Sunday, 11 July 2021 17:04

በትግራይ ክልል የንፁሃን ሞትና ስደት ተባብሶ ቀጥሏል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(4 votes)

  • የመንግስት ደጋፊዎች ነበራችሁ የተባሉ ነዋሪዎች በአደባባይ እየተገደሉ ነው
       • የትግራይ ዲሞክራሲዊ ፓርቲ ከ20 በላይ አባሎቼ ተገድለውብኛል ብሏል
       • በራያ አዘቦ አካባቢ ከ50 በላይ የራያ ተወላጆች መገደላቸው ተገልጿል
       • ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ክልሉን ለቀው በእግራቸው ደሴ ገብተዋል
       • የትግራይ ወጣቶች ወደ ጎረቤት አገራት እየተሰደዱ ነው ተብሏል
                
          መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም በማወጅ መከላከያ ሰራዊቱን ከትግራይ  ማስወጣቱን ተከትሎ ወደ መቀሌ ከተማ የገባው የትግራይ ታጣቂ ኃይል፣ በክልሉ የሚኖሩ ንፁሃንን “የመንግስት ደጋፊዎች ነበራችሁ” በሚል እየገደለ እንደሚገኝ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ለአዲስ አድማስ እንደገለጹት፤ መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም አድርጎ መቀሌን ለቆ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በከተማዋ በአደባባይ ንፁሃን እየተገደሉ ነው፡፡
መንግስት የህግ ማስከበር ዘመቻውን ከመጀመሩ በፊት ከህውኃት አመራሮች ጋር ነገሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፈፀም ተደጋጋሚ ሙከራ ማድረጉን ያስታወሱት ዶ/ር አረጋዊ፤ በተለያዩ ጊዜያት የአገር ሽማግሌዎችን በመላክ ለሰላም ያለውን ፍላጎት ያሳየ ቢሆንም የህውኃት አመራሮች ለሰላም የተዘረጋውን የመንግስት እጅ በማጠፍ፣ ሽብርና ጦርነትን መርጠዋል- ብለዋል፡፡ መንግስት በአካባቢው ያለውን ሁኔታ ለማረጋጋትና በህውኃት አመራሮች የፈራረሰችውን ትግራይን መልሶ ለመገንባትና የዜጎችን ህይወት ከአደጋ ለመታደግ ከፍተኛ ጥረት  ሲያደርግ ቢቆይም የተወሰኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ከታጣቂ ሃይሎች ጋር በማበር፣ ተደጋጋሚ ችግሮችን በመፍጠራቸው መንግስት የመከላከያ ሃይሉን ከመቀሌ ከተማ ለማስወጣት መገደዱን ተናግረዋል፡፡ የመንግስት መከላከያ ሃይል መቀሌን ለቆ ቢወጣም፣ በሌሎች የትግራይ ክልሎች ውስጥ አሁንም እንደሚገኝና ህዝቡን ከአደጋ የመጠበቅ ስራውን እየሰራ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
የትግራይ ህዝብ ከአራት አቅጣጫ በሚመጣ ጉዳት እየተጎዳ ነው ያሉት ዶ/ር አረጋዊ፤ በአሸባሪው ታጣቂ ሃይል የሚደርስበት ስቃይ ሞትና ስደት ማብቂያው ያሳስባል ብለዋል፡፡ ህዝቡ በጦርነት፣ በረሃብና በስደት እየተሰቃየ መሆኑን ጠቁመው፤ በርካታ የትግራይ  ወጣቶች ወደ አፋር ኤርትራና ሱዳን እየተሰደዱ ናቸው-ብለዋል፡፡
ታጣቂ ሃይሉ “የመንግስት ደጋፊዎች ነበራችሁ” በሚላቸው ወገኖች ላይ በአደባባይ ኢ-ሰብአዊ የሆነ የግድያ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን የጠቆሙት የፓርቲው ሊቀመንበር፤ ለዚህም እምብዛ የተባለው ተወዳጅ አርቲስት ላይ የተፈጸመው ዘግናኝ ወንጀል ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ወጣቱ አርቲስት “ከመንግስት ሃይሎች ጋር ሰርተሃል” በሚል ሰበብ በአሸባሪ ሃይሎች በጩቤ ታርዶ ከተገደለ በኋላ አስክሬኑን ለጅቦች እንዲሰጥ መጣሉን የተናገሩት ዶ/ር አረጋዊ፤ ይህን ሁኔታ ለመቀበልና ለማየት ያልቻሉ የአካባቢው ሰዎች አስክሬኑን ከወደቀበት አንስተው መቅበራቸውንና በዚህ ሳቢያም  ከፍተኛ ዋጋ  መክፈላቸውን ገልፀዋል፡፡
 እነዚሁ ሃይሎች አስክሬኑን የቀበሩት ሰዎች አድኖ በመያዝና በመደብደብ “የቀበራችሁበትን ቦታ መርታችሁ አስክሬኑን አውጡ” በማለት  አስክሬኑን ከተቀበረበት  አስወጥተው እጅግ ዘግናኝ በሆነ መንገድ ቆራርጠው ለጅቦች እንዲሰጥ አድርገዋል፤ ይህም  በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ ዘግናኝና አረመኔያዊ የሆነ ወንጀል ነው ሲሉም ዶ/ር አረጋዊ ከሰዋል፡፡
በክልሉ የንፁሃን ሞት በየዕለቱ ተባብሶ መቀጠሉን የገለፁት ዶ/ር አረጋዊ፣ የትግራይ ዲሞክራሲዊ ፓርቲ አባላት የሆኑ ከ20 የሚበልጡ ሰዎች ከቤተሰቦቻቸው መሃል እየተወሰዱ በአደባባይ ተገድለዋል ብለዋል፡፡ ዛሬም ድረስ በትግራይ በተለይም በመቀሌ ከተማ በየቀበሌውና በየወረዳው ንፁሃን በግፍ እየተገደሉ መሆኑንም ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
የራያ ራዩማ ዲሞክራሲዊ ፓርቲ በበኩሉ፤ የአገር መከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ክልል ከወጣ በኋላ በህውኃት ሃይል ቁጥጥር ስር የወደቀው በደቡባዊ ትግራይ የሚገኘው የራያ ዘቦ አካባቢ  ተወላጆች ለሞትና ስደት መዳረጋቸውን አመልክቷል፡፡ እስካሁንም ከ50 በላይ  ንፁሃን የአካባቢው ተወላጆች መገደላቸውንና ከ30ሺ በላይ የሚሆኑ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ለስደት መዳረጋቸው ተገልጿል፡፡
መቀመጫውን በአዲስ አበባ አድርጎ አለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶችን ጨምሮ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ የሚገልፀው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፤ የህውሃት ታጣቂ ሃይሎች በክልሉ ህዝቦች ላይ እያደረሱ ያሉትን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊያወግዝ እንደሚገባ አመልክቷል፡፡
መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ክልሉን ለቆ ከወጣ በኋላ በክልሉ ለው ተጨባጭ ሁኔታ እጅግ አስከፊ እየሆነ መምጣቱን የጠቆመው ጊዜዊ አስተዳደሩ፤ በተለይም የጊዜያዊ አስተዳደሩን የህይወት አድን ተልዕኮ ጥረት ሲያግዙ የነበሩ በርካታ ዜጎች በታጣቂ ቡድኑ መገደላቸውን ገልጿል፡፡ ባለፉት ሰባት ወራት በራያ፣ በእንደርታ፣ በመቀሌና አዲግራት በበጎ ፈቃደኝነት ህዝቡን ሲያገለግሉ የነበሩ ባለሙያዎችና ቤተሰቦቻቸው የታጣቂ ቡድኑ ኢላማ መሆናቸውንም ጊዜያዊ አስተዳደሩ አመልክቷል፡፡
መከላከያ ሰራዊት ክልሉን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ፣ በትግራይ ክልል ውስጥ በተፈጠረው ቀውስ ሳቢያ የሞቱ፣ የተደፈሩ፣ የተሰደዱና ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ወገኖች ቁጥር ከእለት ተእለት እየጨመረ መሄዱን የጠቆመው ጊዜያዊ አስተዳደሩ፤ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ሁኔታው በፅኑ እንዲወግዝ ጥሪ አቅርቧል፡፡ በርካታ የትግራይ ወጣቶች ወደ ሱዳን፣ ኤርትራና አፋር እየተሰደዱ ነው ብሏል፡፡ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ኤጄንሲ በበኩሉ፤ በአካባቢው የተከሰተውን ቀውስ ተከትሎ፣ በርካታ የትግራይ ወጣቶችና በተለያዩ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ተጠልለው የነበሩ ኤርትራውያን ስደተኞች ወደ ጎረቤት አገራት እየተሰደዱ መሆናቸውን አመልክቷል፡፡
በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች በእግራቸው ክልሉን እየለቀቁ በመውጣት ወደ  ወሎና አፋር አካባቢዎች እየገቡ ሲሆን እስካሁን በመቶዎች የሚቆጠሩ  የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በተለያዩ አቅጣጫዎች ክልሉን ለቀው መውጣታቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በዩኒቨርስቲ ግቢ ውስጥ የመንግስት ደጋፊና ተቃዋሚ የሚል መደብ ተፈጥሮ በርካታ ተማሪዎች በታጣቂ ሃይሎቹ ታፍነው ተወስደዋል ያሉት ምንጮች፤ ለተማሪዎቹ ደህንነት ሃላፊነት የሚወስድ አንድም አካል አለመኖሩ አሳሳቢ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
በመቀሌው ሃይደር ሆስፒታል ውስጥ የተግባር ትምህርት ላይ የነበሩና ዘንድሮው የሚመረቁ ተማሪዎችን ጨምሮ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ብቻ ከ30 በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች በእግራቸው ደሴ ከተማ መግባታቸውን እነዚሁ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡  በእግራቸው በተጓዙባቸው አካባቢዎች ላይ የነበሩ የትግራይ ክልል ህዝቦች ከፍ ያለ ሰብአዊ ርህራሄና ፍቅር ያሳይዋቸው መሆኑንም ምንጮቻችን ገልፀዋል፡፡
ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም መንግስት ያለቅድመ ሁኔታ የተናጥል ተኩስ አቁም አውጆ  ሰራዊቱን ከክልሉ እንዲወጣ ካደረገ በኋላ የትግራይ ክልል በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ መግባቷንና  በመንግስት በወንጀል   የሚፈለጉ የህውኃት አመራሮች ወደ ከተማዋ  መግባታቸው ታውቋል፡፡

Read 10200 times