Sunday, 11 July 2021 17:05

ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ በፀጥታው ምክር ቤት ድል ቀናት

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(7 votes)

 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት  የጸጥታው ምክር ቤት ጉባኤ በህዳሴው ግድብ ላይ የቀረበለትን ክስ ከተመለከተ በኋላ አገራቱ ጉዳያቸውን በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ሊቀጥሉ ይገባል ሲል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
“የአባይን ልጅ ውሃ ጠማው…” በሚለው አገራዊ ብሂል ንግግራቸውን የጀመሩት የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ፤ “የፀጥታው ምክር ቤት በግድቡ ዙሪያ ሲነጋገር ይህ የመጀመሪያው ሊሆን እኔም በዚህ ምክር ቤት ተገኝቼ ያስረዳሁ የመጀመሪያው የውሃ ሚኒስትር ሳልሆን አልቀርም” ብለዋል፡፡ ጉዳዩ ወደ ምክር ቤቱ መምጣቱ በራሱ አግባብ አለመሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ እየገነባን ያለነው የውሃ ግድብ እንጂ የኒውክሌር ማብላያ አይደለም ሲሉ ጉዳዩ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት መምጣት አልነበረበትም ብለዋል፡፡
“ግድቡን እየገነባን ያለነው በድሃው ህዝባችን ላብ፣ ደምና እንባ ነው፡፡ ይህ ግድብ ሰሞኑን በባዶ እግራቸው ከአረብ አገራት የተባረሩ ዜጎቻችንን ነፃ የሚያወጣና ሰብአዊ ክብራችንን የሚመልስ ነው” ብለዋል- በንግግራቸው፡፡
“በተለያዩ አገራት ተሰደው የሚኖሩ የተሻለ ህይወት ፍለጋ ሲንከራተቱ የባህር ሲሳይ የሆኑ፣ በየኮንቲነሩ አየር አጥተው የሚሞቱ የኢትዮጵያ ልጆች በአገራቸው ኮርተው መኖር ያምራቸዋል፡፡ ደግሞም ይገባቸዋል፡፡” ሲሉም አክለዋል፡፡
በምክር ቤቱ ሃሳባቸውን የገለፁት የግብፁ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሽኩሪ በበኩላቸው በህዳሴ ግድቡ ሳቢያ ከ100 ሚሊዮን በላይ ግብፃውያን ከባድ የውሃ እጥረት አደጋ ተደቅኖባቸዋል፤ የዜጎቻችን የወደፊት እጣ ፋንታ ከግምት ይግባልን” ብለዋል፡፡
“የተፈጠረብንን ችግር በአፍሪካ ህብረት ለመፍታት ብንሞክርም አልተሳካልንም፤ ኢትዮጵያም ያለ ስምምነት ግድቡን መሙላቷን ቀጥላለች፡፡ አለማቀፉ ማህበረሰብና የፀጥታው ምክር ቤት እንዲያደራድረን ያቀረብናቸውን ጥሪዎች ኢትዮጵያ ውድቅ ስታደርግ ቆይታለች። አገሪቱ ፍላጎቷ ናይልን መቆጣጠርና ፖለቲካዊ ተፅዕኖ መፍጠር ነው-” ብለዋል የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ፡፡ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የውሃ ሙሌት ያደረገችው በተሰላ መንገድ ጉባኤው ከመጀመሩ 3 ቀናት በፊት መሆኑ አገሪቱ ለስምምነት ፍላጎት እንደሌላት የሚያሳይ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
“ኢትዮጵያ ነገሮችን ከቀኝ ግዛት ውል ጋር እያያያዘች ውድቅ ስታደርግ ቆይታለች ያሉት ሳሜህ ሽኩሪ፤ አገሪቱ ቅኝ ተገዝታ የማታውቅ ሲሆን ፍላጎቷ ያልተገደበ የውሃ  አጠቃቀም መብት በእጇ ማስገባትና በቀጣይ የፈለገችውን ተጨማሪ ግድብ መገንባት ነው፤ ይህንንም የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር “100 ግድቦችን እንገድባለን” በማለት አረጋግጠውታል፡፡ ጠ/ሚሩ ይህንን ሲናገሩ የኛን ጉዳይ ምንም ሳያገናዝቡ ነበር፤ አሁንም አሳሪ ስምምነት ላይ መድረስ እንድንችል አውሮፓ ህብረት፣ ፣ የተባበሩት መንግስታትና አሜሪካ በድርድሩ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ እናቀርባለን” ብለዋል። በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት የሚካሄደው ድርድር ምንም ውጤት እንደማያመጣም አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
በምክር ቤቱ ሃሳባቸውን የገለጹትና ቀደም ሲል ከግብፅና  ሱዳን  ጎን በመሆን ኢትዮጵያ በግድቡ ላይ በምታደርገው ድርድር ላይ ጫና ሲደርጉ የቆዩት አሜሪካና አየርላንድን ጨምሮ በርካታ አገራት ከግብፅ በተቃራኒው ወገን ቆመው ታይተዋል፡፡
አሜሪካ በተወካይዋ አማካኝነት ጉዳዩ እልባት ማግኘት ያለበት  በአፍሪካ  ህብረት አደራዳሪነት መሆኑን ገልፃለች፡፡ እንግሊዝ በበኩሏ፤ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት የሚመራው ድርድር ውጤታማ እንዲሆን ጠንካራ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቃለች፡፡ ሀገራቱ የተፈጥሮ ሀብትን በአለም አቀፍ መርሆች ላይ ተመስርቶ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ እንዲለማ የሚደረጉ ድርድሮችን እንደምትደግፍም በተወካይዋ አማካኝነት ገልጻለች፡፡
አየርላንድ ድርድሩ ወደ አፍሪካ ህብረት ተመልሶ መካሄዱን እንደምትደግፍ ገልፃ፤ አውሮፓ ህብረትም የታዛቢነት ሚናውን ይወጣል ብላለች፡፡
 በተወካይዋ አማካኝነት አቋሟን ያንፀባረቀችው አፍሪካዊቷ ኬኒያ፤ ድርድሩ ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ በሚለው መርህ መሰረት መካሄድ እንዳለበት ገልፃለች፡፡
ህንድ በበኩሏ፤ አለመግባባቱ በሶስቱ አገራት በኩል በአፍሪካ ህብረት ስር በሚደረግ ድርድር ሊፈታ እንደሚገባና ሌሎች አገራትም ድርድሩን በማስተባበር ረገድ ድጋፍ ሊሰጡ እንደሚገባ አመልክታለች፡፡
ሩሲያ ጉዳይ ዕልባት ማግኘት ያለበት ሶስቱ ሀገራት በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በሚያደርጉት ውይይት እንጂ በሌሎች አገራት  ጣልቃ ገብነት ሊሆን እንደማይገባ አስታውቃለች፡፡


Read 9527 times