Wednesday, 07 July 2021 19:46

የእረኛ የብሶት ግጥሞች

Written by 
Rate this item
(3 votes)

  ግጥም የብዙ ስሜቶች መግለጫ ነው፤ የደስታም የሀዘንም። እረኞች ለውደሳ እንደሚገጥሙ ሁሉ ለእርግማን እና ውስጣዊ ብሶትን ለመግለጽም ይገጥማሉ። እንዲህ አይነት ውስጣዊ ስሜቶች በቀጥታ አይነገሩም፤ የሚነገሩት በዘፈን ውስጥ ነው። በነገራችን ላይ በንጉሣዊውም ሆነ በወታደራዊው (ደርግ) ሥርዓቶች አንዳንድ ዘፈን በመገናኛ ብዙኃን እንዳይተላለፍ ይታገድ ነበር  የሚታገድበት ምክንያት የሚያስተላልፈው መልዕክት የመንግሥትን ጥፋት የሚገልጽ ሲሆን ነው። በዘፈኖቹ ውስጥ በቀጥታ የመንግሥትን ስም በመጥራት ሳይሆን በቅኔ ለበስ በማድረግ ነው፤ ያም ሆኖ ግን እንዲህ ማለት ተፈልጎ ነው በሚል ይተረጎምና ይታገዳል። በእንዲህ አይነት የመንግሥት የጥርጣሬ ክልከላ መንግሥት የባሰ ወቀሳ ውስጥ ይገባል። ህዝብ በዘፈኑ ፖለቲካዊ መልዕክት ክርክር ውስጥ ይገባል። አንዳንዱ ይሄ ነው ትርጉሙ ሲል ሌላው የለም እንዲህ ለማለት ተፈልጎ ነው ይላል። በዚህም ምክንያት ዘፋኙ ያላሰበው ትርጉም ሊሰጥበት ይችላል። ይሄን በመፍራት ሀገርን በተቃራኒ ፆታ (በሴት) በመወከል መዝፈን የተለመደ ነበር።
የእረኛ ስነ ቃልም እንደዚሁ ነው። ሀሳብ የሚገለጸው ለሆነ ነገር ውክልና በመስጠት ነው። የሌላውን ብሶት ለማሰማት ራስን በቦታው በማድረግ ይገለጻል። ጭቆናን ለመግለጽ ነፃነት ናፋቂዎች ራሳቸውን የድርጊቱ ተሳታፊ ያደርጋሉ። ይህን ብሶታቸውን ለመግለጽ የሚመቻቸው ዘፈን ነው። በዘፈን ካልሆነ በቀጥታ መናገር አይችሉም። ለምሳሌ በሰው ቤት ተቀጥራ የምትሰራ ሴት ቀጣሪዎቿን ‹‹እንዲህ በደላችሁኝ!›› አትልም። ወፍጮ እየፈጨች ግን እንዲህ ብላ ትዘፍናለች።
ወፍጮው ውረድ ውረድ
ቋቱ ሙላ ሙላ
በዋዛ አይገኝም የሰው ቤት እንጀራ
ይህቺ ብሶተኛ ሴት  እንጀራዋ ያለው በሰራችው ሥራ ብዛት ላይ ነው። ጉልበቷ ሲደክም ቁጣና ማመናጨቅ ይደርስባታል። ቋቱ ካልሞላ እንጀራ ላትበላ ትችላለች። እንደ እናቷ ቤት በፈለገች ጊዜ ‹‹እንጀራ ስጡኝ›› ማለት አትችልም።
በተመሳሳይ በሰው ቤት ተቀጥሮ የሚሰራ እረኛ ብሶቱን የሚገልጸው በከብቶች ስም ነው። ከጓደኞቹ ጋር የሚነጋገር መስሎ ነው። እግረ መንገዱንም ነፃ መውጣትን ይሰብካል። ከድህነት ነፃ መውጣት ማለት ነው። ከድህነት ነፃ ለመውጣት ደግሞ ጠንክሮ መስራት ማለት ነው። ለዚህም ነው እንዲህ እያለ የሚያንጎራጉረው።
ከብቶችን ላኳቸው ወደ ጥቁር መሬት
የሰው ቤት እንጀራ ይመራል እንደ እሬት
ቀጣሪዎች (ባለሀብቶች) በተቀጣሪዎቻቸው ላይ የሚያደርሱት ግፍ እንጀራን ከእሬት ጋር የሚያወዳድር ነው ማለት ነው። ተቀጣሪ እረኛ የቀጣሪዎቹን የቁጣ ፊት ሲያይ የሚበላው እንጀራ እንደ እሬት ይመረዋል ማለት ነው። ልጃቸው ግን እንዲህ እየተሳቀቀ አይበላም፤ ልጃቸው የቱንም ያህል ሰነፍ ቢሆን እንደፈለገው ይናገራል፣ ይሞላቀቃል። ይሄ ተቀጣሪ ግን አመመኝ እንኳን ማለት አይችልም። ከእንዲህ አይነቱ ግዞት ነፃ ለመውጣት ነው የሚያንጎራጉረው።
እረኞች ብዙ ጊዜ ተቀጥረው በሚሰሩበት ቤት የሚደርስባቸውን በደል የሚገልጹት  በእንጉርጉሮ ነው ። አንጎራጓሪው  በውስጡ የታመቀውን ብሶትና ወደፊት ይሆናል ብሎ የሚገምተውን ችግር ከአዕምሮው አውጥቶ በመናገሩ ከችግሩ የተላቀቀ እየመሰለው ይረካል።
እረኞች ከብቶችን ሩቅ ቦታ ይዘው የሚሄዱ ከሆነ በጠዋት ተነስቶ ለእነሱ ምግብ አይሰራላቸውም። በጠዋት ሳይበሉ ከብቶችን ይዘው ይሄዳሉ። ምሳ የሚላክላቸው ከራባቸውና ከደከማቸው በኋላ ነው። በዚህ ጊዜ በርሃብ አንጀቱ ቢጠበስ
የሰው ቤት እንጀራ ምን ቢጋገር ብዙ
ሳይርብ አይገኝም ሳይቅበዘበዙ
እያለ ብሶቱን ይገልጻል። እረኛ በአካባቢው ነዋሪ ዘንድ ዝቅ ያለ ቦታ የሚሰጠው በመሆኑ ለእረኛ ተብሎ ምግብ አይሰራም። እረኛ ቤት ያፈራውንና የተገኘውን በልቶ ይውላል። ወጥ ከቤት ውስጥ አልቆ ከሆነ በአዋዜ ወይም በድልህ ተደርጐ በደረቅ እንጀራ ይሰጠዋል። ይህ አዋዜ መደጋገሙ ያሰለቸው እረኛ የውስጡን እንደሚከተለው በእንጉርጉሮ ቅሬታና ብሶቱን ይገልፃል።
ማታ በጨው በላሁ እንዲያው በደረቁ
ምሳም በጨው በላሁ እንዲያው በደረቁ
የሰው ቤት እንጀራ ይሄ ነበር ጠንቁ
ራቡና ጥሙ በዛብኝ ሁልጊዜ
የሚቀርበው ምግብ ወጥ የለው አዋዜ
እረኞች በተቀጠሩበት ቤት ውስጥ ከቀጣሪዎቻቸው ልጆች እኩል ምግብ አያገኙም። ለእረኞች ትንሽ ለዚያውም የልጆች ትርፍራፊና ያደረ ምግብ  ይሰጣቸዋል። በዚህ ጊዜ የከፋው እረኛ ብሶቱን ኦንዲህ ሲል  ይገልፃል።
እህቴ ትፍጭና እናቴ ትጋግረው
ይህን በልቷል ብላ የማትናገረው
አንቺ የሰው እናት ይብላሽ አረመኔ
ትኩሱን ለልጅሽ ያደረውን ለኔ
አንቺ የሰው እናት ጠባይሽ ግመኛ
አይቡን ለልጅሽ አጓቱን ለእረኛ
እያለ ያንጎራጉራል ።
እረኛው ቀኑን ሙሉ  የሚውለው ከብት ሲያግድ ነው። በተጨማሪም ይጎለጉላል ያርማል፣ ያጭዳል፣ ያበራያል እንዲሁም ሌሎች የቤት ውስጥ ሥራዎችንም ይሰራል። ይሄን ሁሉ ሲሰራ ውሎና ደክሞም ሰዎቹ የሰራ ስለማይመስላቸው ልፋቱን በሙሉ ገደል ይከቱበታል። በዚህ ጊዜ
ውሃ ወርዶ ወርዶ መቆሚያው አባይ
እናት ወልዳ ወልዳ ለሰው አገልጋይ
እውሃ ቢዶሉት አይሟሟም ኩበት
አይመሰገንም የድሃ ጉልበት
በማለት ብሶቱን  ያሰማል። በተጨማሪ በአካባቢው ብዙ መሬት ያለው ነገር ግን ጉልበቱ ከመድከሙ የተነሳ መሬቱን ማረስ ያልቻለ ሰው መሬቱን ማረስ ለሚችል ሰው በመስጠት አዝመራውን እኩል ይካፈላል። እነዚህን ሰዎች የተመለከተ እረኛ ቢከፋው ጊዜ ጉልበት ካለኝ የእኩል እየሰራሁ፣ እየተዘዋወርኩ እኖራለሁ ለማለት በግጥም ሃሣቡን ይገልጻል።
ሚስትም አላገባ ላሳብም አልቸኩል
የደከመ እያየሁ እገባለሁ የኩል
እያለ ከዚህ ሁሉ ችግር ዕድሜው ለእርሻ ሲደርስ የእኩል እየሰራ መኖር እንደሚችል ይገልጻል። ግጥሙን በብዛት የሚጠቀሙት በችግር ምክንያት ኑሮ የከበዳቸው፣ ትዳር መያዝ ያልቻሉ ሰዎች ናቸው። እርግጥ ነው የሀብታም ልጅ የሆኑትም ትዳር ስለመያዝ ስለማግባት ያንጎራጉራሉ። ለምሳሌ ቤተሰቦች ‹‹ገና ልጅ ነው ሲያድግ ነው የሚያገባው›› ሲሉ የሰማ እረኛ ጉርምስና ከተሰማው እንዲህ ይላል።
አፋፍ ለአፋፍ ስሄድ አገኘሁ እንኳይ
ያላደኩ እንደሆን አላገባም ወይ
እንኳይ ማለት የዛፍ አይነት ሲሆን ፍሬው የሚበላ እና በእረኞች የሚወደድ ነው። ይሄን ዘፈን በቁመታቸው አጭር ሆነው ትልቅነታቸው ያልታወቀላቸው እረኞችም ያንጎራጉሩታል። ‹‹ከዚህ በላይ የማላድግ (ቁመቴ የማይረዝም) ከሆነ ላላገባ ነው እንዴ?›› ብለው እየጠየቁ ነው። በነገራችን ላይ እረኞች ብሶታቸውን የሚገልጹት በድህነት የሚደርስባቸውን ብቻ አይደለም። ምናልባት አሳዛኝ ስለሆነ እና ችግሩም የከፋ ስለሆነ አንጀት ስለሚበላ እሱ ላይ አተኮርን እንጂ በፍቅርም ብሶታቸውን ይገልጻሉ። ፍቅር ግን እንደ ቅንጦት ስለሚታይ፤ በዚያ ላይ ድሃ እና ሀብታም፣ የተቸገረ እና ያልተቸገረ… ብሎ ስለማይለይ ከመዝናኛነት ያለፈ ብዙም ልብ አይባልም። ያም ሆኖ ግን የፍቅር ብሶትም በጥበብ ስሜትን መግለጽን ይጠይቃል። ደግሞስ ፍቅርን ተራ ነገር ያደረገው ማነው? ስለእረኞች የፍቅር ብሶትም ጥቂት እንበላችሁ።
እረኞች የጉርምስና ስሜት ላይ ሲደርሱ ፆታዊ ፍላጎት ይጀምራሉ። ይሄ ማለት ተቃራኒ ፆታቸውን ለማናገር መፈለግ፣ ፆታዊ መልዕክት ማስተላለፍ ማለት
ነው። ደግነቱ ግን እንደ አዋቂዎች አይደለም። አዋቂዎች በቀጥታ ለወሲባዊ ግንኙነት ሲሆን እረኞች ግን ልጅነትም ስላለ መልዕክቱን ብቻ ነው የሚያስተላልፉት። ልጃገረድና ባል ያላትን ሴት ግን  ደፍረው አይናገሩም፤ ነውርም ነው። ባል ያላትን ሴት ቀና ብሎ ማየት ትልቅ ነውር እንደሆነ ያምናሉ። ለዚህም ነው እንዲህ እያሉ ይጫወታሉ።
አጋሙን ግራሩን የፈጠርከው ጌታ
ሸጋ ሸጋውን ሴት አርገው ጋለሞታ
ጋለሞታ ማለት አግብታ የፈታች ማለት ነው። በአዋቂዎች ሲወራ እንደሚሰሙት ደግሞ ጋለሞታዎች ካገኙት ወንድ ጋር ሁሉ ይወሰልታሉ የሚል ሀሜት አለ። ለዚህ ሀሜት የዳረጋቸው የድርጊቱ ፈፃሚ ሆነው ሳይሆን ሁኔታው ነው። ሁኔታው ማለት፤ ለምሳሌ ባለትዳሮች ከባላቸው ጋር ስለሆኑ ይፈራሉ  ይከበራሉ፤ ይሄን አልፎ የሚሄድ ካለ ዱላ (ሲከፋም ጥይት) ይቀምሳል።  ያላገባችን ሴት ወይም ልጃገረዲቱን ደግሞ ለትዳር ካልሆነ በስተቀር ለውስልትና የሚጠይቅ ሰው የለም። ጋለሞታ የሚባሉት ግን ከሁለቱም ውጭ ናቸው። ቢያደርጉትም ባያደርጉትም ሁኔታውን መሰረት በማድረግ ይሄው እረኞች ሁሉ ይመኟቸዋል። ‹‹ሸጋ ሸጋውን ሴት አርገው ጋለሞታ›› ሲሉ እንደፈለገን እንናገር  ምኞታችንን እንግለጽ ማለታቸው ነው።
አንድ እረኛ የእረኝነት ጊዜው የሚያልቅበት የተቀመጠ የዕድሜ ገደብ የለም። ከእረኝነት የሚወጣው የጉርምስና ዕድሜ ላይ ደርሶ ሲያገባ ነው። ከማግባቱ በፊት ግን ከእረኝነቱ ወጣ እያለ ወደ ግብርና ሥራው ያመዝናል። በተለይም በገጠሩ የአገሪቱ ክፍል ደግሞ ከ18 ዓመት በታች ሆኖም ሊያገባ ይችላል። እናም ጉርምስና ሲጀማምረው አለማግባቱን መውቀስ ይጀምራል። ካገባ በኋላ እረኛ አይደለም። የሚመገበውና የሚተኛበት ሁሉ እንደበፊቱ የተገኘውን አይደለም። ሲያገባ የራሱ ጎጆ ይሰራል፤ አልጋ ይሰራል። ከዚያ በፊት ግን የሚተኛው መደብ  ላይ ነው። እናም ባልንጀሮቹ አግብተው እሱ ከቀረ እንዲህ ሲል ብሶቱን ይገልጻል።
አባት አልረገመኝ
እናት አልረገመኝ
የመደብ መኝታ ምነው ደጋገመኝ
የፍቅር ብሶት በወንዶች ብቻ ሳይሆን በሴቶችም ይገለጻል፤ እንዲያውም የሴቶች ንፁህ ፍቅር ነው። የወንዶች አንዳንዱ ፆታዊ ግንኙነትን መሰረት ያደረገ ነው፤ የሴቶች ግን ፍቅርን ብቻ የሚገልጽ ነው።
አንዲት ኮረዳ ያፈቀረችው ጎረምሳ ካለ እሷም ስሜቷን በእንጉርጉሮ ትገልጻለች። ከብት ጥበቃም ይሁን ሰብል ጥበቃ አብረው ይሄዳሉ። የሚሄዱት ተጠራርተው ነው። ይሄ ምናልባትም ልጅ እያሉ ነው፤ እየጎረመሱ ሲሄዱ እንዳይታወቅባቸው አይጠራሩም፤ ሌላ የመግባቢያ ኮድ ይጠቀማሉ።
አፋፉ ላይ ቆሜ ፉጨቴን ብለቀው
ወጣች ከነ ሊጧ ሳትለቃለቀው
እንዲሉ። ፉጨቱ የሚግባቡበት ቋንቋ መሆኑ ነው፤ በፉጨቱ ውስጥ ራሱ የሚግባቡበት ሌላ የተለየ ዜማ ይኖራል። ወደ ሴቶች እንመለስ።
አንዲት ኮረዳ የምትወደውን ልጅ ለማግኘት ሞክራ አልሳካላት ሲል እንዲህ በእንጉርጉሮ ስሜቷን ትገልፃለች።
አፋፉ ላይ ቆሜ ሸግዬ ብልህ
‹‹የለም ቆላ ወርዷል›› አሉኝ እባትህ
‹‹የማናት ምላሳም!›› አሉኝ እናትህ
ሸግዬ ደማሙ እኔን ወዳጅህ!
መጪዎቹ የሐምሌና የነሐሴ ወራት በተለይም ለልጃገረዶች እና ለጎረምሶች ልዩ የፍቅር ወራት ናቸው። እጅግ ይናፈቃሉ።  እነ አሸንዳ፣ አሸንድዬ፣ ሻደይ፣ ሶለል፣ ከሴ አጨዳ፣ እንቁጣጣሽ…. መጣን መጣን እያሉ  ነው። በሰላም ያድርሰን።

Read 2129 times