Monday, 05 July 2021 00:00

አገርና ጋዜጠኝነት ... ጋዜጠኛ ካሳሁን አሰፋ ሲታወስ

Written by  ሥንታየሁ ዓለማየሁ
Rate this item
(0 votes)

 እንደ ኢትዮጵያ ባለ ሰፊ ሀገር ውስጥ ፣ ከስፋትም ደግሞ ልዩ ልዩ ብሔር ብሔረሰብ ባለበት ሀገር ውስጥ፣ ብዝሃነትን ለተለያዩ ፖለቲካዊ ጥቅሞች ሲባል አሉታዊውን ጎኑን ብቻ የሚተነትኑ ልዩ ልዩ ሙያተኞች እንዲሁም ጋዜጠኞች በበዙባት ሀገር ውስጥ የሀገርን ክብርና አንደምታ ከሙያው ጋር ሳይጣረስበት እኩል ማስኬድ መቻል የሱ ገንዘቡና መገለጫው ነበር፡፡ ጋዜጠኝነት ማለት ከፖለቲካው ጋር ብቻ እንካ ስላንቲያ መግጠም አለያም ደግሞ ለገዢና ለተገዢ ብቻ ማጎብደድና ማነብነብ እንዳልሆነ፣ ይልቁንስ የሃገርን ሁለንተናዊ ገጽታ ለመግለጽ፣ ፍቅርንና ችሎታን ለማሳየት ሊገለገሉበት የሚያስችል ሙያ እንደሆነ በተግባር  አሳይቶን አልፏል፡፡
ጋዜጠኛ አራተኛ መንግስት ነው በሚባልበት በዚህ ክፍለ ዘመን፣ ሙያው የሚፈልገውን ስነምግባርና እውቀት ይዞ መንግስትነቱን ማሳየት መቻል ደግሞ እጅግ በጣም መታደል ነው፡፡ ሀገር ሙሉና ታላቅ የምትሆነው በየሙያው የተሰማሩ ግለሰቦች፣ ከሀገር አንጻር አስበው፣ ትልቁን ስዕል ተጋርተው፣ በትጋት ሲታትሩ ነው።  ጋዜጠኝነት ማለት ለሀገር ሲባል ልዩ ልዩ ጉዳዮችን መሞገት፣ መመርመር፣ መተንተን፣ ማቅረብ፣ ማሳየትና ማሳወቅ ነው፡፡ በነዚህ የሙያው ተፈጥሯዊ ሂደቶች ላይ የምናውቀውንና የምንወደውን ለይተን፣ ለምንወዳት ሀገር በሚገባት ልክ መሥራት ከጽድቅ ያህል የሚቆጠር የሙያ መሰጠት ነው፡፡ ሀገርና ሙያቸው ሳይጣረስባቸው አሳልጠው የሚያስኬዱ ሙያተኞች ደስ ይሉኛል፤ ለዚህ ደግሞ ጋዜጠኝነት ሁነኛ ይህንን አላማ ማሳኪያ መድረክ ይመስለኛል።
እሱ ከጋሞ ጐፋ ዞን ፣ ጋርዱላ አውራጃ፣ ጊዶሌ ከተማ ነው የተገኘው። ከአስተማሪነት እስከ ጋዜጠኝነት ባለፈባቸው ዘመናት ኢትዮጵያዊ ቀለሙንና ፍቅሩን አሳይቶናል። በፋና ሬዲዮ "ገጠመኝ እና ማስታወሻ" የተሰኘ ፕሮግራም ያሰናዳ ነበረ፤ ቀጥሎም ከፋና እንደወጣ በብስራት ኤፍኤም በሳምንት ለአራት ቀን የሚቀርብ #አሻም; የተሰኘ ተወዳጅ የሬዲዮ ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ ነበር። እንዲሁም ኢካሽ የሚባል የጋዜጠኝነት ማሰልጠኛ ተቋም ከጓደኞቹ ጋር በመክፈት፣ በሙያው ላይ የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት  ሲታትር የኖረ ነው።
በተለይ በብስራት ኤፍኤም "አሻም" በተሰኘው ፕሮግራሙ፣ ባህልና ኢትዮጵያዊነትን በተለያየ መልክ ሲያቀርብ፣ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍላተ ሀገር እየዞረ፣ በተግባር በአካል ያየውን የጎበኘውን ባህል፣ አኗኗር፣ ዘዬ፣ እምነት፣ ወግና ትውፊት ሲያስቃኘን ኖሯል። መልካምነትንና ያለንን መልከ ብዙ፣ ዘርፈ ብዙ አዎንታዊ ጉዳይ፣ በቅን ልቡ ቅን ሀገሩን በወደዳት ልክ እንድንወዳት፣ በጋዜጠኝነቱ በኩል አስተምሮናል፡፡
አገር በልጆቿ የምትኮራው፣ ኮርቶ የሚያኮራትና የሚያስከብራት፣ የሚሰራላትና የሚተጋላት - እንደ ካሳሁን ዓይነት ልጅ ሲኖራት ነው ብል ብዙም አልተጋነነም፡፡ በዚህ ጣቢያው ሁሉ በጫጫታ በተሞላበት አፍላ ዘመን፣ ቁምነገር ብርቅ በሆነበት፣ የሚዲያ ስራ አሊያም በአንድ ጉዳይ ላይ ብቻ የአድማጭ ጆሮ በሚተገተግበት ወይንም ረብ ያለው ሃሳብ በማይነሳበት በኛ ዘመን፣ የካሳሁን አሰፋ አይነት ጋዜጠኛ በጣት የሚቆጠሩ ናቸው።
ሙያን ለእውነት፣ እውነትን ለመልካምነት፣ መልካምነትን ለሀገር፣ ሀገርን ለልብ የቀረበ አድርጎ ለመስራት  ከጋዜጠኝነት በላይ ትልቅ እድል የሚያመቻች ስራ የለም፤ ነገር ግን ይህንን ለማድረግ ቁርጠኝነቱና ስነምግባሩ እንዲሁም እውቀቱ እየተሳነን ብዙዎቻችን ከመንገድ ተሰናክለናል። ሳይሰናከሉ የሚያሳኩ ግን እነሆ ብሩካን ይመስሉኛል። በተሰማራንበት የሙያ ዘርፍ በአግባቡ ሰርቶ ስኬታማ መሆን ግዴታችን መሆኑ ቢታወቅም ቅሉ፣ ይህንን ማድረግ ሲሳነን ጥቂት ስኬታማዎችን እንደ ብርቅ ለማየት እንገደዳለን፤ ከነዚህ ብርቅዬና አብሪ ኮከቦችና ቅን ሰዎች መሃል አንዱ ካሳሁን አሰፋ ነበረ። ዳሩ ምን ያደርጋል፤ ነበረ ማለት ቀሊል ሃሳብ የሆነበት ዘመን ላይ ሆንንና፣ እንደ ቀልድ ካስሽን "ነበረ" ለማለት ተገደድን።
ነገር ግን ሎሬቱ በግጥሙ፥-
የቃለ እሳት ነበልባሉ
አልባከነምና ውሉ
የዘር-ንድፉ የፊደሉ
ቢሞት እንኳ ሞተ አትበሉ።
--እንደሚል እኛም በውስጣችን ያስተማረን፣ የዘከረን፣ የገሰጸን ኢትዮጵያዊነት አልከሰመምና ካስሽን ቢሞት እንኳ ሞተ አንልም። ይልቁንስ በዚህ ፋንታ እንዲህ ብለን በንጉሱ አንደበት እናዜምለታለን፦
ሞት እንኳን ጨክኖ ወስዶ ከሚያስቀረው
ምናለ ደጋጉን ዳግመኛ ቢፈጥረው
ካሳሁን አሰፋ ልክ በዛሬዋ ቀን ሰኔ 26 ቀን 2012 ዓ.ም ነው ያረፈው፡፡ አሁን አንድ ዓመት ሞላው ማለት ነው፡፡ ነፍሱን በአጸደ ገነት ያኑርልን፡፡ መንፈሱና ስራው በውስጣችን አልሞተም፤ ይልቁንስ በመቀጣጠል ከትውልድ ትውልድ ይተላለፋል አንጂ።
ፕሌቶ ሲናገር፤ የኔ ዘላለማዊነት በሰው ልጅ ልብ ውስጥ ነው ብሏል (My eternity is in the grateful memory of men) በሰው ልጅ ልብ ውስጥ ዘላለማዊ ከመሆን በላይ ምን አለ?! ዘላለማዊነትን እንደ ካሳሁን አሰፋ ባለ የሙያ አክብሮት፣ ፍላጎትና እውቀት እንዲሁም ስነምግባር ልክ እንተግብር፡፡


Read 1654 times