አይደለሁም፡፡ አንድ ቀን ግን የሆነ ምግብ ቤት ውስጥ እራት እየበላሁ ስመለከት የሚከተለውን አስተዋልኩ፡፡ ሰውየው ሁለት ህጻናት ልጆች ባሏት ምስኪን እንጀራ ልጁ ላይ የራሱ ልጅና ሚስቱ በሚያደርሱባት በደል ተበሳጭቷል፡፡ እናም ከእንጀራ ልጁ ጋር ሆኖ የሞቀ ቤቱንና ትዳሩን ትቶ በኪራይ ቤት መሰቃየት ጀመረ፡፡ ይሄ የደነቀው አከራዩ ጠጋ ብሎ፤ ‹‹ለምንድነው ቤትህንና ትዳርህን ትተህ የወጣኸው?›› ሲል ጠየቀው፡፡
ሰውየው መለሰ፡- ‹‹ምክንያቴ ፍትህ ነው፡፡ እነሱ ለሚያደርሱባት ኢ-ፍትሃዊ ነገር የግድ እኔ ከጎኗ ቆሜ ፍትህ መስጠት ነበረብኝ፡፡››
ፍትህ ከቤተሰብ ይጀምራል፡፡ እንደ ግለሰብም እንደ ሀገርም ለመቀጠል ፍትህ የግድ ያስፈልገናል፡፡ የመጀመሪያ ልጁ ሲያጠፋ ያልቀጣ አባት፣ ሁለተኛ ልጁን በተመሳሳይ ጥፋት የመቅጣት የሞራል ልዕልና አይኖረውም፡፡ ባንክ ሲዘረፍ ዝም ያለ መንግስት፣ ስልክ ነጥቆ የሮጠን አንድ ጎረምሳ ቢያሳድድ፣ ያኔ በእርግጥም ለፍትህ ልናለቅስ ይገባል፡፡ ፍትህ ግን እንደ ተውፊቅ አል ሀኪም  "The sultan’s dilemma" (መንታ መንገድ) በቀላሉ የሚደረስባት አልሆነችም፡፡ በዚህች ምድር ራሱ ኢየሱስን ጨምሮ ሶቅራጥስ፣ ማህተመ ጋንዲና ሌሎች ብዙ ሚሊዮናት ምንም የሚያስከስስ ወንጀል ያልነበራቸው ሰብዓዊያን በጭካኔ ተገድለዋል፡፡ አሁንም እስሩ ጉንተላው በማያናማር፣ ካምቦዲያ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ… ቀጥሏል፡፡ በእርግጥ ነጻነት፣ ፍትህ በነጻ የለም! ግን ምን ዓይነት ነጻነት? ምንስ ዓይነት ፍትህ? ገመቹ መልካ (ሞቲ ቢያ) የታሰረው፣ የተገረፈው በእርግጥ ለዚህ የመንጋ ፍትህ ነበርን?  
"The sultan’s dilemma" (መንታ መንገድ) ተውኔት ዘወትር እሁድ በ8 ሰዓት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ለተመልካች ሲቀርብ ነበር፡፡


Read 704 times