Sunday, 11 July 2021 17:33

ኬር ኤዥ ኢትዮጵያ” ለቆዳ ውጤቶች አለማቀፍ ብራንድ አምባሳደር ሾመ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

 ምርቶቹን ለተለያዩ የዓለም አገራት ገበያ እያቀረበ ነው
                             


              “ኬር ኤዥ ኢትዮጵያ” የተሰኘው ቆዳ አምራች ድርጅት ምርቶቹን በስፋት ለማስተዋወቅ አለም አቀፍ ብራንድ አምባሳደር መሾሙን ገለፀ፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት የቆዳ ውጤቶች በማምረት ለሀገር ውስጥና ለተለያዩ የዓለም አገራት ገበያ በማቅረብ በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ያመለከተው ድርጅቱ ምርቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንድስታስተዋውቅለት ዝነኛዋን ተዋናይት አዲስ ዓለም ጌታነህን የዓለማቀፍ ብራንድ አምባሳደር አድርጎ የሾመ ሲሆን ባለፈው ቅዳሜ፣ከሰዓት በኋላ በራዲሰን ብሉ ሆቴል የፊርማ ሥነ-ሥርዓቱን ከአርቲስቷ ጋር አከናውኗል፡፡
“ኬር ኤዥ ኢትዮጵያ” በአሁኑ ሰዓት ከ60 በላይ  ሰራተኞችን ቀጥሮ በከፍተኛ ጥራትና ውበት የቆዳ ውጤቶችን እያመረተ ሲሆን ከአገር ውስጥ ገበያ አልፎ በውጭ አገራትም የቆዳ ውጤቶች ተፈላጊነቱ እየጨመረ በመምጣቱ ከስድስት በላይ ለሆኑ የአለም አገራት ምርቶቹን ለመላክና የበለጠ የውጭ ምንዛሬ ለሀገር ለማምጣት ማሰቡን የድርጅቱ መስራችና ባለቤት አቶ ዘላለም መርአዊ በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ከ60 ሰራተኞች መካከል 48ቱ ሴቶች 8ቱ ደግሞ አካል ጉዳተኞች ሲሆኑ እነዚህን ሙያተኞች በዓለም ገበያ 300 ዶላር የሚያወጣ ጥራትና ውበት ያለውን ቦርሳን ጨምሮ ጫማ ጃኬት፣ቀበቶ ቦርሳና የተለያዩ የመኪና ወንበሮችና የቆዳ ሶፋዎችን በማምረት አስደናቂ ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን አቶ ዘላለም ተናግረዋል፡፡ “ኬር ኤዥ” በቅርቡም የሰራተኞቹን ቁጥር ከ60 ወደ 150 ከፍ ለማድረግ ማቀዱም ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንደኛ፣ በዓለም 5ኛ  የቀንድ ከብት ሀብት ያላት አገር ብትሆንም፣ ከዘርፉ መጠቀም ያለባትን ያህል እንዳልተጠቀመች የሚገልጹት  አቶ ዘላለም፤ ለዚህ በቆዳ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ያሉ በርካታ ማነቆዎችን አስታውሰው፤ ድርጅታቸው ይህን ችግር ለመፍታት “ሌዘር ሲቲ” ለማቋቋም እንዳቀዱ ተናግረዋል፡፡
ምርቱን በአምባሳደርነት እንድታስተዋውቅ የተመረጠችው አርቲስት አዲስ ዓለም “ኬር ኤዥ” ያስቀመጣቸውን በርካታ መስፈርቶች አልፋና ተወዳዳሪዎቿን  አሸንፋ በብዙ ክፍያ ብራንድ አምባሳደር መሆኗን ገልፀዋል፡፡ አርቲስቷም “ለሀገራችን የቆዳ ምርት አለም አቀፍ አምባሳደር እንድሆን የተጣለብኝን ሀላፊነት ለመወጣት የምችለውን አደርጋለሁ” ስትል ቃል ገብታለች፡፡
“ኬር ኤዥ ኢትዮጵያ” በአሁኑ ሰዓት በቀን 300 ቦርሳ ጫማና ጃኬቶችን፣ በቀን 10 የመኪና ወንበሮችንና በቀን 4 የቆዳ ሶፋዎችን የማምረት አቅም ያጎለበተ ሲሆን፣በቅርቡ ይህን የማምረት አቅሙን በእጥፍ ለማሳደግ እየሠራ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ በቅርቡም አሁን ካሉት  ሱቆች በተጨማሪ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ትልልቅ ሱቆችን ለመክፈት ዝግጅቱን ማጠናቀቁም በዕለቱ ተጠቁሟል፡፡ በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ የቆዳ ኤክስፐርቱና የኬር ኤዥ አማካሪ አቶ ቴዎድሮስ ይልማ፣የኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ዳንኤል ጌታቸው፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና በርካታ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡

Read 1847 times