Sunday, 11 July 2021 17:32

107 ዓመታትን ያስቆጠረ ፍጥጫ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 በ47ኛው ኮፓ አሜሪካ የፍፃሜ ጨዋታ ላይ ሁለቱ የደቡብ አሜሪካ ኃያላን ቡድኖች ብራዚልና አርጀንቲና ይገናኛሉ፡፡ የፍጻሜውን ጨዋታ በብራዚል ዋና ከተማ ሪዮ ዲጄኔሮ የሚገኘው ማራካኛ በዝግ ስታድዬም ያስተናግደዋል፡፡ ማራካኛ በተከታታይ ሁለት የኮፓ አሜሪካን የዋንጫ ጨዋታዎችን ማስተናገዱ ሲሆን በ2019 እኤአ ላይ በ46ኛው ኮፓ አሜሪካ ላይ ብራዚል ፔሩን 3ለ1 በመርታት ሻምፒዮን ሆናለች፡፡
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ ባስቀመጠው መረጃ መሰረት ሁለቱ ብሄራዊ ቡድኖች ከ47ኛው የኮፓ አሜሪካ የዋንጫ ፍልሚያ በፊት በ105 ጨዋታዎች ተገናኝተዋል፡፡ ብራዚል 41 እንዲሁም አርጀንቲና 38 ጨዋታዎችን ሲያሸንፉ 26 ጊዜ በአቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡  በትራንስፈር ማርከት መሰረት በተጨዋቾች ስብስባቸው ብራዚል በ913 ሚሊዮን ዩሮ እንዲሁም አርጀንቲና 646 ሚሊዮን ዩሮ ዋጋ ተተምነዋል፡፡
የሁለቱ ብሄራዊ ቡድኖች የእግር ኳስ ፍጥጫ ‹‹ክላሲኮ ዴል አትላንቲኮ›› ወይም ‹‹ሱፕር ክላሲኮ ዴስ አሜሪካስ›› አንዳንዴም ‹‹ዘ ባትል ኦፍ ዘ አሜሪካስ›› ተብሎ ይጠራል፡፡ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ 107 ዓመታትን ያስቆጠረ ትንቅንቅ ሲሆን በ47ኛው የኮፓ አሜሪካ የፍፃሜ ጨዋታ ላይ የሚገናኙት በታሪክ ለ106ኛ ጊዜ ይሆናል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች በ1914 እኤአ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ  ሲጫወቱ  3ለ0 እንዲሁም  በ2019 ላይ ለመጨረሻ ጊዜ  ሲገናኙ 1ለ0 ያሸነፈችው አርጀንቲና ነበረች፡፡ በሰፊ የግብ ልዩነት የተሸናነፉበት የወዳጅነት ጨዋታ በ1940 እኤአ ላይ የተካሄደውና አርጀንቲና 6ለ1 ድል ያደረገችበት ነው፡፡
የሁለቱ ብሄራዊ ቡድኖች ጨዋታ በወዳጅነት፣ በማጣርያ እና በዋና ውድድር ላይ ሲያጋጥም በሜዳ ላይና በደጋፊዎች መካከል ከፍተኛ ትንቅንቅ ከመንፀባረቁም በላይ አወዛጋቢ እና አነጋጋሪ ክስተቶች ይፈጠሩበታል፡፡ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ የእግር ኳስ ተቀናቃኝነት ልዩ መንፈስ የሚታይበት ጨዋታ መሆኑን ይገልፃል፡፡ ታዋቂው የኤኤስፒኤን ESPN ድረገፅ  ከምርጥ የእግር ኳስ የደርቢ ትንቅንቆች አንዱ አድርጎ ሲጠቅሰው ሲኤንኤን በበኩሉ ከእንግሊዝና ከስኮትላንድ ፍጥጫ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ የሚታይ ከባድ ጨዋታ መሆኑን አስቀምጦታል። የዓለማችን እውቅና ምርጥ የእግር ኳስ ተጨዋቾችም በሁለቱ ብሄራዊ ቡድኖች ትንቅንቅ ውስጥ አጋጥመዋል፡፡  
ከአርጀንቲና ማኑዌል ሞሬኖ፣ አዶልፎ ፔዴሬና፣ አልፍሬዶ ዴስቲፋኖ፣ ማርዮ ኬምፐስ፣ ዲያጎ ማራዶና፣ ፈርናንዶ ረዴንዶ፣ ጋብሬል ባቲስቱታ እና ሊዮኔል ሜሲ እንዲሁም ከብራዚል ደግሞ ፔሌ ፣ጋሪንቻ፣ ዚኮ፣ ሮማርዮ፣ ሮበርቶ ካርሎስ፣ ሮናልዲንሆ፣ ሪቫልዶ፣ ካካ፣ ሮናልዶ እና ኔይማር ናቸው፡፡
በኮፓ አሜሪካ ላይ 15 ጊዜ ዋንጫውን በማሸነፍ፤ 6 ጊዜ ሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም 9 ግዜ 3ኛ ደረጃ በማግኘት ኡራጋይ ከፍተኛውን ውጤት አስመዝግባለች፡፡  አርጀንቲና  14 ጊዜ ዋንጫውን ስትወስድ 14 ጊዜ ሁለተኛ ደረጃና 5 ግዜ 3ኛ ደረጃ  እንዲሁም ብራዚል 9  ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት 11 ጊዜ ሁለተኛ ደረጃና 7 ግዜ 3ኛ ደረጃ  በማስመዝገብ በከፍተኛ ውጤታቸው ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን  ይዘዋል፡፡ ፓራጓይ፣ ፔሩና ቺሊ እኩል 2  ጊዜ ዋንጫውን ለማሸነፍ የበቁ ሲሆን እንዲሁም ኮሎምቢያና ቦልቪያ እኩል አንድ ጊዜ ሻምፒዮን ሆነዋል፡፡ አርጀንቲናዊው ኖበርቶ ማርቲኔዝና እና ብራዚላዊው ዚዙንሆ በ17 ጎሎቻቸው የኮፓ አሜሪካው የምንግዜም ከፍተኛ አግቢዎች ናቸው፡፡
አርጀንቲና ኮፓ አሜሪካን 9 ጊዜ  በማዘጋጀት ግንባር ቀደም ስትሆን ኡራጋይ እና ቺሊ እኩል ሰባት ገዜ ፤ ብራዚልና ፔሩ እኩል 6 ጊዜ፤ ኤኳዶር 3 ጊዜ ፤ ቦሊቪያ ሁለት ጊዜ፤ ፓራጓይ፣ ኮሎምቢያ እና ቬንዝዋላ እንዲሁም አሜሪካ በልዩ ግብዣ አንድ አንዴ አዘጋጅተዋል፡፡
በኮፓ አሜሪካ ላይ ለአሸናፊው የምትሰጠውን የመጀመርያዋን ዋንጫ በ1910 እኤአ ላይ የአርጀንቲና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለደቡብ አሜሪካ የእግር ኳስ ኮንፌደሬሽን በስጦታ ተበርክቷል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለአሸናፊው የምትሰጠው ዋንጫ በ1916 እኤአ ላይ ችሳ ኤስካኒ ከተባለና በቦነስ አየረስ ከሚገኝ ሱቅ 2,768.80 ዩሮ የተገዛች ናት፡፡ ዋንጫዋ 9 ኪሎግራም ክብደትና 77 ሴሜትር ርዝማኔ ያላት ስትሆን ከነጠረ የብር ማእድን የተሰራች በመቀመጫዋ በውድ እንጨት ለሻምፒዮኖች መፃፊያ ቦታ በሶስት እርከን የተበጀላት ናት፡፡

Read 369 times