Wednesday, 07 July 2021 19:30

ባይተዋር

Written by  ድርሰት - ክሃሊል አል ፉዛይ ትርጉም - ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(2 votes)

  "--የመንደሯ የግንብ አጥሮች በሙሉ በሆነ ዓይነት የመገለል፣ የመነጠል ስሜት ተሞልተዋል፡፡ አየሩ በጠላትነት ተወሯል፡፡ ተሰምቶኛል፡፡ ልነካው ሁሉ እችላለሁ፡፡ ክቡድ እና እውን ነው፡፡ ሆኖም ከዚህ በኋላ መቼም ይሁን መቼ መንደሯን ለቅቄ አልሄድም፡፡--"
             
             ወደ ተወዳጁ መንደሬ ለመመለስ በታገስኩባቸው ጊዜያት ሁሉ በህልቆ መሳፍርት የውስጤ ስሜቶች የመገናኘት የመተቃቀፍ ናፍቆት፣ ኮትኩቼ ያሳደግኩት የወዳጅነት ጥብቅ ትውስታዎቼ ጋር በሀሳብ ከራሴ ጋር  እየተጫወትኩ፣ በሮዝ ቀለም ሸላልሜ የሰራሁት ህልም ነበረኝ፡፡ እነዚያ ሁሉ ነገሮች ለተለየ ዓላማ የታቀዱ አልነበሩም፡፡ ሆኖም ሁሉም ወደ ተመላሹ እንግዳ በጠላትነት፣ በመረረና በከፋ ጥላቻ፣ በግልጽ ሁኔታ  ወደ ተቀሰሩ እጆች ተቀየሩ፡፡    
የወረቀት ፈረሶቼ ዳርቻ በሌለው ኦናነት ተንቀዋለሉ፡፡ ህልሞቼ ተሰባበሩ፤ የባህር ሞገዶች ከሰሙ፤ በእነርሱ ቦታ ግዙፍ የተቃውሞ፣ ያለመቀበል ተራራ ተገተረ። ሰዎች ይጠይቃሉ… ‹‹ተጓዡ ሰው እንዴት ከሃያ ዓመታት በኋላ ከማናቃቸው አካላት ትብብሩ ተመለሰ?››
ቀደም ባሉት ምሽቶች የመንደሩ አደባባይ በጤዛ የተሞላ ነበር፡፡ በውስጣችን ያንቀላፉት ተረቶች ከነትርክታቸውና ዝርዝራቸው ደጋግመን እናወራቸዋለን። በጨረቃ ብርሃን ወይም በእርሷ ምትክ በምናበራው ፋኖስ ታግዘን ምሽታችንን ጨርሰን ወደ ቤት ስንመለስ እያንዳንዳችን የአልፋታህ ወይም አል ቁርሲ የቁርዓን ጥቅሶች ይጠብቁን ነበር፡፡ ልጆች ነበርን። በጨረቃ ብርሃን ውስጥ እንጠጣለን፤ ወዳልታዩ መሬቶች እንሄዳለን፤ የጠፉ ዓለማትን እንዳስሳለን፡፡ ቢሆንም በመጨረሻ በመንደሯ አደባባይ ሌሊቱ እስኪገባደድ ድረስ እያወራን ራሳችን እናገኘዋለን። እናስ ጊዜ እነዚህን ውብ የልጅነት ጊዜ ትውስታዎችን መጋረድ  ይቻለዋልን?
አንድ ቀን ሌሎች እንደሚያደርጉት ሁሉ እኔም መንደሯን ጥዬ ሄድኩ፡፡ መንደሯን ደህና ሁኚ አልኳት፡፡ ለጊዜው መለስ ቀለስ እያልኩ እጎበኛት ነበር፡፡ ከዚያ ግን ወደ ሆነ ቦታ በጣም ርቄ ተጓዝኩ፡፡ የእኔ ምንም ዜና ለመንደሯ አይደርሳትም፤ የመንደሯም አንዲትስ እንኳን ዜና ለእኔ አይደርሰኝም ነበር፡፡ ግን ከቤት እየራቁ መሄድ ከልብም መነጠልን ያስከትላል፡፡ እናም ተመልሼ በመጣሁ ጊዜ ሁሉም ነገር ተቀይሮ ጠበቀኝ። መለወጡ አካላዊ፣ ቁሳዊ ብቻ ቢሆን ለመቀበል ቀላል ነበር፡፡ ነገር ግን ከዚህ በፊት አስቤው በማላውቀው ሁኔታ የተቀየረው የሰዎች ልብ ነበር፡፡
አንድ ያልተቀየረ ሰው ብቻ አገኘሁ። በተለመደ ፈገግታው መጥቶ ተገናኘኝ፡፡ የተፈራረቁት ዘመናት በገጽታው ላይ ምንም ለውጥ አልፈጠሩበትም፡፡
‹‹እስካሁን በሕይወት አለህ?›› አልኩት፡፡
‹‹የሕይወትን ምስጢር አግኝቼዋለሁ… ሞት የሚጠጋኝ አይመስለኝም፡፡››
‹‹እና የሕይወት ምስጢር ምንድን ነው?››
‹‹ከነገርኩህ እኮ ምስጢር መሆኑ ያበቃል።››
‹‹እንደ አንተ መኖር እፈልጋለሁ፡፡››
‹‹አትችልም፡፡››
‹‹ለምን አልችልም?››
‹‹ምክንያቱም ያንተ ትውልድ እኛ ሕይወትን የምናይበትን መንገድ መረዳት አይችልም፡፡››
‹‹ምን ማለትህ ነው?››
‹‹እነግርሃለሁ፡፡ እንደምታየው ከመቶ ዓመት በላይ ኖሬያለሁ፡፡ ከአንድ ሺህ በላይ ሴቶችን አውቃለሁ፡፡ አሁንም ግን ተጨማሪ ሴቶች እፈልጋለሁ፡፡››
በዚህ ነገሩ አልተገረምኩም፡፡ ከሀያ ዓመታት በፊት ጀምሮ ለሴቶች ያለውን ጥልቅ ፍላጎት አውቃለሁ፡፡ አሁንም ግን በሚያወራቸው ቃላትና በሕይወት ምስጢር መሀል ያለውን ግንኙነት ማየት አልቻልኩም።
‹‹ግን አትችልም›› አልኩት፤ እንዲናገር ላነሳሳው ፈልጌ፡፡
‹‹ያ አንተ የምታስበው ነው! ነግሬሃለሁ…ለሴት እሞታለሁ፡፡ አባቴ ምን እንደነገረኝ ታውቃለህ? ረጅም ሕይወት ለመኖር ከፈለክ  ምንጊዜም ቢሆን ሴትን መፈለግህን ቀጥል፡፡››
መልዕክቱን በአግባቡ ተረድቼዋለሁ፡፡
‹‹ግን ያ ሁሉም የተሳሳተ ነው፡፡›› አልኩ። ‹‹እነዚህን ልህቀ መረዳቶች ልጆችህ ላይም ላይ ልታጋባ ትፈልጋለህን?››
‹‹አይሰሙም፡፡ በአባባሎቼ ይሳሳቃሉ፤ ይቀልዳሉ፡፡ አንደኛው ልጄ ምን እንዳለ ታውቃለህ? በፌዝ መልክ ከሴት ጋር መሆን ፂምህን ሊያሳድግልህ ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ምንም ዕድሜ አይጨምርልህም አለኝ። ላስረዳው የቻልኩትን ሁሉ ጥሬያለሁ። ፂምህን ማሳደግ ከቻለ ሌላውንም ነገር፣ እድሜህን ጨምሮ የማያሳድግበት ምክንያት የለም ብየዋለሁ፡፡ ግን አላሳመነውም፡፡››
እስከ ሞት ድረስ በመጓጓት መልስ የምሻለትን ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡     
‹‹ለምንድን ነው ሁሉም ሰዎች እንዲህ  በጠበኝነት ስሜት የሚያዩኝ?››
‹‹ለምን እነሱን አትጠይቃቸውም?››  
‹‹ሊያናግሩኝም አይፈልጉም እኮ››
‹‹ከድተሃቸው ስትሄድ ይፈልጉህ ነበር፡፡ አሁን ተመልሰህ መጣህ፤ እነሱ ደግሞ ከዚህ በኋላ  አይፈልጉህም፡፡››
‹‹ለምን ነበር የሚፈልጉኝ?››
‹‹መንደሯ በጎርፍ የወደመች ጊዜ ሁሉንም ልጆቿን ትፈልግ ነበር፡፡ ከአንተ በስተቀር ሁሉም ሰው ተመልሶ መጥቷል፡፡››
‹‹የሆነ ሌላ ቦታ የራሴ ትግሎች ነበሩኝ፡፡ ለዛ ነው መምጣት ያልቻልኩት፡፡››
‹‹የትኛውም ትግል መሆን ያለበት ለመንደሯ ብቻ ነው፡፡››
ለመንደሬ ያለኝ ፍቅር ፈጽሞ አልቀዘቀዘም፡፡ ከመንደሯ ጋር ያለኝ ትስስር መላ ሕይወቴ ነው፡፡ አንድ ሰው እንዴት የራሱን ሕይወት ሊከዳ ይችላል? ለእነዚህ ሰዎች መሬቷን እንደማመልከው፣ ምድሪቱን ተደፍቼ መሳም እንደሚዳዳኝ አፈሩን ዘግኜ ፊቴ ላይ መነስነስ እስከመፈለግ ድረስ እንደምወዳት እንዴት ማሳየት ይቻለኛል?
ጥቂት ታዳጊዎች በዙሪያዬ ተኮልኩለው ከሌላ ፕላኔት የመጣሁ እንግዳ ፍጥረት እንደሆንኩ ሁሉ በመደነቅ ያዩኛል፡፡ ከመካከላቸው አንዱን ለማዋራት ብሞክር ሁሉም እንዳልለመደ የጫካ ፈረስ ደንብረው ከአጠገቤ እብስ አሉ፡፡ እዚህ ብቆይ ኖሮ ከእነዚህ ታዳጊዎች አንዱ የእኔ ልጅ ሊሆን በቻለ ነበር፡፡ እዚህ ብቆይ ኖሮ ሁሉንም በተለየ ፍቅር ላወራቸው በቻልኩ ነበር። እዚህ ብቆይ ኖሮ ሁሉም ነገር የሚቻል ይሆን ነበር፡፡
የመንደሯ የግንብ አጥሮች በሙሉ በሆነ ዓይነት የመገለል፣ የመነጠል ስሜት ተሞልተዋል፡፡ አየሩ በጠላትነት ተወሯል። ተሰምቶኛል፡፡ ልነካው ሁሉ እችላለሁ። ክቡድ እና እውን ነው፡፡ ሆኖም ከዚህ በኋላ መቼም ይሁን መቼ መንደሯን ለቅቄ አልሄድም፡፡

Read 1596 times