Print this page
Sunday, 11 July 2021 17:02

ኢሠመጉ በትግራይ ያለው የሠብአዊ መብቶች ጥሰት እንዳሳሰበው ገለፀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 የፌደራል መንግስት የትግራይ ክልልን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ፣ ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እየተፈፀሙ መሆኑን መረጃ እንዳለው የገለፀው የኢትዮጵያ ሠብአዊ መብቶች ጉባኤ(ኢሠመጉ)፣ መንግስት በክልሉ የሠብአዊ መብቶች መጠበቃቸውን እንዲያረጋግጥ አሳሰበ፡፡
ኢሰመጉ በአስቸኳይ መግለጫው፤ የፌደራል መንግስት ሰኔ 21 ቀን 2013 ጀምሮ የተናጥል ተኩስ ማቆም ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ፣ በክልሉ የመብራት ፣ስልክና ባንክ አገልግሎት እንዲሁም የየብስና የአየር ትራንስፖርት መቋረጡን፣ በዚህም በትግራይ የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የሚገኙ ተማሪዎችን ጨምሮ ኤርትራውያን ስደተኞች በምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ለማወቅ አስቸጋሪ  እንደሆነበት አመልክቷል፡፡
እስካሁን ከአለማቀፍ ተቋማት ባገኘው መረጃ  መሰረት፤በሽረ ከተማ  በርካታ ኤርትራውያን  ስደተኞች ላይ ግድያ ስለመፈፀሙ፣ በክልሉ የሚገኘው ታጣቂ ሃይል አሁንም የሠብአዊ ቀውሱን አባባሽ በሆነ ሁኔታ ለጦርነት ዝግጅት እያደረገ መሆኑንና በተለያዩ ንፁሃን ዜጎች ላይ ግድያ መፈጸሙን ኢሠመጉ በአስቸኳይ መግለጫው ጠቁሟል፡፡ አሁንም ክልሉን በተቆጣጠረው ታጣቂ ሃይል ዘርፈ ብዙ የሠብአዊ መብት ጥሰቶች ይፈፀማሉ የሚል ስጋት እንዳለውም ኢሠመጉ ገልጿል፡፡
በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ከተማ በአቲቪስቶች ጋዜጠኞችና የትግራይ ብሔር ተወላጆች ላይ እስራት እየተፈፀመ እንዲሁም የንግድ ቤቶች እየታሸጉ ስለመሆኑ ኢሠመጉ መረጃዎች እንደደረሱት አመልክቷል፡፡
እነዚህ ሁኔታዎች ለሀገሪቱ የሰብአዊ መብት አያያዝ ጥሩ እንድምታ የሌላቸው አስጊ ሁኔታዎች ናቸው ያለው የኢሠመጉ መግለጫ፤ መንግስት ሁኔታው የሚሻሻልበት አዎንታዊ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል፡፡
ኢሠመጉ በመግለጫው፤ በትግራይ ሁሉም ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ፣ ዩኒቨርስቲዎች የተማሪዎችን ደህንነት እንዲያረጋግጡና ለህብረተሰቡ ተማሪዎች ያሉበትን ሁኔታ በማስረጃ በዝርዝር እንዲያብራራ ጠይቋል፡፡
በተጨማሪም መንግስት የደህንነት ስጋት ባላቸው አካባቢዎች ተገቢውን ጥበቃ እንዲያደርግ፣እንዲሁም በአዲስ አበባ የሚፈፀሙ  እስራቶችና የሚወሰዱ እርምጃዎች በበቂ ምክንያት የተደገፉና ህጋዊ ሂደትን የተከተሉ መሆናቸው እንዲያረጋግጥ ያሳሰበው ኢሠመጉ፣፤ ለታሰሩ ሰዎች ፈጣን እልባት እንዲያበጅም  ጥሪ አቅርቧል፡፡

Read 10060 times