Print this page
Wednesday, 14 July 2021 00:00

በሃይቲ ፕሬዚዳንቱ ሲገደሉ፣ ቀዳማዊት እመቤቷ ቆስለዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የኬንያው መሪ ራሳቸው ያወጡትን ህግ በመጣስ ተወቀሱ

            በሃይቲ የታጠቁ ቡድኖች ባለፈው ረቡዕ በአገሪቱ ፕሬዚዳንት መኖሪያ ቤት ባደረሱት ጥቃት ፕሬዚዳንት ጆቨኔል ሞይሴ ሲገደሉ ባለቤታቸው ቀዳማዊት እመቤት ማርቲን ሞይሴ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸው በህክምና እየተረዱ እንደሚገኙ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ባለፈው ረቡዕ ጠዋት የፕሬዚዳንቱን ቤት ሰብረው በመግባት ጥቃቱን የፈጸሙት ታጣቂዎች ማንነት ባይታወቅም አንዳንዶቹ የስፔን ቋንቋ ተናጋሪዎች መሆናቸውን ለማወቅ መቻሉን የጠቆመው ዘገባው፣ የአገሪቱ ጊዚያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ክላውድ ጆሴፍ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ድርጊቱን ኢሰብዓዊና ዘግኛኝ ነው ሲሉ በማውገዝ ህዝቡ እንዲረጋጋ ጥሪ ማቅረባቸውንም አስረድቷል፡፡
በተለይ ባለፉት ወራት በአደባባይ ተቃውሞ ሲደረግባቸውና የስልጣን ዘመናቸው አልፏል በሚል በተቃዋሚ ፓርቲዎች ስልጣናቸውን እንዲለቁ ሲጠየቁ የነበሩት ፕሬዚዳንቱ በታጣቂዎች መገደላቸውን ተከትሎ በአገሪቱ ብጥብጥና ሁከት እንዳይፈጠር ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ መግለጸቸውንና የአገሪቱ ብሔራዊ ፖሊስና የጦር ሃይልም ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን በንቃት እየሰሩ እንደሚገኙ ማስታወቃቸውንና የአሜሪካ መንግስትም ድርጊቱን በተመለከተ ምርመራ መጀመሩን እንደገለጸ አመልክቷል፡፡
ፕሬዚዳንት ጆቨኔል ሞይሴ በ201 በተካሄደው የሃይቲ ምርጫ አሸንፈው በአመቱ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ 11 ሚሊዮን ያህል ህዝብ ያላት ሃይቲ እጅግ ድሃ ከሚባሉት አገራት ተርታ እንደምትሰለፍም አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፤ ኬንያውያን በአገሪቱ የተጣለውን የሰዓት ዕላፊ ገደብ ተላልፈው ከመሸ በኋላ ፕሮጀክት ሲያስመርቁ የታዩትን ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ራሳቸው ያወጡትን ህግ ራሳቸው በአደባባይ ተላልፈዋል በሚል በማህበራዊ ድረገጾች በስፋት መውቀሳቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ባለፈው ማክሰኞ ምሽት በመዲናዋ ናይሮቢ የአምስት ሆስፒታሎች ግንባታ ፕሮጀክቶችን በይፋ ሲያስመርቁ መታየታቸውን ተከትሎ የአገሪቱ ዜጎች ድርጊቱን ማውገዛቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ፕሬዚዳንቱ በበኩላቸው ሆስፒታሎቹን በምሽት ለማስመረቅ የመረጡት በቀን ቢያደርጉት ግርግር ይፈጠራል ወይም የማህበራዊ ርቀት ህጎች ይጣሳሉ ብለው በመስጋታቸው መሆኑን በመግለጽ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አንዳንድ ተሰሚነት ያላቸው ኬንያውያን አክቲቪስቶች ኡሁሩ የሰዓት ዕላፊ አዋጁን በመጣሳቸው በአፋጣኝ ፍርድ ቤት ቀርበው መቀጣት አለባቸው በሚል የድረገጽ ዘመቻ መጀመራቸው የተነገረ ሲሆን፣ አንዳንዶች ደግሞ የትርፍ ሰዓት ስራ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ራሳቸው በተግባር አሳይተዋልና ኡሁሩ የሰዓት ዕላፊ አዋጁን ማስቆም ይገባቸዋል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡


Read 2537 times
Administrator

Latest from Administrator