Tuesday, 13 July 2021 00:00

“ከገለልተኛው የጦርነት ጌታ ተጠንቀቁ”

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

   • በጊዜ ያልገቱት ጦርነት፣ ስነምግባርን ያሳጣል፤ ማጣፊያው ያጥራል።
    • ካልተጠነቀቁ፣ ጦርነት ሱስ ይሆናል፡፡ ጥላቻን እየዘሩ ጦርነትን የማጨድ ሱስ (በኤሪስ ታሪክ)፡፡
    • በሰላም ያልተተካ ጦርነት፣ ያሰክራል፡፡ ማንነትን ያስረሳል፡፡ ከሰውነት ተራ ያስወጣል (በሴክመት ታሪክ)፡፡
         
          አጀማመሩ በአርበኝነት ነበር ይላሉ። “ለእውነት የሚቆም፣ ለቅንነት የሚተጋ፣ በደልንና ጥቃትን ከሩቁ የሚያስቀር፣ ሰላምን የሚሰጥ፣ ፍትህን የሚፈጽም ድንቅ አርበኛ” ነው ብለው አወድሰውታል።
ወረራ ወይም ጥቃት አምርሮ ከመጣ፣ በጀግንነት የሚዋጋ ፊታውራሪ፣ የአርበኝነት ሁሉ አውራ እንደሆነም ተዘምሮለት ነበር። “ጦርነትን አሸንፎ ወደ ሰላም የሚመልስ ጌታ ነው” ብለው በአድናቆት ጽፈውለታል።
ምን ያደርጋል? በዚያው አልዘለቀም። አርበኝነቱን አልተወም፡፡ ሐርበኛ የጦርነት ጌታ መሆኑ አልተሻረም። እንዲያውም ዝናው ጨምሯል።
ነገር ግን፣ የቀድሞ ማንነቱ ተለውጧል። ከስነምግባር ተነጥሎ ርቋል። ‹ለእውነት፣ ለቅንነት፣ ለሰላም፣ ለፍትህ› የሚሉ ነገሮችን ትቷል። ለማንም የማይወግን ሆኗል። የፍርሃት አይደለም። “ሐርበኝነት” ነው ሙያው። ሌላ መዋያ የለውም። ከትጥቅ (ከሐርብ) በቀር ሌላ ንብረት አያውቅም።
ኤሪ፣ ኤረስ፣ ኤሪስ… ይባላል። ጦርነት ንብረቱ ነው። ጦርነት ቢያጣ፣ ጥላቻን ይዘራል፤ ጦርነትን ይፈጥራል። ያመርታል። ሙያውም እንጀራውም ነው። የትጥቅ የጦር አውራ እንደሆነ፣ ማዕረጉ ይመሰክራል - “የጦርነት አምላክ” ብለውታል። በእርግጥ፣ አምላክነቱን ቢያምኑለትም፣ ይወዱታል ማለት አይደለም። እንዲውም ይጠሉታል።
የጦርነት አምላክነቱን አይደለም የጠሉት። ለእውነት ደንታ የሌለው፣ “ከስነምግባር የፀዳ”፣ መርህ የለሽ ገለልተኛ መሆኑን… የምር የምር ሙሉ ለሙሉ ገለልተኛ መሆኑን ነው የጠሉት።
በኢትዮጵያ፣ በግሪክ፣ በባቢሎን፣ በግብፅ፣ በሮም - የጦርነት አማልክት ታሪክ፡፡  
የያኔ ዘመን ሰዎች፣ በየአገራቸውና በየድንበራቸው፣ ጋሻ ከለላ፣ አርአያና አለኝታ የሚሆንላቸው የየራሳቸው አምላክ ነበራቸው። የልምላሜና የአዝመራ አምላክ፣ የእውቀትና የጥበብ አምላክ፣ የምድርና የሰማይ አምላክ፣ የውሃና የነፋስ አምላክ፣ የህግና የስርዓት አምላክ፣ እያሉ ይዘረዝራሉ። ዛሬስ ቢሆን፣ “በህግ አምላክ” ይባል የለ፡፡ የጦርነት አምላክም እንደዚያው ነው።
የግሪክ አቴና እና ኤሪስ፣ የሮም ማርስ፣ የኢትዮጵያ ማህር፣ የግብፅ ሄሩ እና ሴክመት፣ የሱመር ኢንአና፣ የባቢሎን ኢሽታር፣… ብዙ ነው ስማቸው። ግን የጦርነት አማልክት ናቸው። ኤሪ እና ሴክመት ግን ከሌሎቹ ይለያሉ።
በእርግጥ፣ ኤሪስ፣ ገና አጀማመሩ ላይ፣ በጥንት በጠዋቱ፣ ከሌሎቹ የጦርነት አማልክት ጋር ተመሳሳይ ባህርይ ነበረው። ወረራን መክቶ፣ ጥቃትን ድል አድርጎ፣ ሰላምን የሚያበረክት የቅንነት ጋሻና ከለላ ነበር ይላሉ። እንዲያውም፣ የኢትዮጵያ ነገሥታትም፣ መስክረውለታል፡፡ “ማህር” በሚል ስያሜ የሚታወቀው የኢትዮጵያ የጦርነት አምላክ፣ “ኤሪስ” እንደ ማለት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የጥንት ታሪክ ዘጋቢዎች፣ በግዕዝ ማህር ወይም ማህረም ብለው ይፅፋሉ። በግሪክኛ ትርጉሙን ሲጽፉ ደግሞ ኤሪስ የሚለውን ስያሜ ይጠቀማሉ። አዱሊስ ላይ በሐውልት የተቀረፀው የግዕዝና የግሪክ ፅሁፍ ይህን ታሪክ ይመሰክራል።
ማህረም የሚለው ስያሜ፣ ከጨረቃ ጋር የተያያዘ ቢሆንም፣ ሐርብ (ትጥቅ) ከሚለው ቃል የመጣ ነው ይላል - Moon-o-theism የተሰኘው መፅሐፍ። በሌላ አነጋገር፣ ማህረም፣ ከጦርነት አምላክነቱ በተጨማሪ፣ የጨረቃ ጌታ ነው። “ጦርነት”፣ ለማህረም፣ ብቸኛ ሙያው አይደለም፡፡ ይህን ልብ በሉ፡፡ የቀን አቆጣጠርና የወቅት ፍርርቆሽ፣ የክረምትና የበጋ ጌታ እንደሆነ ይታመንበት ነበር - ማህረም። “ምድር” ተብሎ ከሚጠራው አምላክ ጋርም ያጣምሩታል - የአገር የምድር ጌታነትን በመስጠት። ሌሎቹ በታሪክ የተፃፉ የኢትዮጵያ የጥንት አማልክት፣ የሰማይ ጌታ “አስታር” እና የወንዝ የሃይቅ፣ የባህር የውቅያኖስ ጌታ “ባሕር” የተሰኙ እንደሆኑ የጥንት ታሪኮች ይጠቅሳሉ።
የሰማይ የምድር እመቤት-የእግሯ መደገፊያ አንበሶች ናቸው፡፡
የባቢሎን ታሪክ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ይዛመዳል። በጥንታዊቷ ባቢሎን፣ የሰማይ አምላክ መጠሪያ ‹ኢሽታር› ይባላል። ግን፣ ‹የሰማይ ጌታ› ማለት አይደለም። ‹የሰማይ እመቤት› ማለት ነው - ኢሽታር፣ ሴት አምላክ ናት። ከጊዜ በኋላ፣ ምድርንም ጠቀለለችና ‹የሰማይ የምድር እመቤት› ተባለች - Inanna, Lady of Heaven and Earth (2014) በሚል ርዕስ የታተመው መፅሐፍ  ታሪኳን በሰፊው ይተርካል፡፡
 የዛሬ 5ሺ ዓመት ገደማ ነው፤ የኢሸታር አነሳስ፡፡  ያኔ፣ ተወዳጅ የሲሳይ እመቤት ነበረች፡፡ በረከት ሁሉ የሞላት የተረፋት ናት፡፡
የእርሻና የአዝመራ፣ የአበባና የፍሬ፣ የፍቅርና የደስታ አምላክነት፣ የኢታሽር ንብረት ነው። የሰማይ ከዋክብት፣ የአደይ አበቦች ከአጠገቧ አይጠፉም። ከእጇ ዘንባባ አይለያትም። ሰማይን ብቻ ሳይሆን፣ ምድርንም ጠቅልላለችና፡፡
በእርግጥ፣ የሰማይ ግዛቷን ወደ ምድር ያስፋፋችው፤ በአንድ ጀምበር አይደለም። ከሺህ ዓመታት በላይ የፈጀ ታሪክ ነው፡፡ በ480 ገፆች የተተረከውን የሺህ ዓመታት ታሪክ፣  ወደ ጥቂት መስመር እናሳጥረው ብዬ ነው፡፡  
ብዙም ሳትቆይ፣ የጦርነት እመቤትነትን ለራሷ ጨመረች፤ ወይም አማኞች ጨመሩላት። በዘንባባና በአደይ አበባ ምትክ፣ ቀስት ታጣቂ ሆነች። ከትከሻዋ ግራና ቀኝ፣ ሹል የቀስት ጫፎች ይታያሉ። የዘወትር ስንቆቿ ናቸው። በቀኝ መዳፏ፣ ቆልማማ ጎራዴ ጨብጣ፣ በግራ እጇ ገመድ ትይዛለች - አመፀኛችንና ጠላቶችን አሸንፉ፣ ምርኮኞችን አስራ ትጎትታለች። የእግሯ መደገፊያ አንበሶች ናቸው። ይታዘዟታል። እመቤታቸው ናት።
ምናለፋችሁ በሰማይና በምድር አቻ የሌላት፣ እሳት የምትተፉ፣ አውሎ ነፋስ የምታስነሳ፣ ተራሮችን የምትንድ፣ ባህሮችን የምታናውጥ የጦር አምላክ እንደሆነች በባቢሎን ይታመንባት ነበር - ኢሽታር። እንደዚያም ሆና፣ የእርሻና የአዝመራ፣ የፍቅርና የደስታ እመቤትነቷን አልጣለችም። የበገና አፍቃሪ የሙዚቃ እመቤትም ናት እንጂ፡፡ ጦርነት ብቸኛ ሙያዋ አይደለም፡፡
ሰፊ ግዛት የተቆጣጠረው የሮም መንግስትም፣ የራሱ የጦር አለኝታ ነበረው - ማርስ ይሉታል። የመጋቢት ወር፣ ለዚሁ የጦር አምላክ መታሰቢያ እንዲሆን ሰይመውለታል - ማርች እንዲሉ። ኤሪ ግን፣ ከእነዚህ ሁሉ ይለያል።
“ከእውነትና ከስነ ምግባር የፀዳ” የጦርነት ሱሰኛ፡፡
አንደኛ ነገር፣ እነ ማህረምና እነ አቴና፣ ጦርነትን እንደብቸኛ ሙያ አይቆጥሩትም። አቴና፣ የእውቀትና የጥበብ፣ የበረከትና የብልጽግና አምላክ እንደሆነች ይታመንባት ነበር - የፍትህና የሰላም እመቤትም ጭምር ናት።
ሁለተኛ ነገር፣ እነ ኢሽታርና እነ አቴና፣ ገለልተኛ አይደሉም። ሕግና ስርዓት አላቸው። ከመንገድ የወጣውንና የተጣመመውን አይደግፉም። ይገስፃሉ፤ ይከለክላሉ፤ ይቀጣሉ። በተስተካከለና በተቃና መንገድ የሚጓዘውን ደግሞ ያደንቃሉ፤ ይደግፋሉ፤ ይሸልማሉ። አንዱን ይጠላሉ፤ ሌላውን ይወዳሉ።
‹ጥሩ የሰራ፣ መጥፎ የሰራ‹ እያሉ፣ አንዱን እያገለሉ ወደ ሌላው ያደላሉ። ንፁህ ዜጎችን ከጥቃት መከላከል ወንጀለኞችን ደግሞ ማሰር እንደማለት ነው -ነገሩ።
ኤሪ ግን፣ እንደ እህቱ እንደ አቴና አይደለም፡፡ ፍፁም ገለልተኛ ነው። ወደ ማንም የማድላት፣ ማንንም የማግለል ቅንጣት ፍላጎት የለውም። አያረገውም። የኤሪ የሌት ተቀን ፍላጎት፣ የትም ቢሆን፣ የዘላለም ምኞቱ፣ ጦርነት ብቻ ነው። ውሎና አዳሩ፣ ከሐርብ ( ከትጥቅ) ጋር ነው። ኑሮና ቀለቡ፣ ውጊያ ነው።
በእርግጥ፣ ከሌላው ሁሉ ተለይቶና ርቆ፣ ገለልተኛና ብቸኛ ተሁኖ፣ በባዶ ሜዳ፣ ጦርነት አይገኝም። የተቃራኒ ጎራዎች ነው ጦርነት። ኤሪ፣ጦርነት ቢያጣ፣ ጥላቻን ይሰብካል። ቅራኔን ይፈለፍላል፡፡ ተቃራኒ ጎራዎችን ይፈጥራል፡፡ ከዚያ በኋላ ደንታ የለውም። ከአንድ ጎራ በኩል ሆኖ በሌላኛው ጎራ ላይ ይዘምታል። አልያም፣ ከወዲያኛው ጎራ ሆኖ፣ የወዲህኛውን ጎራ ይወጋል። ታዲያ፣ የማድላትና የመወገን ጉዳይ አይደለም - ለኤሪ።
ለየትኛውም ጎራ ግድ የለውም። የትኛውንም አይወድም፤ አይጠላም። ይሄኛው እውነተኛ፣ ያኛው ሃሰተኛ ብሎ አይለይም። ጥሩ እና መጥፎ ብሎ አይዳኝም። መልካም እና ክፉ ብሎ አይመርጥም። በየትኛውም ጎራ ቢዘምት ልዩነት የለውም። ዋናው ነገር፣ ጦርነት መገኘቱ ነው። ጦርነት ከሌለ፣ አንዱን ከሌላው ጋር ያጣላል፡፡ ጥላቻን ይዘራል፡፡
በቃ፣ ጦርነት፣ እህል ውሃው ነው። ለሆነ ሌላ አላማ አስቦ የሚገባበት አይደለም። ጦርነት ነው አላማው። ጦርነት ነው ፍላጎቱና ኑሮው። የሕልውናው ጣዕምና ትርጉም፤ የማንነቱ ምሶሶና ማገር፣ ጦርነት ሆኗል። ከሱስ አልፎ፣ እንደተፈጥሮው ሆኖበታል፡፡ ውጋውና ቁረጠው፣ ፉከራና ኡኡታ፣ ደምና ስቃይ፣ እልቂትና ውድመት፣ ሰው የረገፈበትና ሬሳ የተረፈረፈበት የጦር አውድማ ነው ምሱ።
የላይ ሰፈር ጦር ቢያሸንፍ፣ የታች ሰፈር ጦር ድል ቢያደርግ፣ ለኤሪ ለውጥ የለውም። ወራሪና ተወራሪ፣ በዳይና ተበዳይ፣ ግፈኛና ተገፊ፣ ለኤሪ ትርጉም የላቸውም። ከወራሪው ጦር ጋር ቢዘምት፣ ዞር ብሎ ከተወራሪው ጦር ጎን ተሰልፎ ቢፋለም፣ “ጣጣ” የለውም። እንዲህ ሆኗል፤ የጦርነት ጌትነቱ፣ የጦርነት አምላክነቱ።
እድሜ ልክ፣ የቀን ቀለቡ፣ የሌሊት ህልሙ፣ ትጥቅና ጦርነት የሆነ አምላክ፤ የጦርነት ጥበበኛ ቢሆን አይገርምም። ሃያል ተዋጊ ነው። ግን፤ አቻ የለሽ ጀግና ተዋጊ አይደለም። ወደር የማይገኝለት የጦርነት ጥበበኛም አይደለም። ከእህቱ ከአቴና ጋር ተዋግቶ አሸንፋዋለች - በጀግንነትና በጥበብ ተዋግታ።
በዚያ ላይ ሄርኪለስ (ህርቃል) አለ። እንደ ኤሪ፣ እንደ አቴና አይደለም ሄርኪለስ። የማይሞት ዘላለማዊ አምላክ አይደለም። አዎ፤ ሃያል ነው እንደ አማልክት። ግን ሟች ነው - እንደሰው። ቢሆንም፣ በጀግንነትና በጥበብ ተዋግቶ ኤሪን አሸንፏል። ማሸነፍ ብቻ አይደለም። አባሮታል እያሳደደ። ኤሪ በሽንፈት ሸሸ፤ በፍርሃት እየተርበደበደ ከምድረ ገጽ ፈረጠጠ - ወደ አማልክት መንደር።
የጦርነት አምላክ፣ የውጊያ ጌታ ቢሆንም፣ በጀግንነት የላቀ በጥበብ የመጠቀ መወደር የለሽ ተዋጊ አይደለም። ይሔ የኤሪ ልዩ ባህርይ ነው።
ሌሎች አማልክት፣ በየመስካቸውና በየቦታቸው፣ የብቃት ልሂቃን ናቸው። የእርሻ የአዝመራ፣ የዝናብ የነፋስ፣ የመብረቅ የነጎድጓድ፣ የዋሽንት የበገና፣ የሂሳብ ስሌትና የቀመር፣ የጉዞና የአደን፣ የህግና የስርዓት፣ የጤንነትና የፍቅር፣ የእውቀትና የጥበብ፣ የጨዋነትና የቅንንት፣ የእውነትና የንፅህና፣ የፍትህና የዳኝነት፣…. በየሙያ ዘርፋቸው፣ በየአካባቢያቸው አቻ የለሽ ናቸው - ብዙዎቹ አማልክት። ጥቃት ሲሰነዘርባቸው አፀፋውን ለመመለስ፣ ወራሪ ሲመጣባቸውም መክተው ለማሸነፍ፣... ይታጠቃሉ። ሐርበኛ የጦርነት መሪ ይሆናሉ።
አቴና፣ የፍቅርና የጥበብ፣ የሰላምና የፍትህ አምላክ ብትሆንም፣ ጦርነት ሲመጣ የጦር መሪ ናት-“ አቴና ኤሪያ” በሚል ስያሜ ትዘምታለች። “አቴና ሐርበኛዋ” እንደማለት ነው። የአቴና አባት ዙስ፣ በጦርነት ጊዜ “ዙስ ኤሪየስ” ብለው ይጠሩታል - ዙስ ሐርበኛው።
 ኤሪያ ማለት ‹ሴት ኤሪ‹ እንደማለት ነው። ኤሪየስ ደግሞ “ወንድ ኤሪ” እንደማለት።
ታዲያ፣ ሐርበኛነታቸው ለጊዜው ብቻ ነው - ሰላምን ለማስፈን ብቻ። ጦርነትን ካባረሩ በኋላ፣ ወደ ዋና ሙያቸው፣ ወደ ዘወትር ስራቸው ይመለሳሉ። አቴና፣ የእውቀትና የጥበብ እመቤትነቷ የሰላምና የፍትህ አምላክነቷ ይጠብቃታል - “አቴና ኤሪያ” የሚለው የጦርነት ጊዜያዊ ስያሜ ይቀየራል። ‹ኤሪያ” የሚለው ቅጽል ይሰረዛል።
ለእነ አቴና፣ ጦርነት የዘወትር ህይወት አይደለማ- ጊዜያዊ ነው፡፡ ጦርነትን፣በጊዜ እልባት ይሰጡታል፡፡ እናም፤ ለጦርነት ጊዜ ብቻ ሰላምን እስኪያሰፍኑ ድረስ ብቻ ነው - “ኤሪ” የሚል ቅጽል የሚጨመርላቸው።
ለኤሪስ ግን፣ ጦረኝነት ጊዜያዊ የዘመቻ ስራ፣ ጊዜያዊ ቅፅል አይደለም። የሁልጊዜ ስራው፣ ጦርነት ነው። ጦረኛው ከመባል ውጭ ሌላ ስም የለውም። ጊዜያዊ ቅጽል ሳይሆን የዘላለም መጠሪያ ስሙ ሆኗል - ኤሪ። ጦርነት ሲያጣም እረፍት የለውም። ውዝግብግብና እልህ፣ ብሽሽቅና ስድብ፣ ቅራኔና ውንጀላ፣ ጥላቻና ግጭት፣… በአጠቃላይ ያለእረፍት የጦርነት ወሬና የጦርነት ዘመቻ ከማብዛቱ  የተነሳ፣ለምዶበት ሱስ ሆኖበታል፡፡


Read 1705 times