Tuesday, 13 July 2021 00:00

ውሉ የጠፋው የትግራይ ቀውስና የመፍትሔ ሃሳቦች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 ትግራይ የአሸባሪዎች መናኸርያ እንዳትሆን የሰጉ አሉ
                      
           መንግስት በገዛ ፈቃዱ ትግራይንና መቀሌን ለቆ መውጣቱን ካረጋገጠ በኋላ ራሱን “የትግራይ መከላከያ ሃይሎች” ብሎ የሚጠራው ቡድን፤ መቀሌን ጨምሮ የተለያዩ የትግራይ አካባቢዎችን በሃይል መቆጣጠሩን አስታውቋል፡፡
በጦርነቱ በአሰቃቂ ሁኔታ ሞተዋል ተብለው የነበሩት የቀድሞ የህውሐት ሊቀ መንበርና የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል ከሰሞኑንበክልሉ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው መግለጫ  መስጠታቸውም ተነግሯል፡፡ በሌላ በኩል፣ ሠኞ ሰኔ 28 ቀን 2013 ከአሶሴትድ ፕሬስ ጋር በስልክ ቃለ-ምልልስ ያደረጉት ዶ/ር ደብረፂዮን፤ በፌደራል መንግስት የተወሰደውን የተናጥል ተኩስ አቁም እርምጃ አጣጥለዋል፡፡
“በጦርነቱ አሸንፈን እንጂ በተኩስ አቁም አይደለም ትግራይን ነፃ እያወጣን ያለነው ያሉት ዶ/ር ደብረፂዮን፤ “ትግላችንም የ6 ሚሊዮን ህዝብ መኖሪያ የሆነውን የትግራይ ክልልን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እስከ መጨረሻው ማረጋገጥ ይሆናል ብለዋል፡፡
“ወራሪዎች ከግዛታችን ተጠራርገው እስኪወጡ ውጊያው ይቀጥላል” ያሉት የቀድሞው የህወኃት ሊቀ መንበር “ሚሳየልን ጨምሮ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ታጥቀናል፤ ከፈለግን በማንኛውም ጊዜ እንጠቀመዋለን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በበኩላቸው፤ ባለፈው ሰኞ በፓርላማ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤ መከላከያ ሰራዊት ከትግራይ በገዛ ፈቃዱ መውጣት የጀመረው ከሁለት ሳምንታት ቀደም ብሎ መሆኑን አመልክተው፤ መከላከያው ፈጽሞ በጦርነቱ ተሸንፎ ትግራይን ለመልቀቅ አልተገደደም ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል ከፌደራል መከላከያ ሰራዊት አቅም ጋር የሚገዳደር ሃይል ለመገንባት ሞክሮ የነበረው ህውሐት፤ አሁን  ተንኮታኩቶ እዚህ ግባ የሚባል ጉዳት ማድረስ የማይችል ሃይል መሆኑን ጠቁመው ቡድኑ አሁን ላይ ለኢትዮጵያ ህልውና የከፋ ስጋት አይደለም ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡
የትግራይ ሁኔታም ከፌደራል መንግስቱ ቁጥጥር የማይወጣና መከላከያ ሰራዊት በፈለገ ጊዜ ሙሉ ትግራይን መልሶ መቆጣጠር እንደሚችልም ጠ/ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ አስገንዝበዋል፡፡ የመከላከያ ከፍተኛ አዛዦችም  ሰራዊቱ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ትግራይ ገብቶ ህግ ለማስከበር ምንም የሚያግደው ሃይል እንደሌለ አረጋግጠዋል፡፡
ይሁን እንጂ ራሱን” የትግራይ መከላከያ ሃይል” ብሎ የሚጠራው ታጣቂ፤ ጦርነቱን ወደ ደቡብና ምስራቅ ትግራይ የመቀጠል አላማ እንዳለው ባስታወቀ ማግስት፣ ከአማራ ክልል በሚዋሰንባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ትንኮሳዎች መፈጸሙንና በአማራ ክልል ልዩ ሃይል ተመትቶ መመለሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ይህን የታጣቂውን ትንኮሳ ኢትዮጵያ መንግስት የወሰደውን የተናጠል ተኩስ አቁም ያደነቀው የአሜሪካ መንግስትና የተባበሩት መንግስታት ኮንነዋል፡፡ ታጣቂው ከማናቸውም ትንኮሳዎች እንዲታቀብ አስጠንቅቀዋል፡፡
ዓለማቀፍ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ሂውማን ራይትስ ዎችም ታጣቂው ሃይል አሁንም ጦርነት የማድረግ ፍላጎት እንዳለው ማረጋገጡን፤ በዚህም ሳቢያ  ከፍተኛ የሰብአዊ ቀውስ ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት እንዳደረበት ገልፆ በታጣቂ ቡድኑ ጠብ አጫሪነት ለሚፈጠሩ ችግሮች ሃላፊነት እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡
 ከስምንት ወር ገደማ በኋላ በታጣቂ ሃይሉ እጅ የወደቀችው ትግራይ፣ የአሸባሪ ሀይሎች መናኸሪያ እንዳትሆን የሰጉ አለማቀፍ ተቋማትም አሉ፡፡ ለአብነትም  ክራይስስ ግሩፕ፤ የተባለው ግጭቶችን የሚያጠና ተቋም እንደገለፀው፤ ትግራይ በጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት ስር ካልሆነች፣ የአሸባሪ ሃይሎች መጠለያ እንዳትሆን ያሰጋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፎች ማስተባበሪ ጽ/ቤት በበኩሉ፤ የመከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ለቆ መውጣቱን ተከትሎ፣ የክልሉን የሰብአዊ ድጋፍ ሁኔታ በገመገሙበት ሪፖርቱ፤ የታጣዊዎቹ እንቅስቃሴ የዜጎችን ህይወት በከፋ ሁኔታ ሊያጎሳቁል ይችላል ብሏል፡፡ በአሁን ወቅትም ለተረጂዎች እርዳታ በአግባቡ እየደረሰ አለመሆኑን በማመልከትም፣ ሰብአዊ ቀውሶች አፋጣኝ መፍትሄ እንዲፈለግ አሳስቧል፡፡
የመፍትሔ መንገዶች እንዴት ይፈለጉ?
በችግሮችና ቀውሶች መደራረብ ውሉ የጠፋበት የመሰለው የትግራይ ቀውስ፣ አንዳች መፍትሄ ማግኘት እንዳለበት የተለያዩ አካላት አበክረው እየወተወቱ ይገኛሉ፡፡ መፍትሔ የመሰላቸውንም  ሃሳብ እየሰነዘሩ ነው፡፡ የፌደራል መንግስት በጊዜያዊ መፍትሄነት የተናጠል ተኩስ አቁም በማድረግ፣ ለህዝቡ የጥሞና ጊዜ መስጠትን የመረጠ ሲሆን ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ያስቀመጠው ፍኖተ ካርታ እስካሁን የለም አብዛኛው የታጣቂ ሀይል “ጦርነቱ አልበቃኝም፤ አሁን እቀጥላለሁ” ማለቱ የተሰማ ሲሆን፤ እንደነጀነራል ፃድቃን ገ/ትንሳኤ ያሉ ያሉት ደግሞ “ግዴለም አሁን ጦርነቱ ይብቃና ፖለቲካዊ መፍትሄ ይፈለግ” እያሉ ነው ተብሏል፡፡
በጦርነቱ ልቀጥል የሚለው ሃይል የመጨረሻ ግቡ አድርጎ ያስቀመጠው ዶ/ር ደብረፂዮን እንዳሉት፤ የትግራይን ግዛት ነፃ ማውጣትና የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትን ማረጋገጥን ነው፡፡
ይህም ነፃነቷንና ራሷን የቻለች ሃገረ ትግራይን እስከ ማቋቋም  ሊዘልቅ እንደሚችል የቀድሞ የህውሃት ከፍተኛ አመራር አቶ ጌታቸው ረዳ በተደጋጋሚ ገልጸዋል፡፡
ከህወሐት ጋር ፀብ ላይ ቆይተው በለውጡ ማግስት እርቅ ያወረዱት የቀድሞ የጦር ሃይሎች ኢታማዦር ሹም ሌ/ጀነራል ፃድቃን ገ/ትንሳይ በበኩላቸው፣ ችግሩ በፖለቲካዊ ድርድር መፍትሄ እንዲያገኝ ይፈልጋሉ፡፡ “ጦርነትና የሃይል አካሄድ ከእንግዲህ አዋጪ አይሆንም” የሚል አቋም መያዛቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ሌሎች ተፅዕኖ ፈጣሪ ኢትዮጵያውያንና አለማቀፍ ተቋማትም በትግራይ ጉዳይ ጊዚያዊ መፍትሄዎች ይልቅ በዘላቂ መፍትሄዎች ላይ እንዲተኮር እያሳሰቡ ነው፡፡ የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሀፊ  አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ከሰሞኑ በጉዳዩ ላይ በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት እውነተኛ የተኩስ አቁም ስምምነት በሁለቱም ወገኖች እንዲደረስ፣ ከዚያም ሲያልፍ ግጭቱ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ ድርድር ይካሄድ ዘንድ ተማጽነዋል፡፡ የአሜሪካ መንግስትም ተቀራራቢ ሃሳብ አንጸባርቋል፡፡
ይህን በአዎንታ የተቀበለ የሚመስለው መንግስት በበኩሉ ፤በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ከትግራይ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ለእውነተኛ ሰላም ፍላጎቱ ካላቸው የህውሃት አባላት ጋር ለመደራደር ፍላጎት እንዳለው  ባለፈው ሳምንት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን በኩል ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
የታጣቂ ሀይሉ  ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ፤ ጦርነቱን አቁሞ ለመደራደር ሰባት ቅድመ ሁኔታዎችን እንዳስቀመጡ ይናገራሉ። ከእነዚህም መካከል የአማራ ልዩ ሃይልና የኤርትራ ሰራዊት ከጦርነቱ በፊት ከነበረው የትግራይ ግዛት ሙሉ በሙሉ ይውጡ፣ በትግራይ የደረሰ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ አካል ተጣርተው በጦርነቱ የተሳተፉ አለማቀፍ ፍ/ቤቶች ይቅረቡ፣ የ2013 ዓመት በጀት ይለቀቅልን እንዲሁም የታሰሩ የቀድሞ የህወሐት አባላት ይፈቱልን የሚሉ  ቅድመ ሁኔታዎች ይገኙባቸዋል፡፡
ሌሎች ስለ መፍትሔው ምን ይላሉ?
የኢዜማ እጩ የምርጫ ተወዳዳሪ የነበሩት አቶ ክቡር ገና፤ የአመራር ውድቀት እያጋጠመን መሆኑ የትግራይን ሁኔታ አስቸጋሪ አድርጎታል ባይ ናቸው፡፡
በጠ/ሚኒስትሩ የአመራር ጉድለት ትግራይ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል እያደረጉ ያሉ ሁኔታዎች መኖራቸውን የሚገልጹት አቶ ክቡር፤  የጠ/ሚኒስትሩ መግንስት በትግራይ ለተከሰተው ቀውስ ከሃላፊነት ለመሸሽ እያደረገ ያለው ሙከራ ተገቢነት እንደሌለውና ሞራላዊ እንዳልሆነ ይገልፃሉ፡፡
የትግራይን ቀውስ ለመፍታትም ከህግ ባለሙያዎች፣ ከዳኞች፣ ከምሁራን፣ ከመንግስት ተቋማት፣ ከተቃዋሚ ፖለቲከኞች የተውጣጣ፣ የጦርነቱን መንስኤ ስረ መሰረት መርምሮ መፍትሄ የሚያመላክት ግብረ ሃይል አቋቁሞ፣ ወደ ስራ ማስገባት ወደ መፍትሄው ያደርሳል ባይ ናቸው፡፡
በዚህ ሂደት ተጠያቂ መሆን ያለባቸውም እንደ ጥፋታቸው ልክ ተጠያቂ የሚሆኑበት አሰራር ሊዘረጋ እንደሚችል አቶ ክቡር ባመላከቱት የመፍትሄ ሃሳብ ጠቁመዋል፡፡
የሰብአዊ መብት ተሟጋችና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ጥምረት መሪ የሆኑት አቶ ያሬድ ኃ/ማርያ በበኩላቸው፤ “ይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ ዛሬም ትግራይ የእርስዎ እዳ ነች” ሲሉ በፃፉት መልእክታቸው፣ መከላከያው ከትግራይ መውጣቱና የወጣበት ሂደት… ጥያቄን የሚያጭሩ  መሆናውን ጠቁመው፤  በትግራይ ለተፈጸመው ሁሉ መንግስት ተጠያቂነት እንዳለበት አመልክተዋል፡፡ ለችግሩም የጋራ መፍትሄ መፈለግ ያሻል ብለዋል፡፡

Read 2978 times